የሚያስረክቡትን ሒሳብ ወለድ ለራሳቸው እንዲጠቀሙበት ተፈቅዶላቸዋል
ሁሉም የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በደንበኞቻቸው ተከፍተው ለ15 እና ከዚያ በላይ ዓመታት የባለቤትነት ጥያቄ ሳይቀርብባቸው የቆዩ ተከፋይ ሒሳቦችን፣ ለኢትዮጵያ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስረክቡ ተወሰነ።
ውሳኔው የተላለፈው ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ መመርያ ነው። ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ሳምንት በፊት ያወጣው መመርያ በአሁኑ ወቅት ተፈጻሚ መሆን እንደጀመረም ለማወቅ ተችሏል።
ሁሉም ንግድ ባንኮች በሥራቸው የሚገኘውን ለ15 ዓመታት እና ከዚያም በላይ ለሆነ ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበበትን ተከፋይ ሒሳብ ለብሔራዊ ባንክ ካስረከቡ በኋላ፣ በዚህ ሀብት ላይ የሕግ ተጠያቂነት እንደማይቀርብባቸው መመርያው ይደነግጋል።
የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበበት ተከፋይ ሒሳብ ማለት ‹‹ለ15 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ተከታታይ ዓመታት የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበበት፣ በዋና ገንዘቡ ላይ የመጨመርም ሆነ የመቀነስ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ ወይም የገንዘብ ደረጃ ያለው ማንኛውም ተከፋይ ሒሳብ ነው፤›› ሲል መመርያው ትርጓሜ ሰጥቶታል።
በመመርያው መሠረት ሁሉም ባንኮች ከላይ የተቀመጠውን ትርጓሜ ያሟሉ በሥራቸው የሚገኙ ተከፋይ ሒሳቦች የተገለጸውን የ15 ዓመታት የጊዜ ገደብ ካሟሉበት ቀን አንስቶ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበበት ተከፋይ ሒሳብ መሆኑን የሚገልጽ ማስታወቂያ ተደራሽነት ባላቸው መገናኛ ብዙኃን ለተከታታይ ሦስት ሳምንታት እንዲያስተዋውቁ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሒሳቡን የከፈተ ግለሰብ ሊገኝበት በሚችል አድራሻና ስልክ ጥሪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የተከፋይ ሒሳቡ ባለመብት የመጨረሻው ማስታወቂያና ጥሪ በተደረገለት በ90 ቀናት ውስጥ ያልቀረበ እንደሆነ፣ ባንኩ የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበበትን ተከፋይ ሒሳብ ከአምስት ብር ጀምሮ ብሔራዊ ባንክ ለዚህ ብሎ በሚከፍተው የባንክ ሒሳብ ውስጥ የማስገባት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
ባንኮቹ የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበበትን ተከፋይ ሒሳብ ለብሔራዊ ባንክ ሲያስረክቡ፣ የሕጋዊ ባለመብቱን ሙሉ መረጃም ለብሔራዊ ባንክ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም የይገባኛል ጥያቄ ባለመቅረቡ ምክንያት ወደ ብሔራዊ ባንክ የተላለፉ ተከፋይ ሒሳቦችን መረጃ በድረ ገጻቸው ላይ፣ ለተከታታይ አሥር ዓመታት ለሕዝብ ተደራሽ አድርገው ማቆየት ይጠበቅባቸዋል።
ባንኮች የተጠቀሰውን ሥነ ሥርዓት አሟልተው ያስተላለፉትን የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበበት ተከፋይ ሒሳብ በተመለከተ የሕግ ተጠያቂነት እንደማይቀርብባቸው መመርያው የሚደነግግ ሲሆን፣ በተከፋይ ሒሳቡ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያለው ግለሰብ ጥያቄውን ማቅረብ የሚችለው ለብሔራዊ ባንክ እንደሆነም ይደነግጋል።
ጥያቄ ያልቀረበበት ሒሳብ ወለድ የሚከፈልበት እንደሆነና ባንኮቹ ለብሔራዊ ባንክ የሚያስተላልፉት ፍሬ ገንዘቡን ብቻ እንደሚሆን መመርያው የሚገልጽ ሲሆን፣ ተከፋይ ሒሳቡ ወለድ የሚከፈልበት ከሆነ ባንኮቹ ወለዱን የራሳቸውን ካፒታል ለማሳደግ እንዲያውሉት ይፈቅድላቸዋል።
ይህ በመሆኑም ባንኮች ወደ ብሔራዊ ባንክ ባስተላለፉት ተከፋይ ሒሳብ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ቢረጋገጥ፣ ባለቤቱ ከፍሬ ገንዘቡ ውጪ የወለድ ክፍያ እንደማያገኝ በመመርያው ተመልክቷል።
የባለቤትነት ጥያቄ ያልቀረበበትን ተከፋይ ሒሳብ የሚረከበው ብሔራዊ ባንክ ሀብቱን ጠብቆ የማቆየት፣ ሀብቱን ለብድር የማዋልና የተረጋገጠ ባለቤትነት ሲገኝ ደግሞ የመክፈል ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን በመመርያው ደንግጓል።
ብሔራዊ ባንክ መመርያውን ማውጣት ያስፈለገው የይገባኛል ጥያቄ ያልቀረበባቸው ተከፋይ ሒሳቦች፣ ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግና የባንክ ተጠቃሚዎችን እምነት ለማጎልበት እንደሆነ የመመርያው የመግቢያ አንቀጾች ይገልጻሉ።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የግል ባንክ ኃላፊ፣ እንደዚህ ዓይነት ለረዥም ዓመታት ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ ሒሳቦች ረዥም ዕድሜ ባስቆጠሩ ባንኮች ውስጥ እንዳሉ ገልጸዋል።
አዳዲሶቹ የግል ባንኮች ውስጥም ለረዥም ዓመታት ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ ተከፋይ ሒሳቦች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ነገር ግን በእነዚህ አዳዲስ ባንኮች ያሉት የማይንቀሳቀሱ ሒሳቦች በብሔራዊ ባንክ የወጣውን የ15 ዓመታት የጊዜ ገደብ አብዛኞቹ ላያሟሉ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
እንደዚህ ዓይነት ሒሳቦች በስፋት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊኖር እንደሚችል የገለጹት ኃላፊው፣ ይህም የሆነው ባንኩ ካስቆጠረው ረዥም ዕድሜና ሰፊ የደምበኞች ብዛት አንፃር መሆኑን ጠቅሰዋል። ባንኮች እንደዚህ ዓይነት ሒሳቦችን ከሚይዙባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ የአስቀማጩ በሕይወት አለመኖርና ሕጋዊ ወራሽነትን ማረጋገጥ አለመቻል ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ የብሔራዊ መመርያ አማካይነት ከሁሉም ባንኮች ሊሰበሰብ የሚችለው ሀብት አጠቃላይ ድምር ትንሽ ሊሆን እንደማይችል አክለዋል።