Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ተቋማት ዓመታዊ ጉባዔያቸውን ለማካሄድ ፈተና ገጥሟቸዋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን በማካሄድ ውሳኔያቸውንና የኦዲት ሪፖርታቸውን  ለብሔራዊ ባንክ የማቅረብ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ይህን አስገዳጅ ሕግ ለመተግበር ግን አሁን ላይ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡  

እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት የ2012 የሒሳብ ዓመት ሰኔ መጨረሻ ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ ባሉት ተከታታይ ወራት ውስጥ ይህንን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እስካሁንም በዚሁ መንገድ የቀጠሉ ሲሆን ዘንድሮ ግን እንዲህ ያሉትን ጠቅላላ ጉባዔዎች ለማካሄድ አስቸጋሪ ሁኔታ ከፊታቸው ተደቅኗል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ ባለአክሲዮኖቻቸውን ሰብስበው በቀደመው ሁኔታ ጉባዔያቸውን ለማድረግ የማይችሉ በመሆኑ ነው፡፡ ሁኔታውን የበለጠ አስቸጋሪ የሚያደርገው ደግሞ እነዚህ 35 የሚሆኑ ሥራ ላይ ያሉ የግል ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የባለአክሲዮኖቻቸው ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ተራርቆ ለመሰብሰብ እንኳን የሚያስችል ባለመሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ እንደማክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች በርከት ያሉ ባለአክሲዮኖች ያላቸው የአክሲዮን ኩባንያዎችም፣ በተመሳሳይ በሕግ የተቀመጠውን የጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ አሁን ክልከላ ላይ ያለው በርከት ብሎ የመሰብሰብ ድንጋጌ ተፅዕኖ ስላደረሰባቸው መፍትሔ እየፈለጉ ናቸው፡፡ ከሌሎች በተለየ ግን በርካታ ባለአክሲዮኖች ያሉዋቸው የፋይናንስ ተቋማት ተፅዕኖው ጎልቶ ይታይባቸዋል፡፡    

እነዚህ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአጠቃላይ የባለአክሲዮኖቻቸው ቁጥር ከ260 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡ ይህ ቁጥር አሁን በመደራጀት ላይ ያሉትና ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ ያሉት ከታከሉበት ቁጥሩ ወደ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ ስለሚሆን፣ በአብዛኛው ከአራት ሺሕ እስከ 124 ሺሕ የሚደርስ ባለአክሲዮኖችን የያዙት ባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካልተነሳ ወይም ቴክኖሎጂን አማራጭ አድርገው መሰብሰብ ካልቻሉ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነገር አሳስቧል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ ሕግ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት የባንኮች ማኅበር በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ስለመምከሩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ይኼ ነው የሚባል ውሳኔ አልተላለፈም፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ይህንን በሕግ የሚያስገድዳቸውን ጠቅላላ ጉባዔ በምን መልኩ ያካሂዳሉ? የሚለው ጥያቄ አሁን ላይ መልስ ያልተገኘለት በመሆኑም፣ ባለአክሲዮኖቻቸውን በዚህ ጊዜ ብለው መጥራት አልቻሉም፡፡ የእነዚህ ጠቅላላ ጉባዔዎች አስፈላጊነት በተለያየ መንገድ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ዓመታዊ ሪፖርት ከማድረግና የሥራ አፈጻጸማቸው እንዲሁም ትርፍና ኪሣራቸውን ከማሳወቅም በላይ አብዛኞቹ የፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ የቦርድ አመራሮችን የሚመርጡ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ጭምር ነው፡፡

የጠቅላላ ጉባዎዔዎቹን ወቅቱ ጠብቆ  ማካሄድ በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ የሚፈልጉ እንደ ካፒታል ማሳደግ፣ የየትርፍ ድርሻ ድልድል ውሳኔና ሌሎች ተቋማቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ የሚሰጥባቸው በዚሁ ጠቅላላ ጉባዔ በመሆኑ፣ የጉባዔዎቹ መካሄድ ግድ ስለመሆኑም ያነጋገርናቸው የባንክና የኢንሹራንስ ሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በጥቅል  ሲታይ የዚህ ጉባዔ መደረግ እያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ለቀጣይ የሥራ ጊዜ ወሳኝ በመሆኑ፣ ጉባዔዎቹ እንዴት መካሄድ እንደሚኖርባቸው በቶሎ ሊወሰንም ይገባል ይላሉ፡፡

ይህም በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ምልዓተ ጉባዔ በሞላበት ጠቅላላ ጉባዔ የሚከናወን ሲሆን፣ ተቋማቱም ዕጩዎችን በተለያዩ የመናኛ ብዙኃን ሲያስተዋውቁ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

እንዲህ ላለው ምርጫ ደግሞ የባለአክሲዮኖች ቁጥር ወሳኝ በመሆኑ ሁኔታው በምን መንገድ ይከናወን የሚለውን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ብሔራዊ ባንክም ጉዳዩን በቶሎ አጥንቶ አማራጮችን በማቅረብ ጉባዔዎቹ የሚካሄዱበትን መንገድ ሊያሳውቅ ይገባል ተብሏል፡፡

ከአንዳንድ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመልክተው ደግሞ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖችን ለመሰብሰብ ስለማይቻል የጠቅላላ ጉባዔው ከወትሮው በተለየ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ጉባዔዎቹ የሚካሄዱበት መንገድ መፈለግ አለበት፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች