Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜቴክ ‹‹ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ›› በሚል ስያሜ በድጋሚ ተቋቋመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በከፍተኛ የሀብት ብክነትና የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮች አሉታዊ ስምና ገጽታን ያተረፈው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ ‹‹ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ›› በሚል አዲስ ስያሜ በድጋሚ ተቋቋመ። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሜቴክን እንደ አዲስ በድጋሚ የሚያቋቁመውን ደንብ ረቡዕ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ማፅደቁን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል። 

ሜቴክን እንደ አዲስ የሚተካውን ተቋም መጀመርያ የተረቀቀው ማቋቋሚያ ደንብ ‹‹ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን›› የሚል ስያሜ ሰጥቶት የነበረ ሲሆን፣ረቂቁ ማሻሻያ ደግሞ ‹‹ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ግሩፕ›› የሚል ስያሜሰጥቶት እንደነበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ስያሜዎች ተቀይረው ‹‹ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ›› የሚል ስያሜ በፀደቀው ማቋቋሚያ ደንብ እንዲፀና ተደርጓል።  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባፀደቀው ማቋቋሚያ ደንብ ከዚህ ቀደም በሜቴክ ሥር የነበሩና በብረታ ብረት፣ በአውቶሞቲቭ፣ በእርሻ መሣሪያዎች፣ በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ፣ በኮንስትራክሽን ማሽነሪና ፕላንት፣ እንዲሁም በፖሊመር ምርት ዘርፎች የተሰማሩት ተቋማት ሜቴክን የሚተካው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሥር እንዲደራጁ ወስኗል። 

የቀድሞውን ሜቴክ የሀብት አጠቃቀም ውጤታማ በማድረግና ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር ለማስቻል፣ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስያሜ ተደራጅቶ እንደ አዲስ እንዲቋቋም ደንቡ መፅደቁን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይፋ ያደረገው መረጃ ይገልጻል። 

የሚቋቋመው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ መሠረት የሚተዳደር ሲሆንተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ እንደሆነ የፀደቀው ደንብ ይደነግጋል። 

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከልም የማምረቻ ወይም የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ዲዛይን ማድረግ፣ መገንባት፣ በመፈተሽ ኮሚሽን ማድረግ፣ መጠገን፣ ማደስና ማሻሻል አንዱ ነው። 

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሥነ ሀብታዊና ማኅበራዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ በሚችሉና የገበያ ክፍተትን ለመሙላት በሚረዱ በጤና፣ በግንባታ፣ በማዕድን፣ በኃይል፣ በግብርና፣ በመጓጓዣ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ልዩ ልዩ የካፒታልና የፍጆታ ዕቃዎችንና መለዋወጫዎችን ማምረት፣ መጠገን፣ ማደስና ማሻሻል ሌላው ተልዕኮው መሆኑን ደንቡ ያመለክታል። 

ያመረታቸውን ምርቶች በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች መሸጥና የድኅረ ሽያጭ አገልግሎቶችን መስጠት፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ፈጣን ልማት የሚያግዙ ተጨባጭና የወደፊት ፍላጎቶችን በማጥናትና በመተንተን ምርትና አገልግሎትን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማምረት ሌላው የተቋሙ ተልዕኮ መሆኑን ደንቡ ይደነግጋል።

የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ ሕግጋትና መመርያዎች መሠረት አድርጎ የገንዘብ ሚኒስቴርን በማስፈቀድ ቦንድ መሸጥ፣ በዋስትና ማስያዝ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የገንዘብ ምንጮች የብድር ውል መደራደርና መበደር እንደሚችልም ማቋቋሚያ ደንቡ ይፈቅዳል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው ደንብ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 183/2002 እናዝቋላ ስቲል ሮሊንግ ሚል ድርጅት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 26/1998 ሥር ያሉ መብትና ግዴታዎች፣ ለኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተላልፈው ደንቦቹ መሻራቸውን ይደነግጋል። 

በዚህም መሠረት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንናአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ኢንዱስትሪ ሥር ሲተዳደሩ የነበሩየብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ፣ የኅብረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ፣ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ኢንዱስትሪ፣ የሀይቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የኢንፍራስትራክቸር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ፣ የኢትዮ ፕላስቲክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የምርምርና ልማት ማዕከልና የዝቋላ ስቲል ሮሊንግ ሚል ድርጅት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አባል ድርጅቶች ሆነዋል። 

ሌሎቹ በሜቴክ ሥር የነበሩት ወታደራዊ ምርቶችን የሚያመርቱት እንደ ጋፋት አርማመንት ኢንጂንሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የደጀን አቪዬሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና የመሳሰሉት ድርጅቶች የሚኒስትሮች ምክር ቤት 2012 ዓም ባወጣው ደንብ ወደ ተቋቋመው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መተላለፋቸው ይታወቃል። 

የቀድሞው ሜቴክ ችግሮች ወደ አደባባይ እንዲወጣ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው፣ በአገሪቱ የስኳር ፋብሪካዎች ላይ የታየው የሀብት ብክነትና የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮች መሆናቸው ይታወቃል። 

እነዚህ ችግሮች ተዳፍነው ከርመው በስተመጨረሻ፣ ‹‹ችግሩ ከአቅማችን በላይ ነው›› ብለው የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያውቀው ያደረጉት፣ ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ እንዳወቅ አብቴ (ኢንጂነር) እና በወቅቱ እሳቸው የሚመሩት ማኔጅመንት አባላት የነበሩ አመራሮች እንደሆኑ በስፋት መዘገባችን ይታወሳል። በዋና ስራ አስፈጻሚነት ህይወት ሞሲሳ (ኢንጂነር) እየመሩ ናቸው።

አቶ እንዳወቅ (ኢንጂነር) ከስኳር ኮርፖሬሽን ተነስተው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባነት ላለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታ ካደረጉ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ከአንድ ወር በፊት የሜቴክ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ሾመዋቸዋል። 

በመሆኑም አቶ እንዳወቅ (ኢንጂነር) እንደ አዲስ የሚቋቋመውን ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የሚመሩ ሲሆንየቀድሞውን ሜቴክ የሀብት አጠቃቀም ውጤታማ የማድረግና ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር የማስቻል ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። 

የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚበኋላም ምክትል ከንቲባ ሆነው ከማገልገላቸው አስቀድሞ በሜቴክ ሥር ይተዳደሩ ከነበሩት ድርጅቶች በአንዱ ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት እንዳገለገሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች