Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጠ

በአቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጠ

ቀን:

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ላለፉት ሁለት ወራት በእስር ላይ በሚገኙት የኢዴፓ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው ላይ የተመሠረተው ክስ ዋስትና ያስከለክላልና አያስከለክልም በሚል መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ክርክር ላይ ውሳኔ ለመስጠት የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጠ፡፡

የዞኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ልደቱ የጦር መሣሪያ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1177 አንቀጽ 22(3) ድንጋጌን ተላልፈው፣ ያልተፈቀደ የጦር መሣሪያ የመያዝ ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ መስክረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. መመሥረቱ ይታወቃል፡፡

የተጠቀሰባቸው የሕግ ድንጋጌ ዋስትና ስለማያስከለክል ሕገ መንግሥታዊ የሆነው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠበቆቻቸውና አቶ ልደቱ ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ በአዳር ለመስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ፍርድ ቤቱ ከሰዓት በፊት ቀጠሮ ሰጥቷቸው አቶ ልደቱ የቀረቡ ቢሆንም፣ ዳኞች ሊሟሉ ባለመቻላቸው የዋስትና ጉዳያቸው የታየው ከሰዓት በኋላ ሲሆን፣ አቶ ልደቱ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት በዋስትናቸው ጉዳይ ላይ ክርክር ሲያቀርቡ ዓቃቤ ሕግም ዋስትናውን በመቃወም ተከራክሯል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው መቃወሚያ አቶ ልደቱ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮችን እንደሚያስፈራሩበትና ለሕክምና በሚል ወደ ውጭ አገር ቢሄዱ ሊመለሱ ስለማይችሉ የዋስትና መብታቸው ሊከበር እንደማይገባ በማስረዳት ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በችሎት እንደገለጸው፣ ተከሳሹ መሣሪያ በእጃቸው በሌለበት ሁኔታ ምስክሮች ያስፈራራሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሕክምናን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ባነሳው መከራከሪያ ላይ መከራከሪያ ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ ለተከሳሹ ፈቅዶ ተከራክረዋል፡፡

ለሕክምና ወደ ውጭ ሄደው እንደማይቀሩ የገለጹት አቶ ልደቱ የፌዴራል ፖሊስ ስልክ ደውሎ ሲጠራቸው ያለምንም ማንገራገር ቢሮው ድረስ ሄደው እጃቸውን መስጠታቸው ለሕግ ተገዥ መሆናቸውን ማሳያ መሆኑን እንደተናገሩ በችሎት መታደማቸውን ለሪፖርተር የገለጹት የአዴፓ ሊቀመንበር ተናግረዋል፡፡

የመኢአድ መሥራችና ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ 20 ዓመታት ተፈርዶባቸው እንኳን በውጭ አገር ሄደው መታከማቸውን ያስታወሱት አቶ ልደቱ፣ የሕክምና ጉዳይ ከሕይወት ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደማይከለከል አስረድተዋል፡፡ በውጭ አገር ሄደው መታከም ባይችሉ እንኳን አገር ውስጥ ባሉ የሕክምና ተቋማት መታከምና ሕመማቸውን መከታተል እንዲችሉ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጠበቆቻቸውም ሰፊ ክርክር ማድረጋቸውን ሊቀ መንበሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. መርምሮ በማግሥቱ ውሳኔ እንደሚሰጥ ቀጠሮ መስጠቱም ታውቋል፡፡

አቶ ልደቱ ከድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ በቢሾፍቱ ከተማ ያሉ ወጣቶችን በገንዘብ በመደገፍ ብጥብጥና ሁከት እንዲነሳ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ቤታቸው ሲፈተሽ ፈቃድ የሌላቸው ሁለት ሽጉጦች መገኘታቸውንና ሁለት ሰነዶች መገኘታቸውን መርማሪ ፖሊስ ለከተማው ፍርድ ቤት በማሳወቅ ተጨማሪ የምርምራ ጊዜ ሲጠይቅባቸው መቆየቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...