Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉፌዴራሊዝም በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ

ፌዴራሊዝም በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ

ቀን:

በሙሉጌታ ወልደ ገብርኤል 

የጽሑፉ ዓላማ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) “እንደመር” ሲሉ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የድምር ውጤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን እንዴት መገንባት እንደሚቻል ምክረ ሐሳብ ለመለገስ ነው።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንደርደሪያ

በሃይማኖት (በጠባብነትና በጽንፈኝነት) መንፈስ ሳይሆን በእውነትና በቅንነት ከተነበበ፣ ዓይነ ልቦና የሚያበራ፣ ሸክምን የሚያቀል፣ የሚፈታ፣ ነፃ የሚያወጣ፣ ከአዕምሮ ድህነት የሚገላግል፣ የዕድገትና የለውጥ ጎዳና የሚጠቁም፣ ሁሉም በነፃ ሊያገኘውና ሊጠቀምበት የሚችል፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ተቀድቶ የማያልቅ የዕውቀት፣ የጥበብና የሕይወት ውቅያኖስ የሆነ መጽሐፍ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንብኝም። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን፣ ‹‹እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ከሰጣቸው ውድ ስጦታዎች ውስጥ ዋነኛው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፣ በዚህም መጽሐፍ ከእኛ ከሰው ልጆች ጋር መነጋገሩ መልካምነቱን ያሳያል፤›› ሲሉ እንደተናገሩት፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ሊኖረው ስለሚችል የላቀ አስተዋጽኦና ተፅዕኖ ተመስክሮለት ያደረ ሀቅ ነው፣ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው›› እንዲል መዝሙረኛው።

መጽሐፍ ቅዱስ የዚህች ምድር (የሰው ልጅ) ብሉፕሬን የያዘ መጽሐፍ ነው። ለተከሰተና ገና ሊመጣ ያለውን የሰው ሐሳብ በዚህ መጽሐፍ ከተከተበ ሐሳብ ውጭ አይደለም። ፍልስፍና ነው? ከእግዚአብሔር በላይ ፈላስፋ የለም! ፖለቲካ እንደሆነም የሰው ልጅ ለክብሩ የፈጠረ ፈጥሮም የመግዛትና የማስተዳደር ልዩ ተሰጥኦና ፀጋ የሰጠው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ማናቸውም ፖለቲካዊና ማኅበረሰባዊ ነክ የአስተዳደር ሥርዓትና መዋቅሮች ለትምህርታችን በመጽሐፉ ውስጥ ተቀምጠዋል።

ሦስቱ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ የሕግ ፈላስፎችና የሕግ አዋቂዎች የፈጠሩት ነገር ሳይሆን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል የተቀዳ ዕውቀት ነው ‹‹እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፣ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው›› እንዲል (ኢሳ 33፣ 22)። ጥጉ የሰው ልጅ የቻለውን ያህል ያስብና ይሠራ ዘንድ አዕምሮ የሰጠው የዚህ መጽሐፍ ባለቤት እግዚአብሔር ነው።

የሕገ መንግሥት ኮንፈረንስ (Constitutional Convention) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ጉባዔ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 14 እስከ መስከረም 17 ቀን 1787 በፊላደልፊያ ከተማ ፔንስልቫን ጠቅላይ ግዛት የተደረገ ጉባዔ ሲሆን፣ ዋና ዓላማው አሜሪካ የምትመራበት የመንግሥት ሥርዓትና መዋቅር ለመወሰን የተዘጋጀ መድረክና ሕገ መንግሥቱ የተጻፈበት ወቅትም ነበር። ይህ የሕገ መንግሥት ኮንፈረንስ በመባል የሚታወቀው ጉባዔ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የተውጣጡ ሃምሳ አምስት ተወካዮች የተገኙበት ሲሆን፣ ጉባዔው ለመቶ ቀናት ያህል እንደ ዘለቀና የሞቀ ክርክር የተካሄደበት ታሪካዊ ጉባዔ መሆኑንም ይነገርለታል።

በጉባዔው ከተሳተፉ ሃምሳ አምስት አባላት ሃምሳዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ሲሆኑ፣ ብዙኃኑ በዘመኑ ከነበሩ አንጋፋ የሥነ መለኮት ተቋማት የወጡ የሥነ መለኮት ምሁራን እንደ ነበሩም ይነገርላቸዋል። ይህ ታሪክ ያነሳሁበት ምክንያት አሜሪካውያን በወሳኝ ነገራቸው ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት እንዴት እንደተጠቀሙበት ለማመላከት እንጂ ሰዎቹ “ቅዱሳን” ነበሩ አንድም አሜሪካ “የክርስትያን ደሴት ናት” እያልኩ እንዳይደለ ለአንባቢ ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁኝ።

የፌዴራል ሥርዓትና አሃዳዊ ሥርዓት

አሃዳዊ ሥርዓት በብሉይ ኪዳን

አሃዳዊ ሥርዓት ወይም አሃዳዊ መንግሥት፣ የአንድ አገር የፖለቲካ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ በመያዝና በመቆጣጠር ራሱ ለሚያደራጃቸው ለበታች ከባቢያዊ አስተዳደራዊ ግዛቶች ውሳኔዎችን የሚወስን ቀዳሚና ተከታይ የሌለው የበላይ የሆነ መንግሥት ወይም ሥርዓት ነው። የምንሊክ፣ የጃንሆንና የደርግ መንግሥት አሃዳዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ከመመልከታችን በፊት ግን አሃዳዊ ሥርዓት በብሉይ ኪዳን የነበረውን ገጽታ እንመለከት ዘንድ እወዳለሁ።

የሙሴም አማት አለው፣ አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፣ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፣ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፣ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፣ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፣ ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፣ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው። አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍን መረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፣ ከእነርሱም የሺሕ አለቆችን፣ የመቶ አለቆችን፣ የአምሳ አለቆችን፣ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው። በሕዝቡ ላይ ሁል ጊዜ ይፍረዱ፣ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፣ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፣ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፣ ለአንተም ይቀልልሃል። ይህንም ብታደርግ፣ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝ፣ መቆም ይቻልሃል፣ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ሥፍራው ይደርሳል። ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፣ ያለውንም ሁሉ አደረገ።

ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፣ በሕዝቡም ላይ የሺሕ አለቆች፣ የመቶም አለቆች፣ የአምሳም አለቆች፣ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው። በሕዝቡም ላይ ሁል ጊዜ ፈረዱ፣ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፣ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ። ሙሴም አማቱን ሰደደው፣ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ (ዘፀአት 18፣ 17 27) እንዲል።

እዚህ ላይ ግልጽ ይሆንልን ዘንድ፣ እስራኤል ማነው? ለሚለው ጥያቄ መጠነኛ ማብራሪያ ለማስቀመጥ እወዳለሁኝ። እስራኤል ተብሎ የሚታወቀው የአብርሃም የልጅ ልጅ ያዕቆብ አሥራ ሁለት ልጆች ሲሆኑ እነርሱም፣ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዮሴፍና ቢንያም ተብለው ይታወቃሉ። እንግዲህ የእነዚህ ትውልዶች ናቸው የእስራኤል ጎሳዎች ተብለው የሚታወቁት።

ቀደም ሲል ባነበብነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በግልጽ እንደምንመለከተው፣ ቀደም ሲል ‹‹አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፣ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም›› እንዲል ሙሴ እስራኤልን የመምራትና የማስተዳደር ሥራ ብቻውን ይሠራ እንደነበር በግልጽ እንመለከታለን። በኋላም ከአማቹ በተቀበለው ምክር መሠረት፣ ‹‹ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፣ በሕዝቡም ላይ የሺሕ አለቆች፣ የመቶም አለቆች፣ የአምሳም አለቆች፣ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው›› እንዲል ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎች፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ የታመኑ፣ የግፍን መረብ የሚጠሉ ናቸው ብሎ ያመነባቸው በቀጥታ ራሱ መርጦ በሾማቸው ሰዎችና እስከ ታች ድረስ በዘረጋው መዋቅር ሲመራቸውና ሲያስተዳድራቸው ደግሞ እናያለን። ይህ ኩልል ቅልብጭ ያለ የሙሴ አስተዳደር በአማርኛ ቋንቋ አሃዳዊ ሥርዓት ይባላል።

እግዚአብሔርን በመፍራት የሚታወቀው ሙሴ ይህን ሲያደርግ ግን ሲጠራቸው አቤት ሲልካቸው ወዴት የሚሉ፣ በሆዳቸው የሚደለሉ፣ ተላላኪዎች፣ አጋጣሚውን ሁሉ እየተጠቀሙ ሕዝባቸውን የሚዘርፉና የሚመዘብሩ፣ ርህራሔ የሌላቸው፣ ሕዝብን እያናከሱ ሥልጣናቸውን የሚያደለድሉ፣ ሙሰኞችና ወንጀሎች፣ ሥነ ምግባር የሌላቸው፣ በቅሌት የተዘፈቁ፣ የገዛ ወገናቸውን የሚበድሉ፣ ፍትሕንና ፍርድን የሚያጓድሉ፣ በራስ መተማመን የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው፣ ቃልቻና ጠንቋይ ቤት ተጥደው የሚውሉ፣ ራዕይ አልባ ካድሬዎች (ምስለኔዎች) ሾመ አይልም። የሠፈሩን ልጆች፣ አብሮ አደጎቹንና ጓዶኞቹን ሰበሰበም አይልም። በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ የሌላቸውን ዕውቀት አለን የሚሉ አፈ ጮሌዎችም አልሰበሰበም።

ሙሴ እስራኤል ራሱ በቀጥታ በመረጣቸውና በሾማቸው እንዲሁም በዘረጋው መዋቅር እንድትመራ ቢያደርግም፣ የሠራው ሥራ ሁሉ ቅንነት የተሞላበት፣ የራሱን ጥቅም ለመጠበቅና ሥልጣኑን ለመደላደል ሳይሆን ከምንም በላይ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የባለሥልጣኖቹ የሹመት መመዘኛ በተመለከተም ግልጽ እንደነበር አይተናል። አሃዳዊነት ወይም አሃዳዊ ሥርዓት ጠቅለል ባለ መልኩ የተረጎምነው እንደሆነ፣ የተማከለ ሥልጣን አንድም ከላይ ወደ ታች የሚፈስ፣ ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ የሥልጣን ተዋረድ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። እዚህ ላይ የክልል ሥልጣን የሚባል ነገር የለም። በሌላ አገላለጽ ክልል በራሱ ምንም ዓይነት ሥልጣን የለውም፣ ክልል የሚባል ነገርም አይኖርም። የሚፈጠረውና የሚኖረው ከባቢያዊ አስተዳደር ነው የሚሆነው።

በዚህ ደረጃ የሚቀመጠው ባለሥልጣን ደግሞ ከማዕከላዊ መንግሥት የሚመጣውን ነገር ሁሉ ተቀብሎ ከማስፈጸም ውጭ ምንም ዓይነት ሥልጣን አይኖረውም፣ የለውምም። የክልል ወይም የአከባቢው አስተዳደር ባለሥልጣናት የተለያዩ ፖሊሲዎች በማውጣት ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ የማዕከላዊ መንግሥት ፈቃድ ያገኙ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህ ዓይነቱ አሠራር፣ “እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ” እንዲል እስራኤል፣ በቆዳ ስፋትና በሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ጊዜ ለሙሴ ትልቅ ችግር እንደፈጠረበት፣ ይህን ማድረግም እንዳልቻለና ቀድሞ የነበረውን ሥርዓት ለመለወጥ እንደተገደደ ቀጥሎ በሚቀርበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንመለከታለን።

የፌዴራል ሥርዓት በብሉይ ኪዳን

በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ። እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም አምላካችሁ እግዚአብሔር አብዝቶአችኋል፣ እነሆም እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ። የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ቁጥር ላይ ዕልፍ አዕላፋት ይጨምር፣ እንደ ተናገራችሁም ይባርካችሁ። እኔ ብቻዬን ድካምችሁን ሸክማችሁን ምክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች አስተዋዮዎችም አዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፣ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ። እናንተም እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን አለቆች መረጥሁ፣ በእናንተም ላይ አለቆች የሻለቆችም የመቶ አለቆችም የአምሳ አለቆችም የአሥር አለቆችም ገዦችም በየነገዶቻቸው አደረግኋቸው። በዚያን ጊዜም የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፣ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መፃተኛ መካከል በፅድቅ ፍረዱ። በፍርድም አድልዎ አታድርጉ ታላቁን እንደምትሰሙ፣ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ ከነገርም አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፣ እኔም እሰማዋለሁ ብዬ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው (ዘዳግም፣ 1 9-17) እንዲል።

አሁን የእስራኤል ነገዶች (አሥራ ሁለት ግዛቶች) ግልጽ የሆነ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ‹‹ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች አስተዋዮዎችም አዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች ምረጡ›› እንዲል ነገዶቹ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ መሪዎቻቸውን የመምረጥ ሥልጣን፣ ሁሉም የየራሱ ውስጣዊ መዋቅር ራሱን ችሎ የማዋቀርና የማደራጀት ሙሉ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። መሴ፣ ይህን ሁሉ መልካምና የሚመሠገን ሥራ ካደረገ በኋላ አንዴ የፖለቲካ፣ ሌላ ጊዜ የኢኮኖሚ፣ ሲያሻው ደግሞ የልማት አማካሪዎች እያለ በሰበብ አስባቡ ሰዎች እየላከ በነገዶቹ የውስጥ ጉዳዮቻቸው ላይ ጣልቃ ሲገባ፣ እያቧደነ እርስ በርስ ሲያባላቸው፣ ሲያምሳቸውና ሲያተረማምሳቸው፣ እንዳሻው አድርጎ ይገዛቸውና ይዘውራቸው ዘንድም በመካከላቸው የማይበርድ ፀብና ሁከት ሲዘራ፣ በቀጥታ ለእሱ የሚታዘዙ ምልምሎች አሠማርቶም ያልተገባ ቀረጥ ሲሰበስብ አንድም ቦታ አናገኘውም። ሊቀ ነቢያት መሴ የዘረጋው የፌዴራል ሥርዓት ግልጽነት የተላበሰ ከመሆኑም በላይ፣ ፍርድንና ፍትሕን ስለማድረግ ግልጽና የማያሻማ አቋም የነበረው ሥርዓት ነበር። በቆዳ ስፋትና በቁጥር ከይሁዳና ከምናሴ ነገድ ሲነፃፀር አነስተኛ የሆነ ጎሳ፣ ለምሳሌ የቢንያምና የዛብሎን ጎሳዎች እኩል በፅድቅ እንዲዳኙ፣ ማናቸውም ጎሳዎች የትኛውም ቦታ ቢሄዱ በሕግ ፊት እኩል እንዲታዩ የደነገገና ያደረገ ፍትሐዊ ሥርዓት ነበር።

ፌዴራሊዝም በዋናነት የሥልጣን ክፍፍል ማዕከል ያደረገ ሲሆን፣ የፌዴራል ሥርዓት ማለት በክልልና በአገር ደረጃ ተመጣጣኝ የሥልጣን ክፍፍል የመኖርና የመፍጠር፣ እንዲሁም ራስን በራስ (Self-rule & Sharedrule) የማስተዳደር ሥርዓት ነው። በክልል ደረጃ የሚሰጠው ሥልጣን ሆነ በአገር ደረጃ (የፌዴራል መንግሥት) የሚይዘውና የሚኖረው ሥልጣን የጎላ መበላለጥ አይኖርም። በሌላ አገላለጽ፣ የፌዴራል ሥርዓት የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት እርስ በርስ የሚጠባበቁበት ሥርዓት እንጂ አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት አይደለም። ሁለቱም በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የሚቀመጠው (በተቀመጠው) የሥልጣን ክፍፍል መሠረት የድርሻቸውን ይወጣሉ። የክልል መንግሥት በክልል ደረጃ ያለውን ይሠራል፣ የፌዴራል መንግሥት በተመሳሳይ በፈዴራል ደረጃ የተሰጠውን ሥልጣን ያከናውናል።

ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥት ገንዘብ ማተም፣ የውጭ ግንኙነት፣ የውጭ ሆነ በክልሎች መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ መቆጣጠር፣ የመከላከያ ሠራዊት ማደራጀት፣ ጦርነት ማወጅ ጨምሮ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር በተመለከተ በሚዘረዝረው አንቀጽ 51 የተቀመጡን ተግባራት ያከናውናል። ክልላዊ መንግሥት በተመሳሳይ የክልሉን አስተዳደራዊ መዋቅር ይዘረጋል፣ በክልል ውስጥ የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል፣ ወዘተ.፡፡ በአጠቃላይ በሕገ መንግሥቱ የክልል ሥልጣንና ተግባር በተመለከተ በሚዘረዝር አንቀጽ 52 የተቀመጡን ተግባራት ያከናውናል። በተጨማሪም፣ ለሁለቱም አካላት በጋራ የተሰጡ (Concurrent Power) እና የወል (Joint Powers) ሥልጣኖችም ይኖራሉ። 

የፌዴራል ሥርዓት ምሰሶዎች ናቸው ተብለው የሚታወቁ የሥርዓቱ መገለጫ በጥቂቱ

  1. በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት የሚደረገውና የሚኖረው የሥልጣን ክፍፍል ዋነኛው ነው።
  1. ለክልሎች የሚሰጠውን ሥልጣን የፀናና አይነኬ መሆን፣ ይህ ማለት የክልሎች የሥልጣን ምንጭ ሕገመንግሥቱ መሆኑና የክልሎች ሥልጣን ለመንጠቅ ቢፈለግ እንኳን መጀመርያ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት። ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ደግሞ የክልሎችን ፈቃድ ይጠይቃል። በመሆኑም ክልሎቹ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን ለመለማመድ ወይም ለመጠቀም የፌዴራል መንግሥት ይሁንታና ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልጋቸውም።
  1. በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሚደረገው የሥልጣን ክፍፍልና ምደባ ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን፣
  1. የፌዴራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት አስፈላጊነት ማረጋገጡ። በእርግጥ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ለፌዴረሽን ምክር ቤት ነው የሚሰጠው። በፌዴራል መንግሥታትና በክልል መንግሥት እንዲሁም በክልሎች መካከል ሊፈጠር የሚችለው መሳሳብና ግጭቶችን ለመፍታት ያስችላቸው ዘንድ ጉዳዩን ሊመለከትና ብያኔ ሊሰጥ የሚችል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆን ሲገባው፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የመስጠቱ አንድምታ አሻሚ ነው።
  1. በሁለት ደረጃ የሚከፈለውን የተወካዮች ምክር ቤት መኖርና በተለይ እኩል ውክልና ያለው የፌዴሬሽን የምክር ቤት ጠንካራ መሆን፣ የፌዴራል ሥርዓት መገለጫዎች ተደርገው ይወሰዳሉ።

ጠቅለል ባለ መንገድ ስንመለከተው

በፌዴራል ሥርዓት የፌዴራል መንግሥትና የተለያዩ የክልል መንግሥታት ሲኖሩ፣ በአሃዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ደግሞ አንድ አገር አንድ መንግሥት ብቻ ይኖራል። በፌዴራል ሥርዓት ክልሎች ክልላዊ ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎች ማውጣት ይችላሉ፡፡ በአሃዳዊ ሥርዓተ መንግሥት የክልል ሕግ የሚባል ነገር አይኖርም። የሚኖረው ሕግ አንድ ነው፡፡ እሱም ከማዕከላዊ መንግሥት የሚመነጭ ወይም የሚቀዳ ሕግ ነው። በፌዴራል ሥርዓት ክልሎች የራሳቸው የሆነ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ አካላት ይኖሯቸዋል፡፡ በአሃዳዊ ሥርዓት ይህ ሁሉ ተውጦ አንድ ይሆናል፣ መቀመጫውም አዲስ አበባ ነው። በፌዴራል ሥርዓት የሥልጣን ክፍፍል ተቋማዊ ሲሆን፣ በአሃዳዊ ሥርዓት የሥልጣን ተዋረዱ ነው የሚኖረው፣ ይኸውም በሕግ የሚደነገግ ይሆናል።

የትኛው ይሻላል?

ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች መካከል ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ሳዑዲና ቺሊን ጨምሮ 165 አገሮች አሃዳዊ ሥርዓት የሚከተሉ ናቸው። የሚሻለውን የሚያውቅ ሕዝብ ነው። እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ እየሄድን ያለንበት ምክንያትም፣ “እኔ አውቅልሃለሁ” የልክፍት ፖለቲካ ስለሠለጠነብን ነው። ቻይናም አሜሪካም ለራሳቸው የሚመቻቸውን ነው የመረጡት። እኛም ታሪካችንና ባህላችን ማዕከል ያደረገ ፖለቲካዊ አስተዳደር እንጂ፣ ቻይናን ወይም አሜሪካን መምሰል አይደለም የሚጠበቅብን። ይህ ማለት ግን ከሌሎች ትምህርትና ተመክሮ መቅሰም የለብንም ማለት አይደለም። ዋናው የሚበጀንን ማወቅ ነው።

የጽሑፉ አዘጋጅ ይህን ጽሑፍ ሲያዘጋጅ አሃዳዊ ይውደም! የፌዴራል ሥርዓት ይቅደም! ለማለት አይደለም። አሃዳዊም ሆነ የፌዴራል ሥርዓት ሁለቱም በኢትዮጵያ ምድር የተፈተኑ ሥርዓተ መንግሥት ናቸው። ሁለቱም ከቅንነት የመነጩ ባለመሆናቸውም ዋጋ አስከፍለውናል። አሃዳዊ ሥርዓት ሆኖ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩል ዓይን የሚያይና የሚዳኝ ፍትሐዊ ሥርዓትና መንግሥት ቢሆን ኖሮ የበላይና የበታች፣ አጥማቂና ተጠማቂ፣ መምህርና ደቀ መዝሙር ዓይነት ግንኙነት ባይፈጥር ኖሮ አሃዳዊነት ይውደም! ባላልን ነበር።

የፌዴራል ሥርዓትም በተመሳሳይ ሥርዓቱ የተመረጠበት ምክንያት ለክፋት ሳይሆን ለልማት፣ በሴራ ሳይሆን በቅንነት፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያላንዳች ጣልቃ ገብነት በነፃነት ራሳቸውን ያስተዳድሩ ዘንድ ቢደረግ ኖሮ፣ ፌዴራሊዝምም ቢሆን ተቃውሞ ባልገጠመው ነበር።  

ዋናው ቁምነገሩ አንድ ትግራይ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ወዘተ. ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብረውለት አገሬ ነው ብሎ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ድረስ በመሄድ ሥራ የመሥራትና ሀብት ማፍራት መብት ካለው፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋቸውን የማሳደግና ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ ሥልጣናቸውን ከተጠበቀላቸው ኢትዮጵያ ለምን በአሃዳዊ ሥርዓት ለማች፣ ተለወጠች፣ ሰላሟን አገኘች ብሎ ደም የሚያስቀምጠው ሌላ አካል እንጂ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አይሆኑም።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕግ ፊት እኩል የሚዳኙ ከሆነ፣ እኩል የፖለቲካ ውክልና ኢኮኖሚያዊ ተሳታፊነታቸው ከተረጋገጠላቸው፣ ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው ሁሉም የየራሱ ማንነት እንደጠበቀ በእኩልነት የሚኖርባትና ብዝኃነትን የምታስተናግድ ኢትዮጵያ ስትፈጠር የፌዴራል ሥርዓት ወይ ሞት! የሚሉበት ምክንያት የላቸውም። ፌዴራል ሥርዓትን አሃዳዊ፣ አሃዳዊን የፌዴራል ሥርዓት ብሎ የመጥራት ያህል ነው የሚሆነው። ዳሩ ግን የቀመስነው አሃዳዊነት ይኼ ሲነገር “ዩቶፕያ” የሚመስለውን አሃዳዊነት አይደለም። የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚሻለን የፌዴራል ሥርዓት ነው እያሉ ያሉበት ምክንያት በባንዲራ ስም ከምንጨፈለቅና በቁማችን ከምንሞት፣ የሆነው እስኪሆን ድረስ ምሽጋችንን መያዝ ይሻላል! ብለው ስለሚያምኑ ነው።

ማኦን (Mao) ተከተው የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ሊቀመንበርና የቻይና ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የነበሩ ዴንግ ሺፒንግ (Deng Xiaoping) መንግሥታዊ መዋቅር በተመለከተ፣ ‹‹ዋናው ድመትዋ አይጥ መያዝዋን ነው እንጂ፣ የድመትዋ ነጭና ጥቁር መሆን ትርጉም የለውም›› በሚል ፍልስፍናቸው የሚታወቁ ሰው ናቸው።

የዴንግ ሺፒንግን በምሳሌ ላስረዳ

ጥቁር ድመት ለብዙኃኑ አሜሪካ ከጥንቆላና ከመጥፎ ዕድል ጋር የተገናኘ እምነት ሲኖራቸው፣ ለጃፓናውያን ጨምሮ ለስኮትሽና ለዌልስ ሰዎች ደግሞ ጥቁር ድመት ከብልፅግናና መልካም ጤንነት የተያያዘ ነው። ጥቁር ድመትን አንዱ ማኅበረሰብ በፈገግታ ሲቀበል ሌላኛው ደግሞ በአካባቢው ድርሽ እንዲልበት አይፈልግም። ቤታቸው በአይጥ (አገረ ቻይና በድህነት) ለተወረረባቸው ሰው ግን የድመትዋ ነጭና ጥቁር መሆን ግድም አልሰጣቸውም።

የዴንግ ሺፒንግ ጭንቀት ኮሙዩኒስት ወይም ሶሻሊስት ተብሎ መጠራቱና ትርጓሜአቸውን አለመዛነፉ አይደለም የጨነቀው። ቁምነገሩ ያለው የቻይና ሕዝብና መንግሥት (አገር) የሚፈልጉትን ውጤት ያስገኛል ወይ? ነው ጥያቄው። ቅንነት ከሌለን አሃዳዊም ሆነ የፌዴራል ሥርዓት ለኢትዮጵያ መፍትሔ አይሆንም፣ አያመጣምም። ቅንነት ያለበት፣ በቅንነት የሚሠራ ሥራ ደግሞ አሃዳዊ ተባለ የፌዴራል ሥርዓት የሚፈለገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ልዩ ሕዝብ ሆኖ ሳለ እንደ አንድ ሕዝብ፣ በእኩልነት፣ በፍትሐዊነትና በአብሮነት የሚኖርባት የበለፀገች ኢትዮጵያ ማየት ነው።

አንድ ሌላ ምሳሌ ልጨምር፡፡ አንድ ሙሉ ክፍለ ዘመን (መቶ ዓመት) ኖረው እ.ኤ.አ. በ2018 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተብለው የሚታወቁ የክርስትና እምነት ሰባኪ የነበሩ ወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም፣ የሴቶች ጉዳይ በአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት ዓብይ ርዕስ በነበረበት ዘመን በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ የሚከተለውን ነበር ያሉት። ‹‹መዋኘት ሳልችል ባህር ውስጥ ገብቼ ለነፍሴ ስታገል ማዶ ላይ የቆመው ወንድ ልጅ እንደ እኔ መዋኘት ስለማይችል፣ እኔ እየሞትኩ ቁሞ ከማየት ውጪ ሕይወቴን ሊያተርፍልኝ ካልቻለ፣ በአንፃሩ መዋኝት የምትችል ሴት ልጅ ገብታ ከሞት ካተረፈችኝ ሴትዬዋን የማልመርጥበትና በሕይወት ስላተረፈችኝ ደግሞ የማላመሠግንበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለኝም፤›› በማለት ነበር እምነታቸው ያጋሩት።

ይህ የቢሊ ግርሃም አባባል አሃዳዊ ወይም ሞት! የፌዴራል ሥርዓት ወይም ሞት! እያለ ጎራ ለይቶ እየተቧቀሰንና ጊዜውን በከንቱ እያጠፋ ላለ ልሒቅ ዓይን ካልከፈተ፣ ኢትዮጵያ አሁን በምትገኝበትና ባለችበት የብጥብጥና የመከፋፈል መንገድ ትቀጥላለች። በመጨረሻ አሁን ባለው ነባራዊ የአገራችን ሁኔታ የፌዴራል ሥርዓት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ አምናለሁኝ (በሚቀጥለው ርዕስ “የፌዴራል ሥርዓት እንዴት እንገንባው?” በሰፊው እንመለከተዋለን)። እንደ እኔ እምነት የእስራኤል በሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ጊዜ ሙሴ ዘመኑን እየዋጀ አሠራሩን እንዳስተካከለ ሁሉ፣ የሕዝብ ቁጥራችን በፍጥነት እየጨመረና እየበዛን ያለን ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ መንገድ ብንከተል ተመራጭ ነው።

በቅርቡ የተሻሻለውና በከፍተኛ ሕዝበ ውሳኔ ተቀባይነት ካገኘው የሩሲያ ፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት ጠንካራ ጎኖች መካከል አንዱ፣ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን በከፊል ለምክር ቤቱ መስጠቱ በአዎንታዊነቱ የሚጠቀስ ነው። ከዚህ ቀደም በፕሬዚዳንቱ የተመረጡ ሹመታቸውን ለማፅደቅ ብቻ ምክር ቤቱ (ዱማ) ይላክ የነበረውን አሠራር ቀርቶ፣ የካቢኔውን አባላት የሚመርጥና የሚሾም ምክር ቤቱ እንዲሆን ተደርጓል። ወደ ፕሬዚዳንቱ የሚላከው ለማፅደቅ ብቻ ነው። ይህ አሠራር ከዚህ ቀደም የነበረውን የፕሬዚዳንቱ ፈርጣማ ሥልጣን የሚቀንስና በሕግ አውጪውና በአስፈጻሚው መካከል ሥልጣን የማመጣጠን ተግባር ዕውን ያደረገ ዕርምጃ ሆኗል። 

አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚለው በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ የተቀመጠው ፍልስፍናም ቢሆን እኮ ውስጠ ወይራው አሃዳዊ ነው። አሁን የጨነቀን መንገዱ ነው። መንገዱም የፌዴራል ሥርዓት በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ሥልጣን ሲከፋፈል (የፌዴራል ሥርዓት) ወያነ ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው ሆነ ብሎ ያደርገው ነው የምንል ከሆነ፣ ሥልጣን ሁሉ በአንድ ሰው እጅ ላይ ሲወድቅ፣ እንደ ዕርዳታ ዱቄትና እንደ ዘይት እየተሰፈረ ሲሰጠን ደግሞ (አሃዳዊ ሥርዓት) ፍትሐዊነት ነው የሚባል ከሆነ፣ ሁሉንም ስለማያግባባ ችግር ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ እንደ አገር መቼም አያግባባንም፣ ሊያግባባንም አይችልም።

የፌዴራል ሥርዓት የብሔር ፖለቲካ ነው በማለት ክሳቸውን የሚያቀርቡና የሚያሰሙ እንዳሉም ይታወቃል። ይህ ግን መሠረት የሌለው ተራ ክስና ፕሮፓጋንዳ ነው። የፌዴራል ሥርዓት የብሔር ፖለቲካ አይደለም። የብሔር ፖለቲካም ቢሆን በራሱ ምንም ዓይነት አደጋ የለውም። የብሔር ፖለቲካ አደጋ የሚሆነው ፖለቲካውን በሚመሩ ልሂቃን መካከል እርስ በርስ በሚደረገው የፖለቲካ ሽኩቻ፣ የብሔር ፖለቲካ እንደ ጆከር መጫወቻ ሲሆንና እንደ ጋሻና ጦር መጠቀሚያ ሆኖ ሲያገለግል ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከፌዴራል ሥርዓት ጋር ምንም የሚያገናኝ ነገር የለውም። 

መፍትሔ

 1. ሙሴ፣ ‹‹የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፣ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መፃተኛ መካከል በፅድቅ ፍረዱ። በፍርድም አድልዎ አታድርጉ ታላቁን እንደምትሰሙ፣ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፣ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ›› እንዲል፣ ከሁሉም በፊት መንግሥትና ባለሥልጣናቱ ቅንነትንና ግልጽነትን ሊላበሱና ገንዘባቸው ሊያደርጉ ይገባል (Honesty and Integrity)። ቅንነትና ግልጽነት በሌለበት ልብ የሚሠራ ሥራ በሙሉ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ነው የሚሆነውና። 
 1. ሙሴ፣ ‹‹ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች አስተዋዮዎችም አዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች ምረጡ›› እንዲል መንግሥት በሠፈር ጓደኛ፣ በአብሮ አደግ፣ በዝምድና፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በካድሬ፣ ወዘተ. መመሳሰል በሚሰበሰበው ቡድን አገር እንደማትቀና ሊያሰምርበት ይገባል። ማይክ የጨበጠ ሁሉ በሕዝብ ላይ የሚሾምበት አሠራር ፈጽሞ ሊወገድ ይገባል። ሙሴ ጥበበኞች እንዲል፣ የተመሰከረላቸውና አስተዋዮች እንዲል ሕዝብንና አገርን የማገልገል ሸክምና ራዕይ ያላቸው ማለቱን፣ አዋቂዎች እንዲል ገብቶ የወጣ፣ ያልበሰለና ለብ ያለ ሳይሆን አጣፍፈው የተማሩ፣ የሚሠሩትን/ሥራቸውን አጣፍፈው የሚያውቁ ሰዎች ማለቱን እንደ ሆነ ልብ ልንል ይገባል። በመሆኑም መንግሥት ለሹመት ስለሚያጫቸው ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል። ራዕቱና ሸክሙ ያላቸው አስተዋዮች፣ ጥበበኞችና አዋቂዎችን ብቻ ሊመርጥ ይገባዋል (Meritocracy)።
 1. የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ሊቀመንበርና የቻይና ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዴንሺፒንግና የክርስትና እምነት ሰባኪው ወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም አንስተን በተመለከትናቸው አባባሎች ተጠቃሚዎች ልንሆን ይገባል (Pragmatism)። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን “አሃዳዊ ወይም ሞት!” “የፌዴራል ሥርዓት ወይም ሞት!” ማለታቸውን ትተው ሕዝብንና አገርን በዘላቂነት የሚጠቅም ምክር ያመጡ ዘንድም እመክራለሁኝ።

የፌዴራል ሥርዓት እንዴት እንገንባ?

ቅዱስ ጳውሎስ በልዩ ልዩ ምክንያት ከፍተኛ መከፋፈል ለገጠማቸው የቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈላቸው መልዕክት ላይ እንዲህ ይላል፣ ‹‹አካልም አንድ እንደ ሆነ፣ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደሆኑ፣ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው። አይሁድ ብንሆን፣ የግሪክ ሰዎችም ብንሆን፣ ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። እግር እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፣ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፣ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጓል።

ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው፣ አካል ግን አንድ ነው። ዓይን እጅን አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፣ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፣ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፣ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፣ ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፣ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሳቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሳቀያሉ፣ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል (አንደኛ ቆሮ 12፣ 14-27) እንዲል። ዝርዝር ሀተታ ውስጥ መግባት ሳያስፈልገን ጳውሎስ ያነሳቸው ሦስት መሠረታዊ አስታራቂ ሐሳቦችን እንመለከት ዘንድ እወዳለሁኝ። ይኸውም፣

 1. ‹‹አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና›› እንዲል ብዙኃነትን መግለጡ፣  
 1. ‹‹ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው›› እንዲል እኩልነትን ማስተማሩ፣ 
 1. ‹‹ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው፣ ዓይን እጅን አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፣ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም›› እንዲል አብሮነትን በሚገባ ሲያብራራ እንመለከታለን።

በእኩልነት መሠረት ላይ በምትመሠረተው አገር ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል ላይ የሚያጠነጥነው የፌዴራል ሥርዓት ምንጭ የሆነው ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መሠረት በማድረግ፣ አንዲት ሉዓላዊት አገር በተግባር ካቆሙና ከቆረቆሩ አገሮች መካከል አሜሪካ በፈር ቀዳጅነቷ ትታወቃለች። ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች በፌዴራል ሥርዓት የሚተዳደሩ የዓለማችን አገሮች ልዩ ልዩ መጠነኛ መሻሻሎችና ለውጦች ቢጨማመርበትም፣ በዋናነት መሠረትና መነሻ የሆናቸው ግን ይህ የአሜሪካ የፌዴራል ሥርዓት ነው።

አፈጻጸሙ ላይ ከፍተኛ ችግር ቢታይበትም፣ በሒደት ቅንነት ለጎደለበት አስተሳሰብ መሣሪያ ሆኖ ቢያገለግልም፣ ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገችበት ዋና ምክንያት ግን ቀድመው የነበሩ አሃዳዊ ሥርዓቶች በሙሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ባለመቻላቸው፣ ይልቁንም እንደ ፋብሪካ ዕቃ የሕዝቦችን ማንነት የመጨፍለቅና የመግፈፍ ዝንባሌ በማሳየታቸው፣ ከዚህ የተነሳም በአገሪቱ ላይ የተፈጠሩ ዕድሜ ጠገብ ግጭቶች ለመቅረፍና መፍትሔ ለማበጃጀት ታሳቢ ያደረገ እንደ ነበር ነው። ይህ ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ የተደረገው የፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች የፌዴራል ሥርዓት ከሚከተሉ አገሮች የሚለየው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስከ መገንጠል ድረስ መብት የሚያጎናፅፍ አንቀጽ 39 መጨመሩ ነው (ይህን በተመከለተ በሚቀጥለው ምዕራፍ በሰፊው አብራራዋለሁኝ)።

መጽሐፍ፣ ‹‹ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፣ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው፤›› እንዲል፣ የፌዴራል ሥርዓት በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘንድ ተመራጭ የሆነበትና ያስፈለገበት ዋና ምክንያት አገር ከመፈራረስና ከመበታተን ለመታደግ፣ ግጭቶችን ለማስወገድና መፍትሔ ለመስጠት ታሳቢ ያደረገ ስለሆነ ነው። ታዲያ የማንም ችግር ፈጣሪና የሥልጣን ጥመኛ እየተነሳው ውኃ ቀጠነ እያለ በሚፈጥረውና በሚቀሰቅሰው ችግር ሕገ መንግሥቱን እያስተካከለ ለሚቀርበው የመብት ጥያቄ ማለትም የመገንጠል ጥያቄ ማቅረብ በሚያስችል ሁኔታ መቀመጡ፣ የአንቀጽ 39 በሕገ መንግሥቱ የመካተቱ ጉዳይ ምክንያታዊነት አከራካሪ ነው።

እውነት ነው አንቀጽ 39 ኖረም አልኖረም በቂ ምክንያት ኖሮት “ፍቺን እፈልጋለሁ” ያለ ሕዝብ ማስቆም አይቻልም። ባለፉት ጥቂት ዓመታ በርካታ አገሮች ወደ ህልውና መጥቷል፣ አንዳቸውም ግን አንቀጽ 39 ሕገ መንግሥታቸው ውስጥ አላሰፈሩም። ይህ ዓይነቱ ገፍቶ የሚመጣ ምክንያታዊ የመብት ጥያቄና በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጠው የመገንጠል መብት ሚዛን ግን አንድ አይደለም። መጀመርያውኑ በቅንነት የተቀመጠ እንደሆነ ደግሞ ለወደፊቱ ሊታሰብበት ይገባል።

በተፈጥሮው የአመፅ ባህሪ ያለው የሰው ልጅ መስመር ውስጥ የሚያስገባው የተጻፈ ሕግ ነውና። መጽሐፍ፣ ‹‹እግር እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፣ ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆኗ ይቀራልን?›› እንዲል፣ የፌዴራል ሥርዓት የተፈለገበት ሌላው ምክንያት በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው መገነጣጠልን ለማበረታታት ሳይሆን፣ ብዙኃነትን መሠረት ያደረገ አንድነት ለማጠናከርና “የጋራ ማንነት” ለመፍጠር ነው። በተጨማሪም የፌዴራል ሥርዓት ልዩነትን በማጉላት ሳይሆን፣ ለልዩነቶች ልዩ ዕውቅና በመስጠት በሚፈጠረው የአብሮነት ሕይወት ለጋራ ጥቅም ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት እንጂ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ልዩነት እንደ አንድ ትልቅ አጋጣሚ በመጠቀም ከፋፍለህ ለመግዛት ያመቸን ዘንድ የሚዘረጋ ሥርዓትም አይደለም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...