Wednesday, October 4, 2023

ጤና ሚኒስቴር አገር አቀፍ ምርጫንና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ እንደሚቻል አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ፖለቲከኞች ታስረው ምርጫው እንዲካሄድ መፈቀድ የለበትም የሚል ተቃውሞ ቀርቧል

ጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ እየጨመረና የማኅበረሰብ ጤና ሥጋት ቢሆንም፣ አገር አቀፉን ምርጫ በጥንቃቄ ማድረግ እንደሚቻል የሚገልጽ ምክረ ሐሳቡን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ። 

ከአገር አቀፍ ምርጫ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች፣ የስፖርት ውድድሮችም ሆኑ ሌሎች ነዋሪዎችን በብዛት የሚያገናኙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም ተገቢ ጥንቃቄ እየተደረገ ሊከፈቱ እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። 

የኮሮና ወረርሽኝ የጋረጠውን የጤና ሥጋት ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት፣ ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ በወቅቱ ማካሄድ ባለመቻሉና በሕዝብ የተመረጡ ምክር ቤቶች ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ዘመናቸው መገባደጃ በመቃረቡ፣ ምክር ቤቶቹ ምርጫ እስከሚካሄድ መቀጠል ይችላሉ ወይስ አይችሉም በሚለው ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጉዳዩን በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በኩል አስመርምሮ ጉባዔው የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ማፅደቁ ይታወሳል። 

በዚህም መሠረት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የሥልጣን ርክክብ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤቶችና የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲቀጥል የሕገ መንግሥት ትርጉም መስጠቱ ይታወሳል። 

በተጨማሪም ምርጫው የሚካሄድበትን ወቅት የተመለከተ ውሳኔ በሰጠው ትርጓሜ ማካተቱ ይታወቃል።  በዚህም መሠረት ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የጤና ድርጅቶች የሚያወጡትን መረጃ መሠረት በማድረግ፣ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የሳይንሱ ማኅበረሰብ አካላት፣ ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበትና ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ፣ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሄድ፤›› የሚል ውሳኔ ሰጥቷል። 

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሠ (/) መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ለተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ የኮሮና ወረርሽኝ አሁንም የማኅበረሰብ ጤና ሥጋት ቢሆንም አገር አቀፍ ምርጫው መካሄድ እንደሚችል ገልጸዋል። 

ወረርሽኙ አሁንም የጤና ሥጋት ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበሩት ልምዶች አንፃር ከፍተኛ አለመሆኑን፣ኮሮና ወረርሽኝ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ ስለሚችልና ምርጫው ሲራዘም ከነበርንበት ሁኔታ አንፃር ሲመዘን፣ አሁን ላይ የቫይረሱ ሥርጭትን ለመከላከል የተሻለ መረጃ መኖሩን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። 

ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ የመከላከል ሁኔታዎች በመኖራቸው፣ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ መሻሻል በማሳየቱ፣ የማስክና የሳኒታይዘር ምርት በአገር ውስጥ በስፋት በመኖሩ፣ የጤና ተቋማት ዝግጁነትና ግብዓት አቅርቦት በመሻሻሉ፣ የምርመራ ኪት ማምረትን ጨምሮ የላቦራቶሪ አቅም ማደግና የዘርፈ ብዙ ምላሽ በተሻለ ሁኔታ የሚገኝ በመሆኑ፣ እንዲሁም ወረርሽኙ እያለ ምርጫ ካካሄዱ አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ ምርጫውን ማከናወን እንደሚቻል ምክረ ሐሳባቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ምርጫውን ለማካሄድም ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው ሚኒስትሯ የገለጹ ሲሆንከእነዚህም አንዱ ከዚህ በፊት ከነበረው የምርጫ ሒደት በተለየ መልኩ ኮሮና ወረርሽኝን መከላከልን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብና ማስፈጸሚያ መመርያዎችን ማዘጋጀትና በተዘጋጁ ዝርዝሮች መሠረት በሁሉም ደረጃ በበቂ ዝግጅቶች ወደ ትግበራ መግባት የሚያስፈልግ መሆኑን የሚገልጽ ነው። 

በሁለተኛ ቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጡት ደግሞ ወረርሽኙ እያለ ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኝ ሥርጭት ሊከሰት ስለሚችልይህ ከተከሰተ በተለየ ሁኔታ መታየት ሊያስፈልግ እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ ይገባል የሚል ነው። 

ሚኒስትሯ ባቀረቡት ምክረ ሐሳቦችን ያካተተ አጠቃላይ ሪፖርት ውስጥ፣ የጤና ሥጋቱ እያለ ምርጫውንም ሆነ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ እንደሚቻል ለማስረዳት ከተጠቀሙባቸው ሳይንሳዊ አመክንዮዎች መካከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንበል መጠቀምና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የቫይረሱን ሥርጭት በመከላከል ረገድ ያስገኙትን ፋይዳ ነው። 

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ቢያንስ 25 በመቶ በመላ አገሪቱ ማስፈጸም ከተቻለ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀምን ቢያንስ 50 በመቶ ኅብረተሰቡ እንዲተገብር ማድረግ ከተቻለሌላ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ዕርምጃ ሳይወሰድ ሊደርስ የሚችለውን የቫይረስ ሥርጭትና ሞት 92 በመቶ መቀነስ ይቻላል። 

ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች የሰዎችን ስብስብ የሚጠይቁ የተለያዩ ተግባራትንና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ መፍቀድ እንደሚገባ የገለጹት ሚኒስትሯእነዚህ ሁኔታዎች ሲፈቀዱ ወረርሽኙን ከመከላለከል አንፃር በሚመለከታቸው አካላት ዝርዝር ደንብና መመርያ መውጣት እንዳለበትም ጠቅሰዋል። 

በተለይ ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው አስቀድሞ ጠንካራ ግብረ ኃይል በየደረጃው ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባት እንደሚኖርበት መክረዋል። 

ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትን አግባብ አስመልክቶም በመጀመርያ የበሽታው ሥርጭት በአንፃራዊነት ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ትምህርት እንዲጀመር ማድረግና ቀስ በቀስ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ማስፋትየተወሰኑ የትምህርት ክፍሎችን (ደረጃዎችን) በመጀመርያ ከፍቶ ቀስ እያሉ ክፍሎችን መጨመርበአንድ ክፍል ውስጥ የሚኖረውን የተማሪ ብዛት መቀነስ፣ የፈረቃ ትምህርትን ለተወሰነ ጊዜ እንዲጀመር ማድረግ የውኃና የሳሙና አቅርቦቶችን ማረጋገጥ የተወሰኑት ናቸው። 

የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆንከእነዚህ መካከል፣ በቀጣዮቹ ወራቶች የሚካሄዱ በርካታ የሕዝብ በዓላት አከባበር ላይ የሰዎችን ቁጥር መቀነስ እንደሚገባ አሳሰበዋል። 

በምክር ቤቱ የትግራይ ክልል ተወካይ የሆኑት አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ በበኩላቸው አገር አቀፍ ምርጫ አሁን ባለው ዝግ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ መከናወን የለበትም ብለዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በታሰሩበት፣ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ምርጫውን ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንደማያደርገው በመጥቀስየታሰሩት ፖለቲከኞች ሳይፈቱ ምርጫው መካሄድ የለበትም ብለዋል።

የጤና ሚኒስትሯና ባልደረቦቻቸው ያቀረቡትን ምክረ ሐሳብና አጠቃላይ የሁኔታ ሪፖርት ያዳመጠው ምክር ቤቱ፣ ጉዳዩ በዝርዝር ተመርምሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብለት ለሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

ምክር ቤቱ በሚቀርብለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ በመጪው ሳምንት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -