Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበጎርፍ የተመታው ምሥራቅ አፍሪካ

በጎርፍ የተመታው ምሥራቅ አፍሪካ

ቀን:

የዘንድሮ ክረምት ከፍተኛ ዝናብ የሚመዘገብበትና የጎርፍ አደጋ የሚከሰትበት እንደሚሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ያስታወቀው ከወራት በፊት ነበር፡፡ በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አብዝቶ እየጣለ ያለው ዝናብም፣ ጎርፍ እያስከተለ ነው፡፡ በዚህም ሰዎች እየሞቱ፣ ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ፣ ሰብሎችም ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ክረምት ጉዳት የሚያደርሰው የአዋሽ ወንዝ ዘንድሮም ገንፍሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ፣ ከብቶች በጎርፍ እንዲወሰዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአፋር ክልል የሚገኙ 14 ወረዳዎች፣ አርሲ፣ ምሥራቅ ሸዋና በመተሃራ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የአዋሽ ወንዝ ሙላት ችግር ውስጥ ከከተቷቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወንዞች እየሞሉ መንገድ የሚዘጉበት ሁኔታም ተስተውሏል፡፡ ጎርፍ ከ100 ሺሕ በላይ ሰዎችን አፈናቅሏል፡፡ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችንም ጎድቷል፡፡

ክረምቱ ያስከተለው ጎርፍ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሱዳንም ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት ላይ እንደ ግብፅ ጉልህ ባይሆንም የውኃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል ቅሬታ በነበራት ሱዳን ሰሞኑን በደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት የሦስት ወር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

​​በጎርፍ የተመታው ምሥራቅ አፍሪካ

አልጀዚራ እንዳሰፈረው፣ ሱዳንን ባጥለቀለቀው ጎርፍ 99 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከ100 ሺሕ በላይ ቤቶች ደግሞ በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡

የሱዳን ደኅንነትና መከላከያ ምክር ቤት 99 ሰዎች በጎርፍ መሞታቸውንና ቤቶችና ንብረቶች መውደማቸውን ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ ባለፈም ሱዳንን የተፈጥሮ አደጋ ቀጣና ብሏታል፡፡

የሱዳን የሠራተኛና ማኅበራዊ ልማት ሚኒስቴርን ገልፆ ከሞቱት በተጨማሪ 46 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአገሪቱ ሬዲዮ ሱና አስደምጧል ተብሏል፡፡ ሚኒስትሩ ሊና ኤል ቬኪ እንዳሉት የዘንድሮው ጎርፍ ከባድና እ.ኤ.አ. በ1946 እና በ1988 ከተመዘገበው ከፍተኛ የጎርፍ መጠን ያለፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰኔ በሚጀምረውና በጥቅምት በሚያበቃው ክረምት ሱዳን በየዓመቱ ጎርፍና ከባድ ዝናብ ታስተናግዳለች፡፡ የዘንድሮ ግን ለየት ያለ ክብደት ያለው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላም ከባድ ዝናብ እንደሚመዘገብ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ እስካሁን ድረስም ብሉ ናይል 17.58 ሜትር ከፍታ በመሙላት ክብረ ወሰን አስመዝግቧል፡፡

ኬንያም በጎርፍ ቀውስ ውስጥ ከገቡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሌላኛዋ ናት፡፡ በኬንያ ስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ሐይቆችም በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲፈናቀሉ የእርሻ ቦታዎች ወድመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ ቢያጋጥምም የተወሰነ ሜዳና ቤት አጥለቅልቆ ያፈገፍግ የነበረ ቢሆንም፣ የዘንድሮው ግን በተለየ መልኩ ጎርፉና የተኛው ውኃ መልሶ አላፈገፈገም፡፡ ይልቁንም የጎብኚዎች መስህብ የሆኑትን በሪፍት ቫሊ አካባቢ የሚገኙ ሎጆችን፣ ቤቶችንና እርሻዎችን ጎትቷል፡፡

በተለይ በሪፍት ቫሊ የሚገኘው የባሪንጎ ሐይቅ መሙላት ከባድ ጉዳትን አስከትሏል፡፡ የውኃ ሙሌቱ ከአምስት ሺሕ ሰዎች በላይ እንዲፈናቀሉ ሲያደርግ፣ መኖሪያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ሆስፒታሎችን፣ የእርሻ ቦታዎችን፣ መንገዶችንና ደሴቶችን ውጧል፡፡

ሶማሊያም የጎርፍ ሰለባ ሆናለች፡፡ ከሰኔ ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ የሸበሌ ወንዝ ሙላት ከ86 ሺሕ በላይ ዜጎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ 40 በመቶ ያህሉ የሙላቱ መጠን በመቀነሱ ወደቤታቸው ቢመለሱም፣ የሸበሌ ሙላት ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡

የሸበሌ ወንዝ እስከ ነሐሴ ማብቂያ ድረስ 7.56 ሜትር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም ሥጋት ተብሎ ከተቀመጠው በ0.26 ሜትር የበለጠ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በነሐሴ መጀመርያ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ቤት አልባ ሆነዋል፡፡

ግሎባል ዌዘር ሃዛርድስ ሰመሪ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚኖረውን ከፍተኛ የዝናብ መጠን አስመልክቶ እንዳሰፈረው፣ ከከባድ ዝናብ በተጨማሪ በምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ የሚቆይ ሲሆን፣ በኬንያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የሚስፋፋም ይሆናል፡፡

ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተው ከባድ ዝናብ በመቀጠል በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ከፍተኛ ጎርፍ ያስከትላል ሲልም አስታውቋል፡፡

ከፍተኛ የዝናብ መጠን ጥቁር ዓባይና ነጭ ዓባይ ወንዞች እየሞሉ አዋሳኝ የሆኑ አካባቢዎች መጥለቅለቃቸውን እንደሚቀጥሉም አስታውቋል፡፡

ጎርፍ በምሥራቅ አፍሪካ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ አስከትሏል፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኮቪድ-19 ቁጥጥሩን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳዋል ተብሏል፡፡ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እስከ መስከረም ማብቂያ ይቀጥላል የሚል ትንበያ ሲኖር፣ ይህም ተጨማሪ መፈናቀሎችንና ጉዳቶችን ያስከትላል ተብሏል፡፡

በጎርፍ የተመታው ምሥራቅ አፍሪካ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...