Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአዲሶቹን አራት ዓመታት ዓውድ የተቀበለችው ኢትዮጵያ

የአዲሶቹን አራት ዓመታት ዓውድ የተቀበለችው ኢትዮጵያ

ቀን:

‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ!›› ዘመን በተሞሸረ ዓመት በተቀመረ ቁጥር በዝማሬም በንብነባም የሚስተጋባ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ብሂል ነው፡፡

ጠንካራው ክረምት ጋብ ሲልና አዲሱ ዘመን ሊብት ከዋዜማው ጀምሮ ብቅ የሚለው የወቅቱ መገለጫ ዓደይ አበባ ለኢዮሃ አበባዬ መነሻ ናት፡፡ ኢዮሃ የምትለው ቃል ሁለት ቃላት ተጣምረው የፈጠሯት እንደሆነ በመዝገበ ቃላት ተመልክቷል፡፡ ‹‹እይ ውኃ ያደረገውን ተመልከት›› ለማለት ኢዮሃ ተባለ ይላሉ፡፡ ሰኔ ግም (“ም” ይጠብቃል) ብሎ የሐምሌ ጭለማን አልፎ የነሐሴን ጎርፍ ተሻግሮ መስከረም ብቅ ሲል አብራ የምትከሰተው ኃይለኛው ዝናም የሚያፈልቃት ዓደይ አበባ ነችና ‹እይ ውኃ›› ያደረገውን ተመልከት ብለውም ያፍታቱታል፡፡

ዓርብ መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፣ የ13 ወራት ጸጋ መነሻ ሆኖ ተጀምሯል፡፡ ዘንድሮ የአዲስ አንድ ዓመት መነሻ ብቻ ሳይሆን የአዲሶቹ አራት ዓመታት (2013፣ 2014፣ 2015 እና 2016) መጀመርያ ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ የሚመላለሰውና ‹‹ዓውደ ጳጉሜን›› የሚባለው የዓመታት ዙር መነሻነት ይታወቃል፡፡ ጥንተ ነገሩም ሦስቱን ዓመታት 5 ቀን፣ በአራተኛው ዓመት 6 ከምትሆነዋ ጳጉሜን ጋር ይያያዛል፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረትም ‹‹ዓውደ ወንጌላውያን›› የሚል ተጨማ ስያሜ ኖሮት እያንዳንዱ ዓመት በወንጌላውያኑ ማቴዎስና ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ይጠራል፡፡ በዚሁ መንገድ ዓምና ያከተመው 2012 ዓ.ም. የዮሐንስ መንገድ ያለፉት አራት ዓመታት ማብቂያ ሆኖ ሲያልፍ ዘንድሮ የባተው 2013ን ተረኛ ሆኖ የተረከበው ማቴዎስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ምዕመናን ከትናንት በስቲያ ዓርብ ሲገናኙ ‹‹እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ አሸጋገረን›› በማለት መልካም ምኞት የተለዋወጡት፡፡ 2013 ለ4 ሲካፈል 503 ደርሶ 1 ስለተረፈ ነው ማቴዎስ መባሉ፡፡

የመስከረም 1 ስያሜዎችና ልዩ ልዩ አቆጣጠሮች

የዓመት መባቻዋ መስከረም 1 ቀን ልዩ ልዩ መጠርያ አላት፡፡ አንደኛው ዕንቁጣጣሽ ከአበባ ጋር ተያይዟል፡፡ ሁለተኛው በቤተ ክርስቲያን አጠራር “ቅዱስ ዮሐንስ” (አጥማቂው) ተብላም ትጠራለች፡፡ የዓመት ዙረት መነሻ ዋና ዕለት ስለሆነችም “ርዕሰ ዓውደ ዓመት” ትባላለች፡፡

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) በሦስቱ የብርሃን መለኪያዎች በፀሐይ፣ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር ፣ እንዲሁም በጨረቃ ይቆጥራል፡፡ ከክርስቶስ ኢየሱስ ልደት በመነሳት 2013 የተባለው መሬት በፀሐይ ዙርያ ያደረገችውን የ365.25 ቀኖች ዙረት በመፈጸሟ ነው፡፡ ይህ አቆጣጠር ከቤተ ክርስቲያን በተጨማሪ በሲቪል አቆጣጠርም አገልግሎት አለው፡፡ ሌላው ከአዳም ተነሥቶ በሚቆጥረውም 7513 ዓመተ ዓለም ላይ ያመለክታል፡፡ ይህም ስምንተኛ ሺሕ ከገባ 513ኛ ዓመት መሆኑን ያሳያል፡፡

በሌላ የኢትዮጵያ አቆጣጠርም ዓርብ መስከረም 1 ቀን 2021 ዓ.ም. ገብቷል፡፡ ይኸኛው አቆጣጠር ደግሞ የፀሐይና የጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤን (ፋሲካ) እና ዐቢይ ጾም (ሁዳዴ) እንዲሁም መሰል ተዘዋዋሪ በዓሎችና ጾሞች ለማግኘትና ለማወቅ የሚያስችላት አቆጣጠር ነው፡፡ የእስልምናና የቤተ እሥራኤል ሃይማኖታዊ በዓላት የሚገኙትም በዚሁ በ2021 ቀመር ነው፡፡

ዘንድሮ የፋሲካ በዓል ሚያዝያ 24 ቀን ይከበራል፣ ዐቢይ ጾም የካቲት 29 ቀን ይያዛል፣ የቤተ እሥራኤል አዲስ ዓመት ሮሽ ሃሻናህ መስከረም 9 ቀን ማክበር ይጀመራል የሚባለው፣ የነቢዩ መሐመድ መውሊድ ሐሙስ ጥቅምት 19 ይከበራል የተባለው የፀሐይና የጨረቃ ጥምር ኢትዮጵያዊ አቆጣጠርን 2021 ጭምር ይዞ ነው፡፡

ሦስተኛው አቈጣጠር ደግሞ 354 ቀኖች ባለው የጨረቃ አቆጣጠር የሚቆጥረው ነው፡፡ አይሁድ፣ ክርስቲያንና እስላም በዚህ አቆጣጠር ይጠቀማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሌሊቱን የምትቆጥርበት መንገድ አላት፡፡ ዓመታቱንም በጨረቃ 354 ቀን ልኬት ታሰላለች፡፡ ዓርብ መስከረም 1 ቀን የገባው አዲሱ ዓመትም ከክርስቶስ ልደት ሲነሳ 2074 ዓመት፣ ከ9 ወር፣ ከ7 ቀን (ሲጠጋጋ 2075 ዓ.ም.) ይሆናል፡፡

ይህም የዘመን ቁጥር መነሻቸው እንደየትውፊታቸው ሆኖ የዕለት ቁጥራቸው ግን ከጨረቃ አንፃር ክርስትናው ከእስላም (ሒጅራ) ሆነ ከቤተ እሥራኤልም አቆጣጠር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ዓመቱ የባተበት መስከረም 1 ቀን በክርስትና የጨረቃ መስከረም 23፣ በእስልምና አቆጣጠር ሙሃረም 22 ቀን 1442 ዓመተ ሒጅራ (ነቢዩ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ያደረጉት ጉዞ)፣ በቤተ እሥራኤል ኢሉል 22 ቀን 5780 ዓመተ ዓለም ነው፡፡

በግሪጎሪያን አቆጣጠርም ሴብቴምበር 11 ቀን 2020 ሲሆን በጁሊያን አቆጣጠር ደግሞ ኦገስት 29 ቀን 2020 ሆኗል፡፡ 

ዓደይ አበባ ስትገለጥ

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መስከረም ባተ፡፡ ሰኔ ግም ብሎ የሐምሌን ጨለማ አልፎ፣ ዕኝኝ ብላን (ከነሐሴ 28 ቀን እስከ 30 ባለማቋረጥ የሚዘንበው) ጎርፍ በጳጉሜን በኩል ክረምቱ ሲሻገር፣ መስከረምን የምታደምቀው ዓደይ አበባ ትከሰታለች፡፡ በመስከረም የምትፈነዳውና ለኢትዮጵያ ምድር ጌጧ ሽልማቷም የሆነችው ዓደይ አበባ እንደ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ዓደይ ሲፈታ የበጨጨ፣ ብጫ የሆነ አበባ ነው፡፡ ግሱ “ዐደየ” በጨጨ፣ ብጫ መሰለ፤ ነጣ፣ ነጭ ሆነ ሲሉም ይፈቱታል፡፡ በኦሮምኛ ነጭን ዐዲ፣ ፀሐይን ዐዱ የሚለው ከዚህ የወጣ ነው ሲሉም ያክሉበታል፡፡

ስለዓደይ አበባ ተክል ምንነት ሳይንሳዊ መግለጫ ያዘጋጁት ዶ/ር ከበደ ታደሰ የኢትዮጵያ ወፍ ዘራሽ አበቦች (Wild Flowers for Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ስለዓደይ አበባ ከምትበቅልበት ከተለያዩ ከፍታዎች አንፃር በሁለት መልክ እንዲህ ጽፈዋል፡፡   

የተከፋፈሉ ሰፊ ላይዶ ቅጠሎችና ስምንት የተበተኑ መልካበቦች ያሉት ዓመታዊ ሃመልማል፣ ከመንገድ ዳር ዳርና ከቃሊም እንዲሁም በከፍተኛና ድንጋያማ ተዳፋት፣ ከ400 እስከ 2,700 ሜትር ከፍታ ላይ ይበቅላል፤ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥም ያብባል፡፡ በሌላ በኩልም እስከ ኅዳር ድረስ የሚያብበው የሚገኘው ከ2,000 እስከ 3,600 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፡፡ ይህንንም ዶ/ር ከበደ ሲገልጹት፣ ዓደይ አበባ ረጃጅም ግንድና ሰፋ ያለ ላይዶ ቅርጽ ያላቸው ቅጠሎች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚበቅል ከረም ሃመልማል ነው ይሉታል፡፡ መሀላቸው ብርቱካንማ የሆነ ብጫ አበቦች በግንዱ ጫፍ ሰብሰብ ብለው ይታያል፡፡

“ዓደይ ዓደይ የመስከረም እንዳንቺ ያለ የለም” ተብሏል፡፡ “መስከረም መስከረም የወራቱ ጌታ አበቦች ተመኙ ካንተ ጋር ጨዋታ” እየተባለም ድሮ በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ቤት ተማሪዎች ሲዘምሩ እንደነበር መጽሐፋቸው ይናገራል፡፡

‹‹አሮጌው 2012/2020 ከቀለበቱ ዓውድ ይውጣ፣ አዲሱ 2013/2021 በተራው ወደቀለበቱ ይግባ፡፡ በቀለበቱ ውስጥ ሠግረ ክረምት ጥዑም ደወል ይሰማል፡፡ ሐሰት፣ ክፋት፣ ሐኬት ከቀለበቱ ይውጣ፤ ሐቅ ሰላም፣ ቅንነት፣ ትጋት ፍቅር ወደ ቀለበቱ ይግባ፤›› እንዲል፡፡

እሑድ መስከረም 3 ቀን በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ

  • መስከረም 3 ቀን 7513 ዓመተ ዓለም (ከአዳም ተነሥቶ የሚቆጥር)
  • የጨረቃ መስከረም 25 ቀን 7743 ዓመት ከ7 ወር ከ16 ቀን
  • መስከረም 3 ቀን 2013 ዓመተ ምሕረት (ከክርስቶስ ልደት ተነሥቶ በፀሐይ የሚቆጥር)
  • መስከረም 3 ቀን 2021 ዓመተ ምሕረት (ከክርስቶስ ልደት ተነሥቶ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር የሚቆጥር)
  • የጨረቃ መስከረም 25 ቀን 2074 ዓመት ከ9 ወር ከ7 ቀን
  •  ሙሃረም 25 ቀን 1442 ዓመተ ሒጅራ (ከነቢዩ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ስደት ተነሥቶ የሚቆጥር)
  • ኢሉል 24 ቀን 5780 ዓመተ ፍጥረት (የቤተ እሥራኤል አቆጣጠር)
  • ሴፕቴምበር 13 ቀን 2020 (በጎርጎርዮሳዊ አቈጣጠር)
  • ኦገስት 31 ቀን 2020 (በዩሊየሳዊ አቈጣጠር)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...