በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተዘጋጀው የአምስት ሚሊዮን ብር የዕራት መርሐ ግብርና ከተለያዩ ለጋሾች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሸራተን አዲስ ሆቴል ፊት ለፊት ሲገነባ የቆየው የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ፣ ሐሙስ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ተመረቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን የማሳመርና የማስዋብ ዕቅድና የወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት አካል የሆነው ሸገር ፓርክ በውስጡ ሰው ሠራሽ ሐይቅ፣ የሬስቶራንት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች፣ የአበባ መናፈሻ፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ መድረኮችን የያዘ ነው፡፡
ከእንጦጦ እስከ አቃቂ ወንዝ ድረስ 56 ኪሎ ሜትር ርዝመትን አካቶ በ29 ቢሊዮን ብር እንደሚገነባ የተገለጸው የዛሬ ዓመት ገደማ ሲሆን፣ ለግንባታው የሚሆን ገንዘብ ያዋጡ 255 ግለሰቦች በአንድነት ፓርክ ውስጥ በሚገኘው የግብር አዳራሽ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ዕራት ታድመዋል፡፡
በሸገር ፓርክ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ከአንድ ሺሕ በላይ ታዳሚዎች ሲገኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ እንዲሁም ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ታድመዋል፡፡ በዚህ በወታደራዊ ትርዒት የደመቀ የምረቃ ዝግጅት ላይ ዘመናዊ የወታደራዊ መጓጓዣዎች፣ መሣሪያዎች፣ እንዲሁም የወታደራዊ ብቃት ማሳያ አካላዊ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አገሮች፣ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ዕውቅና የተሰጠበት ነበር፡፡ የቻይና መንግሥትን የወከሉት አምባሳደር ታን ጅያን፣ የቻይና መንግሥት የንግድ አታሼ ሊ ዩ፣ የወዳጅነት አደባባይ ዲዛይነር ሺ ሺዮን፣ የቻይና ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የፓርኩ የዲዛይን ማኔጀር አቶ ምንውየለት ምሥጋና፣ አቶ ደረጀ ተክሌ፣ በቀን ሥራ ለተሳተፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ለሌሎች የዕውቅና ሰርተፍኬትና ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ባያደርጉም ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹እንኳን ለ2013 ዓ.ም. በሰላም አደረሳችሁ›› በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸው፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንዲህ ያለ የሕዝብ መዝናኛና በርካታ ጉዳዮች ሊከናወኑበት የሚችል ፓርክ በማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ብዙም የሕዝብ መዝናኛና ፓርክ የላትም ተብላ የምትታማው አዲስ አበባን በሌላ ከፍታ ላይ የሚያስቀምጣት ይሆናል ብለው፣ ከዚህ ባለፈ የሸገር ፓርክም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ልማቶች ተባብሮ መሥራት ሊያስገኝ የሚችላቸው ድንቅ ውጤቶች ማሳያ ናቸው ሲሉ አክለዋል፡፡
ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ወደ አገር ሊሰፋ ይገባል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቀድመው በተናገሩት መሠረት በጎርጎራ፣ በወንጪና በኮይሻ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት ሦስት ቢሊዮን ብር የሚሰበሰብለት የአሥር ሚሊዮን ብርና የአምስት ሚሊዮን ብር ዝግጅቶች ተሰናድተዋል፡፡ ለሦስቱ ፕሮጀክቶች ልማት ስድስት ቢሊዮን ብር ለመስብሰብ ታስቧል፡፡