በኢትዮጵያውያን የተሠራና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል የተባለና ‹‹ጉዞ ጐ›› የተባለ በአምስት ቋንቋዎችና በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የተሠራ የኤሌክሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት መተግበሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ፡፡
ጉዞ ጐ የተሰኘው የበረራ ትኬት ሽያጭ ማከናወኛ ሶፍትዌር በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በትግሪኛ፣ በሶማሊኛና እንግሊዝኛ ወይም እንዲተገበር ያደረገው ሶልጌት ትራቭል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በረራ ካላቸው አሥር አየር መንገዶች ጋር የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴውን በመተግበር፣ በባንኩ በኩል የአየር ትኬት ሽያጭ በኦንላይን መጀመሩን የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች ነሐሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የስምምነት ሰነድ በመፈጸም ትግበራውን ይፋ አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን፣ አዲስ የተተገበረውን የኦንላይን ኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴን በሚመለከት እንደገለጹት፣ የክፍያ ሥርዓትን ከማዘመን አንፃር ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ሶልጌት ትራቭል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያበለፀገው ጉዞ ጐ ዲጂታላይዝ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መተግበሪያ፣ የአየር በረራ ትኬቶችን የመቁረጥና ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የክፍያ መተግበሪያው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ብር (CBE Birr) ወኪሎችና በመደበኛ የቅርንጫፍ መስኮቶች አማካይነት መተግበር እንደሚጀምርና በተጨማሪም በሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ ጋር ለማስተሳሰር እየተሠራ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ጠቁመዋል፡፡
ሶል ትራቭል የኤሌክትሮኒክስ የኦንላይን የጉዞ ወኪል አገልግሎት በመስጠት፣ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ድርጅት መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የሽያጭ መተግበሪያው የተሳሰረው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኤምሬትስ፣ ሉፍታንዛ፣ ኳታር፣ ተርክሽ፣ ኬንያ፣ ዱባይ፣ ገልፍ፣ ግብፅና ሳዑዲ አየር መንገዶች አማራጮችን በተለያዩ መመዘኛዎች በመተፈሽ የተሻለ ሆኖ ባገኙት አየር መንገድ መስተናገድ እንደሚችሉ በፈለጉት ቋንቋ መጠቀም (መስተናገድ) እንዲችሉ ገልጸዋል፡፡
ተጓዦች በአጭር ሰዓት ውስጥ ከሒሳባቸው (ከባንክ አካውንት) ተቀናሽ ተደርጎ የትኬት ክፍያው ተፈጽሞ አገልግሎቱ ማግኘት እንደሚችሉም አክለዋል፡፡ በቀጣይ ተቀዳሚ ደንበኞች የበረራ ቲኬት በብድር መግዛት የሚችሉበት አማራጭን ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን፣ ደንበኞች ‹‹ትኬት ጠፋብኝ›› የሚለውን ሥጋት የሚያስቀርና በረራን በመሰረዝ በድጋሚ ቦታ ማስያዝ የሚቻልበት አሠራር መዘርጋቱንም አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡
የሶል ትራቭል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ሺፈራው፣ ሶል ዲጂታላይዝ ኦንላይን ኤሌክትሮኒክስ የትኬት ሽያጭ ትግበራን በሚመለከት እንደገለጹት፣ አገልግሎት የመተግበሪያው ሶፍት ዌር የተሠራው በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሰሊጥ፣ በቆሎ፣ ቡናና ሌሎች አዝዕርቶችን መሸጥ ሳያስፈልጋት የራሷን ሶፍትዌር በማቅረብና አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያደርጋታል፡፡ ከአንድ ኩንታል የሰሊጥ ሽያጭ የሚገኘው 70 ዶላር መሆኑን ጠቁመው፣ በቀረበው ቴክኖሎጂ ከማንኛውም አገር ሆነው ለሚገኙ መንገደኞች አገልግሎቱን በመስጠት ከአንድ ሰው በደቂቃዎች ብቻ 70 ዶላር ማግኘት እንደሚቻል በንጽጽር አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም በርካታ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሥራዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡