Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ በሁለት ቢሊዮን ብር የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ግል ይዞታ የተዛወረው የሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በሁለት ቢሊዮን ብር አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

በሦስት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በ600 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው ሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ፓርክ አክሲዮን ማኅበር የሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ተረክቦ ሲያስተዳድር ቆይቷል፡፡ አቶ ታምራት ዳመና፣ አላሚን መሐመድና አህመድ አብድሩፍ በተባሉ ባለሀብቶች ሲተዳደር የቆየው ፋብሪካው ክር በማምረት ላይ ይገኛል፡፡

የሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር ተወካይ አቶ ዘለዓለም ኩራባቸው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 14 ሼዶች ያሉት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ታዋቂ የሆኑ አልባሳት አምራች ኩባንያዎች እንደሚገቡበት አቶ ዘለዓለም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ በዓለም ገበያ ታዋቂ የሆኑ ብራንዶች አዲስ በሚገነባው ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ይመረታሉ፤›› ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ 350,000 ካሬ ሜትር ይዞታ ያለው በመሆኑ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በዚህ ክፍት ቦታ ላይ እንደሚገነባ አቶ ዘለዓለም ተናግረዋል፡፡ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ማካሄድ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚቀመጥ ታውቋል፡፡

በ1982 ዓ.ም. በመንግሥት የተገነባው የሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አንሶላ፣ የትራስ ልብስ፣ የተማሪና ሠራተኞች የደንብ ልብስና ክር በማምረት ይታወቅ ነበር፡፡ ፋብሪካው በገጠመው በገበያና የጥሬ ዕቃ ችግር ለረዥም ዓመታት ችግር ውስጥ ተዘፍቆ ኖሯል፡፡ የቀድሞ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በተለያየ ጊዜ ለአገር ውስጥና የውጪ ኩባንያዎች አስተላልፎት የነበረ ቢሆንም፣ የተፈለገው ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ እንዲያውም ፋብሪካው በኢትዮጰያ ልማት ባንክ ዕዳ ተዘፍቆ ቆይቷል፡፡

ከ1,200 ሠራተኞች ጋር ፋብሪካውን የተረከቡት አዲሶቹ ባለሀብቶች የፋብሪካውን አሮጌ ማሽኖች በመለወጥ ሥራውን እንደ አዲስ ማስጀመራቸውን አቶ ዘለዓለም ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ክር በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ የሚገነባው ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ከ35,000 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች