መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝን አስመልክቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ሥራ ላይ ያዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካበቃ በኋላ፣ ለወረርሽኙ ሲደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች ችላ ተብለው አሳሳቢ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ መጠጥ ቤቶች፣ ልኳንዳ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ የምሽት ክበቦችና የተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች ከመጠን በላይ በሰዎች እየተጨናነቁ ነው፡፡ እጅን በሳሙና ወይም በሳኒታይዘር ማፅዳት፣ አፍና አፍንጫን መሸፈን፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ሰዎች ከሚበዙባቸው ቦታዎች መገኘት መቆጠብና የመሳሰሉት የጥንቃቄ መመርያዎች በብዛት እየተጣሱ ነው፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የተጣለው ገደብ ተነስቶ አዲስ መመርያ ቢወጣም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትርፍ እየጫኑ ማጓጓዝ ተቆጣጣሪ የሌለበት እስኪመስል ድረስ በይፋ ሕግ እየተጣሰ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ትምህርት ቤቶች ደረጃ በደረጃ እንደሚከፈቱ ተሰምቷል፡፡ ትምህርት ቤቶች በሚከፈቱበት ጊዜ ሊኖር የሚችለው ሥጋት ከወዲሁ ያስፈራል፡፡ መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ያደረጋቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች መልካም ውጤት ማስገኘታቸው አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ የሚስተዋለው ግዴለሽነት ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ይመስላል፡፡ ለዚህም ሲባል የምርመራ አድማሱን ከማስፋት በተጨማሪ፣ እየተጣሱ ያሉ የጥንቃቄ መመርያዎች እንዲከበሩ ፈጣን የሆነ ቁርጠኝነት መኖር አለበት፡፡
መንግሥት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ በርካታ ዕርምጃዎችን በመውሰዱ የተፈራውን ያህል አደጋ ባይደርስም፣ አሁን የሚታየው አስፈሪ ሁኔታ ጥረቶቹን ሁሉ መና እንዳያስቀሩበት ማሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ በግልጽ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እግር በእግር በመከታተል አደጋውን መቀነስ ተገቢ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ትምህርት ለማስጀመር የሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ ሥጋት ስለሚፈጥር፣ በተቻለ መጠን በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታየውን ችላ ባይነት በማስተካከል የቫይረሱን ሥርጭት መግታት የግድ ይላል፡፡ ለበርካታ ወራት ከትምህርት ገበታ የተገለሉ ተማሪዎች ሲገናኙ የቫይረሱ ሥርጭት ሊስፋፋ እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ ትምህርት ሲጀመር በትምህርት ቤቶች ውስጥ የቫይረሱ ሥርጭት በመጨመሩ ለማቆም መገደዳቸው ይታወቃል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ጉዳይ በሚገባ ቢያጤነው መልካም ነው፡፡ መንግሥትም ሕዝቡን እንደገና ለፀረ ኮሮና ዘመቻ በአንድ ልብ ማንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ የቫይረሱ ሥርጭት ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ ባለባት ኢትዮጵያ፣ ወረርሽኙ የጠፋ እስኪመስል ድረስ ጥንቃቄዎች ችላ እየተባሉ ነው፡፡ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰቦችና የሙያ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎችም ጭምር እየታየ ያለውን መዘናጋትና ደንታ ቢስነት ማስቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሚኒስትሮች ብሔራዊ ኮሚቴ አሁን እየተስዋለ ያለውን አደገኛ አዝማሚያ በፍጥነት ማስቆም አለባቸው፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡም ጠፍቶ የነበረው ሥራ በመመለሱ ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ አሁን እየታየ ያለው ጥንቃቄ የጎደለው ድርጊት የባሰ ቀውስ እንዳያስከትል ትብብር ማድረግ አለበት፡፡ የጠፋ ገበያ ተገኘ ተብሎ የንግድ ቤቶችን በተስተናጋጆች ማጣበብ፣ ከዚህ ቀደም በአሜሪካና በአውሮፓ የታዩ ከቁጥጥር በላይ የሆነ የታማሚዎችና የሟቾች ቁጥር ሊያስከትል እንደሚችል መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት ያቆመ ይመስል የጥንቃቄ ዕርምጃዎችን ችላ ማለት የለበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሥፍራዎች በብዛት የሚስተዋለው እጅን ለማፅዳት ፈቃደኛ አለመሆን፣ አፍና አፍንጫን በአግባቡ አለመሸፈን፣ አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ፣ ሰዎች በብዛት በሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች አዘውትሮ መገኘት፣ እጅ ለእጅ መጨባበጥና መተቃቀፍ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን የጥንቃቄ መመርያ መጣስ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሕግ መተላለፍ ምክንያት ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ የሚያጠቡ እናቶችና ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ቤተሰቦች ለአደጋ እየተጋለጡ ነው፡፡ በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ሆነው የኮሮና ወረርሽኝን እየመከቱ ያሉ የጤና ባለሙያዎችም፣ በቫይረሱ ከመለከፍ አልፈው ውድ ሕይወታቸውን እያጡ ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም እየተስፋፋ ባለበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ ከዓለም የጤና ድርጅትና ከሚመለከታቸው የጤና አጠባበቅ አካላት የሚለቀቁ መረጃዎችን በአንክሮ መከታተል ችላ የማይባል ነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ መረጃዎችና ትንተናዎች ለማኅበረሰቡ አሁንም በፍጥነት መድረስ አለባቸው፡፡ ማኅበረሰቡም በተቻለ መጠን ምንጫቸው የማይታወቁ መረጃዎች ላይ ትኩረት እንዳያደርግና ቸልተኝነት እንዳያጠቃው፣ የሚመለከታቸው አካላት ያለ መታከት መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለጥንቃቄ የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ብሎ በአግባቡ መንቀሳቀስ ካልተቻለ፣ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምሥጉን ጥረቶች በሙሉ መና ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመቀነስና በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ይመከራል፡፡ በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው ሥፍራዎች አለመገኘት፣ አካላዊ ንክኪን ማስወገድ፣ በተቻለ መጠን ከአካባቢ ራቅ የሚሉ ሥፍራዎች የሚደረጉ ጉዞዎችን መግታት፣ በቫይረሱ የሚጠረጠሩ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ መርዳት፣ የግል ንፅህናን መጠበቅ፣ ተዓማኒነት የጎደላቸው አጓጉል ድርጊቶችን ማስወገድ፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥና የመሳሰሉት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቫይረሱን በተመለከተ የተጋነኑም ሆኑ የሚያጣጥሉ መረጃዎችን አለመቀበል፣ እንዲሁም ለአድልኦና ለማግለል የሚያበረታቱ ድርጊቶችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት ከዚህ ቀደም በአስቸኳይ አዋጁ አማካይነት ትምህርት ቤቶችን በመዝጋቱ፣ ስብሰባዎችን በማገዱ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ በማድረጉ፣ ወዘተ የበርካቶችን ሕይወት አትርፏል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ ማኅበራት፣ የግል ድርጅቶች፣ ድግሶችና የመሳሰሉ ዝግጅቶች ያሉባቸው ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙዚቃ፣ የቴአትር፣ የፊልምና የመሳሰሉት ዝግጅቶች ባለመከናወናቸው ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ ጠቅመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥጥር የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ተወጥቷል፡፡ ለምሳሌ በቦሌ ኤርፖርትም ሆነ በተለያዩ የየብስ መግቢያዎች የሚያደርገውን ቁጥጥር በማጠናከር፣ ተጠርጣሪዎችን ወደ ልየታ ማዕከል በፍጥነት እንዲገቡ በማድረግ፣ የምርመራ አቅሙን በማጠናከርና በዘመቻ ጭምር በርካታ ምርመራዎችን በማከናወን ትልቅ ሥራ ሠርቷል፡፡ ማኅበረሰቡም ሳል፣ ትኩሳትና መሰል ምልክቶች የሚታዩባቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ያለ ይሉኝታ በማስታወቅ ኃላፊነቱን ሲወጣ ነበር፡፡ በመገለል ፍራቻ ምክንያት የሚደበቁ ሲኖሩም በፍጥነት ሪፖርት በማቅረብ ዕገዛ አድርጓል፡፡ ማኅበረሰቡ በሰከነ መንገድ መረጃ ሲለዋወጥና ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲያደርግ፣ ሥርጭቱን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በሚገባ ማገዝ እንደሚቻል በተግባር አረጋግጧል፡፡ አሁን ግን በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ መዘናጋትና ችላ ባይነት በመፈጠሩ ስህተትን በፍጥነት ማረም ያስፈልጋል፡፡
ራስን ከወረርሽኙ በመከላከልና የሌሎችንም ጤንነት በመጠበቅ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለወረርሽኙ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ጥንቃቄውን የበለጠ ማጠናከር አለበት፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረገው ቁጥጥር መዘናጋት እንዳይታይበት፣ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሳያሰልሱ ማሠራጨት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በሥራ አካባቢዎች፣ በመኖሪያ ሥፍራዎች፣ በትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ በመዝናኛዎችና በመሳሰሉት የእጅና የአካላዊ ንክኪዎችን በከፍተኛ ደረጃ ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ በጤና ሚኒስቴርም ሆነ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካይነት የሚሰጡ መግለጫዎችን አሁንም በትኩረት መከታተል የግድ ይሆናል፡፡ መንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት፣ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉ ጥንቃቄ አልባ ድርጊቶችን መልሶ በመቃኘት የማስተካከያ ዕርምጃዎችን መውሰድ አለበት፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመርያዎች በግልጽ እየተጣሱ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የተገኙ ምሥጉን ውጤቶችን የሚያበላሹ ድርጊቶች እየተፈጸሙ፣ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በፍፁም አይቻልም፡፡ መጠጥ ቤቶች፣ ጫት መቃሚያዎች፣ ሺሻ ማጨሻዎችና የምሽት ክበቦች በሰዎች ተጨናንቀው እየዋሉና እያነጉ የሕዝቡን ሕይወት ከኮሮና ወረርሽኝ መታደግ አይቻልም፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የጥንቃቄ መመርያዎች እየተጣሱ የሕዝብ ሕይወት ለአደጋ እየተጋለጠ ነው፡፡ በመሆኑም ቀውስ እንዳይፈጠር መንግሥት በፍጥነት የማስተካካያ ዕርምጃ ይውሰድ!