Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቀድሞው ኢን-ኤንድ-አውት በ‹‹ኢንጆይ በርገር›› ስያሜ  

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢን ኤንድ አውት (In-N-Out) በሚል ስያሜው የሚታወቀው የፈጣን ምግቦች አምራች፣ ድርጅት በርገርን ጨምሮ ከዶሮ የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ ምግቦችን በማቅረብ ከአሥር ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡

ድርጅቱ ሰባት ቅርንጫፎች በመክፈት ሲንቀሳቀስ፣ ሁለቱን በራሱ ሕንፃዎች ቀሪዎቹን በኪራይ አማካይነት አገልግሎቱን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት ሥራ ሲጀምር፣ ቦሌ መንገድ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በተከራየው 45 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ20 ሺሕ ብር ካፒታል እንደነበር የድርጅቱ ባለቤት አቶ ሳለአምላክ አንዳርጌ ይገልጻሉ፡፡

በወቅቱ በጥቂት ሠራተኞች እየታገዙ ለተጠቃሚዎች በርገርና ሌሎችም ፈጣን ምግቦችን የማዘጋጀቱን ኃላፊነት ራሳቸው ወስደው ወደ ሥራው እንደገቡ ያስታወሱት አቶ ሳለአምላክ፣ በወቅቱ በቀን እስከ 16 ሰዓት ለመሥራት የሚገደዱበት አጋጣሚ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በዚያች የመጀመርያቸው በሆነችው ካፊቴሪያ ውስጥ እንደ ባለቤት፣ እንደ ምግብ አብሳይና እንደ አስተናጋጅ ሁለገብ ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ የሠራተኞቻቸውን የሥራ ክንውን የመቆጣጠርና አስፈላጊ ዕቃዎችን በየቦታው እየዞሩ የመግዛት ሥራን ጨምሮ ሌሎችም የእሳቸውን ተሳትፎ የሚጠይቁ በርካታ ጉዳዮች ላይ ወዲያ ወዲህ ማለት ግዳቸው ነበር፡፡

አድካሚ የነበረውን ሥራ ለመጀመር ሲነሱ አቅደውና የት እንደሚደርሱ አልመው እንደነበር የገለጹት አቶ ሳለአምላክ፣ በአምስት ዓመት ውስጥ ምን እንደሚያሳኩ በአሥረኛ ዓመት የሥራ ዘመናቸውም ምን ዓይነት ውጤት እንደሚኖራቸው አስቀድመው ወስነው ነበር፡፡

ውጥናቸው በአብዛኛው የሰመረላቸው ይመስላል፡፡ በአሥረኛው ዓመታቸው ላይ ቆም ብለው ሲገመግሙ፣ የድርጅታቸው ካፒታል መጠን 200 ሚሊዮን ብር መድረሱን ዓይተዋል፡፡ አሥር ብቻ የነበሩት ሠራተኞችም ወደ 300 ተበራክተዋል፡፡ በቀን ከ40 የማይበልጥ ምግብ ይዘጋጅባት የነበረችው የመጀመርያዋ ካፊቴሪያም ተስፋፍታ በአሁኑ ወቅት እስከ አምስት ሺሕ ምግብ የሚዘጋጅባቸው ማዕድ ቤቶች አፍርታለች፡፡ በመጀመርያዋ ካፊቴሪያ በቀን ይስተናገዱ የነበሩ ከአርባ የማይበልጡ ደንበኞች እንደነበሩ የጠቀሱት አቶ ሳለአምላክ፣ ዛሬ ላይ በሰባቱ ቅርንጫፎች በቀን ከአራት እስከ አምስት ሺሕ ደንበኞች ያስተናግዳሉ፡፡ እንዲህ ያለውን የድርጅታቸውን እመርታ በመግለጽ አሁን ላይ አስፈላጊ ሆኖ ስለመጣው አዲስ ለውጥ አብራርተዋል፡፡

ከእስካሁኑ የአሥር ዓመታት ልምድ በመነሳት ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት ድርጅታቸው የት ሊደርስ እንዳሰበ የወጠኑትን ሐሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር መንቀሳቀስ የጀመሩት አቶ ሳለአምላክ፣ መነሻ ያደረጉትም የእስከ ዛሬውን የድርጅት ስያሜ በአዲስ  በመለወጥ፣ በሌላ አዲስ ብራንድ ደንበኞቻቸውን እያገለገሉ ለመጓዝ በማሰብ ለውጦች እንዳደረጉ ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው ‹‹In-N-Out›› በአዲሱ ስያሜው ‹‹ኢንጆይ በርገር›› ተብሏል፡፡ ይህን ማድረግ ለምን እንዳስፈለገ ሲያብራሩም፣ በአዲስ መልክ መንቀሳቀስ ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ በዚህ ስያሜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ የበርገር አምራች ኩባንያ በመኖሩ ነው፡፡ በዚህ ስያሜ ከሚንቀሳቀሰው ድርጅት ስያሜውን መዋስ፣ ከዚህ በኋላ በሰፊው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያካሄዱ እንቅስቃሴዎች የማይመችና ወደፊትም የንግድ ምልክት ጥያቄ ሊያስነሳ ስለሚችል ከወዲሁ ለማስተካከል ታስቦ ነው፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ አቶ ሳለአምላክ እንዲህ ብለዋል፡፡ ሥራ ሲጀምሩ የውጪውን ዓለም አሠራር መሠረት በማድረግ እንደነበር አብራርተው፣ የቀድሞው In-N-Out በአዲሱ ስያሜው ኢንጆይ በርገር የተቀየረበት ሌላው ምክንያት፣ ከስያሜውም እንደሚገልጸው ‹‹ገብተህ ውጣ›› ዓይነት ትርጉም ያለው፣ ገዝቶ መውጣት አልያም በልቶ እንደጨረሰ ወዲያው መውጣት የሚል ዓይነት አንደምታ ያለው በመሆኑም ጭምር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ የዚህ ዓይነቱ የመስተንግዶ ሐሳብ ብዙም የሚስማማ ሆኖ ስላላገኙት In-N-Out በአዲሱ ስያሜው ኢንጆይ በርገር ተቀይሮ ቢንቀሳቀስ የበለጠ ተስማሚነት ያለውና በርካቶች እንደ ልብ የሚያስተናገዱበት የሬስቶራንት ሐሳብ መሆን እንዲይዝ በማስፈለጉ የስያሜ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓል፡፡ ይህ በመሆኑም በአንዱ ቅርንጫፍ ብቻ በአንድ ጊዜ 250 ደንበኞች ማስተናገድ የሚያስችል አቅም የተፈጠረውም ከዚህ ሐሳብ በመነሳት እንደሆነ አቶ ሳለአምላክ ይገልጻሉ፡፡

በአዲሱ ስያሜ መንቀሳቀስ እንደ ጀመረ ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ ኢንጆይ በርገር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሲያስፋፋው የቆየውን  አገልግሎት ወደ ክልል ከተሞች ብሎም ከኢትዮጵያ ውጪ በተመረጡ አገሮች ውስጥ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ማቀደኑን የድርጅቱ ባለቤት አስታውቀዋል፡፡ ይህም የስያሜ ለውጥ ለማድረግ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነው ተጠቅሷል፡፡

የስያሜ ለውጡ ግን ስም በመቀየር አልፎ በቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል በመያዝ በአገር ውስጥና በውጭ ለመንቀሳቀስ በየደረጃውም ፍራንቻይዝ በማድረግ ሥራውን የማስፋት ዓላማውን ወደ ተግባር ለመቀር እንዲያስችለው ጭምር ነው፡፡ ይህ በመሆኑም በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ከ100 እስከ 150 ቅርንጫፎች የመክፈት ዕቅድ መያዙን አመልክተዋል፡፡

የኩባንያ ስያሜና መለያ በማሻሻል የበለጠ ለመንቀሳቀስ መነሳት በንግድ ዓለም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል የሚሉት አቶ ሳለአምላክ፣ ‹‹ስያሜን መቀየር ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በአገራችንም የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ አንዳንድ ድርጅቶች ስም ሲቀይሩ አንዳንዴ ዱብ ዕዳ ሲሆን ይታያል፤›› በማለት ኢንጆይ በመባል የስያሜ ለውጥ የማድረጉ ሥራ በሙያተኞች የተጋገዘ በመሆኑ ጭምር ብዙ ግርታ እንደማይፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡  

ኢንጆይ በርገር በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን እንቅስቃሴ ወደ ሌሎችም አገሮች ለማስፋፋት ይረዳው ዘንድ የስም ለውጥ ሲያደርግ፣ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ ራሱን የለወጠ ተቋም አስቀድሞ ማሟላትና ማከናወን የሚጠበቁበትን ሥራዎች በመወጣት ያደረገው እንደሆነ ከአቶ ሳለአምላክ ገለጻ መገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ቀድሞውንም በአዲስ ስያሜ ዳግም የመምጣትና ሥራቸውን የማስፋፋት ግብ ስለነበራቸው፣ ከሁለት ዓመት በፊት ድርጅታቸው የራሱን መለያ ዓርማ ማስቀመጥ እንደጀመረ አስታውሰዋል፡፡ የስያሜ ለውጡም እንዲሁ እንዳልተደረገ አመላክተዋል፡፡

ኢንጆይ የሚለው መጠሪያ የጣው፣ የብራንድና የስያሜ አወጣጥ ላይ የሚሠሩ ተቋማትን በመጋበዝ ነው፡፡ ይህ ተከትሎም ለአዲሱ ስያሜ የታጩ 25 አማራጮች ቀርበው፣ የበለጠ ድምፅ ያገኘው ኢንጆይ በርገር የሚለው በመሆኑ ተመርጧል፡፡

በዚህ መንገድ ስሙን ለውጦና አዳዲስ አገልግሎቶችን አክሎ የቀረበው ኢንጆይ በርገር፣ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ካፒታሉን በቢሊዮን ደረጃ ለማሳደግና ገበያውን ለማስፋት አቅዷል፡፡ ለዚህም ተጨማሪ ቅርንጫፎች ከመክፈት ባሻገር በሰፊው ለመንቀሳቀስ የሚረዱትን የፍራንቻይዝ አገልግሎቶችን በመጠቀም፣ በቅርቡ እንደሚጀመር የሚጠበቀውን የስቶክ ገበያ ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ኢንጆይ ወደ ክልል ከተሞች፣ ወደ ጎረቤት አገሮች እንዲሁም ወደ ዱባይና ወደ ሌሎች አካባቢዎች የመሄድ ሐሳብ አለን፤›› ያሉት አቶ ሳለአምላክ፣ ሐሳብ ብቻም ሳይሆን አሁን ያለውን የድርጅቱን ካፒታል ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በማሳደግ  ከቢሊዮን ብሮች በላይ ወደ ሚያንቀሳቅስ ትልቅ የአክሲዮን ኩባንያነት እንዲለወጥ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች