Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጎሕ ቤቶች ባንክ የ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰቡን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ በተለየ አገልግሎት ለመቀላቀል የአክሲዮን ሽያጭ ሲያካሂድ የቆየውና በምሥረታ ላይ የሚገኘው ጎሕ ቤቶች ባንክ በአገሪቱ ሕግ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን የተከፈለ ካፒታል መጠን አሳስቦ ማጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ ከባንኩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንድ ባንክ ለማቋቋም ያስፈልጋል ብሎ ያስቀመጠውን የ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መጠን ማሟላት በመቻሉ፣ የጎሕ ቤቶች ባንክን የምሥረታ የሚያረጋግጠውን ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡

ጎሕ ቤቶች ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ የጀመረው መስከረም 2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ እስካሁን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተፈረመ ካፒታልና ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉን የገለጹት በምሥረታ ላይ የሚገኘው ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን ናና ናቸው፡፡ ባንኩ ከዚህ በኋላ የመሥራቾች ጠቅላላ ጉባውን ለመጥራት ይቻል ዘንድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄውን እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡  የመሥራች ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ እንዲቻል ለሰላም ሚኒስቴርም ጥያቄ መቅረቡ ታውቋል፡፡

ምላሹ እንደተገኘም የባንኩን ምሥረታ የሚያረጋግጠውን ጠቅላላ ጉባዔ የሚጠራና የሚያካሂድ ሲሆን፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ጥያቄው የሚስተናገድበት ሁኔታ ታይቶ መሥራች ጉባዔውን በቴክኖሎጂ ጭምር  ታግዞ ሊያካሂድ የሚችል ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡ 

እንደ ባንኩ መረጃ የባንኩን የተፈረመና የተከፈለ ካፒታል አክሲዮኖችን የገዙት ከስድስት ሺሕ በላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የአክሲዮን ሽያጩን መጠን 50 ሺሕ ብር በማድረግ አክሲዮኑን መሸጥ የጀመረው ጎሕ ቤቶች ባንክ፣ ለመቋቋም የሚያስችለውን ካፒታል ማሰባሰብ ቢችልም የአክሲዮን ሽያጩን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በማከናወን የሚያጠቃልል ይሆናል፡፡ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አክሲዮኖችን የሚገዙት መሥራች ባለአክሲዮኖች እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

እንደ ባንኩ አደራጆች መረጃ የባንኩ የምሥረታ ጉዔውን ካደረገ በኋላ ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ እስከ ጥር 2013 ዓ.ም. ድረስ ባንኩን ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል፡፡

ጎሕ ቤቶች ባንክ ከመደበኛ ባንኮች በተለየ በቤት ግንባታና በተያያዥ የባንክ አገልግሎቶች ገበያውን የሚቀላቀል መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ ለመሥራት የወደደውም አሁን በተጨባጭ ካለው የመኖሪያ ቤት ችግር መነሻነትና ያለውን ሰፊ የገበያ ዕድል በጥናት በማረጋገጡ ነው፡፡

እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ የዚህ ባንክ ዕውን መሆን መኖሪያ እንዲኖራቸው የሚሹ ወገኖችን በተግባር ህልማቸውን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ቦታ ሊይዝ የሚችል ባንክ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

ጎሕ ቤቶች ባንክ አንጋፋ የሚባሉ የፋይናንስ ባለሙያዎችና በንግዱ ዓለም ስመ ጥር የሚባሉ የቢዝነስ ሰዎች መሥራች የሆኑበት ነው፡፡

በዋና መሥራችነት የተካተቱት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና፣ የቀድሞ የወጋገን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አረዓያ ገብረ እግዚአብሔር፣ የቀድሞው የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አመርጋ ካሳ፣ የቀድሞ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ የጊፍት ሪል ስቴት ባለቤትና ሥራ አቶ ገብረየስ ኢጋታ፣ የቀድሞ የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ፋሲካ ከበደ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና አማካሪው ውብሸት ዠቅአለ (ዶ/ር) እና የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ዮሴፍ አሰፋ ይጠቀሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች