Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትርብርቦሽ ምጣችን መሆን የለበትም!

ርብርቦሽ ምጣችን መሆን የለበትም!

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

 ኢትዮጵያን በአጠቃላይም ሆነ የተወሰነ የሕዝብ አካሏን የመበቀል ዓላማ የሌለን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከመባላትና ከመበታተን መትረፍ ከምድራዊ ሲኦል ማምለጥ (ከምንም ነገር በላይና በፊት ተቀዳሚ ጉዳያችን) መሆኑ የገባን፣ መትረፊያችን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ውስጥ ተቃቅፎ ሰላምን፣ ዴሞክራሲን፣ የተመጣጠነና ከጎረቤቶቻችን ጋር የተሳሰረ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት መሆኑን የተረዳን ሁሉ፣ የርብርቡ አካልና ንቁ ተሳታፊ መሆን ኃላፊነታችን ነው፡፡

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ክልል የመሆን ጥያቄ ያለንና ለውጡ ያሳሳናል የምንል ሁሉ አለንበት፡፡  በዚህ ደረጃ ላይ “እየዬም ሲዳላ” መሆኑን ማስተዋል መካሪ የማይሻ ኃላፊነት ነው፡፡ ትንሽ ብንታገስ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ጥሎን አይጠፋም፡፡ በሕገ መንግሥት የተቀመጠ መብታችን በቀውጢ ሰዓት ‹‹የመንግሥትን እጅ ጠምዝዝ. . . የወረርሽኝና የመበታተን አደጋ ባለበት ሰዓት አስጨንቀህ ውሳኔ ሕዝብ  አካሄድ. . .›› አይልም፡፡ ከመመንተፍ ብዙም ባልራቀ አኳኋን በጭንቅ ሰዓት ክልልነትን ላፍ ለማድረግ የሚካሄደው መወራጨት፣ አሁን የሚገኝና በኋላ የሚገኝ ክልልነት ልዩነት አለው በሚል አስተሳሰብ ከሆነ፣ ወደፊት የሚመጣ መሻሻልና ለውጥ የማይነካው አይኖርም፡፡ በቅድሚያ ይህንን አስጨናቂ ጊዜ አልፈን ምርጫም ሆነ ውሳኔ ሕዝብ  ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ሲመጣ፣ አከላለልን የሚመለከቱ ምክረ ሐሳቦች (ከመንግሥትም መጡ ከቡድኖች) የተብላላ ውይይትና ክርክር ተካሂዶባቸው ዞሮ ዞሮ የሚመለከታቸው የክልል ልሁን ጥያቄ ያነሱ ሕዝቦችን ይሁንታ ማግኘታቸው (ለተፈጻሚነታቸው) የግድ ነው፣ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት፡፡

እንደዚያም ሆኖ፣ ‹‹የእኔን ብሔር መጠሪያ፣ የእኔን ከተማና የእኔን ‹ባንዲራ› የያዘ ክልል መፍጠሬን ለድርድር አላቀርብ! ከፈለጉ ሌሎች የእኔን ባንዲራና የእኔን ብሔር መጠሪያ ተቀብለው የእኔን ዋና ከተማ ዋና ከተማዬ ብለው መቀላቀል ይችላሉ፣ አለዚያ እነሱም አንደ ፍጥርጥራቸው›› የሚል ዓይነት ከወዲህና ከወዲያ አብሮ መልማት የሚሹ ሕዝቦችን አላደራርስ የሚል ደንቃራ አቋም ጌታ ሆኖ ሊቀጥልም አይችልም፡፡ የፌዴራል የበጀት ድጎማ ከአሁኑ የበለጡ ብዙ የድጎማ አሰፋፈር መመዘኛዎች (ለልማት ቀና የሆነ አደረጃጀት ውስጥ መሆንን፣ ሙስናንና ብክነትን የማሸነፍ ስኬትን፣ ለኢንቨስትመንትና ለሥራ ፈጠራ ማድላትን፣ ሥራ አጥነትን የማቃለል ውጤትን፣ የተመጠነ ቤተሰብ ግንባታን፣ ወዘተ. ሁሉ) የሚያስተውል መሆኑም አይቀርም፡፡

ይዋል ይደር እንጂ ለሰካራሞችና ለአጭበርባሪዎች የተመቸው ሕገ መንግሥትም እንዳያምታታ ሆኖ መሻሻሉም አይቀርም፡፡ ሦስት ምሳሌዎችን ላንሳ፡፡ አንደኛ አሁን ያለው መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትርጉም ጥያቄ ለፌዴራሽን ምክር ቤት አቅርቦ ትርጓሜና ውሳኔ “ሲቀበል” ሕወሓት ‹‹የዓብይ መንግሥት ራሱ ትርጉም ጠያቂ፣ ራሱ ተርጓሚ፣ ራሱ ወሳኝ ሆኖላችሁ! አምባገነንነት ማለት ይህ ነው! . . .›› እያለ በመጮህ ብልጥ የሆነ ቢመስለውም የሚጮኸው፣ ይጮህ የነበረው በራሱ ላይ ነበር፣ ያጋለጠውም ራሱን ነበር ነውም፡፡ ያችን ከቁጥጥር የማትወጣ ሥልት ያቀናበራት ለራሱ አምባገነንነትን ሲል ራሱ ነበርና፡፡ እንዲህ ያሉ እውነተኛ የሕዝብ ወሳኝነትንና  የሦስትዮሽ (የመንግሥት) የሥልጣን ተገናዛቢነትን በአገረ መንግሥቱ ውስጥ በአግባቡ ያላወቀሩ አንቀጾች ከመሻሻል አያመልጡም፡፡

ሁለተኛ ሕወሓት በክልል ደረጃ ይህንን (ምርጫ) ለማድረግ ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድልህም ሲባል ሮጦ በማምታቻነት የሚያነሳው መብታችን እኮ እስከ መነጠል ድረስ ነው የሚል ነው፡፡ እሱን ያዩ አንዳንድ የክልል ጥማተኞችም ‹‹አከላለልን እንምከርበት፣ አካታች በሆነ አኳኋን. . .›› የሚል ሐሳብ ሲመጣባቸው አንቀጽ 39ን መመከቻ እስከ ማድረግ ሲሄዱ ታይተዋል፡፡ ይህ ማለት በቀላል አነጋገር በትዳር ውስጥ ስላለ የጋራ ትድድርና ኃላፊነት ሲወራ፣ ብፈልግ እኮ እስከ መፍታት ድረስ የራሴን ዕድል መወሰን መብቴ ነው እያሉ የማይገናኝ ነገር ማገናኘት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ መውጣት ተፈልጎ ከሆነ በግልጽ ፍላጎትን ማስቀመጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ  አንድነት ውስጥ መኖር እስከ ፈለጉ ድረስ ደግሞ ሕግጋቱን ማክበር ግድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ፣ የአንቀጽ 39 (አንድ) እስከ መነጠል የሚሄድ መብት ሌሎች ሕግጋትን ለመሻርና ለመርገጥ ያስችላል አይልም፡፡ አንደዚያ ቢል ኖሮ የሚኖረው “ሕገ መንግሥት” አንቀጽ 39 ብቻ (ሕገ መንግሥት አልባነት) በሆነ ነበር፡፡

ሕገ መንግሥቱ እንዲያ ባይልም በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ውስጥ በመኗኗሪያነት ያሠፈራቸውን አንቀጾችና ከኢትዮጵያ መውጣት የፈለገ የሚስተናገድበትን ድንጋጌ አዳብሎ በማስቀመጡ፣ ለሰካራሞችና ለአምታቺዎች ተመችቷል፡፡ ይህም በማሻሻያ መስተካከሉ በፌዴራላዊ ዴሞክሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኗኗርባቸው መብቶችና ሕጎች ለብቻቸው መቀመጣቸው፣ ከኢትዮጵያ ውጪ የመሆን የሕዝብ ጥያቄ ሲነሳ ደግሞ የሚስተናገድበት ሥርዓት ደረጃ በደረጃ መታለፍ ያለባቸውን እርከኞች ይዞ ተገቢ ሥፍራውን መያዙ አይቀርም፡፡

በተረፈ የእያንዳንዱ ብሔረሰብ/ብሔር ዕድል በየራሱ መዳፍ ውስጥ አለመሆኑና ራስን በራስ ማስተዳደርና ‹‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን›› መምታታት የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ራስን በራስ ማስተዳደር ዕውን እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ እያንዳንዱ የራሱን ዕድል እንዲወስን የሚፈቅድ ነባራዊና ህሊናዊ እውነታ ቢኖር ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ካልተሰባሰብን አሳር ይገጥመናል የሚል ሥጋትና ጭንቅ ባልገባን ነበር፡፡ ይህን ሁሉ የመሰባሰብ ትግል የምናደርገው ዕጣችን እርስ በርስ የሚወሳሰን፣ በእኛ ብቻ ሳይሆን በጎረቤቶታችንና በዓለም አዝማሚያ ሁሉ የሚወሰን ስለሆነ ነው፡፡ በፌዴራልና በክልልም ሆነ ከዚያ በታች ባለ ተዋረድ የሥልጣን ክፍፍል የምናደርገውም ዕጣችን በየራሳችን ፍላጎትና ውሳኔ የማያልቅ ስለሆነ ነው፡፡ እዚህም ላይ የጠራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ ‹‹የራሳችንን ዕድል ራሳችን እንወስናለን፣ ሌላው በእኛ ዕድል ላይ አይወስንም! እኛም በሌላው ዕድል ላይ አንወሰንም!›› ብሎ ማለት መቃዠት ነው፡፡

ሦስተኛ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 (ሦስት ሐ) መሠረት፣ ክልል ልሁን ባይ ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ባለው ምክር ቤት የሁለት – ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት አግኝቶ አባል ሆኖ ለቆየበት ክልል ጥያቄውን ማቅረብ አለበት፡፡ ክልል የመሆን ጥያቄ ማንሳት የሚሻ ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤታዊ የሁለት – ሦስተኛ ውሳኔን ለማግኘት በቅድሚያ ምክር ቤት ሊኖረው ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ለማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ የተፈቀደ ነው፡፡ አንቀጽ 39 (ሦስት) ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው ይላልና፡፡ እናም ትንሽ ትልቅ ሳይባል አቅም አለህ የለህም ሳይባል ክልል ለመሆን የመጠየቅ ድፍን ዕድል ለሁሉም (በጥቂት ሺዎች የሚቆጠር የሕዝብ ብዛት ላለው ቁንጣሪ ማኅበረሰብ ሁሉ) ክልልነት የተፈቀደ ነው፡፡ መስከር ለፈለገ ሁሉ እንዳይሰክር የሚከለክለው ሊኖር አይችልም እንደ ማለት ነው፡፡ ይህም ሆነ ሌሎች ለስካር የተመቹ ነገሮች በደንብ ታሰቦባቸውና የጎደሉም ታክለው የሕዝቦችን እውነተኛ ፍላጎትና መግባባት የያዘ ሕገ መንግሥት መቀዳጀታችን አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባፀደቁት ሕገ መንግሥት መገዛት ደግሞ የፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አካል የሆነ ክፍለ ሕዝብና “ክልል” ሁሉ የውዴታ ግዴታቸው ነው፡፡

ሰክሮ የሚያስክር ሕገ መንግሥታችንን አርመንና እኛም ከስካር ወጥተን በጊዜ ሒደትና ልምድ ለተቀናጀ ልማትና መለማማት በሚስማማ አኳኋን የአስተዳደርና የኢኮኖሚ አወቃቀራችንን አስተካክለን፣ አረንጓዴና የተመጣጠነ ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ እንገነባለን፡፡ ይህ ማለት በየወረዳና በየዞኑ ከዳር ዳር የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የደንና የማዕድን እኩል የልማት ቅንብር እንደ ዩኒቨርሲቲ ዕደላ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ወይም ‹‹የኢንዱስትሪ ፓርክ ይኑረን! ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ለእኛም ይድረሰን!›› የሚል ድምፅ በተሰማበት ሥፍራ ሁሉ የተባለው ሁሉ ይገጠገጣል ማለት አይደለም፡፡ ከግብርና ማቀነባበሪ አንስቶ እስከ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ድረስ፣ የውስጥና የውጭ ንግድ መስተጋብራዊ አዋጪነት በሚሳለጥባቸው የሥፍራ ነጥቦች ላይ መዋቅራቸውን ይዘረጋሉ፡፡

ከእነዚህ ጋር የግብርና፣ የደንና የማዕድን ሀብታችን ይመጋገባል፡፡ በኢኮኖሚያችን ዝንጉርጉነት ውስጥ የየዘርፎች ድምቀትና ግዝፈት በሁሉ አካባቢ አንድ ዓይነት አይሆንም፡፡ አንዱ ጋ የቱሪዝም ኢንዱስትሪና የደን ሀብት ልማት ከፋብሪካው ገዝፎ ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ ሌላ ሥፍራ የማዕድን ልማትና ፍብረካው አይሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ የየአካባቢው አዋጪና ዕምቅ አቅም እየለማ ከሌላው ዘርፍ ጋር መመጋገቡ፣ አንድ ላይ የተሳለጠ የኢኮኖሚ መስተጋብር መፍጠሩና የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ የተመጣጠነ ልማት ማቀዳጀቱ ነው፡፡ ይህም ማለት በመሠረታዊና በዘመናዊ መሠረተ ልማት ፍላጎቶች ድርሻ መንጓለልን (ከተማና ገጠርነት፣ መለስተኛ ከተማና የናጠጠ ከተማ መሆን፣ የቀርነትና የሥልጣኔ ወይም የተጠቃሚነትና የተጎጂነት ምልክት መሆናቸውን) ማስወገድ የእኩል ልማት መድረሻችን ነው፡፡ በቀላል አማርኛ አንዱ ጋ በጭራሮ ዳስ፣ ሌላው ጋ በተቀማጠለ አያያዝ የሚሰጥ ትምህርት አይኖርም፡፡ ሁሉም ዓይነት ዕድል በእኩል ጥራት ለሁሉም መዳረሱ የግድ መሟላት ያለበት የመልማት መብት ነው፡፡

የዚህ ዓይነት ልማት ውስጥ ሲገባና ዴሞክራሲ ባህል ሲሆን፣ አዳዲስ ፍላጎቶች አብረው መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ከእነዚህ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱ ኮንፌዴራላዊ ግንኙነት ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት ዛሬ የምንብከነከነው ድህነት አመጣሽ የመሬት ስስትና ሌሎች ቅራኔዎች አናጭተውን ከሰላሙም ከዕድገቱም ከነፃነቱም ሳንሆን እንዳንቀር ነው፡፡ የተመጣጠነና የሚመጋገብ ኤኮኖሚ ይዞ በክልል ኅብረት ውስጥ መኖር ደግሞ የበለጠ ለመመንደግና በበርካታ የሥልጣኔ መብቶች ለመንበሽበሽ ሞተር ሊሆነን ይችላል፡፡ ከኢንዱስትሪያዊ ልማትና ከዴሞክራሲ ባህል የሚወለድ ኮንፌዴራላዊ ኅብረትን መድረሻችን ለማድረግ የምትሹም፣ የዛሬ አገራዊና ቀጣናዊ እውነታችን ግድ የሚለንን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገራዊ አንድነት መሳፈራችሁ አስተዋይነት ነው፡፡ በአጭሩ ዛሬ አንድ ላይ ልንተባበር የምንችለው ኃይሎች ይህን ያህል በሰፋና በራቀ አድማስ ውስጥ የምናስብ ሁሉ ነን፡፡

መተባበራችን ምን ለማድረግ?

) ቀደም ብሎ እንደተገለጸው፣ በአሁኑ ደረጃ “ኢፌዴሪ”  የሚለው ስም ከይዘቱ የበለጠ ነው፡፡ እናም አገረ መንግሥቱ ባልተሟላ የጨቅላ አቅሙ ከማይችላቸው ከባድ ፈተናዎች ጋር እየተጋፈጠ “ጉትያ አብቅል! ቆመህ ሂድ!” (ገለልተኛ ሁን፣ ፍትሕ አታዛባ፣ ሰብዓዊ መብትን አትጣስ፣ እኩል ዜግነትን ውለዳት) እየተባለ ቁም ስቅል ሲያይ፣ ስህተት በስህተት ጥፋት በጥፋት ሆኖ ለመክሸፍ ዕድል አለው፡፡ ከክሽፈት አምልጦ ሁሉንም በእኩል የሚያገለግሉ ሃይማኖት የለሽ፣ ፓርቲ የለሽና ብሔር የለሽ የሆኑ የዴሞክራሲ ሥርዓተ መንግሥት ተቋማትን እንዲገነባና የዴሞክራሲ ልምምድን እንዲያጎለብት መተባበራችን በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡ በዚሁ  ሒደት ውስጥ በክልል ደረጃ መገንባት ያለባቸው ብዝኃነትን ያንፀበረቁና በወገንተኛነት ያልተሰነከሉ ተቋማትም ለመሟላት ዕድል ያገኛሉ፡፡

የፌዴራል የደኅንነትና የወንጀል የምርመራ ተቋማት፣ የፌዴራል ፖሊስና የፌዴራል ፍርድ ቤቶችም በየክልሎቹ ተገቢ አውታሮቻቸውን ለመዘርጋትና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የመወጣት ልምምድ ውስጥ ለመግባት ዕድል ያገኛሉ፡፡ የሰብዓዊ መብት፣ የጋዜጠኛነትና የሲቪል ማኅበራት መዋቅሮችና እንቅስቃሴዎችም እንደዚያው ሥርጭታቸው ይሰፋል፣ ይረዝማል፡፡ በመተባበራችን ምክንያት ከአልቃሻና ከግርግራም ፖለቲካ ይልቅ፣ አዎንታዊ የዴሞክራሲና የአዲስ ሕይወት ግንባታ እንቅስቃሴዎች መላወስና መፍለቅለቃቸው ይደምቃል፡፡ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴያችን አዲስና ትኩስ ደም የማምረት ማህፀኑ ይለመልማል፡፡ ትብብራችን ትርምሳምነትን ያብርድ እንጂ ለለውጡ መንግሥት “አዎ” ባይና “እሺ” ባይ (አጨብጫቢ) አይደለምና ለውጡ በእኝ እኝና በእልህ ለእልህ መዳፋት ውስጥ ሳይወድቅ፣ በሂሶችና በምክሮች ተጠቃሚነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የለውጥ ጉዟችን የእነ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነንና የእነ ሌንጮ ለታን መሰል የሰከነ አስተዋይነት በትብብር መንገድ ሳያቀርብና ሳያሰባስብ፣ መሰናክሎችን ለማለፍ የሚያስችሉ ብልኃቶችና ሐሳቦች ሀብታም እንደምን መሆን ይችላል!?

የዳር ተመልካችነት (ከፖለቲከኛ እስከ ምሁርና እስከ ብዙኃን) ወደ ንቁ ተሳታፊነት ተቀይሮ፣ የተበታተኑ ኃይሎች አንድ ላይ አብረው በአልቃሻና በግርግራም እንቅስቃሴ ፋንታ አዎንታዊ እንቅስቃሴ መፍለቅለቁ በራሱ፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በጥላቻ የተመረዙና የራሳቸውን አጥፊነት ከማየት ይልቅ መንግሥትን የሁሉ ጥፋት ምንጭ ሲያደርጉ የቆዩ ሰዎችን/ቡድኖችን ለራስ በራስ ትዝብትና ፀፀት ይገፋፋቸዋል፡፡ በትብብራችን ሰላማችንና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴያችን መለምለሙ ብቻውን የሴራ፣ የሻጥርና የትርምስ ኃይሎችን ያብረከርካቸዋል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ሊጠቀስ የሚገባው የትግግዝ ሥራም አለ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር ሆነው የሩዋንዳ ዓይነት ፍጅት ሊያስከትሉና የአፍሪካ ቀንድን የትርምስ ቀጣና ሊያደርጉ የሚችሉ ጽንፈኛ ኃይሎች የሚዲያ ሥርጭት እንዳያገኙ፣ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትን ሁሉ ከጎን አድርጎ ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ ትግል የማካሄድ ትግል የሚቦዘንበት አይደለም፡፡ ይህ ትግል እንዲሳካ ቢያንስ በግዝፈት የተፈጸሙትን በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ትኩስ የጅምላ ጥቃቶች በምሥልና በዓይን ምስክርነት ያደራጀ ሰነድ ማውጣት የማይታለፍ ነው፡፡

) ጥላቻና በቀል የሚወልደውን ቀውስ ስንታገል በሌለ አቅጣጫ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብሔራዊ ባንክን ቁጥጥር አላልቶና ገመና ሽፈና ውስጥ ከትቶ፣ መንግሥታዊና የባንኮች የውጭ ብድር በሽፍንፍን ጋሽቦ፣ ወደ ንዋይና ወደ ኢኮኖሚ ቀውስ እንዳያንከባልለን የሚደረገው ጥንቃቄና ትግል ለአንድ አፍታም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የባንኮችን “ሀብት” በአንድ ጀንበር ዶግጋ አመድ ሊያደርግ የሚችል የዕዳ ቀውስ አንዴ ከጠለፈን፣ የቴሌኮምን ንግድ 40 በመቶ ድርሻ ከመሸጥ ያለፈና ሌሎች የሕዝብ ይዞታ ሆነው መቀጠል የሚገባቸውን ሀብቶች ለውጭ ኩባንያዎች እስከ ማሳለፍ ድረስ የስንግ ተይዞ መንበርከክ ሊደርስብን ይችላል፡፡

ይህ እንዳይሆን ርብርባችን የንዋይና የኢኮኖሚ ፈርጅ (በሃዋላ በኩል የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ አቅም ማጠናከርን፣ ወጪ ንግድን ወደ ዕመርታ መውሰድንና ገቢ ንግድን በአገር ውስጥ ምርት መተካትን ያሳለጠ የተጋድሎ ፈርጅ) ያለው መሆኑ ግድ ነው፡፡ የኢኮኖሚና የንዋይ ተጋድሏችን ከሰመረ በቴሌኮም 40 በመቶ መሸጥ ላይ ያለን ተቃውሞ ፍሬያማ መሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የውጭ ኩባንያ ቴሌኮም ውስጥ መዝለቅ የውጭ ኃይል ስለላ (የስለላ ሥራ) ማጀት ድረስ እንዲገባ የሚመች መሆኑ፣ ንግዱ የማይነጥፍና አንጀት አርስ ገቢ ማስገኘቱና እንዲህ ያለው ገቢ ለሕዝባችን ልማትና ለኅብረተሰባዊ ዕድር እጅግ አስፈላጊ መሆኑ፣ ለውጭ ቢሸጥ ግን በብር የሚሰበሰበው ትርፍ በዋነኛነት ወደ ውጭ ምንዛሪ እየተቀየረ (የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ጥሪት እየተሻማ) የሚወጣ መሆኑ፣ የቴሌኮም አገልግሎትን የማዘመን ተልዕኮ የሚጠይቀን ለውጭ ኩባንያ የማይነጥፍ ሲሳያችንን ማካፈል ሳይሆን፣ መንግሥት አገልግሎቱን መጫወቻ እንዳያደርገው ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በተገነባበት ድባብ ውስጥ ቴሌኮም ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ እየገዛና በውስጥ አቅም እያዳበረ የሚራመድ ብሔራዊ ሻምፒዮን እንዲሆን መንከባከብ መሆኑ ሁሉ ተቃውሟችንን ያግዛል፡፡ ይኸው ቀና ተቃውሟችንም ለዓብይ መንግሥት ከእነ ዓለም ባንክ ተፅዕኖ ለማምለጥ የጓሮ በር ሆኖ ሊጠቅምም ይችላል፡፡

ለውጥ ፈላጊዎች (ከምሁር እስከ ተራ ሰው፣ ከቤት እስከ ውጭ አገር) ተያይዘውና ሰላምን ነፃነትንና ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴን ሙጥኝ ብለው የዴሞክራሲና የልማት አብዮት መክፈታቸው በራሱ፣ ጥይትና ሴራ እየተኮሱ ሕዝብን አጫርሰው የሕዝብ ደም የጠጣ መሬት ነፃ ለማውጣት የሚለፉትን አሮጌ ጽንፈኞች ከወታደራዊ ባዙቃና መትረየስ የበለጠ ጥቃት ያደርስባቸዋል፡፡ ከሕዝብ እየተነጠሉ ተፍረክርከው እየተሸረፉና እየተቦደሱ የመመናመን ምዕራፍ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ ሞትና ውድመት የሚደግሱ አስተኳሾችን አድብቶና አጥንቶ ከመቅደም፣ ከማራወጥና ከመልቀም ጋር የጥፋት ሠፈርን ትተው ወደ ለውጡ ሠፈር መምጣት የሚሹትን መጥራትና እየተቀበሉ ማነፅ ሲተጋገዙ ደግሞ ለውጡ በድል ላይ ድል ይጨምራል፡፡

የሕወሓት አሮጌ 17 ዓመታት ሙሉ የሕዝብ ደም በተገበረበት መስዋዕትነት የኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ላይ ቢወጡ፣ በዘረፋና በግፍ ተጨማልቀው የትግል አደራ በል መሆናቸው ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ ትግራይን የቅጥቀጣ አገዛዛቸው ማዕከል አድርገው ለትግራይ ሕዝብ ሌላ ጥሪቱንና ልጆቹን የሚበላ ጦርነት እየደገሱ መሆናቸው፣ እንጥፍጣፊ የሕዝብ አሳቢነት እንኳ እንዳልተረፋቸው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝና የአንበጣ አደጋ ባለበት ጊዜ የደገሱትም “ምርጫ” ከቀጣፊነት ይበልጥ የጨካኝነታቸውም ሌላ ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ድርጊቶቻቸውና በኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ላይ የሚፈጽሙት ሸፍጥ መጋለጡ፣  ከትግራይ ወጣቶች ትግል ጋር እየሰፋና እያደገ ቢሄድ፣ የወጣቶቹ ትግል ወታደራዊ ልብስ እንዲለብሱና ጠመንጃ እንዲያነግቱ እስከተደረጉት የነገ ተሰዊዎች ድረስ ቢሰፋ፣ ከዚህ ሁሉ ጋር በቀሪው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የመብቶች ልማት ግስጋሴ አቁለጭላጭነቱ ቢጎለብት ውጤቱ ቀላል አይመስለኝም፡፡ ለወ/ሮ ሙፈሪያት አንሰፍሳፊ ዕንባና የሃይማኖት አባቶችን ለጨመረ ሽምግልና ያልተበገረ ጭንጫ ልብ ወይ ለማጎንበስ ይገዳዳል፣ ወይ በትግራይ ወጣቶችና ከሕውሓት ውስጥ በውጡ ለውጥ ፈላጊዎች ቅንጅት ተወግዶ ለውጡ አገር አቀፍ ምልዓቱን ይቀዳጃል፡፡

) በዚህ ክፍል በሕዝብ ለሕዝብ መተባበር ላይ አትኩሬ በቀጥታ ሕዝብን አንድ ላይ ሰብስቦ የማናገር ያህል እያሰብኩ ጥቂት ነጥቦች እተነፍሳለሁ፡፡ ከሕዝብ አባላት በኩል በሰኔ 20ዎች ‹‹በተፈጸመው የጥፋት ሥራ አፈርን! አንገት ደፋን! ወገኖቻችንን ነው ያጣነው! ተቸግረን ያሳደግናቸውን ልጆቻችንን ጥላቻ ሰረቀብን! ወዘተ. ወዘተ.›› ሲባል ሰምተናል፡፡ የተመረርንበት ጥፋት እንዳይደገምና ልጆቻችን የሰይጣን ቁራጭ እስኪመስሉ ድረስ ልቦናቸውን የሰለበው ጥላቻና በቀል እንዲወገድ ማሰብ አንድ ነገር ነው፡፡ የገጠመን ችግር ግን ከልጆቻችን አልፎ ሕዝብና ሕዝብን ወደ መቀናደብ ሊወስድ የሚችልም ነው፡፡ የሁሉም ሕዝብ ሁነኛ ፍላጎት ሰላም፣ ነፃነትና ክብር ያለው ኑሮ ነው፡፡

እነዚህን ፍላጎቶች በማስገኘት ረገድ ፀረ አፄና አፄ አምላኪ ሆነው የተፋጠጡ ቡድኖች ይጠቅሙናል? የአፄዎች አወዳሾች በውዳሴያቸው በቀለኞችን ያጨሳሉና አማርኛ ተናጋሪ ውጥንቅጦችን ለጥቃት ያጋልጣሉ፡፡ ፀረ አፄነትንና አፄያዊ ግፍን የሚያጦዙት በበኩላቸው “ተቆረቆርንልህ” የሚሉትን ሕዝብ ለበቀለኛ ቁጣ ያነሳሳሉ፡፡ ሁለቱም እርስ በርስ ወደ መፋጀት ይመሩናል፡፡ በዚህም ሰላማችንን፣ ዝምድናችንን፣ ነፃነታችንንና የፍትሕ እሴታችንን ነጥቀው በደም ያጨመላልቁናል፡፡ እዚህ ገሃነም ውስጥ ላለመግባት ምን እናድርግ? መምከርና መፍትሔ መዘየድ አንገብጋቢ ጉዳያችን ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንዱ ተቀዳሚ ተግባር “ነፍጠኛ ጠላትህ!” በሚሉትም ሆነ ነፍጠኛነትን በሚያወድሱት ላይ ማደም፣ ለሁለቱም ዓይነት የፀብ ፖለቲከኞች ጆሮም መድረክም መንፈግ ነው፡፡ ሁለቱም የጦዙ (ነገረኛ) አመለካከቶች የወጣቶቻችንን ህሊና የበረበሩት ከሰማይ በመጣ ጥሎሽ አይደለም፡፡

እኛው ታላላቆቹ አወቅን ባዮች በመጽሐፍት፣ በመገናኛ ብዙኃንና ሰው በሰው አማካይነት ነው የጠቀጠቅንባቸው፡፡ ጥቅጠቃው ዛሬም እየተፈታተነን ነው፡፡ ሰኔ አጋማሽ ውስጥ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ በተዘጋጀ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የጦዘ ትረካ በመረራ ጉዲና የቀረበው ለመግባባት ሳይሆን፣ በምክር ቤቱ ውስጥ የአፄኞችና የተፀራሪዎቻቸው ረድፍ ቦግ እንዲል (ፓርቲዎች በሁለቱ ጎራ ሠልፍ እንዲሠሩ) ነበር፡፡ ይህ ሊገለጽላቸው የማይችልና በፖለቲከኛ የታሪክ ትረካ ላይ አንወያይም ብሎ ማለፍ የተሰወራቸው ቆሞ ቀሮች ግን፣ ለጎራቸው ሲብከነከኑ መታየታቸውን ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡ ከዚህ አልፌ ምኒሊክ በ19ነኛው ክፍለ ዘመን ፈጸመው የሚባለውን ቅጣት የዛሬ በቀለኞች እየፈጸሙት ሳሉ፣ እነሱን ትቶ በምኒልክ ላይ በሚያተኩር ጤና ቢስ ትረካ ላይ ምን ልል እችላለሁ!? የዚህ ጤና ቢስ ትረካ አቅራቢ ደግሞ መሀል መንገድ ላይ ያሰባስበናል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው መረራ ጉዲና መሆኑ!! ከዚህ የምንገነዘበው ለሁለቱም ጽንፈኞች ጆሮ አንሰጥም ብሎ ማደሙ የመንግሥትን፣ የፖለቲከኞችን፣ የማኅበራዊ ኑሮና የሥነ ልቦና ባለሙያዎችንና የመገናኛ ብዙኃንን ርብርብም እንደሚሻ ነው፡፡ የታሪክ ባለሙያዎችም ሁለቱንም ጽንፈኞች የሚያኮመሽሽ፣ ከጡዘት ርቆ በኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ የሁሉንም ሕዝብና ገዥዎች አስተዋጽኦ የሚያሳይ ሥራ እንዲሰጡን ያስፈልጋል፡፡

ይህም ብቻ አይበቃም፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ዝምድናን የሚያጠብቁ፣ ለከፋፋዮች የማይመቹ ሥራዎችንም መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ዳግማዊ ምኒልክ ያሉ አፄዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያላቸው ሥፍራ የመላ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ እነዚህን ባለታሪኮች ከአማራ ሕዝብ፣ ከአማራ ክልልና የዞን መስተዳድሮች ጋር ያጣበቀ (አማራ የብቻ ባለቤትነትና ባለአደራነት ያለበት የሚያስመስል) የጎራ ሠልፍና እንቅስቃሴ፣ ከፋፋዮች የሕዝቦችን ዝምድና ለመበጥበጥ እንዲችሉ መንገድ የሚሰጥ ነውና በዚህ የቋፍ ጊዜ ከዚህ ዓይነት ተግባር መቆጠብ ይበጃል፡፡ 

በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የመጣንበት የታሪክ ጉዞ የአማርኛን ቋንቋ የየአካባቢው ሕዝብ እንዲጋሩ አድርጓል፡፡ አሁንም በመግባቢያነቱ ሀብቴ ብለው እየሠሩበት ይገኛሉ፡፡ በዚያው ልክ በየአካባቢዎች ባሉ ከተሞች ውስጥ ያሉ ቅይጥይጥ ማኅበረሰቦች የዓውዳቸውን ማኅበረሰብ ቋንቋ በመግባቢያነቱ ተጋርተው የጋራ ማንነታቸው መገለጫ አለማድረጋቸው፣ ዓለም ሦስት አራት ቋንቋ በሚናገርበት ዘመን ውስጥ ቀላል ጉድለት አይደለም፡፡ ይህንን ጉድለት ለመሙላት መፍጨርጨር የአካባቢ ቋንቋን በተለያዩ የማኅበራዊ ኑሮ ሁኔታዎች (በግብይይት፣ በስብሰባዎች፣ በዕድሮች፣ በመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ወዘተ.) ለመገልገል መጣጣር ለነገ የሚባል አይደለም፡፡

ይህን ለማድረግ ስንችል ልጆቻችን በአንድ ጊዜ ከአንድ በበለጡ ቋንቋዎች ውስጥ ለማደግና ብዙ ቋንቋዎችን እንደ ውኃ ለመናገር ይችላሉ፡፡ ባለብዙ ቋንቋ ተናገሪ እንዲሆኑ አድርገን ልጆችንን ማሳደግ፣ ለብዙ ነገር የሚጠቅም ትልቅ ስጦታ ለልጆታችንን ማጎናፀፍ ነው (አሁንም አንደኛ ደረጃ ትምህርት በአማርኛ በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች የየአካባቢው ቋንቋ ትምህርት አይሰጥ እንደሆነ እሱንም ማካተት ተገቢ ነው)፡፡ በቋንቋና በባህል ከመላላስ ጥረት ጋር በተለያዩ የዝምድና መፍጠሪያ መንገዶች መተሳሰርንም ማስፋትና ማጠናከር፣ ከዚያም አልፎ በሽርክና መሥራትና ብሔረ ብዙ ባለቤትነት ያላቸው የንግድ ሥራዎችን መክፈትና ማስፋፋት፣ ከፋፋይነትን ለማክሸፍ ያለው አስተዋጽኦ በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡

በአካባቢያዊ  የኑሮ ጉዳዮች (ጤና፣ ውኃ፣ ፀጥታና ልማት) ላይ በየጊዜው የሚመክር ቋሚ ጊዜ ያለው የነዋሪዎች ጉባዔ፣ ቅይጥነትን ባልዘነጋ ኮሚቴ የሚመራ መፍጠርና ከይስሙላ ያለፈ እንቅስቃሴ ማድረግም ተፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ጉባዔ ውስጥ ክርር ያለ የቋንቋ አጠቃቀም ሳይዙ፣ በአካባቢው ቋንቋ በአያሌው መግባባት የሚቻል ከሆነ ያንን እየተጠቀሙ በዚያ ውስጥ የቸገረው በአማርኛ ሐሳቡን እንዲገልጽ መፍቀድ፣ ግለሰቦች ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው ቋንቋ እየዞሩ ጉራማይሌ ንግግር ቢያደርጉ እንኳ የቋንቋ ባለፀጋነትን ማየት እንጂ፣ ከጥፋት አለመቁጠር የዴሞክራሲ ልምምዳችንን ያደብራል፣ ቋንቋን መሽካከሪያ የማድረግ መሰሪነትን ያዳክማል፡፡

እነዚህን ሁሉ አቀናጅተን ማስኬድ ከቻልን ግንዛቤያችን በቆሞ ቀሮች የእርግማንና የውዳሴ አቋሞች መደናገሩ ያለፈ ታሪክ ይሆናል፡፡ ሰላማችንና የዴሞክራሲ ግንባታችን ሥር መያዙ፣ ኢኮኖሚያችንም ወደ ብልፅግና ማኮብኮቡ እርግጥ ይሆናል፡፡ የታሪክ ምርምሮችም ያለ ፖለቲካዊ ጎራ እየተፈለቀቁ፣ አንዳቸው በሌላው እየተበጠሩና እየጠሩ ይወጣሉ፡፡ ብዙ ነገሮች የኋሊት የማይቀለበሱበትን እርካብ ከተቆናጠጥን ወዲያ፣ አዲስም ሆነ አሮጌ ፅንፈኞች መድረክ ላይ ወጥተው የእርግማንና የውዳሴ ጥግ የያዘ የቃላት መተጋተግ ሲያካሂዱ ብናይ፣ ትግትጋቸው ሰላማችንን የማይነካ እንደ አስቂኝ ቴአትር እየሳቅንና እየተገረምን የምንዝናናበት ትርዒት ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...