በተመስገን ተጋፋው
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ዕውን ለማድረግ በአዲስ አበባ የልደታ ክፍለ ከተማ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ከ71.7 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድና በስጦታ ማሰባሰቡንና 35.2 ሚሊዮን ብር ቃል ማስገባቱን አስታውቋል፡፡ አስተዳደሩ ለአንድ ወር ከርሱ ጋር የቆየውን የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለአራዳ ክፍለ ከተማ ሲያስረክብ እንደገለጸው፣ ባጠቃላይ 106,985,235 ብር በቦንድ ግዥ፣ በስጦታና ቃል በማስገባት ከዕቅዱ በላይ አጠናቋል፡፡ በርክክቡ ወቅት የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር ዓባይ እንደገለጹት፣ በክረምቱ በተደረገው የመጀመርያ ዙር የግድቡ የውኃ ሙሌት መጠናቀቁና የዲፕሎማሲያዊ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ መደረጉ ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ያደርገዋል፡፡ ፎቶው የልደታ ክፍለ ከተማ የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለባለተራው ለአራዳ ክፍለ ከተማ ሲያስረክብ ያሳያል፡፡