Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አፍሪካ በመሪዎቿ የተጎዳች አኅጉር ነች፡፡ ለአፍሪካ ኋላ ቀርነት መሪዎቿ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ከተገልጋይነት ባለፈ ለቆሙለት ሕዝብ ያገልጋይነት ታሪክ  አልታደሉም። በአኅጉሪቱ አገልጋይ መሪ ማየት እጅግ ብርቅ ነገር ነው። መሪዎቿ ለሙስና የተፈጠሩ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በታሪክ ማህደር የሥልጣኔና የጥንተ ነገር ምንጭ  ብሎ ታሪክ  የሚዘክራት ኢትዮጵያም የመሪዎቿ ታሪክ ከአፍሪካውያን እጣ ፋንታ ብዙም የተለየ አይደለም። አገራችን በታሪክ ሕዝብን ከፍ ዝቅ ብሎ ሊያገለግል የሚችል መሪ አለመታደሏ ድህነትና  ድንቁርና  ከላይ የታደለችው ይመስል ሥር ሰዶ   ኖሮባታል ። ከአምባገነን መሪዎቿ ባለፈ የጎሳና የእርስ በርስ   ጦርነት  ታሪኳ ነባር ሥልጣኔዋ ዘመን ተሻግሮ እንዳይዘምን ደንቃራ ሆኖባት ኖሯል።

ስለዚህአገልጋይ መሪበሚለው ሚዛን ስንመዝናቸው የኢትዮጵያ ነገሥታትም ሆኑ አምባገነን መሪዎቿ ተገልጋይ እንጂ የአገልጋይነት ሚና አልነበራቸውም። ነገር ግን ማንም ኢትዮጵያዊነቱን የሚወድ ይህችን ሦስት ሺሕ ዓመታት ወይዘሮ ከእነማንነቷ፣ ትውፊቷና ባህሏ ሳይበረዝ፣ ቋንቋዎቿ ጭምር ሰብአዊነት ኖሯቸው በሕይወት   ላቆዩልን   ነገሥታት  መሪዎቻችን  ክብር መስጠት የሚያሳፍር ተግባር  አይመስለኝም፡፡

አበው ከአንዴም  ሁለቴ ሰውነትን ከሚያሳንስ  ነጭ ወራሪ  ራሳቸውን ሰውተው አገር አውርሰውናል። ክብር ይገባቸዋል። ጥቁር እንደ በቆሎ ፍሬ ተገላልጦ  ይሸጥ በነበረበት ዘመን  ዓድዋ  ከፍታ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለውሰውነታችንንለዓለም የመሰከሩ ነገሥታት አበውን እርባና ቢስ አድርጎ ለመፈረጅ ጫፍ መርገጥ   ጋጠ ወጥነት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

ስለዚህ በሌለ ትርክት ተመርዞ  ፅንፍ የያዘ ትውልድን በድፍረት  ማስተማር ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል ባይ ነኝ። በተለይ የታሪክ ምሁራን፣ መምህራን  በሚዲያዎች አማካይነት ሚዛን የሚደፋ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል። እነእገሌን እንዳይከፋቸው በሚል ከሙያ በታች አንሶ መቆም ግን  ከሚዲያ ሰዎችም ሆነ ከታሪክ ምሁራን ፈጽሞ አይጠበቅም።

ሌላው አበው ነገሥታት  የአገልጋይነት ሚና ባይኖራቸውም እንኳ ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ሥጋ ሊከፋፍሏት ከተነሱ የጎሳ አበጋዞች የታደጓት ዓለም ይጠቀመው በነበረው የትግል ስልት ነበር። በዲፕሎማሲ  የተሠራ አገር  አለ ብሎ መናገር ይከብዳል።ዓለም ላይ የትኛውም ኃያል  አገር የጎሳ ትግልን አልፎ  የተሠራ  እንጂ በጠረጴዛ ዙርያ  የተመሠረት  አገር  አለ ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡

ምናልባት እንደነ ቫቲካን ያሉ  በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ቁጥር ትንሽ የሚባሉ አገሮች ካልሆነ በቀር  ምዕራባውያንም ሆኑ፣ ቻይና እና ህንድን ጨምሮ  ሌሎችም ምሰሷቸው የቆመው ከአስጨናቂ  የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ነበር። ኢትዮጵያም ጊዜው ያምንበት የነበረ የጦርነት ታሪክ አልፋ የታደልናት የጋራ ቤታችን ናት፡፡

ታዲያ  ይህ የጋራ ታሪካችን  ዛሬ  ላይ  ይህን ያህል ልዩነት ሆኖ ሲያነቃቅሰን   አልፎም  ግጭት ላይ  ሲወረውረን እኛ ከትናንት በምን ተሻልን? ትናንትን በትናንት እንጂ  በዛሬ ሚዛን እየሠፈሩ መፍረድ  ይህን ዘመን የማይዋጅ ሌላ ስህተት መጨመር ይሆናል።

ይሁን እንጂ ነገሥታት የአገልጋይነት ግብር  ባይኖራቸውም እንኳ  አዲስ ሥልጣኔን ግንባር ቀደም ሆኖ በመሻትና  በመምራት ብሎም  ተራማጅ ሆኖ በመከተል  አልፎም  ተጠቅሞ  በማሳየት በኩል  የነበራቸው ሚና  ጉልህ ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ ከዘመነ አክሱም  የኪነ ሐውልት ትሩፋቶች እስከ ንጉሥ ላሊበላና አፄ ፋሲል  በኪነ ሕንፃ ጥበባቸው አሁንም ድረስ  ዓለምን እየመሩ  ነው  

በሌላ በኩልም 18ኛው ምዕት ዓመት አጋማሽና  19ኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ መካከል በነበረው ዘመነ መሳፍንት  ተዳክማና አንድነቷን አጥታ የነበረችውን አገራችንን ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ   ኅብረ አንድነቷን ለማምጣት የሄዱበት ርቀት  ትውልድ የሚያፍርበት  ታሪክ አይደለም፡፡

ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ቀጥለው የመጡት የአፄ ዮሐንስ 4ኛም  ዳግማዊ ቴዎድሮስ ለሀገረ ኢትዮጵያ  አንድነት ከነበራቸው አቋም የተለየ አልነበረም። የተወሰደብንን የባሕር በር  ለማስመለስ ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ ደጋግመው  ደብዳቤ ይጽፉ እንደነበር   የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ትልቁ ታሪክ  ግን አፄ ዮሐንስትግራይ ተነስተው አፄ ቴዎድሮስ በነገሡበት ቤጌምድርና ስሜን ግዛት ውስጥ  በሚገኘው መተማ ላይ መውድቃቸው ነበር። ታዲያ ይህ ትውልድ ከዚህ ታሪክ የመማር ዕድል  ተሰጥቶት ሊማር አለመቻሉ  አያሳዝንም?

ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ወደ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ እስከ ምሥራቅ የዘመቱት፣ የዘለቁት የጥንቷን ኢትዮጵያ መልሶ ለትውልድ ለማስረከብ ነበር፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ የሚንፀባረቀው “አፄ ምኒልክ ተስፋፊ ናቸው” የሚል አገላለፅ ተገቢ አይደለም። ተስፋፊ ማለት ቀድሞ የራስ ያልነበረን  ቦታ  በኃይል መንጠቅ ማለት ስለሆነ። ይልቁንም ንጉሠ ነገሥቱ የጥንቷን ኢትዮጵያ  ከአካባቢያዊ ስሜት አላቅቀው፣ ሉዓላዊት ኢትዮጵያን አስረከቡን  ሊባል ይገባል  እንጂ፡፡

አንዳንዶች ያልተረዱት ነገር  ብዬ የማስበው አፄ ምኒልክን  ባሪያ ፈንጋይ ተብለው በቅርቡ ሐውልታቸው  ከተደረመሰው ከእነ ሰር ጆን ማክ ዶናልድ ጋር ሊመድቧቸው  ፅንፍ መያዙ ነው።

ይህ የለየለት ፅንፍ ገንግኖ ነገ  “ምነው በእንቁላሌ በቀጣሽኝ” ፀፀት ከመሆኑ በፊት  ገዥው አካል  ዳዴ ማለቱን አቁሞ ሕግ  ላይ አጠንክሮ ቢሠራ  መልካም ነው። ይህ ቢሆን ኖሮ በቅርቡ እንደ ቅጠል የረገፉ ነፍሳትን፣ የወደሙ ንብረቶችን በዓይናችን ባላየን ነበር። ሲጀመር የሰው ልጅ መንግሥት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የተገለጠለት ሕግና ሥርዓት እንዲኖረው፣  በሰላም ወጥቶ እንዲገባና ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖረው በማሰብ ነው፡፡

ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር የወጠኑት አፄ ምኒልክ፣የሰው ባሪያ የለውም፣ ሁላችንም የእግዚአብሔር ባሪያዎች ነን  እግዚአብሔር መርጦ፣ ከሰው አልቆ ሲያስገዛን ጊዜ፣ በሰው መጨከን አይገባም፣ ለሰው ቢያዝኑድሜ ይሰጣል፤   ብለው አባ ጅፋርን ይመክሩ እንደነበር  ጳውሎስ ኞኞ  በታሪክ ድርሳኑ ላይ ያስነብበናል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ   ነጋሪት ጎስመውራዊታቸውን በአደባባይ ገስፀው ሥርዓት  ያበጁ፣ ባርነትን የተጠየፉና ያወገዙ  ሰው  ሆነው ሳለ በታሪክ ላይ ያልተፈጸመ ልብ ወለድ ትርክት መለጠፍ  የረባ ርቀት አይወስድም፡፡ በሳል መሪና ዲፕሎማት የነበሩትንዳግማዊ  ምኒልክ ታሪክና  ሐውልት ለማፍረስ  መቧጠጥ፣ ዓድዋ ላይ የሰቀሉትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማን አንድንፈኛ  ቡድን በሰፋው ተራ ጨርቅ ለመቀየር መሞከር  አያዛልቅም፡፡ አልፎም የዓለም ጥቁሮችን ክብር መዳፈር ይሆናል። ምክንያቱም ዳግማዊ ምኒልክ የዓለም ጥቁሮች ቀንዲል የነፃነት ወጋገን ናቸው፡፡ በዓድዋ ከፍታ የሰቀሉት ይህ ሰንደቅም  ምድር ላይ የጥቁሮች ሁሉ የክብር ቀለም ነውና።

ዮሴፍ ዓለሙ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...