Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትካፍ ያዘጋጀው አዲሱ የሥልጠና መመርያ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ያነሳው ይሆን?

ካፍ ያዘጋጀው አዲሱ የሥልጠና መመርያ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ያነሳው ይሆን?

ቀን:

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአብዛኛው በአፍሪካ አገሮች ሲሰጡ የቆዩ ሥልጠናዎችና መሰል አገልግሎቶች እየተሰጡ የሚገኝበት መንገድ ከይዘት እስከ ጊዜ ምጣኔ ድረስ፣ አፍሪካ ለምትፈልገው የእግር ኳስ ዕድገት የማይመጥን መሆኑን በመጥቀስ በሁሉም አባል አገሮች የሚሰጡ ሥልጠናዎች እንዲቆሙ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ይህን የካፍ ውሳኔ ተከትሎ በኢትዮጵያ ከ‹‹ሲ›› እስከ ‹‹ኤ›› የላይሰንስ ሥልጠና ወስደው እስካሁን ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ማግኘት ያልቻሉ መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሥልጠናውን ማግኘት ያለባቸውና ሥልጠናውን መስጠት የሚገባቸው ሙያተኞች ማንነትና ምንነት አከራካሪ ሆኖ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

አኅጉራዊ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ ከሰሞኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያገባቸዋል የሚባሉ ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት በቪዲዮ ኮንፈረስ ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከሥልጠና ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥያቄዎችና ግልጽ ያልሆኑ አሠራሮች ሊኖሩ እንደማይገባ፣ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጨዋቾች ማኅበርን ጨምሮ ሙያተኞች ችግሮች እንኳ ቢኖሩ፣ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለመሻት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰቢያ መስጠቱ ተነግሯል፡፡

- Advertisement -

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፣ ‹‹ካፍ ይህን መድረክ ሲያመቻች የጋራ የምንግባባባቸው ነጥቦች እንዲኖሩን በማሰብ ነው›› በማለት በተለይም በእግር ኳሱ ዙሪያ የሚገኙ ሙያተኞች ከብሔራዊ ተቋሙ ጋር በጋራ ቢሠሩ እንደሚበጅ በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ማሳሰቢያ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡    

በቪዲዮ ኮንፈረንሱ የተሳተፉት የአፍሪካ እግር ኳስ ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አንቶኒዮ ባፎንና የካፍ ቴክኒክ ዳይሬክተር ራውል ችፔንዳ እንዲሁም በካፍ የሴቶች እግር ኳስ ልማት ማናጄር መስከረም ጎሽሜ ሲጠቀሱ፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ አቶ ሰውነት ቢሻው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ በካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱና የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መሆናቸው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽ የወጣው ዘገባ ያስረዳል፡፡

ካፍ ለአፍሪካ እግር ኳስ መፈጠር ትልቅ ድርሻ የነበራቸው አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ካፈራች አገር ብዙ እንደሚጠብቅ፣ ለዚህ ዋናውና መሠረታዊ ችግር ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁሉም የአፍሪካ አገሮች የሚሰጠው ሥልጠና ኢንስትራክተሮችን ጨምሮ ጥራት ያላቸው አሠልጣኞችን ለማፍራት የማያስችል በመሆኑ፣ የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሁሉም አገሮች የሚሰጡ ሥልጠናዎች እንዲቋረጡ ውሳኔ ላይ መድረሱን የካፍ  ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አንቶኒዮ ባፎን በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ለተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ማስረዳታቸው ታውቋል፡፡

‹‹ጥሩ ሥልጠና እንዲኖር ለማድረግ መጀመርያ መሠራት ያለበት በአሠልጣኞች አሠልጣኝ (ኢንስትራክተር) ላይ ነው፡፡ ጥሩ ኢንስትራክተሮች ሲኖሩ ጥሩና ጥራት ያላቸው አሠልጣኞች ይኖራሉ፣ ጥሩ አሠልጣኞች ሲኖሩ ጥሩና ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን ማግኘት ይቻላል፣ የአሠልጣኞች ጥራት ስለሚያሳስበን አዲስ የሥልጠና ኮንቬንሽን (መመርያ) አዘጋጅተናል፤›› ያሉት ደግሞ የካፍ ቴክኒክ ዳይሬክተር ራውል ችፔንዳ ናቸው፡፡  

ከካፍ ቴክኒክ ዳይሬክተር አስተያየት በመነሳት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ‹‹ቀበሌ መታወቂያ ሲታደል የኖረው›› የአሠልጣኝነት ብቃት ማረጋገጫ ምን ያህል ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ እንደነበር በርካቶችን የሚያስማማ ሆኗል፡፡

በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ቀጣዩ ተናጋሪ የነበሩት የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ የካፍ መሥራች አገር ብትሆንም የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማኅበር ሲኖራት ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ማኅበሩ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በተለይም ከሥልጠናና መሰል አገልግሎቶች ጋር በተገናኘ በርካታ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ተገዷል፣ እኔ እንደ ተጨዋቾች ማኅበር ፕሬዚዳንትነቴ ጥያቄዎች ሲመጡ መልስ መስጠት ስለማልችል ጥያቄዎቹን ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ግዴታ አለብኝ፡፡ ከዚህ ቀደም በርካታ የቀድሞ ተጨዋቾች የካፍ ላይሰንስ ሥልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ አልመጣላቸውም፡፡ በእርግጥ ይህን አሁን ያለው የፌዴሬሽን አመራር ችግር እንዳልሆነ ይሰማኛል፣ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ ነው፡፡ እንዲያውም ከየትኛውም የእግር ኳስ አመራር በተሻለ አሁን ያለው አመራር እኛን ለማናገር በራቸው ክፍት ነው፤›› በማለት ማኅበሩ እየገጠመው ያለውን ተግዳሮት መናገራቸው ታውቋል፡፡

ሥልጠናና መሰል አገልግሎቶችን በሚመለከት መልስ የሰጡት የካፍ ቴክኒክ ዳይሬክተር ራውል ችፔንዳ፣ ‹‹የቀድሞ የካፍ ቴክኒክ ዳይሬክተር ከቦታው ከተነሱ ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ በመሆኑም አሁን የተነሳውና ላይሰንስ ያልወሰዱ ሰዎች ጉዳይ ሲስተሙ የሚያሳየው የአንድ ዙር ሠልጣኞችን ብቻ ነው፡፡ [ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ተደጋጋሚ ሥልጠናዎች ሲሰጡ የነበረ መሆኑ ልብ ይሏል]፡፡ አዲስ የተዘጋጀው የሥልጠና ኮንቬንሽን እግር ኳስ ተጫውተው ያለፉ ተጨዋቾች ‹‹ፋስት ትራክ›› የሚስተናገዱበት አሠራር አለው፡፡ ኢንስትራክተሮችን በተመለከተ 56 ያህል ኢንስትራክተሮች ከተለይዩ አገሮች ተሰባስበው እንዲሠለጥኑ ተደርጎ ካለፉት 21 ኢንስትራክተሮች አንዱ ኢትዮጵያዊው አብርሃም መብርሃቱ አንዱ ነው፡፡ አብርሃም ከአፍሪካም አልፎ በፊፋ ደረጃ (High Performance) ኢንስትራክተሮች አባልም መሆን ችሏል›› በማለት ለቪዲዮ ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡

በኢንስትራክተር ደረጃ ኢትዮጵያ ያሏት ኢንስትራክተሮች በቂ እንዳልሆኑ ያከሉት ራውል ችፔንዳ፣ ቁጥራቸውን ከዚህ በላይ መጨመር እንደሚገባ ማስረዳታቸው ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተለይም ከአሠልጣኞች አሠልጣኝ  ጋር በተገናኘ ከሚነሳው ችግር አንዱ የሙያተኞቹ የብቃት ማረጋገጫ የአገልግሎት ጊዜ ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ ራውል ችፔንዳ ‹‹በማንኛውም አባል አገሮች የኢንስትራክተሮች ማሻሻያ ሥልጠና አለመሰጠቱና ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ችግር ብቻ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤›› ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡

ካፍ ቀደም ሲል አዲስ የሥልጠና ኮንቬንሽን ማዘጋጀቱን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ በኮንቬንሽኑ ተጠቃሚ የምትሆንበት አሠራር መመቻቸቱ ሲነገር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ካፍ ባመቻቸው በዚሁ ቪዲዮ ኮንፈረንስ፣ ‹‹አዲሱ የሥልጠና ኮንቬንሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ በየትኛውም የካፍ አባል አገሮች ላይ ተግባራዊ አልተደረገም፣ ከዚህ ቀደም ሞሮኮ ላይ እንደ ‹‹ፓይለት›› ፕሮጀክት የፕሮፌሽናል ላይሰንስ ሥልጠና ከመሰጠቱ ባሻገር በሌሎች አገሮች አልተጀመረም፤›› በማለት ኮንቬንሽኑን ተግባራዊ የሚያደርጉ አገሮች የተቀመጡ መሥፈርቶች ማሟላት ግድ እንደሚል የካፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አንቶኒዮ ባፎን ከኮንቬንሽኑ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ብዥታ በዚህ መልኩ ማጥራት እንደሚገባ አሳስበዋል ተብሏል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉዳዩ መጥራት እንዳለበት ጥያቄ ከሚያነሱ ማኅበራት መካከል የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ የካፍ ምክትል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንቶኒዮ ባፎን ለዚህ ጉዳይ የሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በጋና እግር ኳስ ውስጥ አሁን በኢትዮጵያ የሚደመጠው ዓይነት ችግር ነበር፣ ችግሩ የተወገደው የጋና ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ ነው፡፡ ማኅበሩ እንዲቋቋም ያደረግኩት እኔ ነኝ ፡፡ እናንተንም ለማገዝ ዝግጁ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፤›› ብለው ካብራሩ በኋላ እንደ ማኅበር ጥያቄ ሲኖረው ጥያቄውን ማቅረብ የሚገባው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሆን እንዳለበት ጭምር መናገራቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...