በሦስት ቀናት ውስጥ ከነሐሴ 30 ቀን እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በ69151 ሰዎች ላይ በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 3132 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን 53 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ እንደ ኢንስቲትዩቱ መግለጫ ነሐሴ 30 ሕይወታቸው ያለፈው 17 ሲሆን በጳጉሜን 1 እና 2 በቅደም ተከተል የ21 እና 15 ሰዎች ሞት ተመዝግቧል፡፡ በጽኑ ሕክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙት 309 ሰዎች ናቸው፡፡
እስከ ጳጉሜን 2 ቀን ድረስ ለ1,063,454 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ እስከተጠቀሰው ዕለት ቫይረሱ ያለባቸውና ሕክምና እየተከታተሉ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር 36,924 ነው፡፡ የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚሳየው፣ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 21,789 ሲደርስ፣ 309ሰዎች በፅኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ናቸው።
ኮቪድ-19 በወረርሽነት ዓለምን ካካለለ ስምንት ወር ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ወራት ሕዝበ ዓለም ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ እንዳይያዝ የጤና ባለሙያዎችና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ ተቋማት ማስገንዘቢያዎችን ከመስጠት ችላ ያሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡
ኮቪድ-19 የሚተላለፍበት መንገድ አስመልክቶ እስካሁን ያለው አቋም፣ በሽታው ከሕመምተኛው አፍንጫ ወይም አፍ በሚወጣ ጥቂት ፈሳሽ አማካይነት የሚተላለፍ መሆኑ ነው፡፡ ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ሲያስነጥስም ሆነ ሲተነፍስ ወደ ሌሎች ከማስተላለፍ ባለፈ፣ ከሕሙማን የሚወጣ ፈሳሽ ያረፈበትን ቦታ የነኩ ሰዎችም በበሽታው በቀላሉ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸው ቅርርብ ከአንድ ሜትር በላይ መሆን አለበት የተባለውም በሽታው በትንፋሽ ስለሚተላለፍ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ቫይረሱ በአየር ውስጥ ሳይሆን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የመተንፈሻ አካላት ከወጡ ፍሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ብቻ የሚተላለፍ መሆኑን ነው፡፡
ይሁን የቅርብ መረጃዎች የኮሮና ቫይረስ በአየር ላይ የመተላለፍ ዕድሉ ሰፊ መሆኑ እየገለጹ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት በቫይረሱ የመጋለጥ ወይም ያለመጋለጥ ዙርያ የቀረቡ ጥናቶች ላይ እየመከረ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በአየር ላይ ቫይረሱ በመቆየት ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ተተኳሪ ጉዳዮች
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት አገላለጽ፣ ኮሮና ቫይረስ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን የያዘ የቫይረስ ቤተሰብ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በሽታን ያስከትላል፡፡ በሰዎች ላይ የሚከሰተው ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ከተራ ጉንፋን እስከ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካል ችግር የሚያደርስ ነው፡፡