Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናእነ አቶ እስክንድር ነጋ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደኅንነት ከታሰበ ዋስትናችን ተጠብቆ በምርጫ...

እነ አቶ እስክንድር ነጋ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደኅንነት ከታሰበ ዋስትናችን ተጠብቆ በምርጫ እንሳተፍ አሉ

ቀን:

ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ክስ የሕዝብ ሰላምንና የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል፣ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝና የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተዘጋጅተዋል በማለት የዋስትና መብታቸው እንዳይፈቀድላቸው መከራከሩን በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ምላሽ የሰጡት እነ አቶ እስክንድር ነጋ፣ መንግሥት ወይም ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደኅንነት የሚያስብ ከሆነ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው፣ በመጪው አገራዊ ምርጫ እንዲሳተፉ መደረግ እንዳለበት ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ዋስትና እንዲከበርላቸው የጠየቁት፣ የተመሠረተባቸውን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብር ተግባራትና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አንደኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት መስከረም 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ካነበበላቸው በኋላ፣ ስለመብት የሚያነሱት ጥያቄ ካላቸው እንዲናገሩ ጠይቋቸው ነው፡፡

እነ አቶ እስክንድር የተከሰሱት በመጪው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ባሉበትና ሕዝቡም ድምፁን ሊሰጣቸው ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ሳለ  መንግሥት ውጥረት ውስጥ በመግባቱ መሆኑን ጠቁመው፣ ምርጫው በሕዝብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደኅንነት የሚታሰብ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ዋስትናቸውን አክብሮላቸው በምርጫው መሳተፍ እንዲችሉ ጠይቀዋል፡፡ ያ የማይሆን ከሆነ ግን ምርጫውም ቅቡልነት እንደማይኖረውና የሕዝብ ሰላምም የሆነ የአገር ደኅንነት እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

እነ አቶ እስክንድር የዋስትና መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት ደጋግመው ፍርድ ቤቱን የጠየቁት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊትና በተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ እስከ 25 ዓመታት ሊያስቀጣቸው ስለሚችል የዋስትና መብት ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ በመከራከሩ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን የዋስትና ጥያቄ በሚመለከት ባቀረበው የመቃወሚያ መከራከሪያ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ዋስትና ሕገ መንግሥታዊና መሠረታዊ መብት ነው፡፡ ቢሆንም ግን በሕግ አግባብ ሊከለከል እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) ተደንግጓል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 (1) ድንጋጌም ስለሚከለከልባቸው ምክንያቶች በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ድንጋጌው የተከሰሰ ሰው በፈጸመው የወንጀል ድርጊት ሰው ከሞተ፣ የሚሞት ከሆነ፣ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ውድመት መድረሱ ከታወቀ እንደሚል ጠቅሶ፣ ተከሳሾቹም በተሳተፉበት የወንጀል ድርጊት 14 ሰዎች መሞታቸውንና ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን በክሱ መጥቀሱን አስረድቷል፡፡

በመሆኑም የወንጀሉ ድርጊት እስከ 25 ዓመታት የሚደርስ ፅኑ እስራት ሊያስቀጣቸው እንደሚችልና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 67 (ለ) ድንጋጌም ለዋስትና መከልከያ ምክንያቶችን ካስቀመጠው ድንጋጌ አንፃር፣ የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት ስለማይኖረው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

ተከሳሾቹ የሕዝብ ስስ የሆነንና በቀላሉ ስሜት ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሃይማኖትንና ዘርን መሠረት ያደረገ የአመፅና የሽብር እንቅስቃሴ በማድረግ ‹‹ሥልጣንን በኃይል እንይዛለን፣ ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት አይኖርም፤›› በማለት ሕዝብን ለከፍተኛ ዕልቂት የሚያነሳሳና አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት መፈጸማቸውን አስረድቷል፡፡

 በመሆኑም ዋስትና ቢፈቀድላቸው ሕግ አክብረው ይገኛሉ የሚል ግምት ስለሌለው፣ የዋስትና ጥያቄውን በድጋሚ ተቃውሟል፡፡ የዋስትና መብት እንዴት መከበር እንዳለበትም የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ እንደሰጠበትም ቅፅና የመዝገብ ቁጥር ጠቅሶም አስረድቷል፡፡

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞትን ምክንያት በማድረግ በትግራይና በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ካስተላለፉት እርስ በርስ የሚያጨራርስ የአመፅ ጥሪና ተልዕኮ አንፃርም ወንጀሉ ከባድ በመሆኑ፣ ከአጠቃላይ የሕግ ድንጋጌና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ዓላማ አኳያ ሕግ መተርጎም እንዳለበት፣ የሕዝብንና የአገርን ደኅንነት ከመጠበቅ አንፃርም ዋስትና መፈቀድ እንደሌለበት ዓቃቤ ሕግ ደጋግሞ በማውሳት ተከራክራል፡፡

በሁለት ጠበቆች የተወከሉት አቶ እስክንድር፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ሥዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሴ የዓቃቤ ሕግ ክርክርን በመቃወም ተከራክረዋል፡፡ ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዓቃቤ ሕግ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(6) ድንጋጌ ጠቅሶ ዋስትና እንደሚከለክል አሳውቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የጠቀሰው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ትክክል ቢሆንም፣ ያ የሚሆነው በልዩ ሁኔታዎች እንጂ ሁሉንም ተከሳሾች የሚያጠቃልል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 (1) ድንጋጌ መተርጎም ያለበት፣ ከሕገ መንግሥቱ እንግሊዝኛ ትርጉም (. . . In Exceptional Circumstances Prescribed by Law) የሚለውን አጣምሮ መሆን እንዳለበትም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 63 (1) ድንጋጌን ሕገ መንግሥቱ በዝምታ እንደሻረው ጠቁመው፣ ምክንያታቸው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የፈቀደውን የዋስትና መብት የሥነ ሥርዓት ሕጉ ሊሽረው አለመቻሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንዳለው፣ ትርጉም ተሰጥቶት ዋስትና መከልከያ ከተደረገ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን መሆኑንም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ መሠረታዊ መብቶችን በሚመለከት ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ተቀብላ በማፅደቅ የሕጓ አካል ማድረጓን አስታውሰው፣ በደንበኞቻቸው ላይ የተጠቀሰው ዋስትና ማስከልከያ አንቀጽ መተርጎም ያለበት ከስምምነቶቹ ጋር በተጣጣመ መንገድ መሆኑንም ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡

ዋስትና የሚከለክለው ተከሳሹ ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ ሳይሆን  በዋናነት ከባህሪው ጋር በተገናኘና አደገኛ መሆኑ ሲረጋገጥ እንደሆነ የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ደንበኞቻቸው (እነ አቶ እስክንድር) ቋሚ አድራሻ ያላቸው፣ በመሠረቱት የፖለቲካ ድርጅት አገርና ሕዝብ ለማገልገል እየሠሩና በሕዝብ አመኔታን ያተረፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር ካልሆነ በስተቀር በደረቅ ወንጀል ተጠርጥረውና  ተሳትፈው የማያውቁ በመሆናቸው፣ የዋስትና  መብታቸው ተከብሮላቸው ከእስር ቢፈቱ ሌላ ወንጀል ሊፈጽሙ ወይም ከአገር ሊወጡ የማይችሉ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የዋስ መብትን በሚመለከት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ትርጉም እንደሰጠበት የጠቀሳቸው ውሳኔዎች፣ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው፣ የተለያዩ ሌሎች ትርጉሞች የተሰጡባቸውና ደንበኞቻቸው ከተከሰሱበት ክስ ጋር የማይገናኝ የክስ ሒደት ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች በመሆናቸው ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ገና ክስ አቅርቦ ሳለ እስከ 25 ዓመታት ያስቀጣል ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ በቀረበው ክስ ላይ ማስረጃ ቀርቦ፣ ተመዝኖና ከሕጉ ጋር ተገናዝቦ ፍርድ ቤቱ ትርጉም ሳይሰጥበት የደንበኞቻቸውን ነፃ ሆኖ የመገመት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጥስ በመሆኑ፣ ተገቢ አለመሆኑንና ሊታረም የሚገባው መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብላቸው ጠይቀዋል፡፡ ክሱ ተከሳሾቹን ከፖለቲካ ገለል ለማድረግ የተዘጋጀና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ክስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዲስ አዋጅ ቁጥር 1176 አንቀጽ 6(2) ድንጋጌን ጠቅሶ፣ አቶ እስክንድርንና በክሱ ስማቸው ቢጠቀስም በቁጥጥር ሥር አለመዋላቸው የተገለጸውን አቶ አሸናፊ አወቀና አቶ ፍትዊ ገብረ መድኅን (አቶ እስክንድር ሕዝብ ለማደናገር የተጠቀሰ ተከሳሽ ነው ብለውታል) የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት፣ ‹‹የሽብር ወንጀል ለመፈጸም መዘጋጀት›› የሚል በመሆኑ፣ የተፈጸመ ወንጀል እንደሌለ ከሚያሳይ በስተቀር ዋስትና የሚያስከለክል ተጨባጭ የተደረገ ነገር ስለሌለ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ይኼ ሆን ተብሎ የፍትሕ ሥርዓቱን ለመፈታተንና በፍርድ ቤቱ ላይ ጫና ለመፍጠር የቀረበ ክስ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ‹‹ወንጀል ለመፈጸም ሲዘጋጁ ነበር›› ተብሎ መሠረታዊ የሰዎች መብት መገደብ እንደሌለበትም ጠቁመዋል፡፡

የሦስት ልጆች አባት መሆኑን፣ ቋሚ አድራሻ ያለውና የሕዝብ አደራ ተቀብሎ ከዳር ለማድረስ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲያስከብርለት የጠየቀው ተከሳሽ ዳግም ስንታየሁ ቸኮል ነው፡፡ ሃይማኖትና ዘርን መሠረት ያደረገ ብጥብጥና ዕልቂት እንዲፈጠር፣ ሕዝብ ሰላም እንዲያጣና የአገር ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ መጠቀሱን አስታውሶ፣ ዓቃቤ ሕግ ካለው በተቃራኒ የሚሆነው እነሱ በመታሰራቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ የእነሱ መታሰር ሁከትና ብጥብጥ እንዲቀጥል የሚያደርግ እንጂ የሚያቆም እንዳልሆነም አክሏል፡፡ መታሰራቸው አገር ከመበጥበጥ ባለፈ እንዲረጋጋ እንደማያደርግም ጠቁሟል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች ቋሚ አድራሻ ያላቸው፣ የቤተሰብ ኃላፊና በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በሚሠራ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሕጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን አስረድቶ፣ ዋስትናቸው እንዲከበርላቸው ደጋግሞ ጠይቋል፡፡

ጌትነት በቀለ የተባለው ተከሳሽ የቀረበበት ክስ ለወጣቶች ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት፣ ለረብሻና ለአመፅ እንዲወጡ መመልመሉንና ማደራጀቱን የሚገልጽ መሆኑን ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡ ቄሮዎች በሌሉበት አብያተ ክርስቲያናትን ሊያቃጥሉ እንደሆነ በመግለጽ ነዋሪው እንዳይረጋጋ፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት እንዲነሳ መቀስቀሱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ መጥቀሱንና ይኼንንም ሲያደርግ የፊትና የኋላ ሰሌዳ ቁጥሩ በጭቃ የተሸፈነ ላዳ ታክሲ በመጠቀም መሆኑንም ጠበቆቹ አስታውሰው መቃወሚያቸውን አቅርበዋል፡፡

የዋስትና መብት ጉዳይ የሚመለከተው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ፣ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌና ከቀረበው ክስ ሁኔታ አንፃር መሆኑን ጠቁመው፣ በደንበኛቸው ላይ የቀረበው ክስና የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ እንደማይገናኙ ገልጸዋል፡፡ የክሱ ይዘት አይደለም ዋስትና ማስከልከል ተከራክሮ ለማስቀጣት የሚያስችል አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የተከሰሰ ሰው በሙሉ ዋስትና ይከለከላል ማለት እንዳልሆነና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌንም የሚጥስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብሔርን ከብሔር ወይም ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ እንቅስቃሴ በማድረግ የተከሰሰ ሰው ዋስትና እንደሚከለክል በግልጽ የተደነገገ ሕግ እንደሌለ ጠቁመው፣ የመኪና መስታወት መስበር የሚያስቀጣው 450 ሺሕ ብር በመሆኑ ዋስትና ሊያስከለክለው ይችላል ማለት ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ጠበቆቹ ተከራክረዋል፡፡

የቅጣት ጣሪያን መሠረት አድርጎ ዋስትና እንዲከለከል ክርክር ማቅረብ፣ የሰውን ልጅ መቀጣጫ ማድረግ መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ ክስና አንቀጽ ተዛምዶ በሌለበት ሁኔታ ከአሥር እስከ 25 ዓመታት ያስቀጣል ስለተባለ ብቻ መሠረታዊ የሆነው የዋስትና መብት ሊከለከል እንደማይገባ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ደንበኛቸው የሚጠየቀው በ450 ሺሕ ብር ቢሆን እንኳን ዋስትና ሊከለከል እንደማይችል፣ ዓቃቤ ሕግ የተረጋገጠ የሒሳብ ግምት ባላቀረበበት ‹‹ይኼንን ያህል›› በሚል ግምት ለማስከልከል መከራከር ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ የደንበኛቸው ዋስትና እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ በደንበኛቸው ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 240 መነሻ ቅጣቱ አሥር ዓመታት መሆኑንና መዳረሻው 25 ዓመታት መሆኑን በማስታወስ፣ ዓቃቤ ሕግ ገና ክርክር ሳያደርግና ከ15 ዓመታት በላይ ማስቀጣቱን ሳያረጋግጥ ‹‹25 ዓመታት ይፈረድባቸዋል›› በማለቱ ያቀረበው ክስ አመክንዮአዊም ሕጋዊም አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የተከሰሰን ሰው መረጃና ማስረጃ መርምሮና መዝኖ ቅጣት ሊወስን የሚችለው ፍርድ ቤት ሆኖ ሳለ፣ የተከሳሹን ነፃ ሆኖ የመገመት መብት በመተላለፍ ይፈረድበታል ማለት ተገቢ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡

ዜጋን ማሰርና በእስር ቤት እንዲማቅቅ ማድረግ እውነተኛ ፍትሕ ለማስፈንና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ከምትንቀሳቀስ አገር የማይጠበቅና ተገቢም እንዳልሆነ የገለጹት ጠበቆቹ፣ የዋስትና መብትን መገደብ ሕገ መንግሥቱን መጣስ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር መንግሥትን የሚያስጨንቅ አጀንዳ ማንሳታቸው፣ ለእስር እንደዳረጋቸው ድጋሚ ዕድል ሲሰጠው የገለጸው አቶ ስንታየሁ፣ የመንግሥትን ሥራ እንዲሠሩ የተመደቡ የከተማዋ ኃላፊዎች ሕገወጥ የመሬት ወረራ ሲደረግ ዝም ማለታቸውን ማጋለጥና በሕገወጥ መንገድ መታወቂያ ሲያድሉ ማጋለጥና መቃወም ‹‹በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ተንቀሳቅሰዋል›› ሊያስብል እንደማያስችል አስረድቷል፡፡  

መንግሥትን የሚያስጨንቅ አጀንዳ ማንሳታቸው ‹‹የጦስ ዶሮ›› እንዳደረጋቸው ጠቁሞ፣ ማስጨነቅና መታገል ሥራቸው በመሆኑ የሕግ አንቀጽ ባልተጠቀሰበት ሁኔታ ከ15 ዓመታት በላይ ስለሚያስቀጣ በሚል የዋስትና መብት መከልከል ተገቢ ባለመሆኑ እንዲፈቀድላቸው ጠይቋል፡፡

ዓቃቤያን ሕግ በቅርቡ የተሾሙ ከመሆናቸው አንፃር ከፍተኛ ጫና ውስጥ መሆናቸውን እንደሚረዱ የገለጸው አቶ ስንታየሁ፣ ፍርድ ቤቱ ግን ‹‹ይኼ ታሪካዊ የክስ ሰነድ በመሆኑ ሕግና ሕጉን ብቻ ተከትሎ በአግባቡ እንዲያይልን እንጠይቃን፤›› ብሏል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ዋስትና እንድንከለከል ቢከራከርም ወደፊት ዋጋ እንደሚያወራርድበት አውቆ በትክክል መሥራት እንዳለበት በመጠቆም፣ ‹‹የምንደፍረው ሕዝብም ሆነ የምንጣላው ሃይማኖት የለም፤›› ሲልም አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በተጠየቀው የዋስትና መብት ላይ ብይን ለመስጠትና በክሱ ላይ የመጀመርያ መቃወሚያ ለመቀበል፣ ለመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...