Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከጭንቅ ወደ ዕረፍት ያሻግረን!

ነባሩን የ2012 ዓ.ም. ሸኝተን አዲስ 2013ን ጀምረናል፡፡ በ2012 ዓ.ም. አገር በእጅጉ የተፈተነችበት፣ በኢትዮጵያ እንደሚፈጸሙ የማይገመቱ የጭካኔና የአራዊት  ተግባራት የተስተናገዱበት ዓመት ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በውስጥ ችግርም ሆነ ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ የገጠሙ ፈተናዎች በተለያየ ፈርጅ የሚታዩ ናቸው፡፡

የበረሃ አንበጣ ቤተኛ መሆኑ፣ የጎርፍ አደጋ እዚህም እዚያም መከሰቱና በርካቶችን ማፈናቀሉና ማጉላላቱ ተሰናባቹን ዓመት አሳዛኝ ክስተቶች ያስተናገደ አድርጎታል፡፡ ፖለቲካን ከትጥቅ ትግል አያይዘው ጫካ የገቡ፣ መንግሥት ሽፍቶች የሚላቸው ቡድኖች ጥቃት ሲያደርሱ የነበሩበት ወቅት ነበር፡፡ ሰላም አደፍራሾች የተበራከቱበት ዓመት እንደ ዘበት ተሸኝቷል፡፡ የምርጫ መራዘምን ተከትሎ የተፈጠረው ውዝግብ፣ ኢሕአዴግ ከስሞ የብልፅግና ፓርቲ እንደ ውሕድ የተመሠረተበት፣ በሕወሓትና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት የፖለቲካ ትኩሳቱን በማጋጋል በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ የያዘበት ዓመት ነበር፡፡

ከፖለቲካ አንፃር በርካታ አለመግባባቶችና ውዝግቦች የታዩበት፣ መደማመጥ አበሳ የሆነበት፣ ጽንፈኝነት እዚህም እዚያ የነገሠበት፣ ለሰው ሕይወት፣ ለንብረት መውደም ሰበብ የነበረበት ጦሰኛ ዓመት አሳልፈናል፡፡ በሰበብ አስባቡ የተፈጠሩ ቀውሶች የሃይማኖት ተቋማት ጭምር ለጥቃት እንዲጋለጡ፣ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት እንዲጋዩ፣ የትምህርት፣ የጤናና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጠራራ ፀሐይ እሳት ሲለኮስባቸው ታይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የፖለቲካው ዙረትና አካሄድ አደገኛ እንደነበር ያስታውሰናል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን በእያንዳንዱ ሁከትና ግርግር የጠፋው የሰው ሕይወት ያሳዝናል፡፡ በጭካኔ ሕይወታቸውን ያጡ ንብረታቸውን የተነጠቁ ዜጎች ቁጥር ቀላል የማይባል መሆኑንም እናስታውሳለን፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ የፖለቲካው ጡዘት በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ሳያንስ የኮሮና ወረርሽኝ ሲታከልበት ኢኮኖሚውን በእጅጉ ተገዳድሮታል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ለወትሮውም ፈተና የበዛባትን ኢትዮጵያ የበለጠ ውጥረት ውስጥ በመክተት የስንግ ወጥሯት አልፏል ማለት ይቻላል፡፡ ወረርሽኙ ከኢኮኖሚው በተጓዳኝ ማኅበራዊ ቀውስ መፍጠሩም ዋጋ እያስከፈለ መጥቷል፡፡ አገር ያሰበችውን በተገቢው መንገድ እንዳታሳካ፣ ዜጎች እንደ ልባቸው እንዳይሠሩ አስገድዷል፡፡

ከ20 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ተለያይተው የዓመቱን አጋማሽ ያሳለፉበት ዓመት ሆኖ ማለቁ ትልቅ መስዋዕትነት የተከፈለበት ዓመት ያሰኘዋል፡፡ የ2012 ዓ.ም. ሰው ሠራሽና ድንገተኛ አደጋዎችን ጨምሮ ሌሎችም ተግዳሮቶች የተበራከቱበት ነበር፡፡ እነዚህን ያልታሰቡ ተግዳሮቶች ለመቋቋምና ችግሮቹንም ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ አገር እንድትረጋጋ፣ ኢኮኖሚውም ከተጎዳው የበለጠ እንዳይጎዳ ያግዛሉ የተባሉ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከቀናት በፊት ዓምና የሆነውን ዓመት ስናስብ፣ ጎሮሮ ላይ ከተሰነቀረ አጥንት የማይተናነሰው ችግር   የዋጋ ግሽበት ነበር፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ሲታከልበት፣ በምርትና አገልግሎቶች ላይ የታየው የዋጋ ንረት ጉልበቱ የበረታበት ዓመት ነበር፡፡ የዋጋ ንረት የዜጎች ፈተና በመሆን ወደ አዲሱ ዓመት አብሮን ተሻግሯል፡፡

እንዲህ ካሉ አጣብቂኞች በመለስ የተሸኘው ዓመት በመልካምነት የሚወሱ አገራዊ ክንውኖች የታዩበትም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተደራራቢ ችግሮች እዚህም እዚያም መበርታታቸው ግን የመልካም ሥራዎችን ውጤት ለማጣጣም የማያመች አድርጎታል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ቢኖር፣ ጽንፍ የረገጠው የፖለቲካ ቀውሶች ባይፈጠሩና የኮሮና ወረርሽኝ ጋሬጣ ባይመጣብን ኖሮ ምራቅ የሚያስውጡ ውጤቶች ሊታዩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁንና በዓመቱ የተስተናገዱት ቀውሶችና አደጋዎች ወሳኝ አገራዊ ክንውኖች በተፈለገው ደረጃ ትኩረት እንዳይሰጣቸው አስገድዷል፡፡

የተሸኘውን ዓመት በመልካም ከምናወሳባቸው ከብዙ በጥቂቱ ለማስታወስ ያህል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌት መሳካት ትልቅና ቀዳሚው ብሔራዊ አጀንዳ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት የአንድነት ፓርክ የእንጦጦና የሸገር ፓርኮች እውን መሆን አገሪቱን የቀረ የለውጥ ጅምር ውጤት መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ በዚህ ረገድ የታየው እመርታ ዓመቱን በመልካም ከሚያስታውሱን ጉልህ ክንውኖች ውስጥ የሚሠለፍ ነው፡፡

ከአሮጌው ዓመት መጥፎ ተግባራት ይልቅ በጎዎቹን ይዘን ወደ አዲሱ ዓመት የምናሻግርበት፣ ክፉውን በዚሁ ይብቃን ብለን የምንተውበት ጊዜ እንዲሆን እንመኛለን፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የተሻለ የምንሠራበት ይሁንልን፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩና ለወገኑ አስተዋጽኦ በማበረክት በመልካም የሚወሳበት አዲስ ዓመት እንዲመጣ እንመኛለን፡፡ አዲሱን ዓመት ስንቀበል እንደ ዜጋ እኔ ለአገሬ የሚል ባለድርሻ እንዲበዛላት፣ ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት የሚተጋበት ዓመት መሆን አለበት፡፡ ከመንግሥትም የምንጠብቃቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ ከሚወቀስባቸው ነገሮች አንዱ ሕግ ማስከበር ላይ የመልፈስፈሱ ነገር ነውና ይህንን አርሞ፣ ዜጎች የመኖርና በሕይወት የመቆየት ዋስትናቸው ተከብሮ ከሥጋት የሚላቀቁበትን ሥራ ከመንግሥት እንጠብቃለን፡፡ መጪው ዓመት ምርጫን ጨምሮ ትልልቅ ክንውኖች የሚሰተናገዱበት እንደመሆኑ እንደ ትናንቱ ክፍተት መፍጠር ‹‹የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም››ን እንዳልሰሙ መሆን ነው፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው ከኮንዶሚኒየም ዕደላና ከመሬት ወረራ ጋር ለተያያዙ ሕገወጥ ተግባራት ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድ ታስቧል፡፡ በአዲሱ ዓመት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መንግሥት ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር ተከትሎ የተበላሸውን አስተካክሎ፣ የጎበጠውን አቃንቶ ሲንቀሳቀስ ማየት እንሻለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት