በየዓመቱ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከሚደረጉ የተለያዩ ጥረቶች አንዱ አካል የሆነው የመንገድ ደኅንነት ትምህርት፣ በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ሊካተት ነው፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢሊያና ሆቴል ባካሄደው የምክክር መድረክ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት እንደተቀረፀና በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ መሰጠት እንደሚጀምር ወ/ሮ ሙሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንድም ሰው በተሽከርካሪ አደጋ መሞት የለበትም›› በሚል መሪ ቃል የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሕዝባዊ ንቅናቄ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ‹‹ከጳጉሜን እስከ ጳጉሜን እንደርሳለን›› የሚል መፈክር በማንገብ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት በተለያዩ ዘዴዎች በመሰጠት ላይ ነበር፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሚያካሂደው ተከታታይ የመንገድ ደኅንነት ዘመቻዎች ውጤት እየተገኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከ4,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን በተሽከርካሪ አደጋ ያጣሉ፡፡ በ2012 ዓ.ም. 4,133 ሞት የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር አሥር በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ 6,929 ከባድ የአካል ጉዳትና 5,247 ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡
በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ደኅንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ለማ የተሽከርካሪ አደጋ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የእያንዳንዳችንን ቤት እያንኳኳ ነው፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ የመገናኛ ብዙኃን በማኅበረሰብ ውስጥ ግንዛቤ በመፍጠር ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አነስተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ያላት ቢሆንም፣ በዓለም በተሽከርካሪ አደጋ በቀዳሚነት ከሚዘረዘሩ አገሮች ተርታ ተሠልፋለች፡፡ በቅርቡ የተሽከርካሪዎች ቁጥር 1.2 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በ10,000 ተሽከርካሪዎች 34.4 አደጋ እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡ ከሚደርሱት የተሽከርካሪ አደጋዎች 68.4 በመቶ በአሽከርካሪዎች ስህተት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞች ውጤታማ የሆነ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለማካሄድና ግንዛቤ ለመፍጠር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴርና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በቅርበት ተባብረው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ወ/ሮ ሙሉ በበኩላቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመንገድ ደኅንነት ለማረጋገጥና ሕዝባዊ ግንዛቤ ለመፍጥር ቆርጦ መነሳቱን ገልጸው፣ ከመገናኛ ብዙኃንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ከሚኒስትሯ ጀምሮ ሁላችንም በዚህ ጉዳይ በቁርጠኝነት በመሥራት ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡