በዓለምገና ታዬ
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በክልሉ ያሉ አመራሮች በፌዴራል ደረጃ ያሉትም ጭምር ክልሉ በሕዝብ ይሁንታ አለመመሥረቱንና በዚሁ ምክንያትም እንደ ገና መዋቀር እንዳለበት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ የደቡብ ክልል ተወላጅ በመሆኔና ነዋሪነቴም በዚያው ስለሆነ የዘገየም ቢሆን ወቅቱ አላለፈምና እንደ አንድ ዜጋ የሚሰማኝን ለማንፀባረቅ ካለኝ ፍላጎት የተነሳ ከታች የሚከተለውን ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡
ኢሕአዴግ ደርግን ካስወገደ በኋላ የመንግሥት ሥልጣንን ሲይዝ አገሪቱን በ14 ክልሎች አዋቀረ፡፡ እነርሱም ክልል አንድ ትግራይ፣ ክልል ሁለት አፋር፣ ክልል ሦስት አማራ፣ ክልል አራት ኦሮሚያ፣ ክልል አምስት ሶማሌ፣ ክልል ስድስት ቤኒሻንጉልና ጉሙዝ፣ ክልል ሰባት ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ከምባታ ጠምባሮና ሀላባ፣ ክልል ስምንት ሲዳማና ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ፣ ክልል ዘጠኝ ወላይታ፣ ጋሞጎፋ፣ ዳውሮ፣ ክልል አሥር ደቡብ ኦሞ፣ ክልል 11 ከፋ ሸካና ቤንች ማጂ፣ ክልል 12 ጋምቤላ፣ ክልል 13 ሐረሪ፣ ክልል 14 አዲስ አበባ ናቸው፡፡
በዚያን ጊዜ እነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ክልል ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝ፣ አሥርና አሥራ አንድን የሚያስተሳስር የደቡብ ሕዝቦች ኅብረት የሚባል የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረታቸው በኢሕአዴግ ላይ የበላይነት መያዛቸው ሥጋት ላይ የጣለው የወያኔ መንግሥት የደቡብ ክልል ካድሬዎችን በማስተባበር ከላይ የተጠቀሱትን አምስት ክልሎች በማዋሃድ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መሥርቶ ክልላዊ አንድነት ያለው ደኢሕዴን የተባለ ድርጅት የፖለቲካና የአስተዳደር ጥንካሬ እንዲኖረው በማድረግ በእነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ድርጅት ላይ በኃይል ጭምር የበላይነትን ተቆናጦ እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቷል፡፡
የደቡብ ክልል ሲመሠረት ዋነኛው ምክንያት ፖለቲካዊ ቢሆንም በሥሩ የነበሩት ክልሎች ተቀራራቢ ባህል ያላቸው፣ ተመሳሳይ ሥነ ልቦና ያላቸውና ኩታ ገጠም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ያላቸው መሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ የደቡብ ክልል በዚህ መልኩ ቢመሠረትም የሕዝብን ይሁንታ ባለማግኘት ትግራይም ሆነ አማራ፣ ኦሮሚያም ሆነ ሶማሌ፣ አፋርም ሆነ ጋምቤላ ሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በሕዝብ ይሁንታ የተደገፉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የደቡብ ክልልን ከሌሎች ተለይቶ ክልሉ ተጨፈለቀ ተብሎ ዛሬ እንዲፈርስ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘረው ሐሳብ ውኃ የማይቋጥርና ምክንያታዊ ያልሆነ ነው፡፡
በደቡብ ክልል (መጠሪያውን ለማሳጠር ብዬ ነው ይቅርታ) የከፋ ሸካና ቤንች ማጂ ዞኖች ከሐዋሳ ያላቸው ርቀት ረዥም በመሆኑ ክልል መጠየቃቸው ምክንያታዊ ነው ሲባል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት ጭምር ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ይህም ክልሉን ለማፍረስ በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ ከደቡብ ክልል በቆዳ ስፋት ሦስት እጥፍ የሚበልጡት ኦሮሚያና ሶማሌ ክልል እንዲሁም በ150 ፐርሰንት የሚበልጠው አማራ ክልል ይህ ጥያቄ አልተነሳባቸውም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ርቀት ለክልል መፍረስ ምክንያት ቢሆን ኖሮ ኢሉአባቦራን፣ ጅማን፣ ወለጋን፣ ሸዋን፣ አርሲን፣ ባሌንና ሐረርጌን አንድ ላይ አጠቃሎ በያዘው ኦሮሚያ ክልል ከሱዳን ጠረፍ በመሀል አድርጎ ኬንያ ጠረፍ ከዚያም ድሬዳዋ ጫፍ ድረስ ያለው ሕዝብ በአንድ ክልል ሥር ባልተዋቀረም ነበር፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ከኬንያና ሶማሊያ ድንበር እስከ አፋርና ጅቡቲ አዋሳኝ የተንጣለለው ሶማሌ ክልል ከዶሎ ኦዶ እስከ ቀላፎ፣ ከቶጎጫሌ እስከ አፋር ያለው ሕዝብ በአንድ ክልል መቆየት አይፈልግም ነበር፡፡ ከሱዳን ጠረፍ እስከ ምንጃርና ሸንኮራ የተዘረጋው የአማራ ክልል ቆዳ ስፋት ጎንደርን፣ ጎጃምን፣ ወሎንና ሸዋን በአንድ አጠቃሎ ይዞ መቆየት አይችልም ነበር፡፡
በደቡብ ክልል ሥር ያሉ ዞኖች የሕዝብ ብዛታችን ትልቅ በመሆኑ መበታተን አለብን እንዳይሉ ከ33 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የያዘው የኦሮሚያ ክልልና ከ27 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያለው የአማራ ክልል ሁለቱም ገና ድሮ በተበታተኑ ነበር፡፡
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር ያሉ ሕዝቦች ለመንግሥታዊ አገልግሎት ሐዋሳ ድረስ መምጣት አላስፈለጋቸውም፡፡ ምክንያቱም የክልሉ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማስፈንና ሌሎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የመወሰን ሥልጣንን ለታችኛው የአስተዳደር መዋቅር በስፋት አውርዷል፡፡ ዜጎች ለፍትሕ ጉዳይ ሐዋሳ ድረስ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ቀጠሮአቸውንና ችሎቱን እዚያው ባሉበት በፕላዝማ የሚዳኙ ሲሆን ተዘዋዋሪ ችሎትም ሌላው አገልግሎት ነው፡፡ ወጪ በዛብን ለሚሉትም የወጪ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ በጀት ነው የሚመደብላቸው፡፡ የወጪ ፍላጎት ማለት አንድ ልማት ለማስፈጸም በአካባቢው ያለው የአንድ ግብዓት ወይም አገልግሎት የወቅቱ ነጠላ ዋጋ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በጀት የሚመደብላቸው ወጪአቸውን ያገናዘበ እስከ ሆነ ድረስ ርቀት ለወጪ መጨመር ምክንያት ሆኖ ለመበታተን ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡
ሲዳማ ዞን ከክልሉ ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ያሉ ሌሎች አሥራ አንድ ዞኖችም ክልል ለመሆን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል የመሆን መብት የሰጠ እንደመሆኑ መጠን የክልል ጥያቄው ማቆሚያ እንደሌለው በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡ ለምሳሌ ከጋሞጎፋ ዞን ተነጥሎ ዞን የሆነው ጎፋ ዞን አሁን ደግሞ የቁጫ ሕዝብና የቡልቂ አካባቢ ሕዝብ ራሳችንን መቻል አለብን የሚል ጥያቄ አንስተውበታል፡፡ በጉራጌ ዞን የማረቆ፣ የቀቤና፣ የሶዶ፣ የወለኔና የመስቃን አካባቢ ሕዝቦች ለአምስት አይቀራመቱትም ተብሎ አይታሰብም፡፡ የ‹‹ራሳችንን ችለን ከዞን/ከክልል እንውጣ›› ጥያቄ መንግሥት ከልማት ይልቅ ለአስተዳደራዊ ወጪ በጀት እንዲመድብ ከማስገደዱም በላይ በአጠቃላይ ለአገሪቱ ህልውና ደንቃራ ነው፡፡
ሲዳማ ክልል ሲሆን በአጠቃላይ ሒደቱ በሥርዓትና በተረጋጋ ሁኔታ ተጠንቶ አልተወሰነም፡፡ ሕዝብም በአግባቡ አልተወያየበትም፡፡ በደፈናው እንደ ኤርትራው መገንጠል ‹‹ነፃነት ወይም ባርነት›› ዓይነት ‹‹ጎጆ ወይም ሻፌታ›› በሚል በጥድፊያ ነው የተከናወነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ባካሄደው የሲዳማ ውሳኔ ሕዝብ ዓይነት መጪው አገራዊ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነም በግሌ ባልሳተፍ ደስ ይለኛል፡፡ በድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ክልል እንዲመርጥ ጫናዎች ነበሩ፡፡ በአንድነት ጉዳይ ቅስቀሳ እንዳይካሄድ ሁለንተናዊ ተፅዕኖዎች ነበሩ፡፡ ዞሮ ዞሮ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሒደቱ ላይ ችግሮች ቢኖሩም አጠቃላዩን ውጤት የሚያስቀይሩ አይደለም በሚል በለሆሳስ አልፎት አፅድቆታል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚገርመው ለውሳኔ ሕዝብ ማስፈጸሚያ የዋለው ገንዘብ ከደቡብ ክልል መሆኑ ነው፡፡ ሲዳማ ክልል መሆንን ሲመርጥ በደቡብ ክልል ሥር ያሉት ዞኖችና ወረዳዎች ወጪውን እንዲሸከሙ ተደርጓል፡፡ በዚህ ዓይነት ወላይታም ክልል ሲሆን ለውሳኔ ሕዝብ ማስፈጸሚያ ከቀሪዎቹ ዞኖች እየተቀነሰ ይሰጠዋል፡፡ በመቀጠልም ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀዲያ እያለ በቀሪዎቹ ላይ ተከታታይ ዕዳ ይጫናል፡፡ ስለዚህ የመጨረሻው ዕዳ ተሸካሚ ላለመሆን ዞኖች ለክልልነት መሽቀዳደም አለባቸው ማለት ነው፡፡
ሲዳማ በደቡብ ክልል ሥር በነበረበት ወቅት የበለጠ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ ስላልነበረ ክልል ለመሆን አሳማኝ ምክንያት አቅርቧል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የሆነው ሆኖ የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ያበቃና ያከተመ ጉዳይ በመሆኑ ለቀሪው የደቡብ ክልል ዞኖች ውሳኔ ስንሰጥ ምክንያታዊ መሆንና ከሲዳማ ክልል የመሆን ውሳኔ ትምህርት መውሰድ ይጠበቅብናል፡፡
ለቀሪው የደቡብ ክልል የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ መንግሥት በድንበርና ወሰን አከላለል ኮሚሽን በኩል አስጠናሁት ባለው መሠረት ክልሉ አራትና አምስት ቦታ እንዲዋቀር ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹55 ለ 1›› የሚለው ከሲዳማ ውጪ ያሉት ቀሪዎቹ ሃምሳ አምስት ብሔረሰቦች የደቡብ ክልልን እንደያዙ እንዲቆዩ ቢደረግ የተሻለ ነው የሚሉም አሉ፡፡
መንግሥትን በአጀንዳ ማጨናነቅ፣ በሕዝብ በተለይም ‹‹መጤ ነው›› ተብሎ በሚታመነው ዜጋ ላይ ግድያና ዝርፊያ ማካሄድ ለክልል ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ማግኛ ዘዴ መሆኑ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
ያለሕዝብ ውሳኔ፣ ያለመንግሥት ዕውቅና ‹‹እንኳን ወደ ወላይታ ብሔራዊ ክልል መጡ!›› የሚሉ ባነሮች በየወረዳው ተሰቅለው ነበር፡፡ ይህ የሆነው በራሳቸው በብልፅግና ፓርቲ አባላትና በዞኑ የመንግሥት አመራሮች ይሁንታ ጭምር ነው፡፡
በየዞኑ ያሉ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ሕዝብንና መንግሥትን ሰላም የሚነሱበት፣ አልፎም የፌዴራል መንግሥትን ሥልጣን የሚፈታተኑበት ሥውር እጅ ሆነው እያገለገሉ ናቸው፡፡
አሁን ሕዝብ አሳር መከራውን እያየ ያለው፣ በኢመደበኛ አደረጃጀቶች ነው፡፡ ማንኛውም ጥያቄ በውይይት ሳይሆን በጉልበት የማስፈጸም ባህል እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን እንዲያከስሙ ወይም ተጠያቂነት ወዳለበት ሕጋዊ አደረጃጀት እንዲለውጡ በተከታታይ ቢጠየቁም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በኢመደበኛ አደረጃጀቶችና አቋማቸው ባልጠራ የገዥ ፓርቲ ካድሬዎች ስውር እጅ ምክንያት የአገር መሠረተ ልማት ውድመትና የሕዝብ ዕልቂት ብቻ ሳይሆን የአገራችን ህልውናም አደጋ ላይ ነው፡፡
ለሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ በመሰጠቱ ምክንያት መላው ደቡብ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ከዚህ በኋላ 56ቱም ብሔረሰቦች ክልል እንሆናለን ብለው ቢጠይቁ አትችሉም ለማለት የማይቻል ከመሆኑም በላይ ከዚህ መለስ የሚመጡ የመፍትሔ ሐሳቦች ምንም ያህል ሳይንሳዊና እውነት ቢሆኑ ለማዳመጥ ያለው ፈቃደኝነት አነስተኛ ነው፡፡
በተለይም ክልሉ ሦስት፣ አራት ወይም አምስት ቦታ ቢደራጅ የሚለው ሐሳብ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ምክንያቱም አራትና አምስት ሆነው የመሠረቱት ክልል ርዕሰ ከተማ በአንድ ዞን የክልል ጥያቄ ምክንያት ሊቀሙ ስለሚችሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ሐዋሳ፣ 14 ዞኖች አንድ ከተማ አስተዳደርና አምስት ልዩ ወረዳዎች በርዕስ ከተማነት የመረጧት የደቡብ ክልል መቀመጫ ናት፡፡ ሐዋሳ እንደዚህ ተስፋፍታ ትልቅ ከተማ ለመሆን ከየዞኑ በጀት ተቀንሶ ለዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ ለመሠረተ ልማቶች ማስፋፊያ፣ ለክልል ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ግንባታ ግዙፍ በጀት ከየዞኑ ተቀንሶ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሲዳማ ክልል በመሆኑ ምክንያት ሐዋሳ ከተማችን ናት በማለት ዕድሜ ልካቸውን ሲገነቧት ኖረው ዛሬ አያገባችሁም ተብለዋል፡፡
የንብረት ክፍፍል ይኖራል ቢባልም ዋናውን መሠረታዊ እምነት የጣሰ ይሆናል፡፡ ዛሬ ሦስት አራት ሆናችሁ በአንድ ክልል ተደራጁ ቢባልም ተቀባይነት የሌለው ነገ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይገጥመናል በሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ጎፋ፣ ዳውሮ ወይም ጋሞ ዞኖች ከወላይታ ጋር በአንድ ክልል ሥር ተደራጁ ቢባሉ ሶዶን በክልል ርዕሰ ከተማነት ከገነቧት በኋላ ወላይታም ክልል ለመሆን ጥያቄ ቢያቀርብ በተመሳሳይ ሁኔታ እንቀማለን ብለው ይሠጋሉ፡፡
ስለዚህ እንደ አንድ ዜጋ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርብ ብባል፣ ሒደቱ አሳማኝ ባይሆንም ሲዳማ ክልል ሆኗል፡፡ ስለዚህ ማሰብና መጨነቅ ያለብን ለቀሪው የደቡብ ክልል ነው፡፡ ክልሉን በሦስት፣ በአራት ወይም 56 ቦታ ማደራጀት አስተዳደራዊ ወጪን ከማናር ውጪ ጠብ የሚል ጥቅም የለውም፡፡
ሲዳማ ዞን ክልል በመሆኑ ምክንያት በ2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት ያገኘው የበጀት ጭማሪ የለም፡፡ በየዓመቱ በሁሉም ደረጃ ከሚገኝ መጠነኛ ጭማሪ በስተቀር ሲዳማ በዚህ ዓመት ያገኘው የበጀት መጠን ዞን በነበረበት ጊዜ ያገኝ የነበረውን ያህል ነው፡፡ ይህም ሆኖ፣ ወደ ሃምሣ የሚሆኑ ክልላዊ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን ማቋቋም፣ ለእነዚህ አላቂና ቋሚ የቢሮ ዕቃዎችን ማሟላት፣ ቢያንስ ለእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት አንድ ተሽከርካሪ መግዛት፣ ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ በጀት መመደብ፣ ከአምስት ሺሕ ያላነሰ የሰው ኃይል መቅጠር ይጠበቅበታል፡፡ በሥሩ ሌሎች ሦስት ወይም አራት ዞኖችን እንደ አዲስ ስለሚያዋቅር ወጪው በዚሁ መልኩ እጅግ እየናረ ይሄዳል፡፡ ክልሉ በዚህ ዓይነት የትምህርትና የጤና አገልግሎት ለማቅረብ፣ የመጠጥ ውኃን ለማዳረስና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም በጀት ያጥረዋል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲዳማ ዞን ሆኖ ለልማት ያገኝ የነበረውን በጀት ክልል በመሆኑ ምክንያት ለአስተዳደራዊ ወጪ ለማዋል ስለሚገደድ የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚቸገር እሙን ነው፡፡
የፌዴራል የድጎማ በጀት በቀመር የሚከፋፈል እስከሆነ ድረስ ለአንድ ሕዝብ በወረዳ፣ በዞንም ሆነ በክልል ቢደራጅ ልዩነት የለውም፡፡ ስለዚህ የመንግሥት አገልግሎትን ከተጠያቂነት ጋር ይበልጥ ወደ ታችኛው የአስተዳደር እርከን በማውረድ ተደራሽ ማድረግ ቁልፍና ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በተጨማሪም በአጓጉል ካድሬዎች እየደረሰበት ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር በወሳኝ መልኩ ሊፈታ ይገባዋል፡፡ ከሲዳማ ውጪ ያለው ቀሪው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአንድነት ከመቀጠል ውጪ አማራጭ የለውም፡፡ የሚያገኛትን በጀት አስተዳደራዊ ወጪን በማያስከትል መልኩ ለልማት ማዋል የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በክልሉ ያሉ ዞኖችና ወረዳዎች ከ2013 በጀት ዓመት የሚታሰብ ብር በብድር ወስደው በ2012 በጀት ዓመት ሥራ ላይ ያዋሉ በመሆኑ፣ አብዛኛዎቹ እንኳን በክልል ደረጃ ለመዋቀር ቀርቶ ያሉበትንም አስተዳደራዊ መዋቅር ለማስቀጠል ከማይችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው፡፡ ከዓመት ዓመት የሠራተኛ ደመወዝ እንኳን ለመሸፈን የሚንገዳገዱ ናቸው፡፡ በራሳቸው ገቢ ወጪያቸውን የመሸፈን ባህል ስላላሳደጉ የፌዴራል የድጎማ በጀት ባይኖር ኖሮ ገና ድሮ ህልውናቸው ባከተመ ነበር፡፡
ስለዚህ ይህ እውነታ ለሰፊው የደቡብ ክልል ሕዝብ በየደረጃው ተገልጾለት በአንድነት ለመቀጠል ራሱ እንዲወስን ማስቻል ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ያለውን የተማረ አካል በማግለል በካድሬዎች ግርግርታ ክልሉን በቅርጫ ለመከፋፈል የሚደረግው ግፊትና ግጭት ማቆም አለበት፡፡ በሰከነና በሰለጠነ አኳኋን ለሕዝብ የሚጠቅም አደረጃጀት ሥራ ላይ ማዋል ግዴታችን ነው፡፡
ሐዋሳ ከተማ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከበጀታቸው ቀንሰው የገነቧት ከተማ እንደመሆኗ መጠን የሲዳማ ሕዝብ ከከተማዋ ሊያገኝ የሚችለው ጥቅም በሕግ እንደተጠበቀ ሆኖ ለቀሪው የደቡብ ክልል መቀመጫ እንድትሆን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ለደቡብ ክልል ሌላ ርዕሰ ከተማ እንወስንለት የሚባል ከሆነም ሁሉም የእኔ ከተማ ካልሆነ ሌላውን ዞን አላምንም ወደሚል አቅጣጫ ሐሳቡን ስለሚያዞር ተመልሶ ያው ጭቃ ነው የሚሆነው፡፡
ወረዳ፣ ዞን ወይም ክልል ለመሆን ድንጋይ መወርወር፣ ጎማ ማቃጠል ወይም መንገድ መዝጋት አያስፈልገውም፡፡ ቅንነቱ ካለ ጥያቄው ደረጃውን ጠብቆ በማቅረብ ምላሽ በትዕግሥት በመጠበቅ ሁሉም ነገር ሲደራጅ በውሳኔ ሕዝብ ማስፈጸም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የሚመሩት መንግሥት ቁልፍ የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በሚታትርበት በአሁኑ ወቅት ላይ ተነስቶ ዛሬውኑ ካልተወሰነልኝ ማለት ለሕዝብ ከማሰብ ሳይሆን የንፁሀንን ደም ለማፍሰስ ከመቋመጥ የተነሳ ነው፡፡
የግብፅ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ እ.ኤ.አ. ጁን 3 ቀን 2013 በመሩት አገራዊ ስብሰባ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስቆም ከተሰነዘሩት አንድ ስድስት ከሚሆኑ አማራጮች ውስጥ የኢትዮጵያን ሰላም ማናጋት አንዱ መሆኑ በይፋ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ነፍጥ ያነሱ ተቃዋሚዎችን መርዳት አለብን ሲሉ አይማን ኑር የተባሉ ተሰብሳቢ ሐሳብ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን መሐመድ አንዋር አል ሳዳት የተባሉት ሌላው ተሳታፊ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች መካከል ግጭት እንዲነሳ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ መክተት ግድቡን በማስቆም ረገድ ውጤታማ ያደርገናል በማለት ያቀረቡት ሐሳብ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ዓለም የተከታተለው ነው፡፡ በተግባርም ግብፃውያን በካይሮ የኦነግ አባላትን በማሰባሰብ ፀረ ኢትዮጵያ ዲስኩሮችን ሲያሰሙ በተጨባጭ ያየነው ነው፡፡
ስለሆነም በየሥፍራው ያሉ ግጭቶች ግብፅ የምታካሂደው ፕሮጀክት አካል መሆናቸውን የግድ ከመንግሥታችን መግለጫ ወይም ማረጋገጫ መጠበቅ የለብንም፡፡ ይሄ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡
ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሰት ትርምስ ግብፅ በሥልጣን ያኮረፈ ድርጅትና ግለሰቦችንም ጭምር ትጠቀማለች፡፡ ኦሮሚያ ክልልም ሆነ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ ክልልም ሆነ ጋምቤላ፣ ደቡብ ክልልም ሆነ ድሬዳዋ አስተዳደር፣ ሐረሪ ክልልም ሆነ አፋር ግጭት ከተከሰተ ዞሮ ዞሮ ማጠንጠኛው፣ ጭራው የሚገኘው ከግብፅ ዘንድ ነው፡፡
ስለዚህ፣ በአሁኑ ወቅት ከመንግሥታችን ጋር በሰላማዊ መንገድ በውይይት ችግሮችን ከመፍታትና ለአገራዊ አንድነት መፍትሔ ከመሻት ይልቅ ዛሬ ካልተፈጸመልኝ ብሎ በየሰበብ አስባቡ ድንጋይ መወርወር፣ ሕዝብን መግደልና ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደምና መንገድ መዝጋት በቀጥታ ከግብፅ መንግሥት ጋር ተባብሮ በታላቁ ህዳሴ ግድብና አልፎም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተቃጣ አደጋ በመሆኑ መንግሥትም ሆነ ሕዝባችን አንታገሰውም፡፡ አጥፊዎች አገር ከሀዲዎች ለሌላው ትምህርት በሚሆን መልኩ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡
አገር በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት፣ በኢኮኖሚ ፈተናዎች፣ በአገራዊ ምርጫ አጀንዳና በዓባይ ፖለቲካ ጡዘት ውስጥ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ማንኛውም የወረዳ፣ የዞንና የክልል መሆን ጥያቄ መመለስ የሚቻልበት የተረጋጋ ሁኔታ ስለሌለ በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ የጊዜ ገደብም ሊቀመጥለት ይገባል፡፡ ክልል መሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢሆንም መብት ጠያቂዎች ክልል ለመሆን በሚያስችል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቁመና ላይ መድረሳቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም በላይ ማንኛውም ልዩ ወረዳም ሆነ ዞን ክልል ለመሆን ካስፈለገው ከፌዴራል የበጀት ድጋፍ ወጥቶ በራሱ ገቢ በጀቱን ለመሸፈን በሚያስችል አቅም ላይ መድረሱ ካላረጋገጠ መፈቀድ የለበትም ባይ ነኝ፡፡
ደቡብ ክልልን በማፍረስ በአገራዊ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተሳትፎው ላይ አቅም እንዳይኖረው እስከወዲያኛው ለመበታተንና ለማዳከም ብሎም የራስን ተፅዕኖ በማሳረፍ የሚደረገው ተንኮልና ሴራ ሊወገዝ ይገባል፡፡
የክልሉ ሕዝብ መበታተን ይጠቅመኛል ካለም አንድ መሆኑ ያመጣውን ጉዳት በመመርመርና በስፋት ተወያይቶ በረጋ መንፈስ ጊዜ ሰጥቶ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ የአንዳንድ ካድሬዎችና የኢመደበኛ አደረጃጀቶችን አካሄድ በፅኑ መቃወም ያስፈልጋል፡፡ ከክልልና ከዞን ጥያቄ የአገር ህልውና ይቀድማል፡፡
በቅርቡ የወላይታ ተወካዮች ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ምክር ቤት አባልነት ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ የሕዝብን ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው የፓርላማ አባልነትን ያለ ሕዝብ ይሁንታ መልቀቅ ከፍተኛ ጥፋት ከመሆኑም በላይ ከፌዴራል እስከ ዞን ባሉ የመንግሥት መዋቅር ሥልጣን ላይ ተፈናጠው ደመወዝ እየበሉ ከመንግሥትና ከሕዝብ ፍላጎት ባፈነገጠ መልኩ የአፍራሽነት ሚና መጫወታቸው የሚጠይቅ አካል ቢኖር ከባድ ወንጀል ነበር፡፡ ከደቡብ ክልል ምክር ቤት አባልነታቸውን የለቀቁትም ከአስፈጻሚው አካል ሥልጣንም መልቀቅ (መባረር) አለባቸው፡፡
በደቡብ ክልል የሚታየው ግዙፍ ችግር የመነጨው በዋናነት ደኢሕዴን ራሱን በግምገማ አለማጥራቱ ነው፡፡ ደቡብ ክልልን ከላይ እስከታች ከሕወሓት ጋር ተሻርከው ሲያስጨንቁት የነበሩት ግፈኞች ዛሬም ድርጅቱን ተጣብተው ነው ያሉት፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራና በሶማሌ ክልል የተደረጉት ተደጋጋሚ የማጥራት ዘመቻዎች በደቡብ አንዴም አልተደረገም፡፡ ለዚሀ ነው ክልሉ በችግር ማጥ ውስጥ የተዘፈቀው፡፡
የደቡብ ክልል በስሜት ከመመራት ወጥቶ ለሕዝብ በሚጠቅም ጉዳይ ላይ ሕዝብ እየመከረበት ውሳኔው በየደረጃው ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ ክልሉ ሌሎች እንደሚመኙለት ቁልቁል መውረድ የለበትም፡፡ ባይሆን አስተዳደራዊ ወጪውን ቆጥቦ በጋራ የሚያማክል አንድ ክልላዊ አስተዳደር ኖሮት ይህንኑ አጠናክሮ ልማትን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊና ወሳኝም ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡