Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአዲስ አበባ ስፖርት ትንሣኤ ያገኝ ይሆን?

የአዲስ አበባ ስፖርት ትንሣኤ ያገኝ ይሆን?

ቀን:

አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ስፖርት ጉልህ ድርሻ አበርክተው ያለፉ ስፖርተኞችን በማፍራት በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ ይሁን እንጂ ከተማዋ በአሁኑ ወቅት ስሟንና ዕድሜዋን የሚመጥን ብቻ ሳይሆን፣ በቅጡ ሊወክሏት የሚችሉ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንኳ አለመቻሏ ይነገራል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቀርበው በከተማዋ ውስጥ ቀደም ሲል የነበሩ ክፍት ቦታዎች ለግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲውሉ መደረጉ በዋናነት ሲጠቀስ፣ ሌላው በእኔነት ስሜት ለአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ዕድገት በዕቅድ የሚንቀሳቀስ አመራር ዕጦትና ያሉትም ቢሆኑ የከተማዋ ታዳጊዎች ላይ ከመሥራት ይልቅ የሌሎችን በመቀበል ለውድድር ብቻ ትኩረት መስጠት የሚሉት ለአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ውድቀት ምክንያት መሆናቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታን ጨምሮ ለሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶች የሚሰጠው ትኩረት ለስፖርቱ አነስተኛ መሆኑና ስፖርቱን እንዲያስተዳድር የሚሾሙ አመራሮች ብቃቱና ዝንባሌው እንዲሁም የአካዴሚ ዕውቀቱ ተመዝኖ ሳይሆን፣ ከሌሎች የልማት ተቋማት ዞር ለማድረግ በሚል መንፈስ መሆኑን በትልቁ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ የእኔነት ስሜት፣ የማዘውተሪያ ሥፍራ ዕጦትና መሬት መውረድ የማይችሉ ዕቅዶች ብዙዎቹ የከተማ ታዳጊዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ሥፍራ እንዲያሳልፉ፣ አለፍ ሲልም ለሱስና መሰል ችግሮች እንዲጋለጡ ምክንያት መሆኑ ጭምር በሰፊው ይነገራል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን በእነዚህ ችግሮች ተተብትቦ ለሚገኘው የከተማዋ ስፖርት ወደ ቀደመ ስምና ዝናው ለመመለስ ምን አቅዷል በሚሉትና ሌሎች ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙርያ ከኮሚሽነሩ አቶ ዮናስ አረጋይ ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ስሟንና ዕድሜዋን የሚመጥን የስፖርት መሠረተ ልማት እንደሌላት ይነገራል፡፡ ከዚህም በላይ ከተማዋ በተለያዩ የውድድር መድረኮች ከአብራኳ በፈሩ ታዳጊዎች ስትወከል አትታይም፣ ታዳጊዎችን በማፍራት ከቀደምቷ አዲስ አበባ ይልቅ የክልል ከተሞች በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ብዙ ማሳያዎች አሉ፣ ችግሩ ይታወቃል?

አቶ ዮናስ፡- ከሁሉ በፊት የአገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ ዋና ማጠንጠኛ ስፖርት ልማት እንደሆነ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ስፖርት ልማት መሆኑ ቢገባንም፣ በተለያየ ደረጃ ላይ ግን ልማት የሚመስለን ግንባታና መሰል ጉዳይ ለመሆኑ ስፖርቱ ያለበትን ደረጃ አመላካች ነው፡፡ ስፖርቱ ሲለማ የሚገኘው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ አምራች ኃይል በአካሉ የጠነከረ፣ በአዕምሮው ደግሞ የዳበረ ዜጋ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው በስፖርት ነው፡፡ ይህ ባለመደረጉ ሌላው ቀርቶ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ብቻ በጣም ትንንሽ የሆኑ ሕፃናት ተጎጅ ሲሆኑ እያየን ነው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች በመነሳት ለአዲስ አበባ ስፖርት ዕድገት ይበጃል ብለን አራት ተግባራትን ለይተናል፡፡ በቅደም ተከትል ስናስቀምጣቸው የመጀመርያ ማስ ስፖርት፣ ሁለተኛው ማዘውተሪያ ቦታና ሦስተኛው ታዳጊ ወጣቶች ላይ መሥራት ሲሆን፣ አራተኛው ውድድር ነው፡፡ ማስ ስፖርትና ውድድር በአገሪቱ በተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ቀሪዎቹ ታዳጊ ወጣቶችና ማዘውተሪያ ሲሆኑ፣ ውድድር በሌለበት ታዳጊ ወጣቶች ላይ እንሥራ ብንል የተሻሉትን ለመለየት ውድድር የግድ ስለሚያስፈልግ ማሳካት አልተቻለም፡፡ ማዘውተሪያ ቦታዎችም ለውድድር ተብሎ ስለሆነ የሚዘጋጁት ችግር መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ዝም ብለን ማዘውተሪያዎችን እንገንባ ቢባል ለግንባታ የሚያግዘን ገቢ ውድድሮች በመቋረጣቸው ሊገኝ አልቻለም፡፡ እዚህ ላይ ስፖርቱ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የመንግሥት ቋት በሚጠይቅበት አገር ከውድድር የሚገኝ ገቢ የሚለው ብዙም ባያስኬድም፣ ቫይረሱ የሚተላለፍባቸው መንገዶች በንክኪ መሆኑም በራሱ ጥርጊያ የሆኑ ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ለማዘጋጀት እንቅፋት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ከተማ አስተዳደሩ ወደ 63 የሚጠጉ ጥርጊያ የማዘውተሪያ ሥፍራዎችን አዘጋጅተን አጠናቀናል፡፡ ለምርቃት የክረምቱን መውጣት እየጠበቅን ነው፡፡ ይህ በቂ ነው ብለንም አናምንም፣ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

ሪፖርተር፡- የከተማውን የስፖርት ቤተሰብ ወረርሽኙን ለመከላከል ስትጠቀሙበት ታይቷል፣ በዚህስ ያገኛችሁት ጥቅም አለ ማለት ይቻላል?

አቶ ዮናስ፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ 36 ፌዴሬሽኖች በተለይም ደም ለመለገስ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ደግሞ ሕዝብ በብዛት በሚሰባሰብባቸው እንደ ሜክሲኮ፣ አራት ኪሎ፣ መርካቶ፣ መገናኛና ሌሎች አደባባዮች ላይ የስፖርቱ ቤተሰብ ራሱንና ቤተሰቡን ከወረርሽኙ መከላከል ይችል ዘንድ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ለተቸገሩና በሰላሙ ጊዜ የአገር ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ከ400 በላይ ስፖርተኞች በኮሚሽኑ አማካይነት ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ችግሩ ከተከሰተበት እስከ አሁን ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ለስፖርቱ ቤተሰብ ዕገዛ ተደርጓል፡፡ ከህዳሴ ግድብ ሙሌት ጋር በተገናኘ በአዲስ አበባ የሚገኙ ፌዴሬሽኖች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የመጀመርያዎቹ ነን፡፡ የማኔጅመንት አባላት ከወርኃዊ ደመወዛቸው ከመቶ እስከ አሥር በመቶ ለህዳሴ ግድቡ አውለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከማዘውተሪያ ሥፍራ ጋር ተያይዞ ኮሚሽኑ የሠራው ሥራ እንደሌለ ይነገራል፣ ዓመታትን ካስቆጠረው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጀምሮ በተጨባጭ ያለው ነገር ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ከያዛቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጠቀሳል፡፡ እውነት ነው ግንባታው ዓመታትን አስቆጥሯል፣ በአሁኑ ወቅት ግን ግንባታው ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ተጠናቋል፡፡ የሚቀረው ስክሪኖቹንና መሰል ትንንሽ ሥራዎች ካልሆነ በስተቀር በአጠቃላይ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎለት ግንባታው በሚፈለገው ልክ ተጠናቋል፡፡ እንደሚታወቀው ስታዲየሙ በርካታ አመራሮች ሲፈራረቁበት የቆየ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከመንገድ ጀምሮ የዓለም አቀፉንና የአኅጉር አቀፉን ስታንዳርድ በጠበቀ አግባብ ግንባታው ተጠናቋል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈዴሬሽን በኩል የፊፋና የካፍ ሙያተኞች መጥተው ዕውቅና እንዲሰጡት እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ይህ በተለይ ከተማችን ጤና ቡድን ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ የነበረውን ተግባር እንዲቀየር መነሻ ይሆነናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ውድድር ተኮር ሆኖ የቆየውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለመለወጥ ዕቅድ እንዳላችሁ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ፋይዳ ምን ሊሆን ነው?

አቶ ዮናስ፡- ትኩረታችን ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት ጀምሮ በየደረጃው እስከ 20 እና ከዚያም በላይ የሚገኙ የታዳጊዎች ላይ ነው፡፡ ስታዲየሙ በአብዛኛው የታዳጊዎች ማዕከል ሆኖ ግልጋሎት እንዲሰጥ ነው የምንፈልገው፡፡ ከአዲስ አበባ ከ121 ወረዳዎች ሁለት ሁለት በድምሩ ወደ 390 ያህል ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶችን መልምለን ሥልጠና ለመስጠት ነው ዕቅዳችን፡፡ ለዚህም ሲባል በውጭ ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ጋር ግንኙነት ማድረግ ጀምረናል፡፡ አንዳንዶቹ የፕሮጀክቱን ሐሳብ ሲቀበሉት ቀሪዎቹን ደግሞ የማሳመን ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ተስፋ ሰጪ ግብረ መልስ እያገኘን ነው፡፡ ከተማችን ስፖርተኞችን ተቀባይ ሳትሆን የታዳጊዎች መፍለቂያ እንደምትሆን የምናረጋግጥበት ብቸኛው ፕሮጀክታችን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የአቃቂ ስታዲየም ግንባታ 70 በመቶ ተጠናቋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሳር የማልበስ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ትራኩም ቢሆን ከግንባታው ጋር የተያያዙ ቀሪ ሥራዎች እስኪጠናቀቁ ካልሆነ የትራኩ ማንጠፊያ ተጠናቋል፡፡ በእርግጥ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ፣ የጣሪያው ብረቶች እየቆሙ ነው፡፡ አዲስ አበባ ሁሉም እንደሚያውቀው ትልቅ ከተማ በአንድ ለእናቱ ስታዲየም ተወስና ያለችበት ሁኔታ የሚያበቃበት ጊዜ እሩቅ አይደለም፡፡ ሌሎችም የራስ ኃይሉ ሜዳ ጨምሮ በርካታ ማዘውተሪያዎች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሌላው ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባር ላይ የሚውል ፓርኮችን ወደ ስፖርት ፓርክነት እንዲቀየሩ ማድረግ ነው፡፡ በአዋጅም እንዲወሰን አስደርገናል፡፡ ሰባ ደረጃ ለዚህ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል፡፡ ሰዎች ምን ያህል በዚህ ሥፍራ እየተዝናኑ ጤናቸውን እየጠበቁ እንደሆነ በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ እንደ ቀደምት ከተማነቷ የራሷ የሆነ የስፖርት ሳይንስ ምርምር የሚደረግበት ተቋም የላትም፡፡ ስፖርት ኮሚሽኑ ለመጪዎች የውድድር ዘመን የራሱ የሆነ የምርምር ተቋም የማስገንባት ዕቅድ እንዳለው ይነገራል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ ዮናስ፡- እውነት ነው ይህንኑ በአዋጁ እንዲካተት አድርገናል፡፡ ማዕከሉን የምናስገነባው በወወክማ አሊያም ራስ ኃይሉ ላይ  ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ስፖርት ሳይንስ ነው እያልን፣ አንድ እንኳ የምርምር ማዕከል የለንም፡፡ ይህን ማድረግ ስንችል ነው ታዳጊዎችን በበቂ ሁኔታ ማፍራት የምንችለው፡፡ ለዚህ ሲባል በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ምን ዓይነት ተሰጥኦ እንዳለ ተለይቶ ታውቋል፡፡ አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስና ሌሎችንም የታዳጊዎች ተሰጥኦና ክህሎት ለየትኛው ስፖርት እንደሆነ አጣርተን አውቀናል፡፡ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ከዚያም በከተማ ደረጃ መሰጠት ያለባቸው ሥልጠናዎች ዕድሜን አቅምንና ክህሎትን መሠረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡ እንዳለፉት ጊዜያት በጅምላ ሥልጠና የሚሰጥበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ በጀትም የምንይዘው ይህንኑ ታሳቢ አድርገን ነው፡፡ ይህን የምናደርግበት ዋናው ምክንያት የቆየውን የዕድሜ፣ የምልመላ፣ የክህሎትና ሌሎችም ችግሮች ለማጥራት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ መሥራት ካልቻልን የምንፈልገውን ጥራት ማምጣት አንችልም፡፡ የግድ ወደ ትክክለኛው አሠራር መምጣት ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ቁርጠኛ አቋም አለን፡፡ ጥንቃቄ ሳይለይ ግንዛቤ ለመፍጠር በተመረጡ ቦታዎች ላይ የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ እንዲያደርግ እያደረግን ነው፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ አዋቂዎችና ሕፃናት ከመኖሪያ ቤታቸው ሳይርቁ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ በአጠቃላይ አዲስ አበባ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ወደ ነበረችበት ለመመለስና ስፖርተኞችን ከሌሎች ክልሎች የምትቀበል ሳይሆን፣ የምትሰጥ ለማድረግ በዕቅድ መሥራት ለነገ የምንለው ጉዳይ እንዳልሆነ ተረድተናል፡፡ ካለው ውስብስብ ችግር አኳያ ውጤቱን እኛ ባንደርስበት እንኳ ቀጣዮቹ ትውልዶች እንዲጠቀሙበት ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዕቅዳችሁን ለማሳካት በዋናነት ችግር ይሆንብናል የሚሉት ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- እንደሚታወቀው አዲስ አበባ የመሬት ችግር የለባትም፡፡ ችግሩ መሬቱ የሚሰጠው ለፌዴራል ተቋም ነው፡፡ ይህን ማስተካከል የእኛ ተግባር ነው የሚሆነው፡፡ በተቻለ አቅም ከዝምታ ወጥተን ከተማችን የምትፈልገውን የስፖርት ልማት ለማምጣት በዕቅድና በፕላን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡ ስፖርቱን ማልማት ትውልድ የመፍጠርና የማነጽ ጉዳይ ስለሆነ የግንዛቤ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በርካታ ሲንከባለሉ የመጡ ውዝፍ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ለዚህ ነው ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ውድድር አቁመን ወደ ታች ወርደን መሥራት ይኖርብናል ያልኩት፡፡ አዲስ አበባን በመወከል ሲከናወኑ የነበሩ ውድድሮች ውሸትና ለታይታ ካልሆነ ፋይዳ እንዳልነበራቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቁጭ ብለን መክረን ተስማምተን ነው ውሳኔ ላይ የደረስነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእርስዎ እምነት የውድድሮች ዓላማና ግብ ምን ነበር?

አቶ ዮናስ፣ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ውድድር ካለ አበል አለ፡፡ በውድድር ሲጠቀም የኖረው እውነተኛው አትሌት ሳይሆን በዙሪያው የተሰባሰበው ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ተዋንያኑ ውድድር እንዲኖር የሚፈልጉት በሐሳብ እንጂ እውነተኛውን አትሌት ለመፍጠር እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን ደፈር ብሎ በመግባት አንድ ቦታ ላይ እንዲቆም ካልተደረገ ያስቸግራል፡፡ በዚህ ደረጃ ችግሮቻችንን ስንለይ የመጀመርያው ማዘውተሪያ ሲሆን፣ ሁለተኛው ታዳጊዎችን ማፍራት የሚለው ነው፡፡ ችግሩ ስፖርቱን ኅብረተሰቡ እንዲወደውና እንዲያዘወትረው አለመደረጉ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ስብሰባ ሳይሆን ማስ ስፖርት የመጀመርያው ምርጫችን አድርገን እየሠራን ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እንደምናገኝበት አልጠራጠርም፡፡ የስፖርቱ ዋነኛው ችግር አመራሩ ላይ ነው፡፡ በአግባቡ ከተመራ ውጤት የማይመጣበት ምክንያት የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነ በስፖርቱ አበርክቶ ለነበራቸው ግለሰቦችና ተቋማት የዕውቅና ፕሮግራም አዘጋጅቷል፣ ምክንያት ይኖረው ይሆን?

አቶ ዮናስ፡- መድረኩ በአጠቃላይ የተለያዩ ዓላማዎች ያሉት ነበር፣ አንዱና የመጀመርያው ክብርት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ የእንኳን ደህና መጡ የትውውቅ ፕሮግራም ሲሆን፣ በፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ታላላቅ አትሌቶች፣ የፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች፣ የክለብ አመራሮችና ዕውቅ የስፖርት ሰዎች የነበሩበት ነው፡፡ ሌላው የስፖርት ዋነኛው አንቀሳቃሽ አማተር ነው፣ ለዚህ አካል የምሰጠው ስጦታ ሞራል መጠበቅና ቀጥሎ የተሻለ እንዲሠራ ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ ያንን አድርገናል፡፡ ሌላው እዚያና እዚህ የምንመለከተው የጥላቻና የመጠላለፍ መንፈስ እንዲሰበርና ይቅር ለመባባል ነው፡፡ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከኢትዮጵያ አልፈው አፍሪካን መምራት የቻሉ  ናቸው፡፡ ያ የሆነበት ምክንያት መጠላለፍ ስለሌለ ነው፡፡ መጠላለፍ ስፖርቱን እየጎዳብን ነው፡፡ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ መድረኮች ላይ ተወካይ እያጣን ነው፡፡ ሰው ስለሌለን አይደለም፣ ሰው አለን ግን ክፉ የሆነ መጠላለፍ ተጠናውቶናል፡፡ ለስፖርታችንና ለሰላማችን ስንል ችግሩን ለምን ልንለው ይገባል፡፡ በዚህ ደረጃ እንደ አዲስ አበባ የሚጠበቅብንን መወርወር ከቻልን ነገና ከነገ ወዲያ ወደ ሌሎች ክልሎች ይሄዳል፣ ማድነቅ መሸነፍ እንዳልሆነ ሊገባን ይገባል፡፡ ስለሆነም የፕሮግራሙ ማጠንጠኛ ዕውቅና ለሚገባቸው ዕውቅና ለመስጠት ነው፡፡ ሌላው ለከተማችን ተማሪዎች ጫማ ማድረግ እንዲችሉ ለማድረግ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሦስት ቀን ውስጥ እስከ 20 ሺህ ለሚጠጉ የከተማችን ተማሪዎች ጫማ እንዲለብሱ ለማድረግ ነው፣ ተሳክቶልናልም፡፡

ሪፖርተር፡- በስፖርቱ መቀየር አለበት የሚሉት ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- አንዱና ዋነኛው የአመለካከት ችግር ነው፡፡ ስፖርት ቁልፍ ሴክተር መሆኑን አምኖ ለዚያ የሚመጥኑ አመራሮች ያስፈልጉታል፡፡ ከስፖርት ውጭ ለነበሩ ቁልፍ ሴክተሮች ተመድበው የማይመጥኑ ከሆነ ገሸሽ እንዲሉና ስፖርቱ ላይ እንዲመደቡ የሚደረግበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ካልተቀየረ ስፖርቱን መቀየር አይቻልም፡፡ መታረም ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስፖርቱ አቅም፣ ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝነትና ቀናነት ያላቸው አመራሮችን ይፈልጋል፡፡ ግን ደግሞ እስካሁን ባለኝ ምልከታዬ ይህን አላስተዋልኩም፡፡ አመራሩ በሠራውና ባስገኘው ውጤት የሚለካ፣ ተቆጥሮ የተሰጠውን ቆጥሮ የሚያስረክብ ሲሆን ያለአንዳች ጥርጣሬ ስፖርታችን ይለወጣል፡፡ ‹‹አሳ ያለባህር፣ ዶሮ ያለእንቁላል›› እንደሚባለው ስፖርትም ያለአቅምና ዕውቀት ሊሆን አይችልም፡፡                                          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...