በላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)
በመጀመርያ ብዙ ሰዎች አሁን በመጣብን አባዜ “የየትኛው ፓርቲ አስተሳሰብ ነው አንተ የምታራምደው” እያሉ ሰሞኑን ይጠይቁኛል፡፡ መልሱ በጣም ቀላል ነው፡፡ የማንም ፖለቲካ አባል ሳልሆን፣ አገሬን ከፖለቲካው ገለልተኛ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ግዛት እየሰፋም እየጠበበም ቢሆን፣ አንዳንዶች የታሪክ ምሁሮች ከስምንት ሺሕ ዓመታት በፊት የራሷን የግዛት ከልል ይዛ የኖረች አገር ነበረች ቢሉም፣ አብዛኛው ሕዝብ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ የራሷን መንግሥት መሥርታ ትተዳደር እንደነበር ያምናል፡፡ በመሀሉም በመሳፍንትና በባላባቶች ግዛቷ ተከፋፍሎ፣ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ መንግሥቱ ደካማ ሆኖ፣ ህልውናው ወደ መጥፋት ተቃርቦ ነበር፡፡ ከ150 ዓመት በፊት አፄ ቴዎድሮስ ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያ ከመሳፍንት አገዛዝ አላቀው አንዲት ሉዓላዊ የኢትዮጵያ መንግሥት ለመመሥረት ጅማሮ አደረጉ፡፡ ከዚያም በመቀጠል የመጡት ነገሥታት ይኼን ጅማሮ በማጠናከር አሁን የያዘችውን የኢትዮጵያን ቅርፅ መሠረቱ፡፡ እዚህ ላይ ግን አስረግጦ መናገር ወይም መታወቀ ያለበት እነዚህ አፄዎች ኢትዮጵያን አልመሠረቱም፡፡ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ያደረጉት በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍላ በየጎጡ ትተዳደር የነበረችውን ኢትዮጵያ በማዕከላዊ ወይም በአሃዳዊ መንግሥት እንድትተዳደር ነው ያደረጉት፡፡ በአፄዎቹ እንደገና የተቋቋመችው ኢትዮጵያ ግን አንድ መንግሥት ሊኖረው የሚችለውን ቁመና ሙሉ ለሙሉ ይዛ ሥልጣኔ በቶሎ ሊያመጣላት አልቻለም፡፡ ለዚህም ሦስት ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
አንደኛው በየቦታው ተቆጣጥረውት የነበሩትን መሳፍንትና የባላባት ግዛት በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ማምጣት ከባድና ጊዜ የወሰደ ሲሆን፣ አፄዎች ማለትም ቴዎድሮስ፣ ተክለ ጊዮርጊስና ዮሐንስ የሞከሩትን የዳግማዊ ምኒልክና የኦሮሞው ራስ ጎበና ጥምረት መንግሥት መሥርተው ዛሬ ኢትዮጵያ የያዘችውን ግዛት ቅርፅ እንዲኖራት ቢያስችሉም በኋላም የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ይኼንኑ በእነ አፄ ምኒልክ የተቀየሰውን የኢትዮጵያን ግዛት በማጠናከር ዛሬ የምትገኘውን ኢትዮጵያን ቢያስረክቡንም፣ በአንዳንድ የግዛቱ መሳፍንትና ባላባቶች በኋላም ልጆቻቸው የአፄውን ግዛት ባለመቀበላቸው ዘመን ተሻጋሪው ችግር እስካሁን የሐሰት ታሪክ እየፈጠሩ በመኖራቸው አገሪቷ በሥልጣኔ እንዳታድግ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከነዚህም አንዱ በምኒልክ ግዛት ማሰባሰብ ጊዜ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ተጥሷል የሚባለው ነው፡፡ እዚህ ላይ አሃዳዊ መንግሥት ለማምጣት ንጉሦቹ ኃይል መጠቀማቸው ዕውን ነው፡፡ ማንኛውም አገር ደግሞ አሁን የያዘውን ቅርፅ እንዲይዝ የተደረገው በኃይል ነው፡፡ አለበለዚያ ከሺሕ በላይ ትንንሽ አገሮች በዓለም ላይ ይፈጠሩ ነበር፡፡ ሌላው ከዚሁ ጋራ ተያይዞ የሚነገረው የፈጠራ ታሪክ “የምኒልክ ጦር አገር ሲያዋህዱ፣ የሴቶችን ጡት ይቆርጡ ነበር” የሚለው ነው፡፡ እዚህ ላይ የምኒልክን ጦር የሚመሩ ራሶችና ደጃዝማቾች በአንድ ሥርዓት ባለው ንጉሥ የተመለመሉና በሕግና ሥርዓት የሚተዳደር ወታደር ይዘው የሚዘምቱ መሆናቸውን መገንዘብ በቂ ነው፡፡ ሌላው ሕዝቡን በጭካኔ አስገብረው በኋላ አብረው ለመኖር ስለሚያስቸግራቸው ይኼን ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ ከዚህም በላይ እንዲህ ያለ ድርጊት በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ተዘግቦ አይታወቅም፡፡ እንዲያውም ምኒልክ በታሪክ ከሚታወቁበት አንዱ በባህሪያቸው ሩህሩሀ መሆናቸው ስለሆነ ይኼ ታሪክ ፖለቲከኞች በሐሰት ፈጥረው ለፖለቲካ ፍጆታ የተጠቀሙበት ተራ አሉባልታ ነው፡፡ ምኒልክ ያደርጉ የነበሩት ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ፣ ለሁሉም መሳፍንትና ባላባቶች ጥሪ የሚያቀርቡት “ግዛታችሁ በኢትዮጵያ ሥር ነውና ለኢትዮጵያ መንግሥት ገብሩ፣ ግዛታችሁን አልወስድባችሁም፤” ነው፡፡ ይኼን የተቀበሉ በወለጋ በትግራይና በጅማ ወዘተ. ምንም ጦርነት በአካባቢያቸው ሳይደረግ በማዕከላዊ መንግሥት ሥር በመሆን ግዛታቸውን አስተዳድረዋል፡፡ በሌላ በኩል ግዛታቸውን ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ያላስገቡ፣ በኃይል ከመሳፍንትና ከባላባቶች ጋር በመዋጋት የምኒልክ ጦር በማሸነፍ እንዲገብሩ ተደርጓል፡፡ የተሸነፉት መሳፍንትና ባላባቶችን ንጉሡ ምሕረት በማድረግ “ግዛታችሁን ደሃ ሳትበድሉ እንድታስተዳድሩት ሰጥቼአችኋለሁ” በማለት ምኒልክ ወደ ግዛታቸው ይሉኳቸው ነበር፡፡ በታሪክ የተጻፈ አንድ መስፍን ግዛቱን እንዲያስገብር ምኒልክ “ልጄ በማርያም ይዤሃለሁ ጦርነት ሳንሄድ ገብር” ብለው ቢልኩበት እንቢ ብሎ ጦርነት ከምኒልክ ሠራዊት ጋራ ይገጥማል፡፡ ተሸንፎ መስፍኑ ምኒልክ ጋ ይቀርባል፡፡ ምኒልክም ከጎናቸው አስቀምጠው “በማያስፈልግ ጦርነት ከሁለታችንም ወገን ብዙ ሕዝብ አስጨረስን፡፡ የአባትህ ግዛት ነውና አንተ በሠራኸው ጥፋት አልወስድብህም፡፡ ምሬሃለሁ፡፡ ግዛትህን ደሃ ሳትበድል አስተዳድር” በማለት መስፍኑ ያልጠበቀውን ከተናገሩ በኋላ ምኒልክ በመቀጠል “ለመሆኑ አንተ ጦርነቱን ብታሸንፍ ኑሮ እኔን ምን ታደርገኝ ነበር” ብለው ሲጠይቁት ውሸት እንዳይናገር ውለታው ከብዶት “እኔ ብሆን ኖሮ በሞት እቀጣህ ነበር” በማለት እውነቱን ተናገረ፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ሩህሩህነት ተመልክቶ ነው ከዳር እስከ ዳር እምዬ ምኒልክ ብሎ ስም ያወጣላቸው፡፡
ሁለተኛው ሥልጣኔ በኢትዮጵያ እንዳይመጣ ተተብትቦ ያስቸገራት የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ፍላጎት በኢትዮጵያ ላይ ማየሉ ነው፡፡ አፍሪካውያን ወርረው እንደያዙ ኢትየጵያንም በየጊዜው ወረው ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ቆራጥ መስዋዕትነት ቢገቷቸውም በዙር አገዛዝ ለአንድነት አፈንጋጭ መሳፍንትና ባላባቶች በኋላም ልጆቻቸው የጦር መሣሪያ በመስጠት፣ ንጉሦቹ ተረጋግተው እንዳይሠሩ፣ መሳፍንቱ እንዲያምፁባቸው በማድረግና ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የዕድገት መሣሪያ የሆነው ቴክኖሎጂ እንዳይደርስ ማዕቀብ በማድረግ ሥልጣኔ አገሪቱ እንዳታገኝ ያደረጉት ጫና ቀላል አልነበረም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት ሥልጣኔ ፍለጋ ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያ ሲለምኑ “እውር ነኝና ብርሃን ስጡኝ” ብለው ጠይቀው መልስ ያላገኙትና በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በተላላኪዋ ግብፅ በኩል “ኢትዮጵያ አትሠልጥን” ትርክት የዚሁ የምዕራባውያን ሴራ ፖለቲካ ነው፡፡ ሦስተኛው ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ለማምጣት ንጉሦቹ ያልቻሉት አፄዎቹ ከጥንት ከአባቶቻቸው የወረሱትን አስተዳደር ነው እንጂ የሚያውቁት በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ አስተዳደርም ሥልጣኔም መኖሩን አያውቁም ነበር፡፡ ይኼም የሆነበት ምክንያት አገሪቷ ከውጭ የሚመጣባትን የቅኝ ግዛት ወረራ ለመቋቋም ከሌላው ዓለም ድንበሯን ዘግታ ስለነበረ የኢንዱስትሪ አብዮት በዓለም ሲፈነዳ ለኢትዮጵያ ሳይደረስ በመቅረቱ ነው፡፡ ሥልጣኔም ሆነ ልማት በኢትዮጵያ ያልመጣበት ምክንያቶች ከላይ የዘረዘርኳቸው ቢሆንም ለሥልጣኔ አለመምጣት ከሚጠቀሱት ውስጥ የመንግሥት መሪ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
መሪ ብቻውን ለምን አስፈለገ? ቢባል ንጉሥ ፕሬዚዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር በዕውቀት ላይ ተመሠረተ አርቆ አሳቢና በራሱ የሚተማመን ካልሆነ በሥሩ የሚሠሩትን ሚኒስትሮችም ሆነ ሹማምንት ለማሠራት አይችልም፡፡ እንዲያውም በሹመት የሚያመጣቸው ከሱ ያነሱ እሺ ጌታ የሚሉትን ነው፡፡ ስለዚህ አንድን አገር ተብትቦ የያዘውን ኋላ ቀርነት በጣጥሶ ዕድገት ለማምጣት መሪ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህም ነው በጀርመን ቢዝማርክ፣ በእንግሊዝ ቸርችል፣ በቱርክ አታቱርክ፣ በቻይና ማኦሴቱንግ ወዘተ. ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሠርተው አገራቸውን አሁን ላለበት ዕድገት በማድረሳቸው ዘለዓለም ሲታወሱ የሚኖሩት፡፡ እነዚህ አገሮች መሪዎቻቸውን የሚያደንቁዋቸው ያመጡላቸው ልማት/ዕድገት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ስለ አገኘ ነው፡፡ ሥልጣናቸውን ከተዉ በኋላ ሕዝቡ የሚያደንቃቸው ለአገሪቱ የዘረጉት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ነው አንድ አገር “የበቃ መሪ በምዕት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ልታገኝ ትችላለች፤” የሚባለው፡፡
በኢትዮጵያ የነበሩት መሪዎች ሁሉም ምንም አልሠሩም ለማለት ሊከብድ ይችላል፡፡ የጊዜያቸውን ነባራዊ ሁኔታ መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ግን መስማማት ያለብን መሠረታዊ የመንግሥት አሠራርን ዘርግቶ ለዘመናዊ ኢትዮጵያ መሠረት የጣለ መሪ እንዳልነበራት አሁን የምናየው ውጥንቅጥ ማሳያ ነው፡፡ ይኼ እንደ ተጠበቀ በየዘመኑ የነበሩ መሪዎች ዘመነ መንግሥታቸው ምን እንደሚመስል ዓይተን ምን በጎ ነገር ምን ጉድለት እንዳላቸው እንይ፡፡
መሪዎችና ዘመነ መንግሥታቸው
ኢትዮጵያ የዘመናዊ ዓለም ሥልጣኔን ተገንዝባ ለመቀበል ፊቷን ያዞረቺው ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ነው ብንል ብዙ አንሳሳትም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ሙሉ ዘመናቸውን ከአፈንጋጮች ጋራ ሲዋጉ ከማሳለፋቸውም በላይ በጋፋት ላይ በዚያኔ በዓለም ትልቁ ቴክኖሎጂ የሚባለውን የጦር መሣሪያ ለማምረት ቢሞክሩም ስላልተሳካ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የተዋደቁ መሪ ነበሩ ከማለት ሌላ ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለማምጣት መሠረት ነበሩ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከቴዎድሮስ በኋላ ከመጡት ነገሥታት ጎልተው የሚጠቀሱት አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ አፄ ምኒልክና መንግሥታቸው የዘመናዊ ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን የሚያሳዩ አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በመጀመርያ ሰሜን ላይ ያለውን የኢትዮጵያ መዲና ወደ መሀል ኢትዮጵያ በማምጣት አዲስ አበባ ላይ መሠረቱ፡፡ በዚህ ብቻ ሳይቆሙ ለከተማዋ የሚያስፈልገውን ማገዶ ለሟሟላት ከአውስትራሊያ ባህር ዛፍ አምጥተው በመትከል በዚያን ጊዜ የነበረውን የማገዶ ችግር አስወገዱ፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት አዲስ አበባ በዚያን ጊዜ ጫካና ማንም ያልሠፈረባት የዝሆንና የአንበሳ መኖሪያ ነበረች፡፡ ጥቂት ጎጆዎች በፍል ውኃ (ፊንፊኔ) አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በነዚህም ጎጆ ቤቶች በመቀመጥ በአባለዘርና በቆዳ በሽታ የታመሙ ሰዎች ፍል ውኃ ይታጠቡባት ነበር፡፡ የተፈናቀለ ሰው አልነበረም፡፡
አፄ ምኒሊክ በመንግሥታቸው ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ሚኒስትሮች የሰየሙ ሲሆን፣ የልማት መሠረት የሆኑት እንደ ትምህርት ቤት፣ ስልክ፣ ባቡር፣ የቧንቧ ውኃ መንገዶችና ድልድዮች ወዘተ. ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ አዘርግተዋል፡፡ እንዲያውም ስልክ በዓለም በመጣ በጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በማዘርጋታቸው ከቀዳሚዎቹ አገሮች ኢትዮጵያን አንዷ አድርገዋታል፡፡ ምኒልክ አዳዲስ የልማት መሠረተ ልማቶችን ቢዘረጉምና የታላቁ ዓድዋ ድል ባለቤት ቢሆኑም መላ የመንግሥት ጊዜያቸው ሕገ መንግሥት የሌለው በዘልማድ የሚሠራ ስለነበረ የዘመናዊ ኢትዮጵያን አቅጣጫ በማሳየት ከነገሡት ነገሥታት ውጤታማ ንጉሥ ከማስባል በስተቀር ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሠርተው ለዛሬው ዕድገታችን መሠረት የጣሉ መሪ ተብለው ሊወደሱ አልበቁም፡፡ ከሳቸው የቀጠሉት ልጅ ኢያሱ የንግሥና ሲመት ያላደረጉ በመሆናቸው እንደ መንግሥት መሪ መቁጠር ያስቸግራል፡፡ ቀጥሎ የመጡት የንግሥት ዘውዲቱና የንጉሥ ተፈሪ መንግሥት ነው፡፡ ንግሥቲቷ እንደ ርዕሰ ብሔር ሲቆጠሩ አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መንግሥት መሥርተው ልማት ለማምጣት በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያ፣ መንገዶችና ድልድዮች፣ የአስተዳደር ሥራዎች የፖሊስና የጦር ማሠልጠኛ ተቋም ወዘተ. በመጀመርያው የንግሥና ዘመናቸው የተመሠረቱ ሲሆን፣ በኋላም ንግሥቲቷ ሲሞቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥቱን አስቀጥለው የልማት ሥራውን እያካሄዱ እያለ ጣሊያን በመግባቱ ሊቋረጥ ችሏል፡፡ ከጠላት በኋላ ሕገ መንግሥትን ዳግም በማዘጋጀት በዚሁ ላይ ተመሥርቶ ዘመናዊ መንግሥት በልዩ ልዩ ሚኒስቴሮች፣ ባለሥልጣኖች፣ መሥሪያ ቤቶችና ኢንስቲትዩቶች ወዘተ. አቋቁመዋል፡፡ በ19ኛው ምዕት ዓመት ያሉት ነገሥታት ሲታገሉ የነበረውን ኤርትራን ማስመለስና የባህር በር እንዲኖራት ማስቻል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ውጤት ነው፡፡ በልማቱ በኩል ንጉሡ ሁሉን አቀፍ ርብርብ በማድረግ በየጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ የጤና ጣቢያ በማቋቋም፣ የአየርና የባህር የትራንስፖርት አውታሮች በመዘርጋት የየብስ ትራንስፖርትን በከተሞችም ሆነ በጠቅላይ ግዘቶች በአስፋልትና በጠጠር በጋና ክረምት የሚጋለግሉ መንገዶችን በማስፋፋት ሕዝቡ የሥልጣኔ ትሩፋትን እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ አነስተኛ፣ መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በስኳር፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በነዳጅ ማጣርያ (ፔትሮሊየም ሪፋይነሪ) ወዘተ. ሰፋፊ እርሻዎች ካዱን የመሰሉ፤ በምግብና መጠጥ፣ የብስኩት፣ የዱቄት፣ የቢራ፣ የለስላሳና የአረቄ ወዘተ. ፋብሪካዎችን በመክፈት አገሪቱ ዘመናዊ እንድትሆን ጥረዋል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሚመሠገኑበት ምክንያት ዋናው ለትምህርት የሰጡት ከፍተኛ ተነሳሽነት ነው፡፡ በተለይ ከጠላት በኋላ ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ወደፊት ልትራመድ የምትችለው በትምህርት ነው ብለው ራሳቸው ከንጉሥነታችው በተጨማሪ በመጀመርያዎቹ ዓመታት የትምህርት ሚኒስትር በመሆን ለተግባረዕድ፣ ለንግድ፣ ለእርሻ፣ ለጤና፣ ለመምህርነትና ለፋብሪካ ወዘተ. ትምህርት ቤቶችን ከፍተው አብዛኛው ለትምህርት የደረሰ ኢትዮጵያዊ ወጣት እዚሁ እንዲማር በማድረግ ጥቂቶቹን ወደ ውጭ አገር በአገሪቱ ገንዘብ እንዲማሩ ያደረጉ ሲሆን፣ እነዚህም ውጭ አገር ተልከው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ማደግና መስፋፋት ጥልቅ ሚና እንዲጫወቱ አድርገዋል፡፡ እዚህ ላይ መታወስ ያለበት በተለይ በመጀመርዎቹ ዓመታት ንጉሡ ለትምህርት ጥቅም ሕዝቡ ገብቶት ልጆቹን እንዲልክ ማባበያ ለወላጆችና ለልጆች በመስጠት ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ በአጠቃላይ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አሁን ኢትዮጵያ የምትገለገልበትን መሠረተ ልማት፣ ዘመኑ ያመጣው አዳዲስ ካልሆነ በስተቀር በሙሉ የተመሠረቱት በመንግሥታቸውና በእሳቸው ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ጥሬ አቋም አላቸው ብለው ከሚጠቀሱት የመንግሥት መዋቅሮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ፖስታና ቴሌ የፖሊስና የጦር ማሠልጠኛና አካዴሚዎች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮሌጆችና ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩቶች ወዘተ. ከሚጠቀሱት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የውጭ የፖለቲካ ግንኙነታቸውም አገሪቱ ትልቅ ዝናና ከበሬታ እንድታገኝ አስችለዋታል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤቱን እዚህ እንዲያደርግና የገለልተኛ መንግሥታት ማኅበር በማቋቋም፣ ከቅኝ ግዛት አገዛዝ በተለይ የአፍሪካ አገሮች እንዲወጡ፣ በወታደር፣ በፖለቲካ፣ በገንዘብ ዕገዛ በማድረግ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ አገሮች ሰላም እንዲያገኙ በኮንጎ፣ በናይጄሪያና በሱዳን ወዘተ. ያደረጉት ጥረት ታሪካቸውን ዘለዓለማዊ ያደርገዋል፡፡
ከነበሩት አፄዎች ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያን ለማልማት ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ቦታ ቢያሰጣቸውም፣ በተለይ ከላይ በአገሮች ታዩ እንደሚባሉት መሪዎች ፖለቲካውን አስተካክለው ለፖለቲካው አጋዥ የሚሆን በነፃ የሚንቀሳቀሱ ጠንካራ የፓርላማ ሥርዓት የመንግሥት ተቋም የሕግ አውጪና ተርጓሚ ወዘተ. አቋቁመው ዘላቂ የሆነ ማኅበራዊውና ኢኮኖሚውን የሚለውጥ መሠረት ባለመጣላቸው፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ቆራጥ መሪ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ በተጨማሪም ከሚያስወቅሳቸው ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከልማቱ ተደራሽ አለመሆኑና ድህነት አለመጥፋቱ ከ90 በመቶ በላይ የሆነው ገበሬ ጭሰኛ በመሆን የለፋበትን ለባለ መሬቶች እንዲሰጥ ሕጉ በማስገደዱ የንጉሣዊው ሥርዓት ፍፁማዊና ባላባት በመሆኑ በብዙ ወጣቶች ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተቀባይነት አለማግኘታቸው ወዘተ. ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ በንጉሦቹ ዘመን አመራሩ ወጥ በመሆኑ አገርን በልማት የሚያሸጋግር መሪ ንጉሥ ለማግኘት ቀላል ነበር፡፡ ሁሉም ነገር የሚቸረው ከንጉሡ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የወጣው ሕገ መንግሥት ሲጀምር “ንጉሠ ነገሥቱ ለሕዝባቸው በገዛ ፈቃዳቸው የሰጡት” ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ በነዚያ ዘመናት ከነበሩት ንጉሦች አንዱን መርጦ አምላክ ለኢትዮጵያ አለመፍጠሩ ነው እንጂ ጥሩ ንጉሥ ቢፈጠርላት ኑሮ እንደ ጃፓንና እንግሊዝ በማኅበራዊና ኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያ ትሆን ነበር፡፡ ከበደ ሚካኤል፣ ጃፓን እንዴት ሠለጠነች በሚለው መጽሐፋቸው ጃፓን በአንድ ወቅት በሥልጣኔ ከኢትዮጵያ ጋራ እኩል አንደ ነበረች፣ ጃፓን ባደረገችው ለውጥ ስትሠለጥን ኢትዮጵያ ሳትሠለጥን እዚያው እንደ ቀረች የጠቀሱት ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ ስለዚህ በነገሥታቱ ዘመን ከነበሩት ነገሥታት አንዳንዶችን በጊዜያቸው ጥሩ ሠርተዋል ተብሎ ታሪክ ቢዘክራቸውም ለኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሠርተው ዛሬ ያጋጠመንን ችግር እንዳይኖረን ስላላስቻሉ ከንጉሦቹ መሀል በመሪነት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አምጥቷል ብለን የምንጠቀሰው ንጉሥ የለም፡፡
ከ45 ዓመታት በፊት የዘውድ አገዛዝ ተወግዶ በተከታታይ የመጡት መንግሥታት አመሠራረታቸው የደቦ ስለሆነ፣ ከውስጣቸው መሪ ባለመውጣቱ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከድሆቹ አገር ተርታ እንዳትወጣ አድርጓታል፡፡ 120 ወታደሮችን በማሰባሰብ የዘውድ አገዛዙን ገርስሶ የመጣው ደርግ በመጀመርዎቹ ዓመታት ማንኛውንም ውሳኔ እስከ መግደል ድረስ የሚወሰነው 120ዎቹ እጃቸውን በማውጣት ነበር፡፡ በኋላም አካባቢው ያሉትን ዋና ዋና የደርግ አባላትን፣ ምሁራንንና ወጣቱን በጭካኔ ጨፍጭፈው/ገለው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም “ብቸኛ መሪ” ሆነው ብቅ አሉ፡፡ በእሳቸው መሪነትና በምሁራኑ ትብብር በሥልጣን ዘመናቸው አንዳንድ መሠረታዊ ለውጥ ጭሰኛን ማጥፋት፣ የከተማ ቦታና ቤት የመንግሥት ማድረግ ወዘተ. የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ከማምጣት ውጭ በአምባገነንነት በተሠራው የሰውን ልጅ ማጥፋት ወንጀል ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያን ወደ ሲኦል የወሰዱ መሪ ናቸው ተብሎ ቢገለጽ ብዙም ከእውነታው አይርቅም፡፡
ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥት ቀጥሎ የመጣው ሌላ የደቦ መንግሥት ራሱ የብሔሮችን ክልል ፈጥሮ የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት ነው፡፡ ይኼ መንግሥት ለ27 ዓመታት በቆየበት ዘመን ይዞት በመጣው አዲስ የተወሰኑ ብሔሮች ስብስብ ፖለቲካ ምክንያት አገራዊ አጀንዳን በማሳነስ ክልላዊ በማድረግ ለኢትዮጵያ ቆራጥ መሪ ለማምጣት አላስቻለም፡፡ በመንግሥት ዘመኑ የተሻለ ልማት ከበፊት ካሉት መንግሥታት ያመጣ ቢሆንም ልማቶቹ ለኢትዮጵያ ከሚጠቅሙ ይልቅ ለክልሎች እንዲጠቅሙ ተብለው የተቋቋሙ፣ በብሔሮች መካከል አንዱን ትልቅ ተጠቃሚ ሌላውን አናሳ በማድረግ የግጭት መንስዔ የሆኑና ፍታሐዊነት የጎደላቸው፣ በየክልሉ ያሉ የፈረጠሙ ድርጅቶች የልማት አውታር የሚባል ዘርግተው ከሕዝቡ ይልቅ ለግለሰቦች ኪስ መደለቢያ ሙስና የነገሠበት ወዘተ. በመሆናቸው የመጣው ልማት አገሪቱ ላይ እርካታን ሊሰጥ አልቻለም፡፡
በኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን ጎልተው የወጡት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ አባሎቻቸው ለእሳቸው ያላቸው ከበሬታ ከሰማይ በታች እንደ እሳቸው ያለ በኢትዮጵያ አልተፈጠረም ብለው ያደንቁዋቸው ነበር፡፡ እንዲያውም እሳቸው ከሞቱ በኋላ በዩኒቨርሲቲያችን እሳቸውን ለማስታወስ በተደረገው ስብሰባ ላይ ሁሉም እየተነሳ እሳቸው ለብቻቸው ኢሕአዴግን እንደ መሩ የመጣው ልማት በእሳቸው አርቆ አሳቢ መሪነት እንደሆኑ ድርሳን ሲያወሩ፣ ስብሰባውን በዘጋቢነት የተጋበዘው ጓደኛዬ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ “ምንድ ነው የምታወሩት፣ አቶ መለስ በሕይወት እያሉ ራሳቸው ሲያወሩ እኔ በኢሕአዴግ ነው የምመራው ይሉን ነበር፡፡ አሁን ደግም ያለ የሌለውን ሥራ ለእሳቸው ከሰጣችኋቸው እናንተ ምን ትሠሩ ነበር?›› በማለት ዘገበ፡፡ በዚህ ዘገባው ደስ ያላላቸው የስብሰባው አዘጋጆች ጓደኛዬን ከስብሰባው በኋላ እንደ ወቀሱት ትዝ ይለኛል፡፡ እኔ እሳቸውን በአካል በሥራ ምክንያት የማግኘት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡ ከፍተኛ ዕውቀት እንደተላበሱ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ ሚኒስትሮቹም ሆኑ የበታች ሹማምንት ሲታዘዙዋቸው ጥያቄ እንደማያነሱ ታዝቤያለሁ፡፡ ይኼንን ዕውቀትና ሙሉ የበላይነት (Absolute Power) ተጠቅመው፣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንድ በማድረግ ሥልጣን የሚመነጨው በብሔር ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ብለው (ለእሳቸውም ብሔር የሚጠቅመው ይኼው ነበር) የዜጋ ፖለቲካ ባለማድረጋቸውና ኢትዮጵያዊነትን በሁለተኛ ደረጃ በመያዛቸው ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በተቃራኒ በመሄዳቸው ምሥጉን መሪ የመሆን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ በገዛ ሥልጣናቸው በአፄ ዮሐንስ ተጋድሎና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እልህ አስጨራሺ ትግል የመጣውን የባህር በር አሳልፎ በመስጠት አገሪቱን ለዘለዓለም ፀፀት መስጠታቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ መሪ ተደርገው ለዘለዓለም ይታወሳሉ፡፡ በመጨረሻም የኢሕአዴግ መንግሥት ይዞት የመጣው የብሔር ፖለቲካ የሁሉም ብሔሮች ልሂቃን ለእኔ ብሔር የሚል ስግብግብነት በመፍጠራቸው በብሔሮች መካከል ልዩነት ተፈጥሮ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ጫፍ ደርሶ እናያለን፡፡
እንግዲህ እዚህ ላይ የምናየው ኢትዮጵያ እንደ ቀደምት ባለታሪካዊነቷ አንድ ዘመን ተሻጋሪ መሪ እስካሁን እንዳላገኘች ነው፡፡ ይሄ ጽሑፍ የሚዳስሰው ያለፉትን መሪዎች ታሪክ በመሆኑ የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን አይመለከትም፡፡ ከመሪ ምን እንደሚጠበቅ ለምሳሌ ዘመን ተሻጋሪ መሪ ከሆኑት ውስጥ የቱርኩን መሪ ሙስጠፋ ከማል አታቱርከን ልንወስድ እንችላለን፡፡ ቱርክ በ20ኛው ምዕት ዓመት በሃይማኖትና በብሔር ተከፋፍላ ደሃ ከሚባሉት የአውሮፓ አገሮች አንዷ ከመሆኗም በስተቀር በአንደኛው ዓለም ጦርነት ተሸንፋ ንጉሡና ወታደሩ ሲበተኑ አታቱርክ የተበተነውን ወታደር በማሰባሰብ ከአሸናፊው ጦር ጋራ እንደገና በመግጠምና በማሸነፍ አገሩን ከውድቀት አዳነ፡፡ በዚህ ብቻ ሳይቆም በሃይማኖት፣ በብሔር ተከፋፍሎ ደሃ የነበረችውን አገር ከብሔርና ከፖለቲካ ነፃ የማድረግ በቱርክ አገር ሁሉም ዜጋ እኩል የሚሆንበት፣ በማንኛውም አካባቢ ሄዶ ንብረት የሚያፈራበት፣ ሴቶች በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖት የማይጨቆኑበት አዲስ ሕገ መንግሥት በማፅደቅ የቱርክ ሪፐብሊከን መሠረተ፡፡ ይኼንንም ሕገ መንግሥት በመጠቀም አታቱርክ ከፍተኛ ለውጥ (Rigorous Reform) በአገሪቱ ሥርዓት ላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል በማምጣት ቱርክን ከውድቀት አውጥቶ፣ የበለፀገች አገር እንድትሆን ዘመን ተሻጋሪ ሥራ በመሥራቱ እስከ ዛሬ የዘመናዊ ቱርክ አባት ብለው ቱርካውያን ይጠሩታል፡፡ ከአታቱርክ ተግባር ከሚጠቀስለት ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ የቱርክ ወንዶች ከባህል ጋራ ተያይዞ የሚለብሱት የነበረው እጀ ጠባብና ተነፋናፊ ሱሪ ሲሆን፣ ጭንቅላታቸው ላይ ሻሽ በመጠምጥጠም ነበር፡፡ አታቱርክ ቱርክ እንደ አውሮፓውያን መልበስ አለባት ብሎ ስለሚያምን ሕዝቡ እንዲከተለው ራሱ አርዓያ በመሆን ወደ ፓርላማ የምዕራባውያንን ልብስ ለብሶ ሲመጣ ባህል አጥባቂ ነን ብለው የሚያስቡ ወግ አጥባቂዎች እርግፍ አድርገው በመተው እንደ አታቱርክ መልበስን ጀመሩ ይባላል፡፡ ዛሬ ከ100 ዓመት በኋላ ማንኛውም ቱርካዊና የውጭ ዜጋ አንካራ የሚገኘውን የዘመን ተሻጋሪ መሪ የአታቱርክን ሥራ በሙዚየም ለመጎብኘት በሠልፍ ተራ መጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ እኔም ዕድል አግኝቼ ጎብኝቼዋለሁ፡፡
እንግዲህ ኢትዮጵያውያን የሚመኙት እንደ አታቱርክ ያለ መሪ አምላክ እንዲያመጣላቸው ነው፡፡ በአገራችን ባህል እንዳየነው መሪዎችን እንደ ጣኦት እናመልካለን፡፡ መሪው የተናገረው ትክክልም ይሁን ሐሰት እንዳለ በበጎ ሁኔታ እናስተጋባለን፡፡ በቅንነትም ሆነ በጥቅም ፍለጋ መሪን ስንከተል ዓይናችንን አናሽም፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መሪን በሚፈራ እንደ ጣኦት በሚመለከትበት አገር አምላክ ለኢትዮጵያ እስካሁን መሪ አልፈጠረላትም እንጂ ሕዝቡ ለጥ ሰጥ ብሎ መሪ ያዘዘውን ስለሚሠራ ኢትዮጵያን በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ማሳደግ ብዙም አይከብድም ነበር፡፡
እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ መሪ ቢሰጣት ከመሪው የምንጠብቀው በተለይ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ፖለቲከኞች ፈጥረው ዓለም በ20ኛው ምዕት ዓመት የተወውን የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት በአገራችን ላይ ያመጡትን ችግር ለአንዴም ለሁሌም በጣጥሶ በመቅረፍ አገሪቷ እንደ ታሪኳ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚም አድጋ ሁሉም ዜጋ በኢትዮጵያ እኩል ሁኖ የሚደሰትባት አገር እንዲፈጥርልን ነው፡፡ ይኼም መሪ አዲስ ሕገ መንግሥት በመቅረፅ ማንኛውም ሰው በሰውነቱ እንዲከበር ኢትዮጵያዊ የሚያሰኘው ዜግነቱ እንጂ ብሔሩ እንዳልሆነ፣ የፈለገውን ሃይማኖት፣ ቋንቋና ባህል እንዲያከብር፣ በማንኛውም ቦታ ሄዶ መኖርና ንብረት ማፍራት ወዘተ. አስተማማኝ ማድረግ ነው፡፡ አገሪቱን ለልማት ምቹ በሆነ ፌዴራላዊ አስተዳደር/ግዛት በመክፈል እንጂ አንድ ብሔር አገሪቱን ቆርሶና አጥሮ የሚጠብቃት አለመሆኑን የሚያረጋጥ ሕገ መንግሥቱ ሦስቱን የሥልጣን እርከኖች ማለት የሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚውን በዴሞክራሲ በደንብ የለየ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን ድንጋጌዎች የያዘ፣ ሕዝቡ ቋንቋውና ባህሉን የሚጠብቅለትና በምንም አኳኋን በብሔርና በሃይማኖት ተደራጅቶ ሥልጣን ለመያዝ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም እንደማይችል ወዘተ.ተደርጎ መቀረፅ አለበት፡፡
ለማጠቃለያ በአፅንኦት መታሰብ ያለበት እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ክልል አጥሮ ከብሔረሰቡ ውጭ ያለው መጤ ነው ብሎ ኢትዮጵያውያንን በአገራቸው እንደ ባዕድ የሚቆጠሩበት ሥርዓትን ለማምጣት መጣር ከመተላለቅ ይልቅ የሚያመጣው ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ያለችው በ21ኛው ምዕት ዓመት ማለትም የኢትዮጵያ ዜጋ ኢትዮጵያዊ ነው ብሎም አፍሪካዊ ነው፡፡ ከዚያም የምድር ሰው ነው ተብሎ በሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ፖለቲከኛ ብሔሬን ይዤ ክልል መሥርቼና ከኢትዮጵያ ገንጥዬ ለመኖር እችላለሁ ብሎ ማሰብና ለጦርነት ሕዝቡን ማነሳሳት አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አለማወቅ ነው፡፡ ማንም ብሔር የራሱን ክልል ቆርሶ ከኢትዮጵያ ሊወጣ አይችልም፡፡ በየብሔሩ በተለያዩ ፖለቲከኞች መካከል ክፍፍል አለ፡፡ ሌቦች ሲሰርቁ ይስማማሉ፣ ሲከፋፈሉ ይጣላሉ እንደሚባለው የራሴን ብሔር ለየሁ ቢባል፣ በኋላ የርስ በርስ ጦርነቱ ይቀጥላል፡፡ በኢትዮጵያዊ ውስጥ ማንም ብሔር አሸናፊ ሊሆን አይችልም፡፡ የተነሳው የርስ በርስ ጦርነት ማቆሚያ ያጣል፡፡ ኢትዮጵያ ብትፈርስ ሁሉም አገር ያጣል፡፡ ይኼ እንዳይሆን ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ተባብረው ዴሞክራሲን መሥርተው አብሮ መኖር ነው ብቸኛው መፍትሔ፡፡ ይኼንንም የሚያደርግ እግዚአብሔር መሪ ይስጥ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ (ዶ/ር፣ኢንጂነር) ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡