Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሄደውን ሸኝተን የመጣውን ተቀብለናል!

ሰላም! ሰላም! እንዴት አላችሁልኝ? እንዴት ነው አገሩ? አየሩ? የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን ወግ ስንሰልቅ ከቁምነገር መራቅ የለብንም፡፡ መቼም በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጭማሪ የሚባለው ነገር ግዴታ ሳይሆን አይቀርም መሰለኝ አንድም የሚቀንስ ነገር ጠፍቷል። ሕይወት ኑሮን ቀለል፣ ላላ፣ ዘናና አስደሳች ያደርጋል እንጂ ለምን ውጥረት በውጥረት ያደርገናል? የባከኑት በርካታ ዓመታት እየቆጩኝ ስለሆነ ነው   የጠየቅኳችሁ እንጂ፣ ለሌላ አይደለም አደራ። ዘንድሮ እኮ አለማወቅም ራሱ ጨምሮላችኋል። እውነቴን እኮ ነው! ያው ሳያውቁ፣ ሳይመረምሩና ሳይረዱ አዋቂ መምሰል በዝቷል ማለቴ ነው። የሆነ ነገር ስታወሩ ዝም ብሎ ሲያዳምጥ የቆየ ጀብራራ፣ ‹‹I know…›› ይላችኋል። ካወቅክ ምን አስለፈለፈኝ ብላችሁ ዝም ብትሉት፣ ‹‹ጨዋታህን አቋረጥከውሳ?›› ብሎ ለንዝንዝ ይነሳል። እሺ አሁን ይኼን ምን ትሉታላችሁ? ‹‹ዲስኩር ያሳበጠው ሁሉ ነገሩን በሙሉ የልጅ ጨዋታ አድርጎት ይረፈው? መጥኔ!›› ይሉ የነበሩት ባሻዬ ሰሞኑን ድምፃቸው ጠፍቷል፡፡ በአዲስ ዓመት መግቢያ ምን አስለፈለፈኝ ብለው ይሆናል፡፡ በእሳቸው ምትክ ዛሬ እኔ አለሁ፡፡

ይገርማችኋል እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በአጉል ወሬ አላምንም፡፡ ይኼ ከላይ ነካ ነካ ያደረግኩት ለጨዋታ ያህል መሆኑን አጢኑልኝ፡፡ ይኼን አለ ተብዬ ደግሞ መቆሚያና መቀመጫ ልጣ? ሆሆ! ድሮ ሰው ፀጥታውንና ሰላሙን ያጣ የነበረው አገሩ በጠላት ስትወረርና አስመራሪው ረሃብ ከደጃፉ ከደረሰ ነበር፡፡ አሁን ግን የሰው መጥፊያው አፉ ሆኗል አሉ። በተለይ ወሬ፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች በማስረጃ የሚታወቁ ናቸው ተብሏል። እነሱ ሥራቸው ስለሚመሰክር እኔን አያገባኝም። ምን ነበር እ . . . አዎ ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል›› ተብሏል እኮ? ኧረ ምን ያልተባለ አለ? ‹‹ጉድና ጅራት ከበስተኋላ ነው›› ሲባልስ ያልሰማ አለ? አንድ ጊዜ አንዱ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ አሉ፡፡ ዳኛው ቆጣ ብለው፣ ‹‹ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?›› ሲሉት ከሳሹን እየገላመጠ፣ ‹‹ልጅ ከሳሽ አባት ዳኛ በሆኑበት እንዴት አላጠፋሁም እላለሁ?›› አለ አሉ፡፡ ዳኛው እየሳቁ፣ ‹‹ተሳስተሃል እኔ አጎቱ እንጂ አባቱ አይደለሁም፡፡ ስም በማጥፋትህ ደግሞ ትቀጣለህ፤›› ብለው ቂሊንጦ ላኩት ተብሎ ተወርቷል፡፡ ሰው በቃ ያለወሬ ነገር የለውም እንዴ?

መቼም ከተነሳ ላይቀር አንዳንዱ ዶክመንተሪ መሥራት ይወዳል ብቻ ሳይሆን፣ ካልሠራ ያቃዠዋል ሲባል ሰምቼ እነግራችኋለሁ ስል ይኼው ረስቼው ነበር። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የወሬ ዶክመንተሪ ጠላት የሚባሉትን ድባቅ መምቻ ጎራዴ ነው፤›› አለኝ። እኔ ግን ግራ ገብቶኝ በዚህ የመደመር ዘመን ደግሞ የምን ጠላት አለ? የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ ሲደጋገፍ እንጂ በጠላትነት ሲፈራረጅ አይታወቅም ብዬ አሰላሰልኩ። ብዙም ሳልቆይ ግን የአገራችን ‹‹ጠላቶች›› ብዛት ታወሰኝና ነገሩ ገብቶኝ ተውኩት፡፡ አዎ! ማለፍ መልካም ነው! ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› ይላሉ ባሻዬ ከነገር ሲሸሹ፡፡ እኛ ግን ከነገር ሳይሆን፣ ከአጉል ነገር ላይ ገልበጥ ብለን ብንቀየስስ? ‹‹ያልተገላበጠ ያራል›› ሲባል አልሰማችሁም? የሐበሻ ልጆች ሆናችሁ ይኼን አታውቁም ማለት ንቀት ስለሆነ ይቅርታ እጠይቃችኋለሁ፡፡ በአዲስ ዓመት መግቢያ ላይ ሆነን ይቅር መባባል አለብን እኮ፡፡

እስኪ ሰሞኑን በጣም አስቀይሞኝ የነበረውን ነገርና የሆንኩትን ላጫውታችሁ። ያስቀየመኝ አንድ አስተያየት ሰጪ ነው። ሰውዬው የአገር ጉዳይ እየተወራ ሳለ ድንገት ጥልቅ ብሎ፣ የአንዱ ተጠርጣሪ ሌባ ጠበቃ ይመስል እንዴት ሕግ ባለበት አገር ይታሰራል ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ፡፡ እኔማ ይኼ ሰውዬ አብሮ ተካፍሎ የበላ ሌባ ነው ብዬ ለፖሊስ ጥቆማ ላቀርብ ስልኬን ብመታ የፖሊስ ነፍሴ ስልክ አይመልስም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የወሬ ቱማታ ከሰማሁ በኋላ ምርር ብሎኝ ባሻዬ ዘንድ ሄድኩ። ነገሬን ሲረዱ፣ ‹‹ቱ ቱ! ምነው አንበርብር ምነው? ከማንም ሌባ ጋር ምን አፍ አካፈተህ፡፡ ይኼ የሰው ከንቱ በለመደ አፉ ሲለፈልፍ ዋጋውን የማያገኝ መሰለህ?›› እያሉ መክረውኝ ተመለስኩ፡፡ ግን ሰው በስንቱ ተስፋ ቆርጦ ይችለዋል? እስኪ አስቡት! መተሳሰብና መተዛዘን በጠፋበት ዘመን ይሉኝታ ቢስነት ሲጨመርበት ተስፋ አያስቆርጥም? ራስ ወዳድነት ተንሰራፍቶ ሌብነት ጣሪያ በነካበት በዚህ ዘመን ሀቀኛ መሆን ምን ያህል ከባድና ቆራጥነት እንደሚጠይቅ ገባኝ፡፡ ለሀቅ የቆማችሁ አዲሱን ዓመት የእናንተ ያድርግላችሁ፡፡ ለሐሰት የቆማችሁትን ደግሞ ልቦና ይስጣችሁ፡፡

አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ምሳሌ ሲገጥማችሁ ምን ትላላችሁ? አንዴ ‘እንዴት ተባለ?’ ብዬ ብጠይቅ የሚነግረኝ ሰው አጣሁ። ልፋ ብሎኝ እንጂ የዛሬ ዘመን ሰው እንኳን ተረትና ምሳሌ ታሪክ የተመሠረተበትን ጥንተ ነገር ሊነግረኝ፣ አጥንቱ ድረስ የሚሰማውን ስሜቱን በቅጡ አፍታቶ መናገር እንደተሳነው ማስታወስ ነበረብኝ። እንዳልኳችሁ ታዲያ ብዙ ነገር ይረሳል። እንኳን በሽታ የመድኃኒት ሰዓትም እንረሳለን እኮ? ብዬ ብዬ ሲደክመኝ ታዲያ ወዲያ ወዲህ ተንገላውጄ ደከመኝና ለሻይ ለቡና አረፍ ወደምልባት ካፌ ጎራ አልኩ። በምናብ የመመነን መብቴን ለመጠቀም። ይገርማችኋል አንዳንዴ በተፈጥሮ የተቀዳጀናቸውን መብቶች የትም ድረስ ገፍተን ለመጠቀም ሳንሞክር ‘ፌስቡክ’ የመጠቀም ነፃነቴን ገደበው ብለን ‘ኔትወርኩን’ የምንራገም ሰዎች ነገር ያሳስበኛል። ይኼም ታዲያ የማሰብ መብቴ ነው እንዳትጋፉኝ። ከግፊያ ነው እንዴ ተጠፍጥፈን የተሠራነው አያስብልም አንዳንዴ?

እናም አንድ ጎተራው የሞላለት እህል የበረከተለት ገበሬ ነበር አሉ። የእህሉ ጎተራ ብቻ ሳይሆን፣ ጥበብ ሞልታ የተረፈችውም ነው። ‹‹መቼም ጥበብ በሕይወት ተሞክሮ ጭምር እንጂ በቀለም ብዛት ብቻ አትገኝም። የምትገኝ እየመሰላቸው ግን ቀንድ የሚያስበቅሉ ቀንዳሞች የሚያስቀምጡም አልሆነ ዘንድሮ፤›› ይላሉ ባሻዬ አዘውትረው ስለጥበብ ሲሰብኩ። አሁን አካሄዴ እንዳይበላሽብኝ የባሻዬን ስብከት ለባሻዬ እተወዋለሁ። መተውን የመሰለ ነገር ምን አለ? እናም ጠቢቡ ገበሬ ሞልቶ ከፈሰሰው የእህል ጎተራው ወረቱን መድቦ፣ ድርቅ ቢከሰት ቤተሰቡ እንዳይራብ የሚቀብረውን ቀብሮ፣ የተረፈውን ገበያ ሊያወጣው ያስባል። ሊሸጠው ያሰበው እህል ብዙ ነበርና ያሉት አህዮች አልበቁትም። የሀብቱን ቅጥ ማጣትና የእህሉን መትረፍረፍ ያየ ሰነፍ ጎረቤቱ ‘እህም!’ ይልና ገበሬው ለጭነት የሚሆኑ ተጨማሪ አህዮች ሊለምን ወንዝ ተሻግሮ ባደረበት፣ እህሉን በታታሪው ገበሬ አህዮች ጭኖ ገበያ ሲያወጣው ተይዞ፣ ‹‹የማን እህል ነው?›› ቢሉት ደንግጦ ‹‹የአህያ ለማኙ!›› ሲል፣ ‹‹እንዴት ጫንከው?›› ይሉታል፣ ‹‹አህዮቹን አባብዬ!›› አለ አሉ፡፡ እንዲያው ፍረዱማ በአገራችን ዱላ እንጂ ሽንገላ አህያን ይገዛል?! ኦ! ለካ ‹‹አትፍረድ ይፈረድብሃል›› ተብለናል! ዘንድሮ እኮ አናጋሪው በዝቷል!

ጨዋታን ጨዋታ ያመጣው አይደል? ‘መብራት ነው በጩኸትም በጨዋታም የማይመጣው’ አትሉም? ለማንኛውም ሁሉም በጊዜው ይመጣል። ‹‹በመንገድ ሥሪት ጣልቃ አትግቡ›› ይላሉ መንገዱን የተመላለሱበት። ‹‹እንዴት?›› ሲባሉ፣ ‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ የሚለውን መጽሐፍ አንብብ፤›› ብለዋችሁ ይቀየሳሉ። ሰውም እንደ መንገድ ባገኘው አጋጣሚና አቅጣጫ የሚቀየስ ሆኗላ። ታዲያ ሰሞኑን ከአንድ ደላላ ወዳጄ ጋር ተደራጅተን ሦስት ያገለገሉ ‘ስካኒያ’ ባለ ተሳቢዎች ልናሻሽጥ ወዲያ ወዲህ ስንል ነበር። እንደ ዝንጀሮ ከአንዱ ግንድ ወደ ሌላው አንዘል ነገር እንኳን በዝላዩ በሩጫውም ውጤታችን እያሽቆለቆለ ነው። እንደ አገር ሳይሆን እንደ ግለሰብ ነው የማወራው። በአገሬ የዝላይ ውጤት አንድም ሰው እንዳይመጣብኝ የቀረኝ ነገር ቢኖር ‘አትምጡብኝ’ የሚል ጽሑፍ የታተመበት ቲሸርት መልበስ ነው። በነገራችን ላይ ቲሸርቱ ማሠራቱን አስቤበት ብሩኋ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹መንታ ትርጉም ደረትህ ላይ ለጥፈህ ስትዞር መንታ ጥፊ አይቀርልህም፤›› ብላ አስተወችኝ። ‘መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል’ ብላ ስትቀጥል ‘ስለቲሸርት ነው ያወራኋት ስለመደብ ትግል?’ እያልኩ ዞረብኝ። ‘ኤኒ ዌይ!’ ያለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው ለካ?

በሉ እንሰነባበት። ሁለቱ ስካኒያዎች ተሸጡልን። አንዱን ይኼው ይዘነዋል። ‘ኮሚሽኔ’ ከበድ ያለ ስለነበር ለማንጠግቦሽ ከወትሮው በበለጠ ለአዲስ ዓመት በዓል ጨመርመር አድርጌ ለአስቤዛዋ ብቆርጥላት ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት፣ ክትፎ ብቻ አደረገችው። ‹‹ምነው?›› ስላት፣ ‹‹የአዲስ ዓመት መቀበያ ነዋ!›› ሆነ መልሷ። ምን ላድርጋት? ‘ተገኘ ብሎ መዛቅ እኮ ለሆድ ብቻ አይደለም ጦሱ። ጎረቤትም ያያል። ስቀለውም ይከተላል’ እንዳልላት ያው ለእኔው ደስታ ስለሆነ ዝም አልኩ። ምሁሩን የባሻዬን ልጅ አዘውትረን ወደ ምንገናኝባት ግሮሰሪ ይዤው ሄጄ የማንጠግቦሽ ‘ክትፎ፣ ክትፎ’ ማለት እንዳሠጋኝ ስነግረው፣ ‹‹ሞኝ ነህ አንዳንዴ እኮ?›› ብሎ አላገጠብኝ። ሞኝነቴን ሲተነትን፣ ‹‹አንተ ብቻህን ያጡ የተቸገሩትን አስበህ፣ አንተ ብቻህን ለዓለም ሰላም መክረህ ዘክረህ፣ ሌብነትና ዝርፊያ ላይ ዝተህ፣ ለዴሞክራሲ ፎክረህ አይሆንማ፤›› አለኝ። ታዲያ የማን ትከሻ ላይ እንጣለው?

ይኼን የሰማ ደግሞ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ኧረ ሰብሰብ ብለህስ ፎክረህ መቼ ሆነ?›› አለው። ‹‹እንዴት?›› ይላል ሌላው። ‹‹ይሰበሰባሉ ይበተናሉ። ያው ችግር፣ ያው ረሃብ፣ ያው ዝርፊያ፣ ያው ግጭት መልክና ዓይነቱን እየቀየረ አለ። ጭራሽ አሁንማ ዝርፊያውና በብሔር መጠቃቀሙ ይሉኝታ የሚባል ነገር አላውቅም ብሎ በገሃድ ሆነ እኮ…›› ብሎ እያንዳንዳችን ላይ አፈጠጠብን። ‹‹ልጄ ያየውን ሁሉ ግዛ እያለ የሚያፈጥብኝ አይበቃኝም? ምን ያፈጥብኛል?›› ይላል ከባሻዬ ልጅ አጠገብ የተሰየመ ጎርደን ጂን በቶኒክ ፉት የሚል። ይኼኔ ተራውን ሌላው ተነስቶ፣ ‹‹አንድ ጊዜ ብቻ ሕዝባችን ድምፁን ቢሰጠኝና የመነጋገሪያውን መድረክ ብይዝ… ‘ሰው መሆን ይቅደም። ፖለቲካና ሴራ ወደ ኋላ!’ የሚል አጭር፣ የአገራችን ሕዝብ በታሪኩ ሰምቶት የማያውቅ ታሪካዊ ‘ስፒች’ አድርጌ ሥልጣኔን በሰላም አስረክብ ነበር። የጣፋጭ አንደበት ንግግር ምን ያህል አሪፍ እንደሆነ እያያችሁ፣ እያዳመጣችሁ አይደል? ለሰዓታት ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ሊበራል ዴሞክራሲ፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ፍቅር ያሸንፋል… ’እያሉ ነገር ከሚያራዝሙብን፣ ‘ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! የእኩልነትና የፍትሕ አምባ’ ብለው በጥዑም አንደበት አንጀታችንን ሲበሉት ደስ አይልም? የከፋው የራሱ ጉዳይ፣ እኔ ግን ልቤ በሐሴት ረስርሷል፡፡ አሁን ዋናው ጉዳይ የሄደን መሸኘት የመጣን መቀበል ነው፡፡ ዓመቱንም ጭምር ማለቴ ነው…›› እያለ ሲቀመጥ ግሮሰሪያችን በሳቅ ተናጋች፡፡ መልካም አዲስ ዓመት! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት