Saturday, June 10, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ ጨዋታ

በፍቅሩ ኪዳኔ (ፓሪስ፣ ፈረንሣይ)

የዛሬ 60 ዓመት ለእንቁጣጣሽ አጥቢያ በሮም ኦሊምፒክ ጨዋታ ፕሮግራም መሠረት የማራቶን ሩጫ የተካሄደበት፡፡ እ.ኤ.አ.1960 ዕለቱ ቅዳሜ ሴፕቴምበር 10 [ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም.] ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሁለት ሯጮች አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራን አሠልፋለች፡፡ የሯጮቹ አሠልጣኝ ስዊድናዊ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን ናቸው፡፡ አዲዳስ ጫማ ተገዝቶ ለሁሉም አትሌቶች ታድሏል፡፡ አበበ ቢቂላ የተሰጠውን ጫማ ሞክሮ ስላልተስማማው በባዶ እግር ለመሮጥ ወሰነ፡፡ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን ክብር ዘበኛ ሚሊተሪ አካዴሚ አስተማሪ ስለነበሩ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በባዶ እግሩ የሚኳትን መሆኑን ስለሚያውቁ አልተገረሙ፡፡ የሮም ከተማ ሙቀት ሯጮቹን እንዳይጎዳ ተብሎ ሩጫው የተጀመረው ከቀትር በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት ተኩል ፒያሳ ዲ ካምፒኮሊም በተባለ ሥፍራ ላይ ነው፡፡ ውድድሩን ያሸንፋል ተብሎ የሚጠበቀው አንድ የመስኮብ ሯጭ ነው፡፡ አፍሪካውያን መኖራቸውን የሚያስታውስ የለም፡፡ ሩጫው ተጀምሮ 20 ኪሎ ሜትር ላይ ሲደርሱ ነው ሁለቱ አፍሪካውያን ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላና የሞሮኮም ተወላጅ ራዲ አብደልሰላም ብቅ ያሉትና ፊታቸውን ያሳዩት፡፡

የሚገርመው ደግሞ ኢትዮጵያዊው የሚሮጠው ባዶ እግሩን ነው፡፡ ፈረንጆቹ አፍሪካ በተለይ ኢትዮጵያ ደሃ ስለሆነች ሕዝቦቿ ጫማ የላቸውም በማለት አምነዋል፡፡ ሁለቱ አፍሪካውያን ጎን ለጎን በመሮጥ የሮማን ጎዳና በጨለማ ተያይዘውታል፡፡ ግራና ቀኝ ችቦ ነው የሚበራው፡፡ ፒያሳ ዲ ፓርታ ካፔና ሲደርሱ አበበ ቢቂላ የአክሱምን ሐውልት ሲያይ ብልጭ አለበት መሰለኝ ሞሮኮውን ጥሎት ገሠገሠ፡፡ ሙሶሊኒም ትዝ ብሎት ይሆናል፡፡ ለማንኛውም የማራቶን ሩጫ ርዝመት 42 ኪሎ ሜትር 195 ሜትር በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ 16.2 ሰከንድ በመፈጸም አዲስ የኦሊምፒክና የዓለም ሪከርድ በማስመዝገብ የመጀመርያው አፍሪካዊ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን በመሆን አገሩንና አህጉሩን ታላቅ ክብር አስጎናፀፈ [ሌላው ኢትዮጵያዊ በባዶ እግሩ የሮጠው አበበ ዋቅጅራ በሰባተኛነት ውድድሩን ፈጽሟል]፡፡ አበበ ቢቂላ ባሸነፈ ማግሥት እንቁጣጣሽ ስለነበር የኢትዮጵያውያን ደስታ ለመገመት አያስቸግርም፡፡ አበበ ወታደር እንደመሆኑ መጠን አዲስ አበባ ሲደርስ ያቀባበሉን ሥነ ሥርዓት ያዘጋጀለት የክብር ዘበኛ ጠቅላይ መምሪያ ነው፡፡ በቀጥታም የሄደው ቤተ መንግሥት ጃንሆይን እጅ ለመንሳት ነው፡፡ እሳቸውም የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ሜዳሊያና የአሥር አለቃ ሹመት ሰጡት፡፡ አበበ ለመጨረሻ ጊዜ በባዶ እግሩ የሮጠው እ.ኤ.አ. በ1961 በአቴንስ ግሪክ አገር ነው፡፡

አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ ጨዋታ

 

ከሦስት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1964 በቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ለመካፈል ሲዘጋጅ ነው ሮም ላይ በባዶ እግሩ መሮጡን ያስታወሱት ጃፓኖች ጫማ እንስፋልህ ብለው ሐሳብ ያቀረቡት፡፡ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ጫማ እያሰፋ የሚያጌጥበት ጊዜ ስለነበር የጃፓኑ ወጪውን የሚችል የለም የሚል መልስ ተሰጠ፡፡ ሐሳቡን ያቀረበው ጃፓን ለአበበ በነፃ ነው ሰፍቼ የምሸልመው በማለት ስላረጋገጠ እግሩን ተለክቶ ተሰፍቶ መጣለት፡፡ ለማንኛውም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስፈላጊውን ትጥቅ ለሁሉም አድለዋል፡፡ የአበበ ቢቂላን ጫማ ሰፍተው ያመጡት አዛውንት የአሲክ ኩባንያ ባልደረባ ነበሩ፡፡ አበበ በዚያ ጫማ ሮጦ ነው በ2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ነጥብ 11 ሰከንድ ውድድሩን ጨርሶና አዲስ የዓለም ሪከርድ አስመዝግቦ እንደ ልማዱ ጅምናስቲክ እየሠራ ሌሎቹ ሯጮች ቶኪዮ ስታዲየም ውስጥ እስኪገቡ ይጠብቅ የነበረው፡፡ ሁለተኛ የወጣው እንግሊዙ ባዚል ሒትሌይ ሲሆን፣ ሦስተኛው ኮኪሽ ሱቡራያ ከጃፓን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከአበበ ጋር ያሠለፈቻቸው ሁለት ሯጮች ደምሴ ወልዴ 10ኛ ቢወጣ ማሞ ወልዴ ግን በ15ተኛው ኪሎ ሜትር አቋርጦ ወጥቶአል፡፡

ከቶኪዮ መልስ ጃንሆይ ለአበበ ቢቂላ የመቶ አለቃ ማዕረግ ሸለሙት፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1968 ለሜክሲኮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ሲዘጋጅ ስለታመመ ጀርመን አገር ሄዶ የአፓንዲሲት ኦፕራሲዮን [የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና] አደረገ፡፡ ሆስፒታሉ ወጪውን የሚከፍለው የጀርመን መንግሥት ነው የሚከፍለው በማለት አስታወቀው፡፡ ከዚህ በቀር እግሩን ትንሽ ያመው ስለነበር ሜክሲኮ ሲደርሱ ልዩ ልዩ ሐኪሞች መርምረውት እንዲያርፍ መከሩት፡፡ እንዲያውም ልምምድ እንዲያደርግ ዝም ብሎ በሩጫው ቀን ብቻ እንዲካፈል የሚል አስተያየትም ተሰንዝሮም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሜክሲኮ ላይ ከአበበ ቢቂላ ሌላ ማሞ ወልዴንና  መርዓዊ ገብሩን አስመዝግባ ነበር፡፡ አበበ ሁለቱ የማራቶን ሯጮች በየቀኑ ልምምድ ሲያደርጉ ማየቱ ስላልጣመው ሌሊት ተደብቆ ይለማመድ ነበር፡፡ አበበ ለሦስተኛ ጊዜ የሚወዳደር በመሆኑ የዓለም ጋዜጠኞች በሙሉ ሊያነጋግሩት ይፈልጉ ነበር፡፡ ጥያቄው ስለበዛ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ስለነበርኩ የፕሬስ ኮንፌራንስ አዘጋጀሁ፡፡ እኔው ራሴ አስተርጓሚ ሆኜ ከአበበ ጋርና ከኦኒ ኒስካኔን ጋር ቀረብን፡፡ የመጀመርያውን ጥያቄ ተርጉሜ ስነግረው፣ “ጋሼ አንተ ከኔ የተሻለ ጉዳዩን ታውቅ የለም ለምን አትመልስለትም” አለኝ፡፡ የኛ አትሌቶች ከልምምዳቸው ውጭ ለፕሬስ የሚጥም ገለጻ ስለማያደርጉ እስካሁን ድረስ ችግር ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የቋንቋም ችግር መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡ እንደ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ዓይነቱ ምሳሌ ሊሆን ይችል ነበር፡፡

የሜክሲኮ ማራቶን ሩጫ ከተጀመረ በኋላ 15ኛው ኪሎ ሜትር ላይ አበበ ቢቂላ አቋርጦ ወጣ፡፡ የእግሩ ሕመም ጠናበት፡፡ በአሥር ሺሕ ሜትር ሩጫ ተካፍሎ የብር ሜዳሊያ ያገኘው ማሞ ወልዴና  መርዓዊ ገብሩ ውድድሩ ቀጥለው ከመሪዎቹ መደብ ውስጥ ተሠልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ማሞ ወልዴ በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ውድድሩን በማሸነፍ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን በመሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙሩን አዘመረ፡፡ ኢትዮጵያም ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ የማራቶን አሸናፊ ሆነች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960ዎች ውስጥ የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጥተው በኦሊምፒክ ጨዋታ መካፈል ጀምረው ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊው በባዶ እግሩ ሮጦ ማሸነፍ እኛ ለምን አንችልም በሚል ፉከራ ሁሉም አገሮች ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ጀምሮ የማራቶን ሯጮች አሠልፈው ነበር፡፡ ቶኪዮ ላይ አበበ ሜዳሊያውን ተቀብሎ ወደ ኦሊምፒክ መንደር ከተመለሰ በኋላ ስታዲየም የሚደርሱ የአፍሪካ ሯጮች ነበር፡፡ ሜክሲኮም ላይ ፋሻ ጠምጥመው የደረሱ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያዊው መርዓዊ ገብሩ እንኳን ስድስተኛ ነው የሆነው፡፡ ማሞ ወልዴ በ10 ሺሕ ሜትር ሩጫ ላይ ለትንሽ ወርቅ ሜዳሊያ እንዳመለጠችው የታዘበ የኮንጎ ስፖርት መሪ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን በፈረንሣይ “ተሰማ ለትንሽ ወርቅ አመለጠህ” ሲለው ጋሼ ይድነቃቸው መለሰና “ኢትዮጵያ ውስጥ ወርቅ ሞልቶናል፡፡ የቸገረን ብር ነው” መለሰለት፡፡

አትሌቶቻችን ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ጃንሆይ አበበ ቢቂላን ሻምበል፣ ሞሞ ወልዴን መቶ አለቃ አድርገው ሾሙዋቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1969 ነው አበበ ቢቂላ የመኪና አደጋ ደርሶበት በጃንሆይ መልካም ፈቃድ ለሕክምና ወደ እንግሊዝ አገር የተላከው፡፡ እዚያም ስቶክማንደቪል በሚባል ዝነኛ ሆስፒታል ስምንት ወር ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1970 አቶ ይድነቃቸውና እኔ አብረን ከአውስትሪያ ስብሰባ ስንመለስ ሄደን ስንጠይቀው ከመላው ዓለም የተላከለት ደብዳቤዎች በአንድ ጆንያ ውስጥ ተጠራቅመው አገኘን፡፡ እኔም በኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊነቴ በርሱ ስም መልስ ለመስጠት ደብዳቤዎቹን ማገላበጥ ጀምርኩ፡፡ ቢያንስ ለትላልቅ ባለሥልጣኖች መልስ ለመስጠት ወሰንን፡፡ እነሱም የታላቋ ብሪታኒያ ንግሥት ኤሊዛቤት የዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ለመሳሰሉት ተገቢውን መልስ ከአዲስ አበባ ልኬያለሁ፡፡ ንግሥት ኤሊዛቤት ግን ሆስፒታል ሄደው አበበን ጠይቀውታል፡፡ እኛንም ስቶክማንደቪል የወሰደን ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንድ ዲፕሎማት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1972 በጀርመን አገር በሙኒክ ከተማ የተካሄደውን የኦሊምፒክ ጨዋታ እንዲመለከቱ ከተጋበዙት የክብር እንግዶች ውስጥ አበበ ቢቂላ ሲገኝ ሌሎቹ የታርዛንን ፊልም የሠራው ጆኒ ዌስሙለር እ.ኤ.አ. በ1924 እና 28 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በዋና የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው የናዚውን መሪ ሒትለር እጁን አልጨብጥም ያለው እ.ኤ.አ. በ1936 በበርሊን ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ አራት የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈው ጥቁር አሜሪካዊ ጆሲ ኦዋንስ ነበሩ፡፡ ማሞ ወልዴ ለአራተኛ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታ በመካፈል በማራቶን ሦስተኛ ወጥቶ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው በ41 ዓመቱ አበበ ቢቂላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1992 ባርሴሎና ኦሊምፒክ ጨዋታ ከመጀመሩ ከ28 ዓመት በፊት ቶኪዮ ላይ ለአበበ ቢቂላ ጫማ ለክተው ሰፍተው የሰጡት አዛውንት የኩባንያው ፕሬዚዳንት ሆነው የአበበን ጫማ በብር አሠርተው እኔ በተገኘሁበት ሥነ ሥርዓት ላይ ለማስታወስ ለኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት፣ ለኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚንትና ለአበበ ቢቂላ ባለቤት ለወ/ሮ የውብዳር ወልደ ጊዮርጊስ አበርክተዋል፡፡ የወ/ሮ የውብዳር ጉዞን ያዘጋጀሁት እኔ ነኝ፡፡ የመጀመርያውን የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ በ10 ሺሕ ሜትር ሩጫ  ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊት ሴት አትሌት ወዳጄ ደራርቱ ቱሉ ብቅ ያለችው ባርሴሎና ነው፡፡ የ60 ዓመት ታሪክ ለመጻፍ ያበቃኝ ለአምላኬ ምስጋና ይድረሰው፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ፣ እንዲሁም የቀድሞ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻ [email protected]ግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles