Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በውጭ ምንዛሪ ብድር መፍቀድ ጥንቃቄ ካልተደረገበት የመንግሥት ዕዳ ነው የሚሆነው›› አቶ አስፋው ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትና የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ አምስት የተለያዩ መመርያዎችን አውጥቷል፡፡ ከእነዚህ መመርያዎች አንዱ የአገሪቱ ባንኮች ከውጭ ባንኮችና ከሌሎች አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ ተበድረው ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲያበድሩ የሚፈቅደው ነው፡፡ መመርያውና አጠቃላይ አሠራሩ እንግዳ ከመሆኑ አንፃር የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩበት ነው፡፡ በዚህና በቅርቡ በወጡት ሌሎች መመርያዎች ላይ ዳዊት ታዬ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትና ከዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ መመርያዎችን አውጥቷል፡፡ እነዚህ መመርያዎች በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ምንድነው? ምን ዓይነት አንድምታስ አላቸው?

አቶ አስፋው፡- አንዱ የሚታየኝ ነገር በፋይናንሻል ትራንስፎርሜሽን ሒደቱ ላይ ብሔራዊ ባንክ ጠንከር ብሎ እየሠራ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ መመርያዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ቀደም ብሎ የባንኮች ማኅበርም ሆነ ባንኮች በተለያዩ ጊዜያት ያነሱዋቸው የነበሩ ጥያቄዎች ስለነበሩ፣ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥም ነው ማለት ይቻላል፡፡ በቅርቡ ከወጡት መመርያዎች ውስጥ አንዱ የአገሪቱ ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ መበደር የሚችሉ መሆኑን የሚፈቅደው ነው፡፡ ከባንክ ውጭ መያዝ ያለበትን የገንዘብ መጠን የሚገድበው መመርያ በቅርቡ ከወጡት ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሌሎች ኢዱስትሪውን ይጠቅማሉ የተባሉ መመርያዎችም ወጥተዋል፡፡ በጥቅሉ እነዚህ መመርያዎች ያላቸው አንድምታ የባንክ ኢንዱስትሪው እየተለዋወጠ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ሌላው ደግሞ ከቀድሞ በተለይ ብሔራዊ ባንክ እየሠራ መሆኑንም ያመላክታል፡፡ ይህ እንግዲህ ገና ጅምር ሊሆን ይችላልና ዘርፉ ላይ የሚደረጉ ለውጦች የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም የሚያስገነዝቡ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዘርፉ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድነው? ዘርፉን ከመክፈት አኳያ መሟላት አለባቸው የሚባሉትን የማሟላት ሒደት መኖሩንም ያስመለክተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ በተለይ በቅርብ በወጡ መመርያዎች ላይ ማኅበራችሁ መመርያዎቹ ከመውጣቱ በፊት ምን ያህል ተሳትፎ አድርጋችኋል? መመርያዎቹ ከመውጣታቸው በፊት እናንተ እንደ አንድ ባለድርሻ ሐሳባችሁን አቅርባችኋል?

አቶ አስፋው፡- በአንዳንዶቹ ላይ ሐሳባችንን ሰጥተንባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ግን የመጨረሻው ሰዓት ላይ ያየናቸው ናቸው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ያደረገበት የራሱ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ወደ መጨረሻው አካባቢ እንድናውቃቸው የተደረጉ መመርያዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንኮች ውጭ መያዝ እንደማይቻል የሚደነግገው መመርያ ረቂቁ ቀርቦ አላየነውም፡፡ ከውጭ አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ መበደር የሚቻል መሆኑን የሚያመለክተው መመርያ ላይ ግን አስተያየት እንድንሰጥበት ረቂቁ ቀድሞ ተልኮልን አስተያየታችንን ሰጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሰጣችሁት አስተያየት ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል ትላላችሁ?

አቶ አስፋው፡- ብሔራዊ ባንክ የሚቀበለውን ይቀበላል፡፡ የማይቀበለውንም እንደዚያው የሚያደርግበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚወጡ መመርያዎች ላይ ሙሉ ለሙሉ ያለ መቀበል ሁኔታዎች እንዳሉ እናስተውላለን፡፡ በእርግጥ የውጭ ምንዛሪ ብድር ላይ አንዳንድ ካነሳናቸው ነገሮች የተቀበሉዋቸው አሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ያልተቀበሉት ይመስላል፡፡ በሌሎችም እንዲሁ፡፡ ከባንክ ውጪ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማስቀመጥ የማይቻል መሆኑን የሚደነግገው መመርያ እንደሚወጣ አላወቅንም፡፡ በእርግጥ ይህንን መመርያ ስንመለከተው እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ድረስ ለምን ተፈቀደ? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ መመርያ ቀደም ብሎ ከባንክ በቀን ማውጣት የሚቻለው 200 ሺሕ እና 300 ሺሕ ብር ነው ተብሎ ተወስኖ ሲያበቃ፣ እንደገና ደግሞ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ ውጭ መያዝ አይቻልም የሚለው አይጣጣምም ከሚል ነው፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ክፍያ የመፈጸም ሁኔታዎች ሊያስገድዱ እንደሚችሉ ይገባኛል፡፡ ገንዘብ ከዚያ በላይ መያዝ እንዳለባቸውም ትረዳለህ፡፡ ይሁን እንጂ ከባንክ ውጪ መያዝ የሚቻለው እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ነው የሚለው መመርያ ውስጥ የተቀመጠው የገንዘብ መጠን በዝቷል እንላለን፡፡

ሪፖርተር፡- 1.5 ሚሊዮን ብር በዝቷል የምትሉት ለምንድነው? ይህ መሆኑ ተፅዕኖው ምንድነው?

አቶ አስፋው፡- ያለው ገንዘብ በሙሉ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ወደ ሲስተሙ ነው ገንዘቡ መዞር ያለበት ብለን እናምናለን፡፡ እንዲህ የምንለው ቤት ውስጥ እንዳይከማች ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ከሲስተም የሚወጣ ገንዘብ ካለ የማከማቸት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የተከማቸ ገንዘብ ደግሞ ሲስተሙ ውስጥ የለም ማለት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ይህ እንዳይሆንና ውጪ ያለ ገንዘብ ለተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ሊውል ስለሚችል፣ የገንዘብ መጠኑ መቀነስ ነበረበት የሚል እምነት አለን፡፡ ይህም መመርያው የወጣበትን ዓላማ እንዳይስት በማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከወጡ መመርያዎች ውስጥ ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ ተበድረው የውጭ ምንዛሪ ለሚሹ ተበዳሪዎቻቸው እንዲያቀርቡ የሚፈቅደው መመርያ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ነው፡፡ በዚህ መመርያ ላይ ምልከታዎ ምንድነው? የመመርያው መውጣት ምን ያስገኛል?

አቶ አስፋው፡- ፖሊሲ የሚያወጡ አካላት የሚመለከቷቸው አንዳንድ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ እውነት ለመናገር ጥንቃቄ ካልተደረገበት ዝም ብሎ በውጭ ምንዛሪ ብድር የመፍቀድ ሒደት የሚያስከትላቸው አሉታዊ ተፅዕኖዎች ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም ጥንቃቄ ያልተሞላበት ከሆነ የመንግሥት ዕዳ ነው የሚሆነው፡፡ የመንግሥት ዕዳ በሚሆንበት ጊዜ በአገር ገጽታ ላይ የሚያመጣው ነገር ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ አገር መክፈል አልተቻለም መባል ለአገር ኢኮኖሚም ለሚመጡ ኢንቨስተሮችም የሚያስተላልፈው አሉታዊ መልዕክት አለው፡፡ ስለዚህ ይህ ያስፈለገው ለምንድነው የሚለውን በጥናት ላይ ተመርኩዞ እንዲተገበር ማድረጉ የሚደገፍ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን አገሪቱም እኛም ካለብን የውጭ ምንዛሪ ጫናና ውጥረት አኳያ በሚታይበት ጊዜ ግን ወጣ ብለን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ለዚህ መፍትሔ ለመፈለግ ወጣ ብለው ማሰብ መጀመሩና እንዲህ ያሉ መመርያዎችን ለመተግበር መነሳሳቱ ጥሩ ነው፡፡ ይህም ከውጭ ምንዛሪ አንፃር  ያለንበትን ጫና በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህንን መመርያ መተግበር ግን ከባድ ነው የሚሉ አስተያቶች ይሰማሉ፡፡ በአገር ደረጃ ጫና ሊያመጣ እንደሚችል፣ በውጭ ምንዛሪ ተበድሮ መልሶ መክፈሉ ከባድ ስለሚሆንና ካልተከፈለ ደግሞ ዞሮ ዞሮ የአገር ዕዳ ስለሚሆን መዘዙ ብዙ ነው የሚሉ አስተያየቶችም ይደመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ ያለው አሠራር የአገሪቱን ባንኮች አቅም ጥያቄ ውስጥ ይከታል ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ በእርግጥ አቅምስ አላቸው?

አቶ አስፋው፡- መመርያውን እንደተመለከትኩት ትልቁ የቤት ሥራ ያለው አበዳሪዎች ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ማንም የሚፈልገውን ያህል ብድር ስለጠየቀ ብቻ እነሱም የሚሰጡ ከሆነ፣ የእነሱ ብድር ተመላሽ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ችግር አለበት፡፡ እንደ አቅም ስመለከተው በጥንቃቄ ከተሠራ ባንኮቹ ይህንን ብድር ሳመጣ ምን ወጪ ያስወጣኛል? ክፍያው ከምንድነው የሚሆነው? ያንን ላደርግ እችላለሁ ወይ? የሚለውን ነገር አስበው መግባት ግን የግድ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በሁለቱም ወገን አበዳሪውም ተበዳሪውም ሊሳሳት ይችላል፡፡ ስለዚህ እዚያ ላይ ትክክለኛ ሥራ መሠራት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ አበዳሪዎቹም በተለይ የውጭ ባንኮች የሚሠሩትና የሚሄዱበት ሒደት ቀላል ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ አበዳሪዎች ከዚህ በፊት የእያንዳንዱን ባንክ ታሪክ ያውቃሉ፡፡ ምን አቅም አለው? ቢበደር ምን ሊከፍል ይችላል የሚለውን ነገር ያዩታል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ አማራጩ ስለተከፈተ ብቻ ገንዘቡ ይፈሳል ብዬ አላስብም፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት አበዳሪዎቹ ባንኮች ብቻ አይደሉም፡፡ ከባንኮች በተጨማሪ ገንዘብ የማበደር ኃላፊነት ያላቸው ኢኪውቲ ኢንቨስተሮችም አሉ፡፡ በኢኪውቲ የሚመጡ ገንዘቦችን የሚያስተዳድሩ የተለያዩ ተቋማት አሉ፡፡

ስለዚህ በውጭ ተጨማሪ ገንዘብ እንዳለ ይገባናል፡፡ ይህንን ገንዘብ የት እናድርገው ብለው የሚጨነቁበት ሁኔታ ይኖራልና የማበደር ፍላጎቱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ እኛ እንደ ባንክ ደግሞ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማሰብ አለብን፡፡ መመርያው ለሁለት ነገር የተቀመጠ ነው፡፡ አንዱ ባንኮች ተበድረው የውጭ ምንዛሪ ለሚያመነጩ ብድር ማቅረብ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ ተበድረን በራሳችን አካውንት ላይ ወይም ደግሞ በብሔራዊ ባንክ የማስቀመጡን ሁኔታ ይፈቅዳል፡፡ ይኼ ደግሞ እያንዳንዱ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ሀብት መያዙ ብዙ የሚያስተካክላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን አስቦ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ተበዳሪው ተበድሮ የውጭ ምንዛሪ ሰጥቶን ብድሩን ለመመለስ የሚቸገር ከሆነ፣ ሌላው አማራጭ ሀብት መያዝ ነው፡፡ በእሱም ቢሆን ግን ነገ ብደሩን ልከፍልበት የምችልበት አማራጭ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ የግድ ነው፡፡ መመርያው ደግሞ ከውጭ አደባሪዎች ጋር የምንዋዋለው ዋነኛው ውል ለክፍያ የዕፎታ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን ያስገድዳል፡፡ የሦስት ዓመታት የዕፎይታ ጊዜ መሰጠት አለበት ብሎ ይደነግጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በጠቀሱልኝ የመመርያው ክፍል ላይ የተቀመጠው የዕፎይታ ጊዜ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እንደ እናንተ ላሉ ባንኮች አንድ የውጭ ባንክ ብድር ሲሰጥ መልሰን የምንከፍልህ ከሦስት ዓመታት በኋላ ነው ቢባል እንዴት እሺ ሊል ይችላል?

አቶ አስፋው፡- ልክ ነው፡፡ አንድ የሚያበድር ሰው ለሦስት ዓመታት የማይከፈለኝ ከሆነ እንዴት ፍላጎት ኖሮት ያበድራል በሚል እንደ ሥጋት የሚነሳ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን እነሱ የሚያመጣውን ገንዘብ ዓይተው አይ ለሦስት ዓመት ዕፎይታ ብሰጥና ወለዱ ቢከፈለኝና ዋናው ቢቆይልኝ ደግሞ ችግር የለውም የሚለውን ነገር ወደ ወጪያቸው ያመጡታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በእርግጥ በመመርያው አጠቃላይ ወጪውም ቢሆን ተወስኗል፡፡ ወጪው ከአምስት በመቶ መብለጥ የለበትም ይላል፡፡ በአጠቃላይ  ይህ ነገር ተግዳሮት ሊኖረው እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ አበዳሪውን ለሦስት ዓመታት ልትሰበስብ አትችልም የሚለው መመርያው ከወጣ በኋላ እንዲህ ያሉ ነገሮች ለአበዳሪዎች እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ወይ ብዬ ስመለከት፣ ያን ያህል እንደማይከብዳቸው ፍንጭ እያየሁ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የዚህን መመርያ ውጤት ተከትሎ የብዙዎች ጥያቄ የሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ በብድር የውጭ ምንዛሪ አምጥተው የሚያበድሩት ለየትኞቹ ዘርፎች ነው? በትክክል በዚህ መንገድ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ መውሰድ የሚችሉት እነ ማን ናቸው? በመመርያው ላይ በግልጽ የተቀመጠው በትክክል የሚገልጸው ነገር ምንድነው?

አቶ አስፋው፡- ይህ ግልጽ ነው፡፡ መመርያው የውጭ ምንዛሪ ሊያመነጩ የሚችሉ ተቋማት ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ እነዚህ እነ ማን ናቸው ካልክ፣ በአገር ውስጥ የተመረተን ምርት ወደ ውጭ ልከው የውጭ ምንዛሪ ሊያመጡ የሚችሉ  ናቸው፡፡ ይህ በምርትም ሊሆን ይችላል፡፡ በአገልግሎትም ሊሆን ይችላል፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከአገልግሎት ዘርፍ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ለምሳሌ የቱሪዝም ዘርፍ ሊጠቀስ ይችላልና እንዲህ ያሉ የአገልግሎት ዘርፎችንም ሊያጠቃልል ይችላል ማለት ነው?

አቶ አስፋው፡- አዎ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ዋናው ዓላማ ዛሬ በውጭ ምንዛሪ የሚበደረውን ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ መክፈል አለበት፡፡ አለበለዚያ ክፍያው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ድርጅቶች ደግሞ የውጭ ምንዛሪውን ያመጣሉ፡፡ በወረፋም ቢሆን ብዙ ባንኮች የሚመርጧቸው ስለሆነ ብዙም ችግር የለም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከዚህ መመርያ መውጣት ጋር ተያይዞ ሌላው ሊነሳ የሚገባው ተብሎ የሚጠቀሰው በመንግሥት ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲመራ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ሌሎች አብረው ሊታዩ የሚችሉ ነገሮች የሉም?

አቶ አስፋው፡- የውጭ ምንዛሪን እኔም ብወስነው ጥሩ ነው፡፡ ገበያ የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ገበያው የሚወስነው ከሆነ ዛሬ በጥቁር ገበያና በሕጋዊ ምንዛሪ የምንመለከታቸውን ዓይነት ልዩነቶች አይታዩም፡፡ ነገር ግን ከይፋዊው መግለጫው እንደ ሰማሁት ወደ ገበያ መሩ አሠራር ከሦስት ዓመታት በኋላ ሊገባ ይችላል ተብሏል፡፡ ነገሩን አሁን ላይ ሆነህ ብርን ከዶላር ጋር ስታስተያየውና የብርን የመግዛት አቅም ስታነፃፅር ብራችን አቅሙ እያነሰ ነው የሄደው፡፡ ስለዚህ ወደ ገበያ መሩ አሠራር እንዲሄድ የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ያለን ነው የሚመስለው፡፡ እንዲህ ዓይነት በተለይ የውጭ ምንዛሪን በገበያ መወሰንና ማስተዳደር ግን ቀላል የፖሊሲ ውሳኔ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮች ከውጭ ባንኮች ተበድረው የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ ለሚችሉ ተበዳሪዎች በመስጠት፣ ብደሩን በውጭ ምንዛሪ እንዲመለሱ የማድረጉ ሥራ በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ሥራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክንም ሊፈትን ይችላል፡፡ በጥንቃቄ ካልተሠራበት በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል፡፡ እንዲህ ያሉ ሥጋቶችን ለመቀነስ መመርያው ላይ የተቀመጠው ነገር አለ?

አቶ አስፋው፡- መመርያው ያስቀመጣቸው ነገሮቸ አሉ፡፡ በተለይ በውጭ ምንዛሪ የሚያበድር ተቋም የሚኖር ከሆነ ይህ ተቋም ምን ዓይነት መሥፈርቶችን ማሟላት አለበት? የሚለውን ነገር በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ ብድሩን ዝም ብለህ መስጠት እንደማይቻል፣ ራሳቸው አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው፣ ልክ ለአገር ውስጥ እንደምናበድረው የእነሱም ብድር ከ70 በመቶ መብለጥ እንደሌለበትና እንደዚህ የመሳሰሉ ያስቀመጣቸው ነገሮች አሉ፡፡ በባንኮችም ዘንድ ደግሞ ይህንን ነገር ስናደርግ መከፈት ያለባቸው የመጠባበቂያ አካውንቶች እንዳሉ፣ በመጠባበቂያ አካውንት ውስጥ የተወሰነ ፐርሰንት እንደምናስቀምጥ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተካተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ተበዳሪዎቹ ከሚበደሩት ገንዘብ በስድስት ወራት የሚከፈለው ገንዘብ ተሰልቶ አስቀድሞ ማስቀመጥ እንደሚገባ በመመርያው ተቀምጧል፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የጠየቀ ተበዳሪ ቀድሞ የስድስት ወራት ክፍያን ቀድመህ ማስቀመጥ አለበት የሚለው ነገር አይከብድም?

አቶ አስፋው፡- አዎ ከባድ ይመስለኛል፡፡ የስድስት ወራት ክፍያውን ቀድመህ ማስቀመጥ አለብህ የሚለው ጋሬጣ እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡ ካልሆነ ግን እንዲህ ያሉ ነገሮችን የማጥበቅ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ሌላው ግን እያንዳንዱን ብድር ከተበደርን በኋላ የምንፈራረመውን ኮንትራት በተመለከተ ለብሔራዊ ባንክ እናሳውቃለን፡፡ ብሔራዊ ባንክ ግን የሚሠራው አለ፡፡ ስለምናበድረው ገንዘብ ሪፖርት ማድረግም አለብን፡፡ የማበድረው ባንክ ምን ማሟላት አለበት የሚለውም በመመርያው ውስጥ ተካቷል፡፡ እኛ ‹‹ኦፕን ፖዚሽን›› የምንለው ነገር አለ፡፡ ያለን የውጭ ምንዛሪ ሀብት ካለን አፈጻጸም አኳያ ታይቶ ከካፒታላችን ጋር ተሰልቶ የሚመጣ ምጣኔ አለ፡፡ የሚበደሩ ባንኮች ይህንን ሁሉ ማሟላት እንዳለባቸው መመርያው ያሳየናል፡፡ ሪፖርቱን በሙሉ ከተቀበሉ በኋላ ወደ አደጋ የሚያመጣ ነገር አለው የሚሉ ከሆነ ተከታታይ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ከውጭ ብድር እንድታገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መጨረሻ ላይ ይፈቅዳል ማለት ነው?

አቶ አስፋው፡- አይደለም፡፡ እኛ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማስመዝገብ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ኮንትራቱንና ሒደቱን በሙሉ ለብሔራዊ ባንክ እናቀርባለን፡፡ እነሱ በቀረበው መረጃ መሠረት በራሳቸው መንገድ የሚሠሩት ነገር ሊኖር ይችላል እንጂ፣ ፈቃዱን የሚያመለክት ነገር መመርያው ላይ የለም፡፡  

ሪፖርተር፡- በውጭ ምንዛሪ የተገኘን ብድር መክፈል የማይቻል ከሆነ ምን ይደረጋል? በመመርያው ውስጥ ይህንን የሚያመላክት ነገር አለ?

አቶ አስፋው፡- እሱ የለም፡፡ እሱ ላይ ነው እንግዲህ አሁን እያንዳንዳችን ተጠንቅቀን መሥራት ያለብን፡፡ የማይከፈል ብድር መሆን የለበትም ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን አደጋው የሚመጣው ያኔ ነው፡፡ ምክንያቱም ይኼ ከውጭ አካላት ጋር የሚያገናኝ ስለሆነ አለመክፈል ማለት ከዚህ በኋላ የአገር ዕዳ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ ጊዜ ብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ዕርምጃ ምንድነው የሚለው ነገር በኋላ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን በቅርበት ይከታተሉታል ብለን እናስባለን፡፡ ከዚህ መመርያ ውጪ መንቀሳቀስ ሊያስከትል የሚችለው ቅጣት ተቀምጧል፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                                              ሪፖርተር፡- ቅጣቱ ምንድነው?

አቶ አስፋው፡- ይህንን ገንዘብ ተበድረህ አምጥተህ ላልተገባ ዓላማ መዋል ያስቀጣል፡፡ ከዚህ ብድር ጋር ተያይዞ የሚደረግ ሪፖርት ወደፊት ካለና ከዚህ ጋር የተያዙ ጉዳዮች ላይ ስህተት ከተገኘ፣ በገንዘብ የሚያስቀመጥ መሆኑን መመርያው አስቀምጧል፡፡ ሌላው መሠረታዊ የሚባለውና በመመርያው የተካተተው ለእያንዳንዱ ባንክ ቦርድ ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ለቦርድ የተሰጠው ኃላፊነት ምን ድረስ ነው? ቦርዶችስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

አቶ አስፋው፡- ይህ ለቦርዶች የተሰጠው ኃላፊነት ወደዚህ እንቅስቃሴ ከመገባቱ በፊት፣ እያንዳንዱ ባንክ ይህንን የውጭ ምንዛሪ የብድር ሁኔታ እንዴት ማስተዳደር እንዳለበት ወይም ማድረግ እንዳለበት ባንኮቹ ፖሊሲ ያወጣሉ፡፡ እያንዳንዱ ቦርድ ያንን ፖሊሲ ማፅደቅ ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ አሠራሩንና ሊኖሩ የሚችሉ አደጋዎችን በትክክል ተለይተው መውጣታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ኃላፊነት ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ባንኮች ወደ ብድር ከመግባታቸው በፊት እንዲህ ያሉ ፖሊሲዎችን ማውጣትና ማፀደቅ አለባቸው፡፡ ይህም ራሱን የቻለ መጠበባቂያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- በጥቅል ይህንን መመርያ እንዴት ይመዝኑታል?

አቶ አስፋው፡- እውነት ለመናገር አዎንታዊ መሆኑን ነው ያየሁት፡፡ ምክንያቱም አሁን እየተመለከትኩት ያለሁት ብሔራዊ ባንክ ወጣ ብሎ እያሰበ መሆኑን ነው፡፡ ሊያስፈልጉ የሚችሉ ለውጦችን እየተቀበለና ድሮ በፍፁም ተብለው የተዘጉ ነገሮችን እየፈተሸ እየከፈተ ነው ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ይህንን ዘርፍ እንንከፍታለን በሚባልበት ሁኔታ እንደ እኔ እምነት ነገሮችን መሞከር አለብን፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ ፈርተን የምንዘልቀው ነገር አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት የለውጥ ሒደት ላይ እንቅፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አሁን በጥንቃቄ እያንዳንዱን እየተመለከቱ የመሄድ ነገር ነው መሆን ያለበት፡፡ ስለዚህ አሁን አፈጻጸሙን በተመለከተ ሊያስከትሉ የሚችሉ አደጋዎችን ሁላችንም እንደ አንድ ሆነን መሥራት አለብን፡፡ እንደ ፋይናንስ ሴክተር የራሳችንን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የሚደረጉ ሒደቶች አይደሉም መሆን ያለባቸው፡፡ ለትርፍ ነው የምንሠራው፡፡ ለባለ አክሲዮኖች ገንዘብ ለማምጣት ነው የምንሠራው፡፡ ለደንበኞቻችን ደግሞ አገልግሎት ለመስጠት ነው የምንሠራው፡፡ ግን በጣም ጥንቃቄ ባለው መንገድ መሥራት ይኖርብናል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ደግሞ በቅርብ ቁጥጥር ሁኔታዎችንና ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎች በዚህ ሁኔታ አሉ ወይ የሚለውን ነገር ደግሞ እያየ ከጅምሩ ነው ማስተካከል ያለበት እንጂ፣ ዝም ብሎ ተለቆ ይህ ችግር መጣ የሚለው ነገር አስፈላጊ አይደለም፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ኃላፊነት እንደሚሰማው ወይም ደግሞ ለኢኮኖሚው በጣም ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ዘርፉ ውስጥ እንዳሉ ተዋንያን እያንዳንዱ ባንክ ኃላፊነት የሚሰማው እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከዚህ አጀንዳ ውጪ አጠቃላይ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ እንዴት ይገመግሙታል? የውጭ ባንኮች ሊገቡ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ አሁንም አለ፡፡ የእነሱ መግባት የአገር ውስጥ ባንኮችን ይጎዳል ወይስ አይጎዳም የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምልክታ ምንድነው?

አቶ አስፋው፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የባንክ ዘርፍ የምመለከተው በሁለት ገጽታ ነው፡፡ አንዱ በውስጥ ያለ ለውጥ አለ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከውጭ የሚመጣ ለውጥ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ውስጣዊ ለውጡ ምንድነው?

አቶ አስፋው፡- ቁጥራቸው በዛ ያለ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪ እየተቀላቀሉው ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ባንኮች አንዳንዶቹ አዲስ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ግን ማክሮ ፋይናንስ የነበሩ ወደ ባንክ የሚቀየሩ አሉ፡፡ በሌላው ባህሪ ስታየው ደግሞ ‹‹ኮንቬንሽናል›› የባንክ ሥራ የሚሠሩ አሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት የሚሰጡ አሉ፡፡ ስለዚህ ወደድንም ጠላንም እዚህ ዘርፍ ውስጥ ያለው ለውጡ አሁን በጣም እየተለወጠ ነው የሚመጣው፡፡ አንዳንድ ባንኮች ደግሞ በከፍተኛ ካፒታል ወደ ገበያው የመቀላቀል ሁኔታ እያሳዩ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ውስጥ ያለው የውድድር መንፈስና የውድድር አቅጣጫ በደንብ አድርጎ የሚጦዝበት ሁኔታ ነው የሚኖረው ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም የሚመጡ ባንኮች ሥራ ላይ ያሉት ባንኮች የሚሠሩትን ለመሥራት ብቻ የሚመጡ ከሆነ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የተለየ ነገር ይዘው መጥተው ገበያውን መቀላቀል አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ደንበኛ የመቀማት ብቻ ዓይነት ወይም ሠራተኛን የመቀማት ዓይነት ነገር የምናመጣ ከሆነ ጥንካሬው ያን ያህል አይታየኝም፡፡ ከውጭ የሚመጡ ባንኮችን ለመቋቋምም ሆነ ያልታዩ አዳዲስ አሠራሮችን ይዘው መምጣት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ በከፍተኛ ካፒታል የሚገቡ ባንኮች ይህንን ማስተዋል አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ ባንኮች መግባትና አለመግባባት ጋር ያለዎት ምልከታስ?

አቶ አስፋው፡- መንግሥት ቀን ባይቆርጥም በተለያዩ አጋጣሚዎች ወይም በተለይ ከአይኤምኤፍምና ከዓለም ባንክ ጋር ባለን ግንኙነት መሠረት፣ ኢትዮጵያ ዘርፉን የግድ መክፈት ይኖርባታል ወይም ትከፍታለች ብዬ አስባለሁ፡፡ መቼ የሚለውን ለመናገር የሚያዳግተኝ ቢሆንም ይከፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ባንኮቹ ቢመጡ እንዴት ነው የምንሆነው የሚለውን ነገር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ባንኮች በሁለት መንገደች ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ ባንኮች ረጋ ብለው የሚገቡ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በየአገራቸው ያለው የቁጥጥር ሥርዓት በጣም ከባድ ስለሆነና ለሚፈጠሩ ክፍተቶች የሚቀጡት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ፣ ሁለተኛ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ብዙ ሌሎች ማሟላት ያለባቸው ሕጎች አሉ፡፡ እነዚያ ሕጎች ተጠናክረው መውጣት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርን የሚከላከሉ ዓይነትና ሌሎች ሕጎች ተጠናክረው መውጣታቸውን ይፈልጋሉ፡፡

የውጭ ባንኮች ወደ አንድ አገር ከመግባታቸው በፊት እንዲህ ያሉ ሕጎች ጠንክረው መውጣታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቢገቡ እነሱ ላይ አደጋ ሊኖር ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች ደግሞ በብዙ አገሮች ዓይተናል፡፡ ነገር ግን የአካባቢውን ባንኮች ስመለከት ግን የምንሠራበት ከባቢ በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለይ በኬንያና በደቡብ አፍሪካ ያሉ ባንኮች ኢትዮጵያ ላይ ዓይናቸውን በጣም የጣሉ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ እዚህ መጥተው ገበያውን ይቀላቀላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይኼ ለእኛ ትልቅ ፈተና ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ እኛ ራሳቸንን ዝግጁ አድርገን መገኘት አለብን፡፡ ወይ ደግሞ ከሚመጣው ጋር በጋራ ለመሥራት ተመራጭ ሆኖ መገኘት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይህ የማይቀር ሒደት ይመስለኛል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...