- ሃሎ … [አንድ የውጭ ድርጅት ለሚኒስትሩ በከፍተኛ ደመወዝ የቀጠረላቸው የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ነበር የደወለው] …. እንዴት አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም፣ እንዴት ነህ?
- ወዳጃችን ደውሎ ነበር። ክቡር ሚኒስትሩ ስልክ አላነሳ አሉኝ እያለ ነው፡፡
- የማይረባ ነው፡፡
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር? ስለ ጋዜጣው ጉዳይ ነበር ሲደውል የነበረው። ቢያናግሩት አይሻልም?
- አንተም የማትረባ ነህ። እኔ ሚኒስትር እንጂ ከጋዜጣ ጉዳይ ጋር ምን ያገናኘኛል?
- ዘንግተውት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን ስልኩን ዝጋው፣ እንደደረስኩ ቢሮዬ እንዳገኝህ!?
[የክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደጋግሞ መጮኹን ያስተዋሉት ሁለቱ አጃቢዎች እርስ በእርስ ተያዩ። ሚኒስትሩ የሚጮኸውን ስልክ እያዩ አያነሱትም]
- ‹‹ምን አባቱ ነው ይኼ›› ሲሉ ክቡር ሚኒስትሩ ሳይታወቃቸው አጉረመረሙ [ወዳጃቸው ነው የደወለው]
- [መሥሪያ ቤታቸው እንደደረሱ ዘወትር እንደሚያደርጉት የኢሜይል መልዕክቶችን ለመመልከት ላፕቶፓቸውን ከፈቱ። ሲደውል የነበረው ወዳጃቸው ሦስት መልዕክቶቹ ተደርድረዋል። ሁሉም ስለ ጋዜጣው ጉዳይ ነው የሚያወሩት]
- መቼ ነው ይኼ ሰውዬ ግን የምነግረውን የሚሰማው [ድምፅ አውጥተው ለብቻቸው አምባረቁ]
- ክቡር ሚኒስትር አውሮፓ ያለው ወዳጅዎት መስመር ላይ ነው ላገናኝዎት? [ጸሐፊያቸው ነች]
- ቶሎ በይ፣ አገናኚኝ፡፡
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጤና እንዳለው ሰው ጤና ይስጥልኝ ይለኛል ደግሞ፣ ጤና ይንሳህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ምን አጠፋሁ?
- በግል ስልኬ አትደውል፣ በኢሜይልም ልታገኘኝ አትሞክር ብዬ ስንቴ ነው የነገርኩህ?
- ክቡር ሚኒስትር አስቸኳይ ሆኖብኝ ነው። በጋዜጣው ላይ የሚወጣው ዘገባ በዕቅዱ መሠረት ለነገ እንዲደርስ ብዬ ነው፡፡
- [ክቡር ሚኒስትሩ አቋረጡት] ለመጨረሻ ጊዜ ነው የምነግርህ አዳምጥ። በኢሜይልም በእጅ ስልኬም አትደውልልኝ። የእኔና የአንተ ግንኙነት በቢሮ ስልክ ብቻ ነው መሆን ያለበት። ይህን የምልህ ለምን እንደሆነ ካልገባህ እወቀው፣ ለእኔም ለአንተም ደኅንነት ስል ነው።
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር የተፈጠረ ችግር አለ እንዴ?
- እንዴት ይገባኻል አንተ? ለጥንቃቄ ግን የቢሮ ስልክ አስተማማኝ ነው። ይኸውልህ እዚህ አገር የግል ጉዳይ በቢሮ ስልክ ይወራል ብሎ የሚጠረጥር ደኅንነት የለም። ስለዚህ ሚስጥራችንም ደኅንነታችንም ተጠብቆ ወዳጅነታችን እንዲዘልቅ የቢሮ ስልክ ብቻ ተጠቀም።
- አሁን በግልጽ ተረድቻለሁ፣ ተቀብያለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሺ እጅህ ከምን፣ ምን አዲስ ነገር አለ?
- ስምምነቱን ፈጽሜያለሁ በነገው ጋዜጣ ላይ ይታተማል። ዲዛይኑንም ተመልክቼዋለሁ፡፡
- ጥሩ ሠርተውታል?
- በሚገባ። የጋዜጣውን የፊት ገጽ ሙሉ በሙሉ እርስዎ ይዘውታል። በዛ ላይ ፎቶዎትና ርዕሱ ተሰማምተዋል፡፡
- ተስማምተው ስትል?
- ፎቶውም የዓመቱ ምርጥ ነው ማለቴ ነው፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- ነገር ግን በነገው ጋዜጣ ለመታተም 70 በመቶ ክፍያው በቅድሚያ መፈጸም አለበት። ያው እንደተነጋገርነው ክፍያው በዶላር ነው መፈጸም ያለበት፡፡
- ስለእሱ አታስብ። ዛሬውኑ በፍጥነት ወደ ባንክ አካውንትህ ይተላለፋል፡፡
- መልካም ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ሚኒስትሩ ስልኩን ዘግተው በደስታ ስሜት ፈገግታ ውስጥ ሳሉ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪው ወደ ቢሯቸው ገባ]
- ከወዳጃችን ጋር ተነጋግረን ስንጨርስ ነው የመጣኸው። ጋዜጣው ነገ እንደሚወጣ አረጋግጦልኛል፡፡
- ቅድም የጋዜጣ ጉዳይ አይመለከተኝም ሲሉ አልነበረ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- የአንተ አማካሪነት ፋይዳ ነው ግራ የገባኝ? እኔ የምልህ መንግሥት የመደበልኝ ሁለት አጃቢዎች ፊት ስለዚህ ጉዳይ እንዳወራ ነው የምትፈልገው? እንዴት ነው የምታስበው ግን?
- ይቅርታ ያድርጉልኝ ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ እኮ አልፎ አልፎ አላስተውልም፡፡
- አልፎ አልፎ ነው የምታስተውለው እንጂ?
- ለማንኛውም ጋዜጣው ነገ እንደወጣ የማኅበራዊ ሚዲያ ሊጋችንን ማንቀሳቀስ እንዳትዘነጋ፣ ሊጉ ካልተንቀሳቀሰ ትርጉም የለውም፡፡
- ይህማ የሥራ ድርሻዬ ነው፡፡ በእኔ ይጣሉት፡፡
- ድርሻ ድርሻ አትበልብኝ አሁን ያዘዝኩህን አድርግ። ድርሻ… ይልቅ ድርሻ ስትል አስታወስከኝ?
- ምኑን?
- ‹‹ገበታ ለሀገር›› ለተባለው ፕሮጀክት የድርሻችሁን አዋጡ የሚለውን የበላይ አካል ደብዳቤ ወደ እናንተ መርቼ ነበር ምን ደረሰ?
- ባዘዙት መሠረት ከዘርፍ ኃላፊው ጋር ለሠራተኛው አሳውቀናል።
- ሠራተኛውን አማከራችሁ?
- ሠራተኛውን ማማከር ጉዳት አለው ብለን ትተነዋል፡፡
- የምን ጉዳት?
- ሠራተኛው በኑሮ ውድነት ምሬት እያሰማ የአንድ ወር ደመወዙን እንዲያዋጣ ማማከር ተቃውሞ ይቀሰቀሳል፡፡
- እና?
- ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ መሆኑን አሳውቀን ሁሉም ሠራተኛ የአንድ ወር ደመወዙን ለፕሮጀክቱ እንዲሰጥ መወሰኑን አስታውቀናል፡፡
- ጥሩ አድርጋችኋል። በዚህ ወቅት ተቃውሞ አልፈልግም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከዚሁ ጋር አያይዤ ያሰብኩት ጥሩ ዕቅድ አለኝ፡፡
- ምንድን ነው?
- የነገውን ዕለት ለመሥሪያ ቤታችን ድርብ በዓል የማድረግ፡፡
- ነገር አታጓት፣ አብራራው፡፡
- ያው ነገ ጋዜጣው የሚወጣበት ቀን በመሆኑ የአገር ውስጥ ሚዲያውም እንደሚያስተጋባው ይታወቃል። ይህንን የበለጠ ለማድመቅ ሠራተኛውን ወደ እንጦጦና ሸገር ፓርክ ወስዶ በማስጎብኘት የአንድ ወር ደመወዙን በፈቃደኝነት ለማበርከት መወሰኑን በማብሰር ዕለቱን ብናደምቀው ጥሩ አይደል?
- አሁን ጥሩ ነገር አመጣህ። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት ይኼ ነው፡፡
- የምን ሁለት ወፍ?
- ሠራተኛውም በዚህ መንፈሱ ይታደሳል፣ እኔም የጠሚው አጋር መሆኔን ወዳጅም ጠላትም ይረዳበታል፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- በል ዝግጅቱ ይፍጠን ጉዞው ለነገ ይሰናዳ። እኔም እንደምገኝ ገልጸህ ለሚዲያዎች ደብዳቤ ላክ፣ አለዚያ እነሱ ላይመጡ ይችላሉ፡፡
[በነጋታው ጠዋት ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው ገብተው በሌላ ስም የሚጠቀሙበትን የፌስቡክ ገጻቸውን እንደከፈቱ ‹‹ኢትዮጵያዊው የዓመቱ የአፍሪካ ሚኒስትር›› የሚል ርዕስና ፎቷቸው ያለበት አንድ የውጭ ጋዜጣ የፊት ገጽ መነጋገሪያ መሆኑን ተመለከቱ። በደስታ ተውጠው እርሳቸውም መረጃውን ሼር ለማድረግ እየሞከሩ አማካሪያቸው ወደ ቢሯቸው ገባ]
- ተመለከትከው?
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር ጥርት ብሎ ነው የወጣው። የፌስቡክ ሊጋችንም ጋዜጣውን የማጋራት ዘመቻውን አጧጡፎታል፡፡
- መልካም፡፡
- ግን አንዳንድ ጭፍኖች ገና ካሁኑ ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡
- የምን ችግር?
- የዓመቱ አፍሪካዊ ሚኒስትር የሚለውን የጋዜጣውን የፊት ገጽ ከሌሎች መረጃዎች ጋር እያጣመሩ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ እየለጠፉ ነው፡፡
- ሌሎች መረጃዎች ማለት?
- በእኛ መሥሪያ ቤት ሥር ያሉ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን አጣምረው የዓመቱ ምርጥ ሚኒስትር እያሉ ለማሽሟጠጥ እየሞከሩ ነው። ግን አያስቡ የጥቂት ጭፍኖች ተንኮል የትም አይደርስም፡፡
- እነዚህ ጭፍኖች አይደሉም፡፡
- እና ምንድን ናቸው?
- ፖለቲከኞች ጥንፈኞች እንላቸዋለን፡፡
- አልገባኝም?
- አይገባህም። እነዚህን ዝም ለማሰኘት ጥንፈኞች እንላቸዋለን። የሚኒስትሩን ብሔር የጠሉ ጥንፈኛ ብሔረተኞች ብለን ጩኸታቸውን መና ስለምናስቀረው ገና ብቅ ሲሉ ጥንፈኛ እንላቸዋለን፡፡
- ጥሩ መፍትሔ ናት። ደግሞ እኮ ጥንፈኛ ነው የሚመስሉት፡፡
- በል ወደ ጉብኝቱ ብንሄድ ይሻላል፡፡
[ሚኒስትሩ ሠራተኞቻቸውን ይዘው በአዲስ አበባ የተገነቡትን መናፈሻዎች እየጎበኙ ነው። ሠራተኛውን በመናፈሻ አንድ ስፍራ ሰብሰብ አድርገው ስለ ፓርኮቹ በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ እያወሩ ነው]
- እንዴት አገኛችሁት ታዲያ? ለውጡ ለውጡ ስንል ለቀልድ እንዳልሆነ የተረዳችሁ ይመስለኛል። ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የመፈጸም ብቃታችን የተገለጠበት አይደለም?
- አይደለም? [ከሠራተኛው መካከል አንድ ድምፅ ተሰማ። ሚኒስትሩ ሊያባርሩት የሚፈልጉት ዘወትር የሚሞግታቸው አንድ የሥራ ኃላፊ ነው]
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- የእኛ ብቃት የተገለጠበት ሳይሆን የተጋለጠበት ብንል አይሻልም ክቡር ሚኒስትር?
- ማወሳሰቡን ተውና ግልጹን ተናገር?
- በእኛ መሥሪያ ቤት ሥር ያሉ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ትዝ ብለውኝ ነው። እኛ መጨረስ ያልቻልናቸው ፕሮጀክቶችን ያጋለጠ፣ በራሳችን እንድናፍር ያደረገ ድንቅ ሥራ ነው ብለን እውነቱን ብንቀበል አይሻልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የእኛ ፕሮጀክቶች መጓተት በእኛ የመጣ ችግር አይደለም።
- በማን የመጣ ነው ታዲያ?
- በአገር የመጣ ነው፡፡
[ሠራተኛው አጉረመረመ]
- እየተማርን እንሠራለን፣ እየሠራን እንማራለን ብለን እንደ አገር በተከተልነው አቅጣጫ የመጣ ችግር ነው።
- የአሁኖቹስ?
- የትኞቹ?
- የመቶ ቀናት ዕቅዶቹ?
- የአሥር ዓመት መሪ ዕቅዳችን አካል እንዲሆኑ ወስነን የለም እንዴ?
[ሚኒስትሩ ጉብኝቱ ላይ በገጠማቸው እየተብከነከኑ ወደ ቢሯቸው ተመልሰው የፌስቡክ ገጻቸውን ከፈቱ። የዓመቱ አፍሪካዊ ሚኒስትር የሚለው በውጭ ሚዲያ ዕውቅና ያገኙበት ዘገባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬተሪ ፌስቡክ ገጽ ተጋርቶ ተመለክተው በፈገግታ ተዋጡ። አፍታም ሳይቆይ የግል ስልካቸው መጥራት ጀመረ]
-
-
- ጤና ይስጥልኝ አለቃ፡፡
- እንዴት አለህ ባለተራ?
- ተራ ነው ያሉኝ አለቃ?
- ተራ ሳይሆን ባለተራ፡፡
- አልገባኝም?
- የሳምንቱ የውጭ ሚዲያ ዕውቅና ባለተራ መሆንህን ተመልክቼ ነው?
- ተመለከቱት አለቃ …
- አዎ። አየሁት፡፡
- የብልጽግና ጉዟችን ከአገር አልፎ አድናቆት እየተቸረው መሆኑ ያስደስታል፡፡
- እየተቸረው ነው?
- እንዴታ፡፡
- አልመሰለኝም፡፡
- ምን ሊሆን ይችላል ታዲያ?
- እየተቸረቸረ!
-