በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ ከተሞች የሚስተዋሉ ማኅበረሰባዊ ችግሮች አገራዊ መፍትሔ ይሻሉ፡፡ ወጣቶቻችንን ለአደገኛ ድርጊቶች የሚገፋፉ ችግሮች እየበዙ ነውና በዚህ ገጠመኝ መነሻነት ጉዳዩን ብናብላላው በማለት ነው፣ ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት የፈለግኩት፡፡ ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝኩ ነበርኩ፡፡ ድሬዳዋ የሄድኩበትን ጉዳይ አከናውኜ ወደ አዲስ አበባ የማደርገው ጉዞ የፈጠነው፣ በነጋታው ለሌላ አስቸኳይ ጉዳይ ወደ ጎንደር ስለምሄድ ነበር፡፡ ከድሬዳዋ የጀመርነውን ጉዞ እያገባደድን አዋሽ አካባቢ ስንደርስ የተሳፈርንበት አውቶብስ ጎማ ፈንድቶ ቆምን፡፡ ጎማ እስኪቀየር ድረስ ከአውቶቡሱ ወርደን እግሮቻችንን ስናንቀሳቅስ በድንገት ከአንድ የማውቀው ሰው ጋር ተያየን፡፡ ያንን ሁሉ መንገድ በአንድ አውቶብስ ስንጓዝ ባለመተያየታችን እየገረመኝ ሰላምታ አቀረብኩለት፡፡
በድንገት ያገኘሁት ይህ ሰው ከስቷል፣ ጠቁሯል ብቻ ከሰውነት ጎዳና ወጥቷል፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠን ካበቃን በኋላ ‹‹ምን ገጠመህ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ይልቅ አጠገብህ የተቀመጠው ሰው ከተባበረን እንጠይቀውና አብረን እያወራን እንጓዝ፤›› አለኝ፡፡ በዚሁ ተስማምተን አጠገቤ ለተቀመጠው ወጣት ይህንኑ ነግሬው በመስማማቱ ከዚህ ሰው ጋር አብረን ተቀመጥን፡፡ አውቶብሱ ጉዞ ሲጀምር የእኛም ወሬ ከቆመበት ቀጠለ፡፡
ይኼ የማውቀው ሰው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ሲሠራ በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ አብረን እንማር ነበር፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ በአንድ ታዋቂ አስመጪና ላኪ ድርጅት ውስጥ አብረንም ሠርተናል፡፡ ከዚያ በኋላ ይኼው ሰው የዲቪ ሎተሪ ደርሶት አሜሪካ መሄዱን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በኋላም አይቼው አላውቅም፡፡ ከተለያየን ቢያንስ 15 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ በሚጓዘው አውቶብስ ላይ ተገናኘን፡፡
‹‹ወንድሜ ምን አጋጠመህ? የት ነው ያለኸው?›› አልኩት፡፡ የዚህን ሰው የቀድሞ ገጽታ ለመግለጽ ያህል በጣም ቀይ፣ ቁመታም፣ ደልደል ያለ ውፍረት ያለውና በጣም ሳቂታና ተጫዋች ነበር፡፡ አሁን ግን ፊቱ ጠቁሯል፡፡ በጣም ከስቷል፡፡ ያ ፈካ ያለ ገጽታ ጠፍቶ ዓይኖቹ ቀና ብለው ለማየት አይደፍሩም፡፡ እንደምንም ትንፋሹን ሰብስቦ፣ ‹‹አሜሪካ ጉድ አደረገችኝ፤›› አለኝ፡፡ ይህን ሲነገረኝ አንድ ወጣት ልጅ እያየን መሳቅ ጀመረ፡፡ ለዚህኛው ግድ ሳልል የቀድሞውን ወዳጄን ማነጋገሬን ቀጠልኩ፡፡
በድጋሚ ‹‹እንዴት?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ አሁንም በግድ ትንፋሹን ሰብስቦ፣ ‹‹ቀን ከሌሊት የሠራሁባት አሜሪካ ገንዘቤንና ሚስቴ ነጠቀችኝ፤›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ገንዘቡንና ሚስቱን የምትነጥቅ አሜሪካ ከየት መጣች አልኩ ለራሴ፡፡ በውስጤ እየተገረምኩ፣ ‹‹ከዚያስ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ምን ከዚያስ አለ፣ በቃ ሚስቴ ያለ የሌለ ገንዘቤንና ንብረቴን ዘርፋ ካንዱ ጋር ስትኮበልል፣ በእሷ ስም የተመዘገበን ዕዳ በማላውቀው ዘዴ ወደእኔ በማስተላለፏ እኔ ወደ እስር ቤት አመራሁ፡፡ በእኔ ስም ያስመዘገበችውን ዕዳ መክፈል ባለመቻሌ ያለችኝን ጠራርገው ከወሰዱ በኋላ ሁለት ዓመት አሰሩኝ፡፡ ከእስር ስወጣ አቅሜ ደቆ ስለነበር ጎዳና ላይ ወደቅኩ፡፡ በስንት መከራ ወዲያ ወዲህ ብዬ ወደ አገሬ ጠፍቼ መጣሁ፤›› ሲለኝ ነገር ዓለሙ ዞረብኝ፡፡ እንዲህ ያለ ታሪክ ሰምቼም አላውቅ፡፡ ያ ወጣት አንገቱን እየነቀነቀ አሁንም ይስቃል፡፡
ይህ ወዳጄ አዲስ አበባ ከመጣ አንድ ዓመት እንዳለፈው፣ በብስጭት ምክንያት የማያውቀውን መጠጥ በላይ በላይ እየጠጣ ለሕመም መዳረጉንና በሳምባ በሽታ በመለከፉ መድኃኒት እየወሰደ መሆኑን ነገረኝ፡፡ ለጊዜው ዘመዶቹ ዘንድ አርፎ ሥራ ለመሥራት ቢሞክርም ቅስሙ በመሰበሩ ሥራ እንዳስጠላውም ነገረኝ፡፡ የአሜሪካው ነገር ከንክኖኝ ‹‹በሚስትህ ዕዳ እንዴት አንተ ተጠያቂ ሆንክ?›› አልኩት፡፡ በንዴት እያየኝ፣ ‹‹አገሩን ብታውቀው ኖሮ እንዲህ አትልም ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሚስቴ በሥራዋ አጋጣሚ ከአንድ ፖሊስ ጋር መቅበጥ በመጀመሯ ያ ሁሉ ሻጥር የመጣው በእሱ በኩል ነው፤›› አለኝ፡፡ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ወጣቱ ቀና ብሎ ዓይቶኝ አንገቱን ደፋ፡፡ አላውቀውም ምን ሆኖ ይሆን?
‹‹አሁን ምን አስበሃል?›› አልኩት፡፡ በግዴለሽነት ትከሻውን እየሰበቀ፣ ‹‹ልመንን ነው›› ሲለኝ ገርሞኝ እያየሁት፣ ‹‹የት ነው የምትመንነው?›› ማለት፡፡ እየሳቀ እያየኝ፣ ‹‹መርካቶ ምናለሽ ተራ›› ሲለኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ አዲስ አበባ ደርሰን ከአውቶብስ ስንወርድ አውቶብሱ ውስጥ ያየሁት ወጣት ጠጋ ብሎኝ፣ ‹‹ያለውን በሙሉ አትመነው የዕፅ ተጠቃሚ በመሆኑ ተጠርዞ የመጣ ወንድሜ ነው፤›› በማለት ሲነግረኝ በቆምኩበት ደንዝዤ ቀረሁ፡፡
ከአሜሪካ የመጣው ሰው እንዲህ ብልሽትሽቱ ቢወጣም፣ በአገራችን ውስጥ በርካታ ወጣቶች በአደገኛ ዕፅ ተለክፈው ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ነው፡፡ ለስንት ቁምነገር የሚጠበቁ ብሩህ አዕምሮ የነበራቸው ወጣቶች እንዳይሆኑ ሆነው እየቀሩ ነውና ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ትልቅ ብሔራዊ ምክክር ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ በርካታ ቤተሰቦች የዚህ ችግር ቀጥተኛ ተጠቂ በመሆናቸው በማኅበር ተደራጅተው ጭምር ውትወታና ጉትጎታ ቢጀምሩ ትልቅ አገር አቀፍ ንቅናቄ መፍጠር ይቻላል፡፡ ወገኖቼ እባካችሁ ይህንን ጉዳይ በቸልታ አንለፈው፡፡
(ኤርሚያስ ይትባረክ፣ ከፍላሚንጎ)