Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተማሪዎች ምዝገባ ከነብዥታዎቹ

የተማሪዎች ምዝገባ ከነብዥታዎቹ

ቀን:

አንድ የኮሮና ወረርሽኝ ተጠቂ በኢትዮጵያ መገኘቱን ተከትሎ መንግሥት ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለሁለት ሳምንት እንዲዘጉ የወሰነው መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡ ውሳኔው ሲተላለፍ ተማሪዎች መጋቢት 21 ቀን ወደ መደበኛ ትምህርት ገበታቸው ይመለሳሉ ተብሎ እምነት ተጥሎ የነበረ ቢሆንም አልሆነም፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያ የሚገኙ ተማሪዎች እቤት ሆነው በቴሌግራምና በሌሎች አማራጭ ዘዴዎች እንዲማሩ ነበር ውሳኔ የተላለፈው፡፡

በኢትዮጵያ በአብዛኞቹ የግልና የመንግሥት በተለይም ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ አካባቢዎች ግን በቴክኖሎጂ የተደገፈውን የቅድመ መደበኛ፣ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከቴክኖሎጂ ተደራሽነት እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ግንዛቤ ችግር ምክንያት በአግባቡ መስጠት አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች በኩል ጥረት ተደርጓል፡፡

አስከፍለው የሚያስተምሩ ከመሆናቸው አንፃርም፣ መጀመሪያ ከ50 በመቶ እስከ 75 በመቶ ብቻ አስከፍለው እንዲያስተምሩ መንግሥት በወሰነው መሠረት ትምህርቱን በቴሌግራምና በዚህ መጠቀም ላልቻሉት የታተሙትን ወይም ሶፍት ኮፒውን ለወላጅ በመስጠት ትምህርቱን ሰጥተዋል፡፡

ምንም እንኳን የዚህ ዓይነቱ አካሄድ የመጀመርያ ከመሆኑ አኳያ የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ የሚያስችል ባይሆንም ተማሪዎች በኮሮና ተፅዕኖ ምክንያት ከሁሉም ያጡ እንዳይሆኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ለሁለት ሳምንት ተብሎ የተዘጋው ትምህርት እስከ ሰኔ 30 ቀን የዘለቀ ሲሆን፣ ትምህርት ሚኒስቴር ከ8ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በስተቀር ሁሉም ተማሪዎች ወደ ቀጣይ ክፍል እንዲሸጋገሩ ወስኗል፡፡

የኮሮና ሁኔታ ታይቶ ተማሪዎች ትምህርት ሲጀምሩ፣ ለሦስት ወራት ያህል ያጡትን የገጽ ለገጽ ትምህርት እንደሚያካክሱ የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለ45 ቀናት ያህል ክለሳ ተሰጥቷቸው ክልላዊና ብሔራዊ ፈተና እንደሚወስዱም አሳውቋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት በኢትዮጵያ በሚገኙ በቅድመ መደበኛ፣ በጎልማሶች ትምህርት፣ በመጀመርያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጡ ከ42 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች የነበሩ ሲሆን፣ በእነዚህም ከ23 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ነበሩ፡፡

ተማሪዎቹን ከወረርሽኙ መጠበቂያው መንገድ ቤት ማስቀመጥ ብቻ መሆኑ ታምኖበት በወቅቱ ውሳኔ መሰጠቱ በርካታ አዎንታዊ ጎኖች ቢኖሩትም፣ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም አልቀረም፡፡ ከትምህርት ገበታቸው ያቋረጡ ሴት ታዳጊዎች በተለይ በክልሎች ለጠለፋና ለጋብቻ ተዳርገዋል፡፡ አንዳንዶች ረዥሙን ሰዓት ቤት በማሳለፋቸው ሳቢያ ለሥነልቦናዊ ለአካላዊ ጥቃት ተጋልጠዋል፡፡ ከትምህርት ቤት ሊያገኙ የሚችሉትን ዕውቀትና ማኅበራዊ መስተጋብር አጥተዋል፡፡ በየአካባቢያቸው ወጥተው እንደቀደመው ጊዜ ከመጫወት ታግደዋል፡፡ ምንም እንኳን ኮሮናን ለመከላከል የሚያስችሉ ቅድመ ጥንቃቄዎች ላይ ኅብረተሰቡ ቸልተኛ ቢሆንም፣ የልጅ ጉዳይ ነውና ወላጆች ልጆቻቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ያቅማቸውን እንደሚያደርጉ በጥቂቱም ቢሆን መታዘብ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ከአውሮፓና አሜሪካ በተለየ መልኩ አዝጋሚ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በኅብረተሰቡ ዘልቆ መስፋፋት ጀምሯል፡፡ በዚህም ለኮቪድ-19 ታካሚዎች የተዘጋጁ የሕክምና ማዕከላት እየሞሉ፣ የፅኑ ሕሙማን ክፍል ታካሚዎችም እየበረከቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም የፅኑ ሕሙማን ክፍል እየሞላ መሆኑን፣ የቫይረሱ ሥርጭት በዚህ ከቀጠለ ሌሎች አገሮች የገጠማቸውን ዓይነት የጤና ቀውስ ሊከሰትና ሰው ሠራሽ የመተንፈሻ አካልም ቢሆን በወረፋ ሊደረግ እንደሚችል አስታውቋል፡፡

የቫይረሱ ሥርጭት በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን እስከሚያሳውቅ ትምህርት እንዳይጀመር ሆኖም ለቅድመ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ የተማሪዎች ምዝገባ እንዲከናወን መወሰኑ በወላጆች ዘንድ ግርታን ፈጥሯል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው የጤና ባለሙያዎችም ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡

ወላጆች በየግል ትምህርት ቤቱ በመገኘት ልጆቻቸውን እያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ቅሬታቸውንና ሥጋታቸውን ከማሰማት አልተቆጠቡም፡፡ በተለይ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በኩል መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ሲገባ ከወሰነው ከ50 በመቶ እስከ 75 በመቶ የሚለው የክፍያ ሥርዓት አለመተግበሩ፣ ትምህርት በቴሌግራም ይሁን የገጽ ለገጽ ግልጽ አለመደረጉ፣ የቫይረሱ ሥርጭት ባየለበት ጊዜ ልጆችን ትምህርት ቤት ለመላክ የተመቻቸ ሁኔታ ሳይኖር ተማሪዎች ይመዝገቡ መባሉ ግራ እንዳጋባቸውም ወላጆች ነግረውናል፡፡

በግል ትምህርት ቤት ውስጥ የወላጅ ኮሚቴ አባል እንደሆኑ የነገሩን አስተያየት ሰጪ እንደ ወላጅ ኮሚቴ ትምህርት በመከፈቱ ላይ ባይነጋገሩበትም፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የቫይረሱ ሥርጭት ግን ትምህርት የሚያስከፍት አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ከቫይረሱ ሥርጭት አንፃር ልጆችን ትምህርት ቤት ለማዋል የሚያስችል አቅም አልተፈጠረም፡፡ ችግሩ ከትራንስፖርት እንደሚጀምር የሚናገሩት የወላጅ ኮሚቴ አባሉ ልጆች ትምህርት ቤት ደርሰውም ኮቪድ-19ን ተከላክሎ ለመማር የሚያስችላቸው ሁኔታ የለም ብለዋል፡፡

በሥራ አጋጣሚ ያዩዋቸው የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች ባብዛኛው ኮቪድ-19ን የመሰለ በቀላሉ ተዛማች ቫይረስን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የተቀመጡ መስፈርቶችን በአግባቡ አሟልተው እንደማይገኙም አክለዋል፡፡

የውኃ፣ የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት፣ የተማሪ ጥመርታ፣ መፀዳጃ ቤቶች የግቢ ሁኔታ አጠያያቂ በሆነበትና የልጆችን የመጫወት ባህሪ መገደብ አዳጋች መሆኑ ቫይረሱን ተከላክሎ ለማስተማር እንቅፋት ናቸው፡፡

ልጆች በፈረቃ ይማሩ ቢባል በቂ መምህራን ማግኘት እንደማይቻል፣ በፈረቃም ቢሆን የተማሪ ጥመርታውን በክፍል እስከ 15 እንኳን ለማውረድ ቢሞከር ቀድሞ በአንድ ክፍል ከሚይዙት ተማሪ አንፃር ቀኑን በሦስት ፈረቃ ቢከፍሉት እንኳን የማይችሉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው፣ በጣም ጥቂት  ከሚባሉ ትምህርት ቤቶች በስተቀር ለቫይረሱ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለመኖር፣ በተለይ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን (ዐፀደ ሕፃናት) ተቆጣጥሮ ለማስተማር የማይቻል መሆኑ፣ የገጽ ለገጽ ትምህርት እንዳይከፈት የሚያደርጉ ምክንያቶች መሆናቸውም ይጠቀሳል፡፡

ሆኖም በኮቪድ-19 ወቅት በግል ትምህርት ቤት የሚያገለግሉ መምህራን መበተን የለባቸውም፡፡ ችግሩን በጋራ ለመወጣት ተማሪዎች እንዲመዘገቡና የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እንዲማሩ በማድረግ የመምህራንንም ህልውና አስጠብቆ መሄድ ይቻላል፡፡

አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ቤት ተከራይተው የሚሠሩ መሆናቸውና ከ200 ሺሕ በላይ መምህራንም በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው ስለሚሠሩ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ክፍያ መፈጸሙ እንደማይጎዳ፣ ይህ የመምህራንንና የትምህርት ቤቶችን ህልውና እንደሚያስጠብቅ፣ ሆኖም ልጆችን ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ሁኔታዎች በሌሉበት ትምህርት ቤት መላኩ አዋጭ እንደማይሆንም አስተያየት የሰጡን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ደረጃ ሲታይ እስከ ሳምንቱ ማብቂያ ባሉት ጊዜያት ምዝገባ የተካሄደው በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ ነው፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች በተጀመረው የተማሪዎች ምዝገባ ላይ ደግሞ ወላጆች ቅሬታን አቅርበዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ መልስ ሰጥቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንደሚሉት፣ ሚኒስቴሩ የ2013 ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን እስከሚያሳውቅ ድረስ ማንኛውም ትምህርት ቤት ትምህርት መጀመር አይችልም፡፡

የመመዝገቢያና የትምህርት ክፍያን በተመለከተም ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም ያወጣውን መመርያ ተላልፈው የመዘገቡ ትምህርት ቤቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ከመመርያ ውጪ የሰበሰቡትን ገንዘብ ተመላሽ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር መጀመርያውኑ ጥርት ያለ መግለጫ ሳይሰጥ ሙሉ ከተከፈለ በኋላ እንደገና ማሳሰቢያ መስጠቱ ግልጽ የአፈጻጸም መመርያ አለመውረዱን ያሳያል ያሉት የወላጅ ኮሚቴው አባል፣ አሁንም የትምህርት አሰጣጡ ላይ ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ፣ ተማሪዎች የገጽ ለገጽ ትምህርት የማይጀምሩ ከሆነ በግል ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ወላጆች ለዩኒፎርምና ለተለያዩ የትምህርት ግብዓቶች የሚያውሉትን ወጪ ወደ ቴሌግራሙ እንዲያዞሩት ጥርት ያለ መረጃ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

ትምህርት መቼና በምን መልኩ እንደሚጀመር ግልጽ መረጃ ባይኖርም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ ለ2013 የትምህርት ዘመን ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዩኒፎርም፣ ጫማና የተለያዩ የትምህርት ግብዓት ለማሟላት 1.7 ቢሊዮን ብር እንደመደበ፣ 600 ሚሊዮን ብር ያህል ደግሞ ከኅብረተሰቡ ዕርዳታ እንደሚጠበቅ አሳውቋል፡፡ ይህ የገጽ ለገጽ ትምህርት መጀመርን አመላካች ሊሆን እንደሚችል፣ ይህ ከሆነም በምን መልኩ ይሆናል የሚለውን ሙያዊ በሆነ አካሄድ አጥንቶ ለትምህርት ቤቶችና ወላጆች ቢያሳውቅ የተፈጠረውን ብዥታ ማጥራት ያስችላል፡፡

‹‹ማስመዝገቡ ሳይሆን ልጄን ትምህርት ቤት እልካለሁ? አልልክም? የሚለውን መወሰን ነው ትልቁ ችግር›› የሚሉት የወላጆች ኮሚቴ አባሉ፣ በርካታ ያነጋገሯቸው ወላጆች ‹‹ላንልክ እንችላለን›› የሚል አስተያየት እንደሰጧቸው ነግረውናል፡፡

እስካሁን ባለን መረጃ በአዲስ አበባ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ያልተጀመረ ሲሆን፣ ኮቪድ-19ኝ ተከላክሎ ለማስተማር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅትም በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ሲከናወን አላየንም፡፡

በግል ትምህርት ቤቶች ምዝገባ መጀመሩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበርና ከወር በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ጣሰው፣ ተማሪዎችን በኮሮና ወቅት ለማስተማር ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል መመርያ ከትምህርት ሚኒስቴር ስላልወረደላቸው ተማሪዎችን ከመመዝገብ ውጭ ምንም እየሠሩ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በነበራቸው ውይይት አራት ሞጁሎች እንደተዘጋጁ ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም፣ ሞጁሎቹ ለጊዜው ስላልተሰጣቸው ሞጁሉን መሠረት አድርገው ለመዘጋጀት እንዳልቻሉም አክለዋል፡፡

‹‹ከትምህርት ሚኒስቴር የሚወርደውን መመርያ በጉጉት እየጠበቅን ነው›› ያሉት አቶ አበራ፣ መመርያው ቢወርድ ያሠራል አያሠራም በሚለው ላይ ተነጋግረን ዝግጅት እናደርግ ነበር ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹የግል ትምህርት ቤቶች ያላቸው አቅም አገሪቷ ያላት አቅም ነው›› ሲሉም፣ የገጽ ለገጽ ትምህርት ቢጀመር ትምህርት ቤቶች ሳሙናና ውኃ ያቀርቡ እንደሆነ እንጂ ሳኒታይዘርና ሌሎች የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ለማሟላት ይቸገራሉ ብለዋል፡፡

ክፍያን በተመለከተ፣ መንግሥት ያስቀመጠው ከ50 በመቶ እስከ 75 በመቶ ክፍያ የሚለው የትምህርት ቤቶችን ህልውና አስጠብቆ መሄድ እንደማይቻል፣ ለ2013 ዓ.ም. የጠየቁት ክፍያም ወላጆች በ2012 ዓ.ም. መጀመሪያ ሲያስከፍሉ የነበረውን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ 72 በመቶ ተማሪዎች በግል ትምህርት ቤት እንደሚማሩ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 60 በመቶ አካባቢ ይሆናሉ የሚል ግምት እንዳለ፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ሳይጨምር ከ200 ሺሕ ሩብ ሚሊዮን የሚጠጉ መምህራን በግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ፣ በአዲስ አበባ ብቻ 1,560 ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችንና መምህራንን በኮቪድ-19 ውስጥ እንዴት መማር ማስተማሩ ሒደት ማሳተፍ ይቻላል የሚለውን ለመወሰንና ለመዘጋጀት ትምህርት ሚኒስቴር ዕቅዱን ቀድሞ ሊያሳውቀን ይገባልም ብለዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ምዝገባ ይካሄድ ብሎ ከመወሰኑ አስቀድሞና በኋላም በእንግሊዝ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገሮች ትምህርት እየተጀመረ መሆኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሠራጫቸው ዜናዎች አስነብቧል፡፡ የገጽ ለገጽ ትምህርት የጀመሩ አገሮች ግን ትምህርትን ያስጀመሩት የበሽታው ሥርጭት ከላይ ደርሶ ማሽቆልቆል ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት እየወጣ እንጂ እየወረደ ባለመሆኑ የገጽ ለገጽ ትምህርት መጀመሩ ያስኬዳል ወይ? ስንል የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አመዘነ ታደሰ (ዶ/ር) ጠይቀናቸው ነበር፡፡

‹‹ይህ የሚሆን አይደለም›› በሚሉት ዶ/ር አመዘነ አገላለጽ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ያህል ተማሪዎች ይመዝገቡ ቢልም፣ የቫይረሱ ሥርጭት እየተስፋፋ ባለበት ሁኔታ ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ ያደርጋል የሚል እምነት የለም፡፡

የተማሪዎች የገጽ ለገጽ ትምህርት መጀመር ቫይረሱ ከተማሪዎች ወደ ቤተሰብ ከቤተሰብ ወደተማሪዎች እንዲሠራጭ እንደሚያደርግ ይህ በተለይ የልብ፣ የስኳርና ሌሎች ሕመም ያለባቸውን ተማሪዎች ለጉዳት ብሎም ለሞት እንደሚያጋልጥም ገልጸዋል፡፡

ልጆች ቤት ሲውሉ አሉታዊ ጫና እንደሚኖር የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚገነዘቡ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ልጆችን  ትምህርት ቤት መላኩ ቫይረሱ ከሚያመጣው ችግር አንፃር አዋጭ እንደማይሆንም አክለዋል፡፡

ትምህርት የጀመሩ ሌሎች አገሮች የቫይረሱን ከፍተኛ ሥርጭት አስተናግደው አሁን በሽታውን እየተቆጣጠሩና እየቀነሰ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ ገና ከፍተኛው ላይ አለመድረሱና መውረድ አለመጀመሩ ለየት ያደርገዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...