Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርበአዲሱ ዓመት ከሴራና ከበቀል የፀዳ ፖለቲካ ይኑረን

በአዲሱ ዓመት ከሴራና ከበቀል የፀዳ ፖለቲካ ይኑረን

ቀን:

በአዕምሮ ጥሩነህ

እኔን ጨምሮ ብዙዎች እየተጠናቀቀ ያለው ዓመት ለኢትዮጵያ በጣም ከባድ እንደነበረ ስለምናውቅ፣ አዲሱን ዓመት የምንቀበለው ጭንቀት ውስጥ ሆነን ነው ቢባል የተጋነነ አይደለም፡፡ በበኩሌ ከሚያስጨንቁኝ ጉዳዮች መካከል በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የሚስተዋለው ፍጥጫ፣ በፍርድ ሒደት ላይ በሚገኙ ፖለቲከኞች ምክንያት የተፈጠረው ተቃርኖ፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ለክልልነት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ምክንያት የተፈጠረው ውጥረት፣ በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ የሚታየው አደገኛ መካረር፣ በህዳሴ ግድባችን ምክንያት ከግብፅ ጋር ከወገነችው አሜሪካ ጋር የገባንበት ቅሬታ፣ የኮሮና ወረርሽኝ ጦስ በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ያለው ውድመትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡ የምጠናቀቅው አሮጌው ዓመት ከባድነት ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይተላለፍ ምን ማድረግ እንዳለብን በእርጋታ መነጋገር ብንችል መልካም ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፍን፣ ቀላል በማይባሉ የውጭ ጠላቶች ለዘመናት የተወጋንና የደማን፣ ያም አልበቃ ብሎን በፖለቲካ ሽኩቻ አንድ የሕዝብ አስኳል የሚባል ትውልድ የፈጀንና ያስፈጀን፣ በእርስ በርስ ጦርነት የራሳችንን አገረ ምድር የደቆስን ነን፡፡ መጥፎ ታሪክ አልፎም ቢያንስ ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት አዲስ መልክ ያለው ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ብንጀምርም፣ በሒደት በተፈጠሩ ቅራኔዎችና ክፍተቶች ምክንያት የችግር አዙሪት መውደቅ መነሳት ልማዳችን መሆኑን በተግባር አሳይተናል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ደም ተቃብተናል፡፡

- Advertisement -

ለውጥ እየጀማመርን ባለንበት ወቅትም ቢሆን ተስፋና ሥጋት የማይለየን ከዚሁ አዎንታ በመነሳት ነው፡፡ እርግጥ ሕዝቡ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት እንደ አገር ቀስ በቀስ እየፈረጠመ የመጣውን ፀረ ዴሞክራቲክና ዘራፊ ኃይል በሥርዓት ማሻሻያም ይባል በተቃውሞ ግፊት መቀየር ችሏል፡፡ በዚህም ለዓመታት የተሰደዱና ያኮረፉ ፖለቲከኞች ተሰባስበው፣ የህሊና  እስረኞች ተፈተው፣ ሁሉን አቀፍ የሚመስል አገራዊ አዲስ መንፈስም መስተዋል ጀምሯል፡፡ በአንድ ወቅት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያለው አስተዳደር ወደ ሥልጣን እንደመጣ አይዘነጋም፡፡

በዚያው ልክ አሁንም ዘረኛና አክራሪ ብሔርተኝነትን የተላበሰው በልሹ ፖለቲካችን እየባሰበት በመሄዱ፣ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ መፍጠር እየተቻለ ተግባራዊ አለመሆኑ ግን አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በመሠረቱ ከለውጥ በኋላም ዘውጌ ተኮር ሚዲያዎች፣ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመብት ተሟጋቾች (አክቲቪስቶች) ተብዬዎችና ጦማርያን እንደ አሸን ፈሉ እንጂ፣ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ኃይሎች ድምፅ ጎልቶ ሲወጣ አልታየም፡፡ በተቃራኒው በለውጡ ያኮረፉ የቀዳማዊ ኢሕአዴግ ኃይሎችና ጠባብ ብሔርተኞች ግንባር ፈጥረው፣ ጠንካራውን የሕዝቦች አንድነት ለማፈራረስ አንድ ጊዜ በብሔር፣ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ (በውጭ ኃይሎችም የታገዘ በሚመስል ደረጃ) ዘመቻ በውስጣችን  እሳት መለኮሳቸው በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ይህም ለውጡ በፍጥነት እንዳይጓዝ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝባችን የለውጡን መንግሥት በጥርጣሬ ዓይን እንዲያየው አድርጎታል፡፡

በመሠረቱ ዛሬ እንደ ሕዝብ በተለይ አዲሱ ትውልድ ለመብቱ ተሟጋችና አልገዛም ባይ መሆኑ የሚያስደስት ነው፡፡ ራስን ለመቻል፣ ለትምህርትና ሀብት ለመጨበጥ የሚያደርገው ጥረትም የሚናቅ አይደለም፡፡ በዚያው ልክ የራስን ታሪክ ከመሥራት ይልቅ ባለፈ ታሪክ መነታረክና መቁሰልን ስንቁ ማድረጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ችኩልነት፣ ስሜትና ራስን ብቻ ማስቀደም (ለእኔ ለእኔ ባይነት) መንሰራፋቱም ይታያል፡፡ በዚህ መዘዝም ተጨካክኖ እርስ በርስ ለመገዳደል አይመለስም፡፡ በጥላቻና በዘረኝነት በመሸበቡም የራሱን ወገን ዘቅዝቆ ለመስቀል የማይመለስ ትውልድ እንደሆነ በገቢር ታይቷል፡፡ ከአገር ይልቅ መንደርንና የራስን ጎሳ የማስቀደሙ አባዜም ገፊ ምክንያቱ ይኸው ተካረረ የዘውግ ፖለቲካን ካባ መደረቡ ነው፡፡

እንግዲህ አዲስ ዓመት ሲገባ እንደ ሕዝብም ሆነ መንግሥት የግልና የጋራ  ሰብዕና፣ ባህሪና አካሄዳችን ዕድሳት እንዲያገኝ መመኘትና የአቅምን ማበርከት ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አዲሱን ዓመት የምንቀበለው በአሮጌ የባህሪ አቁማዳችን ከሆነ፣ በአሮጌ የባህሪ ጨርቃችን ላይ የአዲሱን ዓመት ልብስ እራፊ እንደ መጣፍ ስለሆነ በአዲሱ ዓመት ማግኘት ያለብንን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች ማጣታችን አይቀርም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ጊዜያት ከእነ ጉድለታቸው የጨበጥናቸውን አገራዊ ድሎች ማስነጠቃችን የሚቀር አይሆንም፡፡ በዚያው መጠን ለንፁኃን ዕልቂትና ለንብረት ውድመት መንስዔ የነበሩ ቅራኔዎች እንደ አዲስ እንደማይቀጥሉ ማስተማመኛ የለንም፡፡

በአሮጌው ዓመት ይዘን የከረምነውን መጥፎ (አክራሪ ብሔርተኝነት፣ ያለ መተማመንና የጥላቻ ፖለቲካ፣ አለመቻቻልና አለመከባበር፣ ጥላቻና ጭካኔን የመሳሰሉ ደዌዎች፣) ባህሪያትና አካሄዶች ከራሳችን ላይ አስወግደን ራሳችንን ለአዲሱ ዓመት በሚመጥን ሁኔታ አዘጋጅተን ካልተገኘን፣ እንኳን ከዘመኑ ልንጠቀም ይቅርና እንደ ሕዝብ በራሳችን ላይ የምናስከትለው ጉዳት እጅግ የከፋ ይሆናል፡፡ አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ማኖርም አይቻልም፡፡ አዲሱን ዓመት በአሮጌ ባህሪና አካሄድ መቀበል ማለት በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ አዲሱን ወይን ጠጅ እንደማኖር ነው፡፡ በተበላሸ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ምንም ያህል የበረታ ማሻሻያ ተደረገ ቢባል፣ ሥር ነቀልና አስተማማኝ ብሎም ሁሉ አቀፍ የሆነ ሽግግርን ለማምጣት አዳጋች መሆኑን የተመለከትነው ነውና፡፡ አሮጌውን ልብስ በአዲስ እራፊ እንደ መጣፍ (እንደ መደረት) ያለ አካሄድም በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር መንግሥትንም ሕዝብንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ተደጋግሞ እንደታየው ጉዳት እንጂ ጥቅም አያመጣም፡፡

‹‹በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፣ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፣ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፣ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፣ አቁማዳውም ይጠፋል፣ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፡፡ ሁለቱም ይጠባበቃሉ፤›› መጽሐፍ ቅዱስ (ማቴዎስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 16-17) ማለቱን በማስታወስ፣ ዓለማዊና ምድራዊ አካሄዳችንን ብናጤነው ክፋት የለውም መባሉም ለዚሁ ነው፡፡

ስለዚህ አዲሱ ዓመት ይዞልን የመጣውን የአዲስ ሕይወትና አካሄድ ወይን ጠጅን በአግባቡ ለመጠቀም ሕዝብም ሆነ መንግሥት በውስጣችን ያለውን አሮጌ አስተሳሰብና አመለካከት በማቆም፣ የአሠራር ልምድና አካሄድ አቁማዳችን መቀየርና ለአዲስ ዓመት የሚመጥን ባህሪ፣ ዘዴ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ይዘን መቅረብ አለብን፡፡ ለምሳሌ እንደ መንግሥት ተጨባጭ የርዕዮተ ዓለም፣ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎችን ብሎም ጥላቻና መለያየትን የሚያበረታቱ አካሄዶችን የሚገድቡ ደንቦችና አሠራሮችን በማጠናከር፣ የአገር ሰላምና ደኅንነትን በማረጋጋት አገር ወደ ተረጋጋ ጉዞና ሰላም እንድታማትር ማድረግ አለበት፡፡ እንደ ሕዝብም ለሕግ መገዛትና ለሰላም መቆም ብቻ ሳይሆን፣ ከመንደርና ከብሔር በላይ አገራዊ ጥቅምን ማስቀደምና ለአንድነት መነሳት ያስፈልጋል፡፡

ተደጋግሞ እንደታየው ግን ኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የተለመዱት የዕቅድ አወጣጣችን (ያውም ካወጣን) በአብዛኛው በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ሰዎች ለየራሳቸው ‹‹በአዲሱ ዓመት ቤት እሠራለሁ፣ መኪና እገዛለሁ፣ አገባለሁ፣ እወልዳለሁ፣ ገንዘብ አጠራቅማለሁ፣ ሥራ እቀይራለሁ፣ ሲጋራ፣ መጠጥ. . . አቆማለሁ››. . . ወዘተ. ማለት ይቀናናል፡፡ ይኼ በሌሎች አገሮችም የተለመደ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ግን በጋራ ሆነንም ሆነ በተናጠል ለአገር የምናበረክተው አስተዋጽኦ ወይም ለሕዝቦች ጥቅም የምንወረውራትን ጠጠር አስቦ ማቀድና መተግበር ላይ የጎላ ዳተኝነት ይታይብናል፡፡

መንግሥት በበኩሉ በአዲሱ ዓመት የሚያደርገውን ያቅዳል፡፡ ‹‹መንገድ፣ ግድብ፣ ድልድይ እገነባለሁ፣ የመኖሪያ ቤት ችግርን እቀርፋለሁ፣ ስልክ፣ መብራት፣ ውኃ፣ አስገባለሁ፡፡ ትራንስፖርት አሻሽላለሁ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ እርሻ. . . በገጠርና በከተማ አዳርሳለሁ፡፡ መከላከያና ደኅንነትን አጠናክራለሁ፣ ዓለም አቀፋዊ ግዳጆቼን እወጣለሁ፣ የውጭ ግንኙነቴን አበረታለሁ፣ ለዚህም በቂ በጀት ይዣለሁ. . .›› ወዘተ. እያለ ይተልማል፡፡ እነዚህ ዕቅዶች ቢሳኩም ባይሳኩም መታቀድ ያለባቸው ናቸው፡፡ የሚያስመሰግኑ እንጂ የሚያስወቅሱ አይደሉም፡፡ ዋናው ለውጥ ግን በእነዚህ ቁሳዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይወሰኑ፣ ብዙኃኑን ሕዝብ በማዳመጥ የነገን የአገር መልክና ቁመና ዛሬ መገንባት ግድ ይላል፡፡

እነዚህና ሌሎች የጋራ አገራዊ ዕቅዶች የሚሳኩት ደግሞ ሕዝብና መንግሥት በየፊናቸው ያለባቸውን የአመለካከትና የአካሄድ ችግር ከውስጣቸው አውጥተው ለጋራ ዓላማ  በአዲስ ጥምረት ሲነሳሱ ነው፡፡ አንዱ ወደ ግራ ሌላው ወደ ቀኝ እየተሳሳበ፣ በፖለቲካ ነጋዴውና አፍራሹ ጭምር እየተወናበደ ዕቅድን ለማሳካት መሞከር ከቶ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በተለይ በሕዝቡ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ ሚዲያን የመሳሰሉ የአስተምህሮ መሣሪያዎችና ምሁራንከሚጋጩ ሕልሞችወጥተው ቢያንስ ወደ የሚያቀራርበው ነባራዊ ሀቅ ካልተሰባሰቡ አገርን ማነፅ ማዳገቱ አይቀሬ ነው፡፡ 

በመሠረቱ ሕዝብም ሆነ መንግሥት የተፈጠረው ለታላቅ ምድራዊና ሰማያዊ ዓላማ ነው፡፡ ማንም ዝም ብሎ እንዲፈነጭና ቀጪና ተቆጪ ሳይኖረው እንደ እንስሳ ያገኘውን እየበላ መረን ሆኖ እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡ የየራሱን ፍላጎትና ጥቅም ብቻ እያሳደደ ሕዝብ በመንግሥት ላይ፣ መንግሥትም በሕዝቡ ላይ ጣቱን እየቀሰረ፣ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል መንግሥትን እያስቸገረና እያማረረ፣ መንግሥትም በሕዝብ ላይ እንደ ልቡ እየዘለለና እየጨፈረ እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡ ይህን ሀቅ ሁሉም ቆም ብሎ ሊያጤን ግድ ይለዋል፡፡ ብዙኃኑ ስላልተደመጡ ወይም ዝም ስላሉ ጥቂቶች ከሰውም አልፈው የፈጣሪን ሥልጣን ጭምር በመውሰድ አጉል መንጠራራት ማሳያታቸው፣ አንድ ላይ ይጥለን እንደሆን እንጂ የትም የሚያደርሳቸው አይደለም፡፡

በአንድ አገር ውስጥ ያለው ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም የሚገኘውም ቢሆን እርስ በርሱ በፍቅርና በሰላም ተቻችሎ መኖር አለበት፡፡ በመልክ፣ በፆታ፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በባህል፣ በአካልና በአዕምሮ ተለያይቶ የተፈጠረው እርስ በርሱ እንዲተዋወቅና አብሮ እንዲኖር መሆኑ በቅዱሳን መጻሕፍትም ውስጥ ያለ እንደ መሆኑ፣ በፖለቲካ ነጋዴዎች ስሜታዊ ሥምሪት እየተነዳ ሊተራመስ አይገባም፡፡ ያልበላውን እያከከም የዘመናት ጥቅሙን ማንጠፍም እንደ ውርደት መታየት አለበት (ትናንተ እንደ ቀልድ ትርምስ ውስጥ የገቡት የመን፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን ቀረብ ሲባልም ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን ያስተውሏል)፡፡ ስለዚህ አዲሱን ዓመት የማስተዋልና ለጋራ አገራዊ ዓላማ ትግበራ ለማዋል መነሳት የሁሉም ወገን ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡

በእውነቱ እንኳን ለሺሕ ዘመናት ተዋህደንና ተቀይጠን ለኖርነው ኢትዮጵያዊያን ይቅርና ለማንምና የትም ቢሆን ልዩነት ጌጥ እንጂ ሸክም አይደለም፡፡ አምላክ አለያይቶ የፈጠረውን ሕዝብ የግድ አንድ ዓይነት ለማድረግ የእኔን እምነት፣ የእኔን ባህል፣ የእኔን መንገድ መከተል አለበት ማለትም ፈጣሪን መዳፈር ነው፡፡ ኢትዮጵያንም በልዩነታችን ኮርተን፣ በአንድነታችን ፀንተን፣ ተከባብረንና ተደማምጠን ለመኖር አሁን ከምንገኝበት የተሻለ ጊዜና የፖለቲካ ሥርዓት ልናገን እንደማንችል መረዳት ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተመራጩ መንገድ ራስን መመርመርና በቅድሚያ ውስጥን  መታገል እንጂ፣ ሌሎችን መወንጀል አይደለም፡፡ በጥላቻ ተርጓሚና ባልተጣራ መረጃ ውስጡን እያናወጠ፣ ጥፋትንም አንዱ በሌላው ላይ እያላከከና ጣት እየተቀሳሰረ ባለፈው ዓመት ጆሮ እየሰማ መጥፎ አሠራርን ማስቀጠል ማንንም የማይበጅ ነው፡፡ ሕዝብን የሚለያይ፣ የጥላቻናዘረኛ አስተምህሮ የሰነቀ/ ጦማሪ፣ ፖለቲከኛም ይባል አክቲቪስት ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ሲሉ ቢታቀቡ መልካም ነው፡፡

ሕዝብ የተፈጥሮ በረከቶቹንና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቹን ለራሱ ሲል በራሱ ማስከበር ካልቻለ፣ ማንም ጥገኛ (ቀዳሚውን ኢሕአዴግ እንደ ጥንጣን በልቶ የጨረሰው የውስጥ አስመሳዩና ሌባው እንደነበር ያስታውሷል) እንዳሻው መፈንጨቱ አይቀርም፡፡ ለዚህም ሁሉም ቢሆን ዳግም የጥፋት ሰይፍ ከአፎቱ ሰይወጣበት፣ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን መዋጋት አለበት፡፡

እንላቀቃቸው የሚባሉትን ኢዴሞክራሲያዊነት፣ ሌብነትና ዘረፋ፣ ኢፍትሐዊነት፣ አለመከባበር፣ አለመተባበር፣ ለሰላም እንቅፋት መሆንን ሕዝቡ ራሱ መታገል አለበት፡፡ ግድም ይለዋል፡፡ መንግሥትም ይህ ዓይነቱን ቀናዒ ተግባር ሊያግዝና አይዞህ ሊል ይገባዋል፡፡ እዚህ ላይ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾችም ቢሆኑ፣ ከሕዝብ የጋራ ጥቅም ተቃራኒ መቆማቸው ሊገታና በአዲስ ዓመት ሊታደስ የሚገባው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

በመሠረቱ በየትኛውም ደረጃ ሆነ በማንኛውም አቅጣጫ ሕዝብ መብቱን በራሱ ማስከበር ካልቻለ፣ መብቱ ሲነካ ‹‹ለምን?›› ብሎ ካልጠየቀ፣ ሕገወጥነትን ካልተቃወመ በቀር የአሳሳች ፖለቲከኞችና የጥፋት መንገድ አመላካቾች ሰለባ መሆን ብቻ ሳይሆን የሌቦች፣ የነፍሰ ገዳዮችና የብሔር ቁማርተኞች መጫወቻ መሆኑም አይቀርም፡፡ መንግሥት በየዘርፉ ያወጣለትን ሕግጋት የማስከበር ኃላፊነት በቀዳሚነት የራሱ የሕዝቡ ነው መባሉም ለእዚህ ነው፡፡ በመሠረቱ መንግሥታዊ ሥልጣን የያዘ አካልንስ ቢሆን የሚያባልገውና የሚያበላሸው የሕዝቡ ዳተኝነትና ምንቸገረኝ ባይነት አይደል እንዴ?

ባሳለፍነው አሮጌ ዓመት በገሃድ እንደታየው፣ በየጊዜው በክፉ ሰዎች እየተፈበረኩ ለሚሠራጩ ያልተረጋገጡ ወሬዎች (የጥላቻና አፍራሽ ተረኮች) ሰለባ ከመሆን ራሱን መጠበቅ፣  በዋናነት የሀቀኛ ልሂቃንና የአገር ተቆርቋሪዎች ግዴታ መሆን ነበረበት፡፡ እውነቱን ለማወቅ ጥረት ማድረግም የመላው ሕዝብ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ በየደረጃው የሚገኝን የመንግሥት አካል ተጠያቂና ግልጽ እንዲሆን የሚያደርግ ባህልም ይሉኝታችንን ገፎ መውጣት አለበት፡፡ መንግሥትም ቢሆን አስቀድሞ፣ ካልሆነም ቢዘገይም ተገቢ መልስ ለሕዝብና ለሚመለከተው አካል ሁሉ መስጠት አለበት፡፡

የፖለቲካ ካባ ደርበው የሚያስመስሉትን ሳይሆን የአብሮነትና የአገር ዋልታ የሆኑ የእምነት አባቶችና ሽማግሌዎች፣ ሚዛናዊ ሚዲያዎችና ኃላፊነት የተጣለባቸው የአገር መሪዎች የሚነግሩንን መስማትም ያስፈልጋል፡፡ ሰምቶም እውነቱን እያረጋገጡ መጠቀም የግድ ይሆናል፡፡ አሳዋቂ፣ አስተማሪና አስጠንቃቂ መልዕክቶችን በጥሞና ማዳመጥ የሥልጡን ማኅበረሰብ መገለጫ ነውና፡፡ በተለይ የኮሮና ጫና ሲቀንስ መጪው ጊዜ የምርጫ እንደ መሆኑ ከወዲሁ ፖለቲከኞችም ሆኑ የመብት ተሟጋቾች ለአገር ጉዳይ ይጠቅማል ብለው ለሚነግሩን ሐሳብ፣ የተለያዩ ስም አጥፊ ቅፅሎችን እየለጠፍን ከመተቸትና ከማጣጣል ወይም ከመልዕክቱ በስተጀርባ ሊኖር ስለሚችለው ሥውር ዓላማ ከመጨነቅ ይልቅ፣ ፊት ለፊት በግልጽ የተላለፈውን መልዕክት ማየትና የተሻለውን መምረጥ የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡

እንደ አንድ ባለድርሻ አካል መንግሥትም ሐሳብና መረጃ ሲለቅ ‹‹ውሸቱን ነው›› ካልን፣ መንግሥትም ሲነግሩት ‹‹ስሜን ሊያጠፉ ነው፣ ቀጣፊዎች ናቸው›› የሚል ከሆነ የሕዝብና የመንግሥት ፍላጎት ሊናበብ አይችልም፡፡ በዚህ ለመቀጠል ከተመኘን ደግሞ ውድቀታችን ከባቢሎን የባሰ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ሕዝብና መንግሥት መደማመጥ አለባቸው፡፡ ሕዝብ መንግሥትን፣ መንግሥትም ሕዝብን መስማት አለበት፡፡ ሰው ሲፈጠር ሁለት ጆሮና አንድ አፍ እንዲኖረው ተደርጎ ነው፡፡ ይህም ከሚናገረው እጥፍ እንዲሰማ ነው፡፡

መንግሥትም ካለፉት ዓመታት ችግሮች ተምሮ የራሱ መስሚያዎች ሊኖሩት የግድና ግድ ነው፡፡ የጆሮዎች ቁጥር ደግሞ ከሁለት በላይ ናቸው፡፡ ዋነኛው የመንግሥት ጆሮ ሕዝብ ነው፡፡ ተቃዋሚ ቡድኖችና ግለሰቦች፣ ገለልተኛ የሆኑና ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጠቀሙ ዜጎች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎችና የራሱ በርካታ ተቋማት በሙሉ መንግሥት ስለባህሪው  የሚሰማባቸው ዕድሎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን መስማት አለበት፡፡ የራስን ብቻ እያዳመጡ መደንቆር ውድቀት ነው የሚያስከትለው፡፡

ባለፉት 46 ዓመታት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በግልጽ እንደታየው ‹‹እኔ ብቻ ልናገር፣ የእኔን ብቻ ስሙ. . .›› የሚል መንግሥት ዋጋ የለውም፡፡ ምላስ ብቻ እንጂ ጆሮ ያልፈጠረበት መንግሥት ፍቅርን አያገኝም፡፡ ለራሱ የሚጠቅመውን ብቻ እየመረጠ የሚሰማ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ መስጠት ይሳነዋል፡፡ በዚህም ሕዝቡ ይንቀዋል፣ ይጠላዋል፡፡ ለንግግሩም ጆሮውን ይነፍገዋል፡፡ ቀኝ ሲጠይቁት ግራ የሚያወራ መንግሥት፣ ሕዝቡ ምን ያመጣል የሚልና በጉልበቱ የሚመካ ትዕቢተኛ መንግሥት መጨረሻው አያምርም (ይህንንም በተግባር ከአንዴ ሁለት ሦስቴ ዓይተነዋል)፡፡ በአዲሱ ዓመት በዚህ ሳቢያ የሚነሱ በይዘታቸው ፖለቲካዊ ለሆኑ ጥያቄዎች ሁሉ ተገቢውን መልስ እንዲያገኙ፣ የመተማመንና የመነጋገር ጥረታችንን ልናሳድግ ይገባል፡፡

በአዲሱ ዓመት ከነባር ችግሮቻችን ለመላቀቅ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ መንግሥትም እንደ መንግሥት ራሳችንን እንመርምር፡፡ ‹‹ከሐሰተኛ ወዳጅ እውነተኛ ጠላት ይሻላል!!›› የሚለውን ብሂል ዘንግቶ ማለፍም አይበጀንም፡፡ ዋናው ነገር አንዳችን ሌላኛችንን የምንሰማና ብሔራዊ ራዕይ ያለን ዜጎች እንሁን፡፡ የመንግሥትን ጀርባ ሳይበላው የሚያኩም ሆኑ፣ ሁሉንም ነገር ለመተቸትና ለመቃወም ብቻ የተዘጋጁ ኃይሎች እንዳንሆን መልካሙን ሚዛናዊ መንገድ የምንከተል እንሆን ዘንድ እንነጋገር፣ እንደማመጥ፡፡

የዛሬን ብሥራት በአሮጌ ጆሮ የማዳመጥ ባህል አይጠቅመንምና ይቅርብን፡፡ ያለፈው አልፏልና. . . ዳግም ላይመለስ ሄዷልና. . . አዲሱን ዓመት በአዲስ መደማመጥ ተቀብለን እናስተናግደው፡፡ ከአሮጌው ዓመት የወረስናቸውን ክፉ ነገሮች እንተዋቸው፡፡ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት እጅ ለእጅ ተያይዘን አዲሱን ዓመት ለመቀበል በይቅርታና በመልካም ምኞት እንነሳ፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣንና ለማይገባ ሥልጣን ስንል አንጠፋፋ፡፡ አዲሱን ዓመት ከሴራና ከበቀል ፖለቲካ የፀዳ እናድርገው፡፡ ጭንቀታችን ተወግዶ አዲሱን ዓመት በሰላም ለመቀበል ራሳችንን እናዘጋጅ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...