የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዓለም ባንክ ባገኘው የ150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍና ብድር ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በኢንስቲትዩቱና በሁሉም ክልሎች ዘመናዊ ላቦራቶሪዎች ግንባታና የአቅም ማጎልበት ሥራዎችን እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የሚገነባው ላቦራቶሪ ከሦስት እስከ አራት ዓመት እንዲሁም በየክልሉ የሚገነቡት 15 ላቦራቶሪዎች በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ላቦራቶሪዎቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ወደ ውጭ የሚላኩና ከፍተኛ ደኅንነትን የሚጠይቁ የምርመራ ሥራዎች ባገር ቤት እንዲከናወኑ የሚያግዝ ሲሆን፣ ለምሥራቅ አፍሪካም አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡
በአራት ዋና ዋና መርሐ ግብሮች የተከፋፈለው የፕሮጀክቱ ትግበራ በቀዳሚው መርሐ ግብር የኢትዮጵያን አጠቃላይ የላቦራቶሪ አቅም ማጠናከር፣ ደረጃ ሶስት ባዮ ሴፍቲ ብሔራዊ ሪፈረንስ ላቦራቶሪ (BSL3) በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ የመገንባት፣ 15 የክልል ሪፈረንስ ላቦራቶሪዎችን የመገንባትና ላቦራቶሪዎቹንም በቁሳቁስ የማሟላት ሥራዎች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የአገሪቷን የላቦራቶሪ አቅም ይበልጥ ያዘምናል የተባለለት የባዮ ባንክ፣ የጥገና ማዕከል፣ ዘመናዊ መጋዘን እና የጥራትና ቁጥጥር ማዕከል ግንባታዎች የሚሠሩ ይሆናል፡፡
የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርን ማጠናከሩ በሁለተኛው መርሐ ግብር የተካተተ ሲሆን፣ በሦስተኛው መርሐ ግብር ደግሞ የኢትዮጵያን የኅብረተሰብ ጤና ብሔራዊ የመረጃ አስተዳደር ማዕከል የማጠናከርና የማዘመን ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ በመጨረሻው መርሐ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የፀረ ተዋህስያን መድኃኒት ብግርነት (Antimicrobial resistance) ቋሚ ቅኝት የሚዘምንበት ሥራ እንደሚከናወን ዶ/ር ኤባ አስታውቀዋል፡፡