Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው መንግሥት ዕርባና የለውም

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው መንግሥት ዕርባና የለውም

ቀን:

በዕድላዊት ጌታቸው

በየትኛውም ሥፍራ ሆነ ጊዜ ብልሹ አሠራሮች የሚሰፍኑት ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሳይሆኖሩ ሲቀሩ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት በሕግ ግዴታ አለበት፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 መሠረት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት ይላል፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል በሕግ እንደሚጠየቅም ይደነግጋል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን የመንግሥት አሠራር አሁንም ጨለማ ውስጥ የተደበቀን ጥቁር ድመት ይመስላል፡፡

ኃላፊዎች ሲያጠፉ በሕግ ከሚጠየቁ ይልቅ በተሻለ ሹመት ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወራቸው ለዓመታት የተለመደ ባህል ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ብርቅ በመሆኑ አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት ለሚዲያም ሆነ አሠራራቸውን ለማወቅ ለሚሹ ዝግ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በስድስት ወራትም ይሁን በዓመት ይዘዋቸው የሚወጡ ሪፖርቶች ተዓማኒነታቸው ላይ ሁሌም ጥርጣሬ አለ፡፡ በእርግጥም የዓመታት ልምዳቸውም የሚያሳየው በሐሰተኛ መረጃዎች የታጨቁ ሪፖርቶችን ሲያወጡ የከረሙ ተቋማት፣ ጊዜ የከዳቸው አመራሮቻቸው ሲነሱ የውሸት ገመናቸው አደባባይ ላይ እንደሚዘረገፍ ነው፡፡ ይህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በበርካታ ተቋማት ላይ ተስተውሏል፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት የሕዝብን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡

ባለፈው ሰሞን ኢዜማ የመንግሥትን አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚፈትን ጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ከተማ በመሬት ወረራና በጋራ መኖሪያ ቤቶች አሰጣጥ ላይ ይፋ የተደረገ ጥናት፣ ከመንግሥት በኩል ዘርዘር ያለ ምላሽ የሚያስፈልገው ቢሆንም በሕዝቡ ውስጥ ግን ከዚህ ቀደምም በርካታ ብሶቶች ሲሰሙ ነበር፡፡ ከመሬት ወረራው በተጨማሪ መንግሥት የሚጠየቅበት ጉዳይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ የደረሳቸው ወገኖችን የሚመለከተው ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች መንግሥት ባወጣው የቤት ግንባታ መርሐ ግብር መሠረት ተመዝግበው ሲቆጥቡ የነበሩ ናቸው፡፡ በሕጋዊ መንገድ የቤቶቹ ዕጣ ወጥቶ የዕድለኞች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡

ነገር ግን ከሌላ ወገን በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት ዕድለኞች ቤቶቻቸውን መረከብ አልቻሉም፡፡ የይገባኛል ጥያቄ ያነሱ ወገኖችን በተመለከተም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቁርጥ ያለ ውሳኔ በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ሲኖርባቸው፣ ከመሬታቸው ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ቤቶቹ ተሰጡ ሲባል ግራ ያጋባል፡፡ ተፈናቃዮቹን መልሶ ማቋቋምና መደገፍ የራሱ የመንግሥት ኃላፊነት ሲሆን፣ የመንግሥት አካል በፈጠረው ችግር ምክንያት ምስኪን ቆጣቢዎች መቀጣት የለባቸውም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብቱ የተረጋገጠው በሕግ ስለሆነ ሕግ መከበር አለበት፡፡ መንግሥትም አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ በማድረግ ይህንን መብት ማስከበር አለበት፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት በጎደለው ቁጥር፣ ከሕዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ይህ ጉዳይ አሁንም በአንክሮ ተጢኖ ግልጽ የሆነ ምላሽ መሰጠት አለበት፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ትልቁ በሽታ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ አለመሆን ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነትም እንዳለበት በሕግ ቢደነግግም፣ የፌዴራል መንግሥቱንም ሆነ ክልላዊ መንግሥታትን የሚመሩ ኃላፊዎች ተግባራዊ ሲያደርጉት አልታየም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት አሠራር ድብቅ፣ ለሐሜት የተጋለጠና አንዳንዴም አስማት ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ እየሆኑ ከፍተኛ ጉዳቶች አጋጥመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ ለ27 ዓመታት በመራት ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት በመጥፋቱ ከፍተኛ ሕዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ፣ የሕይወት መስዋዕትነት ባስከተለ አመፅ የአስተዳደር ለውጥ ተደርጓል፡፡

ሥርዓተ መንግሥቱ ተናግቶ የሥርዓት ለውጥ ለማከናወን ግፊቱ ቢቀጥል ኖሮ፣ ኢትዮጵያን አሁን ባለችበት ሁኔታ ለማግኘት ያዳግት ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ሰላማዊ ሽግግር ተደርጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩት አስተዳደር፣ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ ላለፉት 30 ወራት ያህል ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ሆና በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ ለማመን የሚከብዱ በርካታ አዎንታዊ ተግባራት የተከናወኑትን ያህል፣ አገርንና ሕዝብን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የጣሉ አሳዛኝ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል፡፡ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በትረ ሥልጣኑን ሲቆናጠጡ ባደረጉት ንግግር፣ ከሕዝብ የሚደበቅ ምንም ዓይነት የመንግሥት አሠራር እንደማይኖር ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ አሁንም ግልጽነት የለም፡፡ ከራሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ቢሮዎች ለመረጃ ዝግ ናቸው፡፡ ከሚዲያዎች ጀምሮ ኢንቨስተሮችን አካቶ መረጃ የሚፈልጉ ወገኖች፣ ምን ያህል እንደሚሰቃዩ የደረሰባቸው በሚገባ ያውቁታል፡፡ ከመረጃው በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ተቋማትም ሆነ በክልሎች፣ ኢንቨስተሮች ችግር ሲገጥማቸው መፍትሔ ለመስጠት ያለው ተነሳሽነት ያሳዝናል፡፡

ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች ሲስተጓጎሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጉ ማምረቻዎችና የማዕድን ማውጫ ሥፍራዎች ውሳኔ አግኝተው ወደ ሥራ መግባት ሳይችሉ፣ በጉልበተኞች ምክንያት ማምረትና ማጓጓዝ ሲያቅት፣ በአጠቃላይ ለንግድና ለኢንቨስትመንት መሰናክል የሆኑ ችግሮች ሲበረክቱና የሥራ ፈጣሪዎችን ሞራል ሲገድሉ ዝም ሲባል ግራ ያጋባል፡፡ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች መሥራት አቅቷቸው ሥራ ሲያቆሙና ሠራተኞችን ከእነ ቤተሰቦቻቸው ሲበትኑ ማን ነው የሚጎዳው? ያለ ጥርጥር አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት ምን እየሠራ ነው ብሎ አጥብቆ መጠየቅ የሚገባው፡፡

የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው የሚያስፈልገው፣ ሕግ የሁሉም ነገር የበላይ መሆን ስላለበት ነው፡፡ የአገራችን ሰው፣ ‹‹በሕግ ከተወሰደችብኝ በቅሎዬ ይልቅ ያለ ሕግ የተወሰደችብኝ ዶሮዬ ታንገበግበኛለች›› እንደሚለው፣ በሕግ የበላይነት ሥር የማይከናወን ድርጊት ውጤቱ ሕገወጥነት ነው፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት የሕዝብን ደኅንነትና ሰላም ማረጋገጥ ሲሆን፣ የአገርን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነትን ማስጠበቅም ያካትታል፡፡ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን በሌሎች የሚቀማ ከሆነ ግን፣ ጉልበተኞችና ሥርዓተ አልበኞች አገር ያተራምሳሉ፡፡ ማንም ሰው ጥያቄ የማቅረብ መብት ቢኖረውም፣ የጥያቄው አቀራረብ ግን ፍፁም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆን አለበት፡፡ የአገርንም ጥቅም እንዳይፃረር ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡

አንድ ኢንቨስተር በሕጋዊ መንገድ እየሠራ ሳለ፣ ከሕዝብ ጥቅም በተፃራሪ እየተጠቀመ ነው ከተባለ ሕጋዊ ማስረጃ ሊቀርብበት ይገባል፡፡ ከዚያ ውጪ ሥራውን በጉልበት እንዲያቆም ማድረግም ሆነ ማደናቀፍ ሕገወጥ ነው፡፡ ይህ በእርሻ፣ በማምረቻ፣ በማዕድን ማውጫ፣ በቱሪዝም፣ በሆቴል፣ በንግድና በመሳሰሉት የተሰማሩትን በሙሉ ይመለከታል፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ወገኖች የሚጠበቅባቸው ሕግ አክብረው እንዲሠሩ ብቻ ነው፡፡ ሲያጠፉም መጠየቅ ያለባቸው በሕግ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን የመንጋ ፍርድ ሰለባ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ለኪሳራ እየተዳረጉ ሥራ ማቆም የለባቸውም፡፡

የሚሠራን አላሠራ ማለት ወደፊት መሥራት የሚያስቡትን ጭምር ሐሳባቸውን እንዲለውጡ ያደርጋል፡፡ ለመሥራት የሚያስፈልገውን ተነሳሽነት ይገድላል፡፡ ለአገሬ እሠራለሁ በማለት ዕውቀቱንና ሀብቱን ይዞ የመጣ ታታሪ ዜጋን ዕቃውን ሸክፎ ወደ መጣበት እንዲመለስ ይገፋፋል፡፡ ለአገሩ ዜጋ ያልሆነ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል በማለት የውጭ ኢንቨስተሩም ይሸሻል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ኢኮኖሚውን መቀመቅ በመክተት የፖለቲካ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህንን ችግር በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው መንግሥት ኃላፊነቱን ሲወጣ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ስለኢንቨስትመንትና ስለሥራ ፈጠራ መነጋገር አይቻልም፡፡

ብዙዎች ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር እንደሆነች ያምናሉ፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ በፍጥነት መውጣት ካልተቻለ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት ያስጨንቃታል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ክምችት እንቅልፍ ይነሳታል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየባሰበት የሕዝቡን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ በድርቅና በመፈናቀል ምክንያት ሚሊዮኖች አስቸኳይ ዕርዳታ ይለመንላቸዋል፡፡ ሰፊ ለም መሬትና ከፍተኛ የውኃ ሀብት ቢኖርም አሁንም ግብርናው ኋላቀር ነው፡፡ ደካማ የሆነው የአምራች ዘርፍ ከውጭ የሚመጡ የካፒታል ዕቃዎችንና የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን መተካት አልቻለም፡፡ የአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን አሁንም ከፍተኛ ጉድለት አለበት፡፡ ሌሎች ተጨማሪ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡

የሕግ የበላይነት ጉዳይ ሲነሳ ቸልተኛ መሆን አይገባም፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ሕጎች ይከበራሉ፡፡ ነገር ግን ሕጎች ባለመከበራቸው ምክንያት ብቻ ግለሰቦች ራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረጋቸው አገር ተበድላለች፡፡ ይህ በደል በተለይ በቀጥታ ያገኛቸው ወገኖች ምን ያህል አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳደረሰባቸው በስፋት ይታወቃል፡፡ አሁንም የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚፈልጉ ወገኖች በሕግ መጠየቅ ያለባቸው እንዲጠየቁ፣ በየትኛውም ኃላፊነት ላይ የሚመደቡ ወገኖችም በሥርዓት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ ሕገወጥነት ከዚህች አገር በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወገድና ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ድምፅ ማሰማት አለባቸው፡፡

ወንጀል እያንዳንዱ ሰው የሚጠየቅበት እንደ መሆኑ መጠን ከብሔር፣ ከእምነትና ከተለያዩ ማኅበራዊ ስብጥሮች ጋር ሊያያዝ አይገባም፡፡ ማንም ይሁን ማን የመንግሥትን ሥልጣን በአግባቡ አለመምራት ማስጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ትናንት የተፈጸሙ በደሎችን በሌላ ገጽታ በመድገም የአገርን ክብር ማዋረድ ማብቃት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ይፈልጋል፡፡ ይህ ዕውን መሆን የሚችለው ግን አገር በሕግና በሥርዓት ስትመራ ብቻ ነው፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ባሉበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አይቻልም፡፡ በስመ ነፃ አውጪነትና እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ ባይነት ሕዝብን ማታለል አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትም ሆነ የቡድን ዘረፋ ማብቃት አለበት፡፡ ሥልጣን በሕግ ሊገራ ይገባል፡፡

ማንኛውም ሥርዓት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ሲንጠላጠል ተስፋ አይኖረውም፡፡ ሥርዓት አስተማማኝና ዘለቄታዊ መሆን የሚችለው ተቋማዊ ሲሆን ነው፡፡ ተቋማዊ መሆን ማለት በሕግ ብቻ የሚመራ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያገለግሉ ተቋማትን ማደራጀት ነው፡፡ ተቋማቱ መደራጀት ያለባቸው አገራቸውን በሚወዱ አመራሮችና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን፣ በአገልጋይነት መንፈስ የተሰጣቸውን ሥራ በኃላፊነት በሚያከናውኑ ሠራተኞች ጭምር ነው፡፡ ተቋማቱ በዚህ መንገድ ሲደራጁ የመንግሥት ሥራ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት ይከናወናል፡፡ ኢትዮጵያዊያን መብታቸውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውንም ይረዳሉ፡፡

ሌብነትና አጭበርባሪነት አስነዋሪ ይሆናሉ፡፡ አገርን ለማገልገል ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ የብሔር፣ የእምነት፣ የፖለቲካ ወይም መሰል ልዩነቶች የቅራኔ ምንጭ አይሆኑም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዕውቀቱና በጉልበቱ አገሩን ለመገንባት ዝግጁ ይሆናል፡፡ ለዚህም ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እርስ በርስ እየተናበቡና ቁጥጥር እያደረጉ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ተቋማት በጠንካራና በብቁ አመራሮች ሳይደራጁ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነጋገር አይቻልም፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ በመሆኗ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ካልተሰጠ ችግሮች በነበሩበት ይቀጥላሉ፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ለጋራ ራዕይና ዓላማ አንድ ላይ መሠለፍ አለባቸው፡፡ ሠልፉን ለማስተካከል ደግሞ የሕግ የበላይነት ትልቁ መሣሪያ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ላይ መተማመን እንዲቻል መንግሥት ግልጽነትን፣ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ከታች እስከ ላይ የማስፈን ግዴታ አለበት፡፡ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ ለሕግ የበላይነት መገዛት አለባቸው፡፡ መንግሥትና ሹማምንቱም እንዲሁ፡፡ ያኔ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ የመንግሥትም አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን መንግሥት ዕርባና ቢስ ስለሚሆን ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ አለመመራት ሕዝብንና አገርን መጉዳት ስለሆነ ከድርጊቶቻችን እንጠንቀቅ እላለሁ፡፡

ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...