የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሁሉም አገሮች የአሠልጣኞች አሠልጣኝ (ኢንስትራክተሮችን) ጨምሮ ከ”ሲ” እስከ “ኤ” ደረጃ ሲሰጥ የቆየውን የእግር ኳስ አሠልጣኞች ሥልጠና እንዲቋረጥ አድርጎ አዲስ የሥልጠና ኮንቬንሽን (መመርያ) በማዘጋጀት ለአባል አገሮች በትኗል፡፡ ካፍ ኮንቬንሽኑን ለማዘጋጀት የተገደደው ነባሩ የሥልጠና ሥርዓት ከብቃትና ጥራት ጋር ተያይዞ ክፍተት እንዳለበት በጥናት በመረጋገጡ እንደሆነም ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኮንቬንሽኑን ተከትሎ በቴክኒክ ዲፓርትመንቱ አማካይነት ሲሰጥ የቆየው የእግር ኳስ አሠልጣኞች የሙያ ማረጋገጫ ሥልጠና መስጠት ካቆመ ከረምረም ብሏል፡፡ በዚህም ክፍያ በግላቸው ፈጽመው ሥልጠናውን የወሰዱ የመጨረሻዎቹ ሠልጣኞች እስከ አሁን ምንም ዓይነት የብቃት ማረጋገጫ “ላይሰንስ” ያላገኙ በየደረጃው በርካታ ቁጥር ያላቸው አሠልጣኞች ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል፡፡
ይሁንና አባል አገሮች ኮንቬንሽኑን ተቀብለው ወደ መሬት በማውረድ ተግባራዊ ከማድረጋቸው በፊት ከኮንቬንሽኑ ጎን ለጎን በቅድመ ሁኔታነት የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አመልክቷል፡፡ እስካሁን ባለው ኢትዮጵያ ከቅድመ ሁኔታዎቹ (መስፈርቶች) ያሟላችው ቢኖር ኮንቬንሽኑን መቀበሏ ካልሆነ ሌላ የሚጠቀስ ነገር እንደሌለ የሚናገሩ አሉ፡፡
በ2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መድረሱ የሚነገርለት ይህ ኮንቬንሽን፣ አንዳንድ የፌዴሬሽን ሙያተኞች ኢትዮጵያ ኮንቬንሽኑ የሚጠይቀውን መሥፈርት በማሟላቷ ሥልጠናና መሰል ጥቅማ ጥቅሞችን ማግኘት በሚያስችላት ደረጀ ላይ እንደምትገኝ ሲገልጹ የቆዩት የተሳሳተ መሆኑ ከሰሞኑ ይፋ ሆኗል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በካፍ የሥልጠና ኮንቬንሽን መሠረት በኢትዮጵያ ሲሰጥ የቆየው የሥልጠና ሒደት እንዲሁም ይህን ሥልጠና እንዲሰጡ በካፍ ዕውቅና የተሰጣቸውና ኢንስትራክተር ተብለው የተቀመጡ ሙያተኞች የአገልግሎት ጊዜያቸው ብቻ ሳይሆን፣ ኢንስትራክተር ለመሆን ዕውቅናውን ለማግኘት ግለሰቦቹ በእግር ኳሱ ውስጥ ከነበራቸው ተሳትፎ በመነሳት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምርጫና መንገድ ጥያቄ ማስነሳት ጀምሯል፡፡
በአቶ ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራው የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴና የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት፣ አዲሱ የካፍ የሥልጠና ኮንቬንሽን ይዘትና ከኮንቬንሽኑ ጋር ተያይዞ የአሠልጣኞች አሠልጣኝ ተብለው በሥራ ላይ የሚገኙ ሙያተኞች የአገልግሎት ጊዜ፣ የኢንስትራክተሮቹ ማንነትና የእግር ኳስ ተሞክሯቸው እንዲሁም በእነዚህ አካላት ሲሰጥ የቆየው የአሠልጣኝነት ሥልጠናና ተያያዥ የሙያ ማሻሻያ ኮርሶች በቀጣይ ስለሚኖራቸው ግልጋሎት ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ “ካፍ ይህን ኮንቬንሽን ለማዘጋጀት የተገደደው ሥልጠናና መሰል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች የጥራት ችግር ስላለባቸው ነው” ሲሉ፣ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው የኮንቬንሽኑ አስፈላጊነትና ጥራት የሚለው እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም ኢንስትራክተሮች ባላቸው ዕውቀትና ችሎታ እንዲሁም የማስተማር ክሂሎታቸው አንቱታን ያተረፉ በመሆኑ ብዙም ችግር እንደሌለው ገልጸው፣ መግለጫው በዋናነት ያስፈለገው ኮንቬንሽኑን መነሻ በማድረግ የሚታየውን ውዥንብር ለማጥራትና ከዚህ በተጓዳኝ የሚራመዱ ካሉ አደብ እንዲገዙ መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑን ያስረዱበት መንገድ ብዙዎች አስገርሟል፡፡
ምክንያቱም ኮንቬንሽኑ ከኢንስትራክተሮች ጀምሮ ለማንኛውም ሙያተኛ ዕውቅና የሚሰጠው፣ በእግር ኳስ ውስጥ ካለው አበርክቶ በመነሳት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህንኑ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ ከአቶ ሰውነት ቢሻው በመቀጠል ባቀረቡት ገለጻቸው አብራርተውታል፡፡
ኢንስትራክተሩ ኮንቬንሽኑ ከመነሻው ምን ዓይነት ይዘት እንዳለው በዝርዝር ባያስረዱም፣ ሆኖም ግን ከኢንስትራክተሮች እስከ አሠልጣኞች ባለው ደረጃ ሙያተኞች ምን ዓይነት ሥልጠናና ለሥልጠናው የሚያስፈልገውን ጊዜ፣ እንዲሁም ለሠልጣኞችም ሆነ ለኢንስትራክተሮች ኮንቬንሽኑ በመሠረታዊነት ለትክክለኛው ባለድርሻ ትክክለኛውን ሥልጠና ለትክክለኛው ሰው የሚል ይዘት ያለው ስለመሆኑ ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ይሁንና ከሥልጠናዎችና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ሲሠራበት የቆየው ከቀድሞ የካፍ መመርያም ሆነ ከኮንቬሽኑ አንፃር የነበረውን ተግዳሮት ግን ለመግለጽ አልፈለጉም፡፡
ከዚህ በመነሳት ኮንቬንሽኑ በኢትዮጵያ ኢንስትራክተር መሆን የሚገባው ማን ነው? ሙያተኞቹ ለዚህ ኃላፊነት ሲመረጡ ለእግር ኳሱ ያላቸው አበርክቶ ምንድነው? የአገልግሎት ጊዜ ባልታደሰበት ሁኔታ ኢንስትራክተር በሚል ሥልጠና መስጠት ይችላሉ ወይ? አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜስ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ኢንስትራክተሩ፣ “በካፍ መመርያ አንድ ኢንስትራከተር ማረጋገጫውን በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ማሻሻያ ሥልጠና ማዳበር ካልቻለ ሥራ ላይ ነው ብሎ መውሰድ ባይቻልም፣ ዕውቅናው ሊጠራበት ይችላል፡፡ ምልመላና ምርጫውን በሚመለከት በወቅቱ የነበሩ የፌዴሬሽን ኃላፊዎች ካልሆነ በዚህ መድረክ መልስ መስጠት ያዳግታል፤” ብለው ለማንኛውም ከእንግዲህ ያለውን በኮንቬንሽኑ በትክክል ስለተቀመጠ ችግር እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሥልጠና ወስደው ማረጋገጫ ሠርትፊኬት ያልመጣላቸው አሠልጣኞችን በሚመለከት ኢንስትራክተር አብርሃም፣ ኮንቬንሽኑ ቀደም ሲል ከነበረው ለየት ያለና አዲስ የሚባል ቢሆንም፣ ያለውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሳያደርግ ማሻሻያ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ተደርጎ የብቃት ማረጋገጫቸውን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በመመርያው መሠረት ሥልጠና ከ”ዲ” እስከ “ኤ” ደረጃውን ጠብቆ እንደሚሰጥ ባስረዱት ኢንስትራክተር አብርሃም አገላለጽ፣ የ“ዲ” እና የ”ሲ” ላይሰንስ ለመውሰድ ዕድሜው 18 ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ የአገሪቱን ብሔራዊ ቋንቋ መናገርና መጻፍ መቻል ይኖርበታል፡፡ ሠልጣኙ ወደ ሚቀጥለው ማለትም የ”ቢ” ላይሰንስ ለመውሰድ ሁለት ዓመት በሥራ ላይ ሆኖ መቆየት እንደሚጠበቅበትና የ”ሲ”ን የሥልጠና ሒደት ማለፍ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡
ማንኛውም ሙያተኛ የ”ቢ” እና የ”ኤ” ላይሰንስ ለመውሰድ በእግር ኳሱ ማለፍ ብቻ ሳይሆን፣ የፊፋን የሥራ ቋንቋ አንዱን መናገር እንደሚጠበቅበት ያስረዱት ኢንስትራክተር አብርሃም፣ ሙያተኛው ከዚህም በላይ እግር ኳሱን ከክለብ እስከ ብሔራዊና ከዚያም በላይ በአኅጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች የተጫወተ ተጫዋች ኮንቬንሽኑ “ፋስት ትራክ” ብሎ በልዩ ሁኔታ የ”ሲ”ን ደረጃ ሳይወስድ በቀጥታ ወደ “ቢ” ለመሸጋገር ሁለት ዓመት ሥራ ላይ መቆየት እንዳለበት ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም ግን በኮንቬንሽኑ ሥልጠናውን ለመውሰድ የተቀመጠውን ሰዓት ያሟላ ተጫዋች ከሆነ ሁለት ዓመት መጠበቅ አይጠበቅበትም፡፡ የሥራ ቋንቋውን በተመለከተም የ”ቢ”ንም ሆነ የ”ኤ” ለመውሰድ የአገሩን ብሔራዊ ቋንቋ መጻፍና ማንበብ ካልሆነ የፊፋን የሥራ ቋንቋ ማወቅ ግዴታ አይደለም ይላል፡፡
ኮንቬንሽኑ ከ”ዲ” ጀምሮ እስከ ፕሮፌሽናል ላይሰንስ ያለውን የሥልጠና ደረጃ ለማለፍ መወሰድ ይገባል ያለውን የንድፈ ሐሳብና የተግባር ልምምድ በጊዜና በሰዓት ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት የ”ዲ” ላይሰንስ በአጠቃላይ 60 ሰዓት ሲጠይቅ፣ ከዚህ ውስጥ 20 ሰዓት ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ ቀሪው የተግባር ልምምድ ይሆናል፡፡ የ”ሲ” በአጠቃላይ 120 ሰዓት ሲሆን 60ው ንድፈ ሐሳብ፣ 60ው የተግባር ብሎ ያስቀምጠዋል፡፡ የ”ቢ” ለመውሰድ ደግሞ 160 ሰዓት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60 ሰዓት የንድፈ ሐሳብ፣ ቀሪው ደግሞ የተግባር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የ”ኤ” ለመውሰድ 240 ሰዓት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 100 ሰዓት የንድፈ ሐሳብ ሲሆን ቀሪው የተግባር ነው፡፡ የመጨረሻውንና በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ደረጃ በሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካልሆነ በሌሎቹ ገና እንዳልተሰጠ፣ ይሁንና ላይሰንሱን ለመውሰድ ግን 360 ሰዓት የሚያስፈልግ ሲሆን 140 ሰዓት ለንድፈ ሐሳብ፣ ቀሪው ደግሞ ለተግባር ልምምድ መሆኑ ያስቀምጣል፡፡
ኮንቬንሽኑ ከዚህ በተጨማሪ ሥልጠናው በሚሰጥበት ወቅት የ”ዲ” እና የ”ሲ” ኮርስ ከሆነ ከ30 ሰዎች መብለጥ እንደሌለበት፣ ለ”ቢ” እና ለ”ኤ” 25 ሰው ሲሆን ለፕሮፌሽናል ላይሰንስ (ፕሮ) ለ20 ብቻ እንደሚፈቀድ ያስገድዳል፡፡
በመጨረሻም ኢንስትራክተሮችን በሚመለከት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አሏት ተብለው በስም ከተገለጹት መካከል፣ ኑሮዋቸውን በውጪ ካደረጉ ዓመታትን ያስቆጠሩ ይገኙበታል፡፡ ቀሪዎቹን በሚመለከት ብዙዎቹ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ይህ ነው የሚባል ስም ያላቸው አለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በዚያ ላይ በካፍ በቀድሞውም ሆነ በአሁኑ ኮንቬንሽን የአገልግሎት ጊዜው ሦስት ዓመት ነው ይላል፡፡ እስካሁን ባለው የሁሉም የአገልግሎት ጊዜ ከሦስት ዓመት በላይ መሆኑ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ባዘጋጀው መግለጫ አስረድቷል፡፡ ምክንያት ብሎ ያስቀመጠው ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ማደስ ባለመቻሉ ነው፡፡