በታደሰ ሻንቆ
አንዳንድ ሰዎች ፖለቲካን ወይም ፖለቲካ መሥራትን እንደ እግር ኳስ፣ እንደ መጽሐፍ ማንበብና እንደ ጋዜጠኝነት ‹‹ነፍሴ ነው/እወደዋለሁ›› ሲሉ ሰምቼ ገርሞኛል፡፡ የሚሉትን ለመረዳት ሞክሬም አልሆነልኝም፡፡ በኢትዮጵያ እውነታ ቡትለካን እንደ መደበኛ መተዳደርያ መያዝ ወይም ትርፍ ጊዜን የሚያጠፉበት ተወዳጅ ዝንባሌ ሊሆን ስለመቻሉ ማሰብና መገንዘብ ለእኔ ይቸግረኛል፡፡
ፖለቲካ ውስጥ እፍ ብዬ የገባሁበት ታሪክ የጀመረው በዩኒቨርሲቲ ተማሪነቴ ጊዜ ነበር፡፡ ያም ቢሆን ከትምህርት ሥራ ውጪ የትርፍ ጊዜ ፍቅሬ ሆኖ ሳይሆን፣ የወጣትነት ሕይወትን ለፀረ ጭቆና ትግል የመስጠት ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ መጽሐፍ ንባቤ፣ የኢትዮጵያን እውነታና ታሪክ የመረዳት ጥረቴ፣ የጥናት ክበቦች ተሳትፎዬና ህቡዕ የፖለቲካ እንቅስቃሴን መቀላቀሌ፣ ትምህርት አቋርጬ ወደ ክፍለ አገር ‹‹ሥራ ተቀጥሬ›› መሄዴ ሁሉ ፖለቲካን በመውደድ የተመሩ ሳይሆን፣ በጊዜው እንደነበሩ ተራማጅ ወጣቶች ሕይወትን ለለውጥ ትግል በመስጠት የተመሩ ነበሩ፡፡ ምንም ያህል ጥፋት ቢሠራ፣ ያ ጊዜ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንዱን ከአንዱ ሳይለዩ በድቆሳ ኑሮው እየተቃጠሉ፣ ብሶቱን፣ ጉምጉምታውን እየሞቁና አዲስ ዘመን ይመጣል በሚል ተስፋ እየተበረታቱ፣ ተደራጅቶና አደራጅቶ ለማታገል መፍጨርጨር የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ትግሉ ምንቅርቅሩ ከመውጣቱ በፊት፣ የትግል ባልደረቦችን ለጊዜያዊ ጥቅም መሸጥ ይቅርና ላለመታሰር ይደረግ የነበረው ጥንቃቄም ሆነ ሲታሰሩ የነበረው ጭንቅ ከራስ ሕይወት ይበልጥ፣ ከግርፊያ ብዛት የትግል ባልንጀሮችን አሳልፎ ሰጥቶ ትግሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነበር ብል አጉል ማጋነን የሚሆን አይመስለኝም፡፡
በእኛው ጥፋት የከተማው ትግል ተንኮትኩቶ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አምባገነናዊ ሥልጣን ከተደላደለ በኋላ የነበረው ኑሮዬም ቢሆን ‹‹ከእንግዲህ ሩጫችንን ጨረስን››፣ ‹‹ፖለቲካን በሩቁ›› ብሎ የታጋይነት ‹‹ገድል››ን በትዝታ እያወሩ መንከትከት ማንከትከት ውስጥ የተገባበት አልነበረም፡፡ ወይም በደርግ ሰደድ፣ ኢሠፓአኮ፣ ኢሠፓ ውስጥ ገብቶ ስለ‹‹ጭቁኖች›› ነጋ ጠባ የሚያነበንብ የምላስ ‹‹አብዮተኛነትን›› ቦርጭ ማውጫ ወደ ማድረግ አልዞረም፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰው የኖረውን ባለሁለት ፈርጅ (የአንገት በላይና የአንገት በታች/የአደባባይና የጓዳ) ኑሮ መኖር ግድ ነበር፡፡ ቀን ቀን በሥራ ሥፍራና በመኖርያ አካባቢ ስብሰባዎች ውስጥ፣ ተራ ማመልከቻ በመጻፍ ጊዜ እንኳ ‹‹ቆራጡን መሪ›› ማወደስ ‹‹ኢሠፓአኮ/ኢሠፓ ይለምልም!›› እያሉ ማሳረግ፣ ከአደባባያዊ ሁኔታ ሲወጡና ከልብ ወዳጅ ወይም ከቤተሰብ ጋር ሲሆኑ ደግሞ ሌላ ኑሮ ኗሪ፣ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ፣ መሆንን መላቀቅ የሚቻል አልነበረም፡፡ ወጓን ከሳቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የመግባትና በፀረ አብዮትነት የመጠለፍ አደጋ አለ፡፡ ‹‹የአብዮቱ›› ቁንጥጫና የእንግልት አርጩሜ የትም ተባዝቷል፡፡ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ ሐኪም ቤት ሊታከሙ ቢሄዱ፣ ቀበሌ፣ ሱቅና ‹ሱፐር ማርኬት› ቢሄዱ፣ ዳቦ ልግዛ ቢሉ፣ መድኃኒት ቤት ቢገቡ፣ ተሳፍሬ ወደ ክፍለ አገር ልሂድ ቢሉ፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ የትም ቦታ አድልኦ፣ በሠልፍ መገተር፣ የዘመድ ሥራና ሌላ ጉስቁልና በሽበሽ ነው፡፡ በኮርፖሬሽን ሱቅ ውስጥ ዳቦ፣ መድኃኒት፣ ጨርቅ ለመግዛት ተሠልፎ፣ ወረፋ ደርሶ፣ ለሚገዙት ነገር ደረሰኝ ተጽፎ ለክፍያ ሲደርሱ ‹‹ዝርዝር ብር/ሳንቲም አምጣ›› ተብሎ ቲኬት መነጠቅና ዝርዝር ፍለጋ ደጅ ለደጅ መንከራተት እንኳ ያልገባበት ሥፍራ አልነበረም፡፡ ጉቦና ሌብነት እንደ አየር የትም ይገኛል፡፡ ታሞ የተኛ እንኳ ልብሱን፣ ሳንቲሙንና መድኃኒቱን የሚመነተፍበት ሁኔታ በጊዜ ሒደት ተስፋፍቶ ነበር፡፡ ይህንን ዓይነት የበደል አርጩሜ በሞላበት ሕይወት ውስጥ የቅርብ ተስፋ አጥቶ ከአጠገብ ለጠፋ ታጋይነትና ለትግል ባልንጀሮች ሥውር የሐዘን ልብስ ለብሶ፣ በየዕለቱ ከጧት እስከ ማታ በፀረ አብዮትነት ዛቻ፣ በድንፋታ፣ በአድልኦ፣ በጉቦ አለንጋ እየተገረፉና እየተበሳጩ መኖር፣ ቤትም ሲገቡ እንዲህ ሆንኩ እንዲህ ተደረኩ እያሉ በመቃጠልና በመርኮምኮም የቀኑን አበሳ መልሶ መኖር ነበር፡፡ ከቤተሰብ ገለል ብዬ የየዕለቱን ከአጠቃላዩ ጋር እያያያዝኩ አንዳንድ ነገር ልጫር ሲባልም፣ በጽሑፍ መልክ አስከፊውን ኑሮ ከእነ ብሽቀቴ መልሶ ከመኖርና ከማንጎራጎር ውጪ አይኮንም፡፡ በደርግ ዘመን ያሳለፍኩት ኑሮ ይህንን መሳይ ነበር፡፡
ከሥራ ሾልኮ እየጠፉ ሌላ ነገር በማባረር፣ ጉዳይ ባለመጨረስ፣ በቀጠሮ በማመላለስና ሰነድ በመደበቅ የሚነግደው ዝቅጥቅጡ የወጣው ሰው እንኳ ከእንግልትና ከብስጭት አያመልጥም ነበር፡፡ እሱ የሚበላውን ጉቦ ሌላ ቀማኛ በሚያዝበት መስክ ውስጥ እሱም ጉቦ እየሰጠ፣ እሱ በሰዎች ላይ የፈጸመውን እንግልት እሱም እየተቀበለ፣ በአንድ ጊዜ አብሻቂነትንና በሻቂነትን፣ በአንድ ጊዜ ገራፊነትንና ተገራፊነት የሚኖር ነበር፡፡ አብዮታዊ ነን ያሉ ትግሎች ድምጥማጣቸው ከጠፋ በኋላ፣ የሰደድ/የኢሠፓኦኮ/ የኢሠፓ አባል ሆኖ ስለጭቁኑ ሕዝብ ስለአብዮቱ ይነፋ የነበረው ጥሩምባም ቢሆን፣ የአብዮተኛነትም የፖለቲካኛነትም ባህርይ አልነበረውም፡፡ ‹‹ማርክሲዝም››ንም በየውይይት ክበቡና በየስብሰባው ማነብነብ ማርክሲዝም አልነበረም፡፡ ማርክሲዝምም፣ አብዮተኛነትም፣ ፖለቲካም እስከ ላይ ድረስ ሞቶ የእንጀራ ገመድና የመተዳዳሪያ ወግ፣ ልዩ ልዩ ዕድሎችን ማብሰያና ማግኛ የይለፍ ወረቀት ሆኖ ነበር፡፡ እናም በጥቅሉ ባለ ሁለት ነፍስ ሆኖ መኖር፣ የኢሠፓ አባል ሆኖ ቀን ማርክሲት ነኝ እያሉ ጓዳ ጓዳውን ፈጣሪን ማስታወስ፣ ጉቦ እንደሚሰጡ ሁሉ ጉቦ መገንጠልና የስርቆት ሽሚያ፣ ወዘተ ሁሉ የሚያሳፍር አልነበረም፡፡ ወፍ እንደ አገሯ እንደምትጮህ፣ በዘመኑ የኑሮ ዘዴ መጠበብ ተደርጎ ነበር የሚታየው፡፡ መንጠቅና መነጠቅ ካለበት ከዚህ የኑሮ ዘዴ ውጪ ልሁን ያለ ራሱን ጠቅሞ ሌላውን መጥቀም የማይችል “ፋራ” ተደርጎ የሚናቅ፣ የሚጠመድ፣ በዝውውር አማካይነት አይሆኑ ቦታ ሊወረወር የሚችል ይሆናል፡፡ በብቸኝነት መቆዘም ዕጣው ይሆናል፡፡ የእኔ ሕይወት እዚያም ውስጥ ነበር፡፡ ብቸኛ ሆኖ እኔና ያለሁበት ኅብረተሰብ የወደቅንበትን የአዘቅት ሕይወት ለመረዳት መሞከርና ከንፈርን እያኘኩ አንዳንድ ማስታወሻ መያዝም ፖለቲካኛነት አልነበረም፡፡
ፖለቲከኛ መሆን እንደ ፍልቅታ በውስጤ የተፈራገጠው በደርግ መውደቂያ ዋዜማና በወደቀበት አፍላ ጊዜ (እስከ 1984 ዓ.ም.) ነበረ፡፡ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ስለአገራችን ጉዳይ መወያየት በደርግ መውደቂያ ጀማመረኝ፡፡ ጭንቀቴንና ብሶቴን የሚጋራና ከእኔ በላይ የሚያወራ በሽ ነበር፡፡ ጭውውታችንንና ግንኙነታችንን መልክ አስይዘን ለአንዳንድ ነገር እንኳ ስለመሰናዳት ሲነሳ፣ ‹‹በዚህ በፋሽስት አገዛዝ ውስጥ እንዴት ሆኖ…፣ ምን ሰው አለና፣ የትግል ወኔያችን ሞቶ…፣›› የሚል ሰበብ መደርደር፣ ‹‹የሆዳችንን ከተጫወትን ትልቅ ነገር ነው›› ብሎ ማለት፣ ከእነ ጭራሹ የትግል ሽታዋ ከተነሳች ወዲያ በደረሰኩበት አለመድረስ ነበር የገጠመኝ፡፡
ደርግ ወድቆ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲያመራ ጀምሮ የቅዋሜ ‹‹ፖለቲካ›› በየመንገዱና በየቦታው ይቆላ ነበር፡፡ በምሠራበት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሙያ ማኅበር አመራር አባል ለመሆን ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ አብዛኛው የማኅበሩ አባላትና አመራሩ ሕወሐት/ኢሕአዴግን በማማትና በመቃወም የተዋጠ ነበር፡፡ የማኅበሩን አመራር ኮሚቴ የሚመራው ሰው የማኅበሩን ገንዘብ ለግሉ እያጎደለ፣ በቅዋሜ ትግልና በኢትዮጵያ ፍቅር የሚጦፍ ሰው ነበር ተዋናይ፡፡ ከዚህኛው ሰው በተለየ አፍላ አጋጣሚው አያምልጠኝ በሚል ብልጠት ሥልጣን የያዘውን አዲስ ኃይል መጠጋትን ትርታቸው አድርገው “ይቦተልኩ” የነበሩ ሰዎችንም ዓይቻለሁ፡፡ በእኔና በመሰሎቼ አካባቢ አዲሶቹን ሰዎች የመጠጋት ጥቅመኝነት ባይኖርም፣ ያገኘሁት ቦትላኪነት ከማውቀውና ከምናፍቀው የተለየ፣ በሁለት ቦታ ሊመደብ የሚችል ዓይነት ነበር፡፡ አንደኛው እኔም ጭምር ያለሁበት፣ ደከመኝ የማይል ግልጽ መተቻቸትና ክርክር ያልነበረበት፣ በእያንዳንዱ ጉዳይና ጽሑፍ ላይ በደንብ ተዘጋጅቶና ብትንትን አድርጎ የመወያየት ፍላጎትና የትግል ቃጠሎ ያልነበረበት (ሁሉ ነገር ቀዝቃዛ በቀዝቃዛ እርጋታ በእርጋታ የሆነበት)፣ የተወሰኑ ሰዎች የትግል መሰናዶ ሥራውንና ሩጫውን ተሸክመውልን ሌሎቻችን የታጋይነት ወጉንና የፖለቲካ ትንታኔ ማዕዱን ተቋዷሽ መሆን የምንፈልግበት፣ ፖለቲካ የሚባል ነገር ‹‹ወጉ አይቅረኝ›› ወይም ትርፍ አንጀት መሳይ የሆነበት ነበር፡፡ ሁለተኛው በስሜት መወራጨት፣ መናደድ፣ መብሰልሰል እንደ ልብ የሚራጭበት ግን የተገራ፣ በደንብ የተደራጀና በአግባቡ የበሰለ ሐሳብ የማይፈልቅበት፣ አሰር የበዛበት ግብታዊ ተናጋሪነትና መርኮምኮም ጥሬያቸውን ፖለቲካ የሆኑበት ሰፊ ዝንባሌ ነበር፡፡ በዚህ ዝንባሌ ውስጥ ፖለቲካ አመል ዓይነት ነገር ነው፡፡ የፖለቲካው ሰዎችም አመለኞች ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡
ያኮረፉትንና የጠመዱትን የበለጠ ለማስጠላት የሆነ ያልሆነውን ሁሉ እየቃረሙ፣ ሲያንስ ጨመርመር እያደረጉ፣ ማማትና ጥንብ እርኩስ ማውጣት፣ ሕወሐት/ኢሕአዴግን የሚታገል ፖለቲካ ሆኖ አረፈው፡፡ ሐሜተኛው ሁላ ተቃዋሚ ሆነ፡፡ ስለሕወሓት/ኢሕዴአግ በጎ ነገር ሲናገሩና የተሰነዘረውን የተቃውሞ ሐሜት ‹‹አይመስለኝም/ሐሰት ነው›› ሲሉ ወይም ለመተቸት ሲቃጡ ወዲያውኑ በጥርጣሬ መታየት ‹‹ይህ ሰው ሥውር ዓላማና ተልዕኮ ያለው እንዳይሆን ተጠንቀቁት…፣ ዘሩ ምንድነው?…›› የማይመጣ ማስደንበሪያና ማሽማቀቂያ የለም፡፡ ጠንካራ ፖለቲከኛነት (ኃይለኛ ተቃዋሚነት) ምርር ያለ ክፉ ክፉ ነገር መናገር ሆነ፡፡ ሚዛናዊና ጠያቂ ለመሆን መሞከር ደግሞ በአቋም የለሽነትና በወላዋይነት ይተረጎማልና ምን ይሉኝን ፈርቶ የሚያድር ቅልስልስ ነገር ሆነ፡፡ ከላይ እንደተለመደው በፓርቲ መዋቅርና በመሥሪያ ቤት አስተዳደር ዛቻና ግልምጫ፣ እንዲሁም በሬዲዮና በቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ መታፈን መደብደብ፣ ከሥርም እንደዚሁ፣ ጥርጣሬና ፍርጃ ውስጥ ከትቶ ለሐሜት ወረርሽኝ አሳልፎ በሚሰጥ ወሬኛነት መታፈን፡፡ ኢሕአዴግ ለአባልነት ጠይቆ እምቢ ማለት የፀረ ኢሕአዴግነትና የፀረ ሰላምነት ማረጋገጫ፡፡ በኢሕአዴጎች መሀል ሆኖ ኢሕአዴግ ሲሞገስ ዝም ማለት ተቃዋሚነት፡፡ ኢሕዴግን የሚያብጠለጥል ‹‹የግል›› ጋዜጣ/መጽሔት ይዞ መታየት ምርጥ የፀረ ኢሕአደግነት ምስክር ወረቀት፡፡ በዚያው ልክ ኢሕአዴግ በሚታማበት ሥፍራ ውርጅብኝ አለማዋጣትና ቁጥብ መሆን ሊያስጠረጥርና ሊያስገልል የሚችል ጥፋት ሆኖ ነበር፡፡ ደርግ ሄዶ ኢሕአዴግ ቢመጣም ከሁለቱ የአንዱ አንቋላጭ ያልሆኑ የእኔ ብጤ ሰዎች፣ ከብዙ ሰው ጋር እያወሩና እየሳቁ በብቸኝነት መቆራመድ አልቀረላቸውም፡፡
ዙሪያውን ህሊናን፣ ጨዋነትን፣ የእኩል አመለካከትንና መተሳሰብን የሚሸነቁጥ አርጩሜ እንደገና እየተባዛ መጣ፡፡ በብሔር መንጓለልና ማንጓለል በሥራ ቅጥር፣ በዕድገት፣ በሹመት፣ በጭማሪ፣ በዝውውር፣ በቤት ኪራይ፣ በቤት ዕጣ፣ ጥቅም ታስገኛለች በምትባል ነገር ሁሉ ታየ፡፡ ብሔር የለየ ድንፋታና ትዕቢት!.. ብሔር የለየ ፍርኃትና መሸቆጥቆጥ!.. ብሔር የለየ ዝምታ….. ሁሉን ነገር በብሔር ማሥላትና በብሔር ማሰብ፣ እነዚህን ነገረ ሥራዎች እየተመገበ የሚያድግ ብሔር ጠቀስ ድፍርስ ስሜት፡፡ በየመንገዱ፣ በየታክሲው፣ በየመሥሪያ ቤቱ ሁሉ የሚያጋጥም ራስንም እያኘከ የሚመዘምዝ ነገር ሆነና የብሔር ሥሌት የጓደኛነት ምርጫ ውስጥ እስከ መግባት፣ ለእኔ ብጤ ሳንቲም አዘጋገንን እስከ መወሰን ወረደ፡፡ መውረድ ብቻ አይደለም እንዲህ ያለው ጎሰኝት አፍን በመዝጋትና አንገት በመድፋት የማያመልጡት እስከ መሆን ሄደ፡፡ ዝም ቢሉና ላናደው/ላጥቃው ተብሎ የተሰነዘረን አንጓላይነት ከመጤፍ ባይቆጥሩ ‹‹ምን ቢኖረው ነው እንዲህ የሚጀንነው?›› ተብሎ ተንኮል በገቡበት እያሳደደ ይከተላል፡፡ ከሰው ጋር ሲያወሩ፣ በዝምታ በመንገድ ሲሄዱ፣ እቤት ውስጥ ተቀምጠው ቴሌቪዥን ሲያዩም፣ ጎሰኝነት በዓይንና በጆሮ እየገባ ይቧጥጣል፡፡ ስሜትንና የህሊና ሚዛናዊነትን ያደማል፣ ያሻክራል፡፡ ከዚህ ዓይነት መሸማቀቅ ማምለጥ የቻለ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ልዩነቱ የድቀት ደረጃውና መጠኑ የከፋ መሆንና አለመሆን ካልሆነ በቀር፡፡ ‹‹ፖለቲካችን›› በሁለት በኩል ዕድገት ማሳየት ያልቻለው ከአመል (ከዕለታዊ ሐሜት) እና በጅምላ ሚዛን ሰዎችን ከመመዘን አልፎ መሄድ ስላቃተው፣ በጥላቻና በአሉታዊ አመለካከት ከመበላት ራሱን መከላከልም ማከምም ስላልቻለ (በዝቅጠት መበሳበስን ኑሮው ስላደረገ) ይመስለኛል፡፡
ከሰው ጋር ሳይወያዩበት፣ ሳይከራከሩበት ወይም ከተግባር ጋር ሳይፈታተሹበት በሆድ የያዙት ዕውቀትና ሐሳብ አይቀመጥም፡፡ ፖለቲካ የሞተባቸውን አመለኞችንም ሆነ ሎሌ ‹‹ፖለቲካ››ን የኑሮ ማሻሻያ ዘዴ ያደረጉትን ተፀይፎ በዝምታ ልጻፍ፣ ላንብብ ያለም ከዚህ ችግር አያመልጥም፡፡ ዝምታ ዕውቀትና ሐሳብ ያስረሳል፡፡ የመወያየት ክህሎትን ያስጠፋል፡፡ ዝምታና መነጠል በበዛበት ሰው ዘንድ እንደ ጤና አዳምና ዳማከሴ መሰሉ ስም እንኳ አፍ ላይ አልመጣ ብሎ ‹‹ምን ነበር ይኼ …›› እስከ ማለት መዛግ ቅርብ ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያለ ሥጋት የልቤን ተናግሬ፣ ያልጣመኝን ተችቼና ተከራክሬ አድራለሁ ሲባል፣ ብዙ ሰዎች ከዚህ ለመሸሽ እውነተኛ ስሜታቸውን፣ ስድ ሐሜታቸውንና ጥላቻቸውን ይደብቁና ገብስ ገብሱን በማውራት ይቆጠባሉ፡፡ ልባቸውን ለማግኘት የእነሱን አመል ተቀላቅዬ ያሙትን ልማ ሲባል ደግሞ በሐሜታቸው ውስጥ ያለው ጥላቻና ጅምለኛነት (ምክንያታዊነትን የማይወድ አስተሳሰብ) እያዘናጋ ይላመዳል፡፡ ከሁለቱም የዕልቀት ጥርስ ለማምለጥ የሚደረግ መፍጨርጨር እጅግ ከባድ ነው፡፡ ‹‹እስከ መቼ ታፍኜ! እስከ መቼ አጎንብሼና ጥርሴን እኝ እያልኩ የውሽት ኑሮ!›› እያሉ መቃጠልና ‹‹የት አባቴ ልድረስ!›› ባይነት ራሱ ያኝካል፡፡ ጆሮና ዓይንህን ደፍነህ ብር ብለህ ጥፋ የሚል ስሜት እየለቀቀ ያሰቃያል፡፡ እየተርኮመኮሙም መጉበጥ አይቀርም፡፡ ለዚህ እኔና የማውቃቸው አንዳንዶች ተጨባጭ ምስክር ነን፡፡ መረጃ ነጥቦችን ማደራጀትና ደብተር ገልጦ መጀመር የሚያንከፈክፍና እምቢኝ የሚል ነገር ይሆናል፡፡ ጽሑፎቼ በአያሌው ሙሉ፣ ሽክና የሐበሻ ኮሶ የተቀዳለት ሰው ለመጠጣት ተቸግሮ ገባ ወጣ እያለ እንደሚንቆራጠጥ፣ ሽክናውን ቁጭ ብድግ እያደረገ እንደሚሰቃይ እየተሰቃየሁ፣ አቅቶኝ እያስቀመጥኩ እንደገና እልህና እፍረት ጎትጉቶኝ እያነሳሁ የተጻፉ ናቸው፡፡
በተለይ የለውጥ ጭላንጭል በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ታይቶ፣ ብዙ ስደተኛ ድርጅቶችና ሚዲያዎች አገር ውስጥ ገብተው ሥራ ከጀመሩ በኋላ፣ ዋል አደር ብሎ ጅምሩን ለውጥ መተክተክን ሙያቸው ያደረጉ ሚዲያዎች ሲከሰቱ፣ የእነሱን ምንተፍረት ማጣትና ኃላፊነት ያልፈጠረባቸው መሆን ለአጭር ጊዜ እንኳ መከታተል ጭንቅና ፍርኃቴ ነበር፡፡ ጣቢያቸውን ስከፍት ደግ ነገር እንዲያሰማኝ እየፀለይኩ ነበር፡፡ እንደፈራኋቸው የሚያባላ መርዛቸው ሲሞጀርብኝ ሐዘንና ብሽቀት እንቅልፍ አጥቶ እስከ ማደር ይጎዱኝ ነበር፡፡ ጭራሽ ጣቢያዎቹን መሸሽ አመጣሁ፡፡ ብሸሽም የእነሱ ወሬ በሰዎችና በሌላ መገናኛዎች በኩል ዞሮ ያገኘኛል፡፡ ‹‹በእንትና ጣቢያ ምን እንደተባለ ብነግርህ ታብዳለህ!›› ተብሎ ወሬ ሲጀመርልኝ፣ ‹‹አትንገሩኝ ይቅርብኝ›› ብዬ ‹‹መረጃ›› እምቢ እስከ ማለት ደረስኩ፡፡ እንደ ምንም አምጬና እስቲ ዛሬ እንኳ የተሻለ ቢያሰማኝ ብዬ ገና ከመክፈቴ ጋጠ ወጥ ነገር ጆሮዬ ጥልቅ ሲል ጣቢያ ቶሎ ብዬ መቀየር፡፡ የሸሸሁት መረጃ ውራጁ በዚያ በዚህ ብሎ ከጆሮዬ ገብቶ፣ ጻፍ ጻፍ የሚል እልህ ሲያቀጣጥልብኝ ደግሞ እንደገና የሸሸሁትን መረጃ ከውራጅ በተሻለ ደረጃ ለማግኘት መፈለግ ማፈላለግ፡፡ የሸሸሁትን ጣቢያ በየቀኑ እየከፈቱና እየበገኑ መቁለጭለጭ፡፡ መረጃውን ካገኘሁት በኋላ ደግሞ እንደ ኮሶ ይዞ መንቆራጠጥ፡፡ ሳይፈልጉ፣ በቀለበት አፍንጫን ተሰንጎ ለመጻፍ የመገደድ ዓይነት ጭንቅ ውስጥ መውደቅ፡፡ ካለቀ የመድኃኒት ቱቦ ውስጥ ሙጣጭ ነገር ፍጭጭ ለማድረግ ቱቦውን እያለቡ እንደ መልፋት ባለ ሁኔታ፣ የመጻፍ ፍላጎትንና ብርታትን ፍጭጭ የማድረግ ምጥ ውስጥ መግባት፡፡ አሁን የደረስኩት እዚህ ደረጃ ላይ ነው፡፡
አሁን የደረስኩበትን ደረጃና በወጣትነቴ የነበረኝን ሠርቶ ያለ መርካት ሙላት ሳስተያየው ልዩነቱ ‹‹በቃህ የምትችለውን አካፍለሃል፣ ሚዛንህን ስተህ ለፀፀት የማይመች ነገር ከመጫርህ በፊት ምሬትህንና መንገሽገሽህን ይዘህ ከፖለተካ ነክ ጽሑፍ ዘወር በል ይለኛል፡፡ ሲጀማምረኝ እውነትነቱን ልቤ ለመቀበል ይቸገር ነበር፡፡ ለ13 ዓመታት ያህል ያወራሁት ስለአንድ ነገር ነው፣ ተባብሮ ፈተናዎችን ስለማለፍ፡፡ ማድረግ ያለብንን እስካላደረግን ድረስ የጽሑፎቹ ዕርባና አያረጅም፡፡ በዚያ ላይ አሁን ጥይት ጥይት ወጣቶች በየሥፍራው ከኦሮሚያ፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከትግራይ፣ ከደቡብ፣ ወዘተ ተፈልቅቀው ዓይቻለሁና የሕዝብ አሳቢና ነፃ አውጪ ነን ይሉ የነበሩት ሕወሓታዊና ኦነጋዊ ፅንፈኞች ካባቸው ተቀዳዶ፣ በጥላቻና በጭካኔ ሕዝብ አፋጅተው መሬት ነፃ ከማወጣትና የተወሰነ ማኅበረሰብ ከመበቀል በቀር ምንም የሌላቸው ፀረ ሕዝቦች መሆናቸው በሰኔ 20ዎች ከተጋለጠ ወዲያ፣ የለውጡ መንግሥት ወደኋላ በማይመለስ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ቁርጠኝነት ገደል ተሻግሯልና ዝም ብለው የነበሩ የሰከኑ ምሁራንም ወደ ንቁ ሚና መዞራቸው ተሰምቶኛልና ራሴን የማሰናበቻው ጊዜው ከሙሉ ተስፋ ጋር አሁን እንደሆነ ተቀብያለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚም በሩቅም በቅርብም ላሉ የአገሬ ወጣቶች የአደራ ቃል አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አበሳና ታጋሽነት፣ እንዲሁም በሕግ የበላይነት ሥር የማደር ብሩህ ተስፋቸው የሚያንቆራጥጣችሁ ሁሉ ከያላችሁበት ተጠራሩ! ዕውቀትና ጥበባችሁን፣ ያልጨረጨሰ የልቦናና የአዕምሮ ጥሪታችሁን ከሩቅና ከቅርብ አስተባብራችሁ ተዓምር ሥሩ! ተገትሮ ቀርና ብጥስጣሽ ሩጫዎችን ተሻግራችሁ መሬትን ሳይሆን ሕዝቦችን አስማምቶ ነፃ ለማውጣት ባለ በሌለ ኃይላችሁ ተንቀሳቀሱ፡፡ ከሁሉ ቅድሚያ መሸካከርና ጥላቻን አጥባችሁ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለዕድገት መታተርን በሚያቆረቁዙ ሳንካዎች ላይ (በጥራዝ ነጠቅነት፣ በሐሳዊ አዋቂነት፣ በአጨብጫቢነት፣ በባዶ ቁንንነትና በባዶ መናናቅ ላይ) ዝመቱ! በኅብረተሰባችን ውስጥ ግሮ የማደር ንጣፍ አለ፡፡ የኅብረተሰባችን ግሮ የማደር ሥሪት ግን የሠለጠነ ብልጠት ያንሰዋል፡፡ የመንግሥት መሪነት ታሪካችንም እንደዚያው የጮካነት ማነስ ባለታሪክ ነው፡፡ ብልጠት ለዛሬም፣ ለነገና ለተነገ ወዲያም አትራፊና አዳጊ መሆንን አርቆ እያስተዋለ ሲሠራ ሠልጥኗል ማለት ነው፡፡ ቅርብ አዳሪ ብልጠትን አልምቶ (ወደ ርቆ ሂያጅ ኅብረተሰባዊ ንቃት ለውጦ) የልማት እንዝርት ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዚያ መነሻ የሚሆንና ልናሠለጥነው የምንችል የብልህነት ግርድፍ ጥሪት በኅብረተሰባችን ውስጥ አለን፡፡ ያለ ብልህነት (ያለ አርቆ አስተዋይ ብልጠት) የተመነደገ ኅብረተሰብ የለም፡፡
አርቆ አስተዋይ ብልጠት ውጤታማ የሚሆነው ደግሞ የቆሙበት መሬት ያለውን ጥሬ ጥሪትና ያለበትን ዘመን ሲያውቅ ነው፡፡ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን ውስጥ በጥቅሉ የውጭ ዕገዛንና ተገንነትን ከሕዝብ ታታሪነትና ከነቃ ብልጠት ጋር አዘማምዶ፣ ከኋላ ቀር ገበሬነት ወደ ኢንዱስትሪያዊነት የመሸጋገር ታሪክ በተሠራበት ተመሳሳይ ዘመን ውስጥ፣ ሲንጋፖርና ሆንግ ኮንግ በሚባሉ ከወደብነት የማይዘሉ ቁንጣሪ ሥፍራዎች ላይ ደግሞ የቅኝ ገዥነት ሥር ከነበረው ንግዳ ንግዳዊ ቅርስ ተነስቶ፣ የምዕራብ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች ተቀፅላና ተለጣፊ ሆኖ ወደ ኢንዱስትሪ የመሸጋገር ብልጥ ስኬት ተከናውኗል፡፡ በስተኋላ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ በባህረ ሰላጤው ውስን አካባቢዎች ላይ በዘላንነትና በዓሳ አጥማጅነት ጉያ ውስጥ የተገኘ የነዳጅ ሀብት ፀጋን ዘመናዊ ጥበብ፣ ዕውቀትና ሙያ እየገዙ የበረሃ ገነት የመገንባት ብልጠት ታይቷል፡፡
እኛ ያለንበት ዘመንና ጂኦግራፊያዊ ቀጣና የሚጠይቀን ብልጠት ደግሞ ከሌሎቹ የተለየ ነው፡፡ ዘመኑ ልዕለ ኃያላዊ ተገን ይዞ ማደግ የማይሠራበት፣ ዛሬ በሚታየው የቻይናና የአሜሪካ ግብግብ ውስጥ ገብቶ የአንዱ ታማኝ መሆን የማይጠቅምበት የትስስር ዓለም ነው፡፡ ከቀርነት የመውጣትና የመልማት ጉዳይ፣ በአገሮች ጉርብትና መሀልም ሆነ በእያንዳንዱ አገርነት ውስጥ ከጦርነትና ከትርምስ ርቆ የመተሳሰርና አቅምንና ተፍጨርጫሪነትን የማስተባበር ጉዳይ ሆኗል፡፡ ዘመኑ ይህንን ይጠይቅ እንጂ እኛ ያለንበት ቀጣና በጣም ሸርታታማ፣ ሞለጭላጫማና ሞገዳማ እንደ መሆኑ ፈተናው ከባድ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት ብዙ ማተት ሳያስፈልግ ከዓባይና ከተሻጋሪ ወንዞች ጋር ያለ የጥቅም ሽኩቻ አፀናሁ ያሉትን የጉርብትና አጋርነት ምን ያህል ሊያዋዥቅና ወደ ቋፍ ሊገፋ እንደሚችል (ስለህዳሴ ግድብና ስለዓባይ ሲያወሩ የእኔና የእኛ የሚባለውን ማሳሳት እንኳ ምን ያህል ነገረኛ ሊሆን እንደሚችል) ማስተዋል ይበቃል፡፡
ከውጭ ወደ ውስጥ በሚመጣ አቃዋሽነት ሳይላጉና ሳይቀረጠፉ ለመትረፍና ከጎረቤቶቻችን ጋር አብሮ ለመነሳት ዕድል የሚኖረን፣ በውስጥ ያለብንን የትርምስ ጣጣ አሸንፈን የልማት ማዕከል ለመሆን የሚያበቃ ብልጠት ካዳበርን ብቻ መሆኑም ቁልጭ ብሎ ታይቷል፡፡ የህዳሴ ግድብን የመጀመርያ የውኃ ሙሌት ማሳካት ምን ያህል ጭንቃችን እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ የውስጣችንን ቅራኔ ግብፅ እየተጠቀመችበት ይሆን? ተንኮልና ቅጥረኞች አስርጋ ታምሰን ይሆን? የቅርብ ጎረቤት ወታደራዊ ማኮብኮቢያ ሰጥቷት ወይ በረዥም ርቀት ሚሳይል የመመታት አደጋ ደርሶብን፣ የጦርነትና የትርምስ ገሃነም ውስጥ እንገባ ይሆን? ምን ያልተጨነቅንበት ነገር ነበር! ጭንቃችን ተጀመረ እንጂ ወደ ‹ነበር› ታሪክ አልተቀየረም፡፡ መንገዳገድ እስከ ቀጠልንና ብልህነት እስከ ተሙለጨለጨብን ድረስ መጨነቃችን ገና ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ሁሉ ጭንቀት ያደረሰን የውስጥ ገመናችንን አሸንፈን ለራሳችንም ለቅርብ ጎረቤቶቻችንም የልማት መተማመኛ የመሆን የተግባር ብልጠት በአግባቡ ስላልተቆናጠጥን ነው፡፡ የጎረቤቶቻችን አጋርነት የማያወላውልና የማይሸነቆር የሚሆነው ዙሪያውን በአለት ላይ (በጋራ ልማት ላይ) ከታነፀ ነው፡፡ የወጣቶቻችንና የመላ ኢትዮጵያ ሕዝባችን መትረፊያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሰላምን ተቆናጦ፣ ይህንን የነቃ ብልህነት ፈጥኖ ዕውን ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተደጋጋሚ እንደተነገረው ወደ ኋላ ከማየትና ትናንትና ውስጥ ከመልወስወስ ወጥተን ወደፊት በማየት አንድ ላይ ማበራችን መተኪያ የለውም፡፡
አሁን ባለን አያያዝ ብልጠታችንን ከማሠልጠን ይልቅ ከብልጠት ጋር ፀብ የገባን ነው የምንመስለው፡፡ ከመቼውም በተሻለ ነፃነት ውስጥ ተጋግዞ ለዘመነ ዴሞክራሲና ግስጋሴ መሥራት እየተቻለ፣ የመናቆርና የመጠፋፋት መጫወቻ መሆናችንና ንብረትና ቅርስ ላይ በቀል በመወጣት መታወራችን ይህንኑ ነው የሚያሳየው፡፡ ዓብይ አህመድ ብቅ ከማለቱ ከምኒልክ ግቢና ከፊት በር እስከ እንጦጦ ድረስ የሠራው ሥራም ያጋለጠው፣ በብልጠት ደረትና ዓይን ላይ ምን ያህል ተጋድመን እንደኖርንና አሁንም ገሚሶቻችን ለመባነን ፈቃደኛ እንዳልሆንን ነው፡፡ ቅርስ ተዘርፈናል እያልን ለማስመለስ እንጥራለን፡፡ በጓሮ በኩል ግን ዛሬም ድረስ እየሰረቅን እኛው ለፈረንጅ እንሸጣለን፣ ወይም ንዝህላል ሆነን እናስመነትፋለን፡፡ በዚያ ላይ ራሳችን ቅርስ በማውደም የተዋጣልን ነን፡፡ የምኒልክ ሐውልትን ለማፍረስ በተቃጣ ጊዜ ስንቃወም ለቅርስ አሳቢ እንመስላለን፡፡ ግን ለቅርስ ‹‹አሳቢነታችን›› የሌኒንን ሐውልት ምሯል? መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ግለሰባዊ ውዳሴውን በእኛ ላይ ያሰጣባቸው አስረጂ ቅርሶች፣ ፎቶዎች፣ ቅስቶች፣ ሥዕሎች አሉ? ከአዲስ አበባ እስከ ክፍለ አገሮች የነበሩ የአብዮት አደባባዮች ገጽታዎችን ከእነ አከባበራቸው ዛሬ የት ጋ ነው በምሥላዊ ቅርስነት የመዘገብናቸው? የአፄ ኃይለ ሥላሴን ውዳሴ ሊያስገነዝቡን የሚችሉት ሐውልቶች፣ ቤተሰባቸውን የጨመሩ ዓይነት በዓይነት ፎቶዎች (በግድግዳ ተሰቃይ፣ በደብተሮች ላይ፣ በባለመዝጊያ የፊት መስታወት ላይ፣ በእርሳስና በፊደል ላይ፣ በሚታተሙ መጻሕፍት መነሻ ገጽ ላይ…) ርዝራዣቸው አለን? መጽሐፍን ለንጉሡ በገፀ በረከትነት በማበርከት ጊዜ፣ ለንጉሡ አቤት በማለትም ሆነ በማወደስ ጊዜ ላይ ይውሉ የነበሩትን ቃላት፣ በንጉሡና በቤተሰባቸው ስም ይጠሩ የነበሩ ተቋማትን ዝርዝር ከእነ ምሥላቸው ለመዘክርነት እንዲያገለግሉ አደራጅተናል? እነዚህ ቅርሶች ሁሉም በነበሩበት ሥፍራ ሳይነኩ ለምን ያልቆዩ ባይባል እንኳ፣ በሥርዓትና በጥንቃቄ እየተነሱ ለመዘክርነት በታቀደ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከትክክለኛ የዓውድ ትርጓሜ ጋር ተሰድረው እንዲጎበኙ ቢደረጉ ኖሮ ለልማታችን ገቢ ከማጉረፋቸው ሌላ፣ በገዥዎቹ ውዳሴ ውስጥ የኖርነው ሰዎች ትውስታችን እንዳይበንን በጠቀሙን ነበር፡፡ ተወላጆቻችንም ስላላዩዋቸው ገዥዎቻችን ማንነትና ከሕዝብ ጋር ስለነበራቸው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ያልተዛባ ሥዕል ማግኘት በቻሉ ነበር፡፡
ልጆቻችን ከእኛ ከአሮጌዎቹ በላይ ለሁለቱ ዘመናት ቅርብ የሆኑ ይመስል፣ ዛሬ በድፍረት የኃይለ ሥላሴና የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አወዳሽ ሲሆኑ ለማየት የቻልነው በታተመ ታሪክ፣ በፊልምና በደረጀ ቤተ መዘክር ትናንትናን በአግባቡ እንዲገነዘቡ ስላላደረግን ነው፡፡ የኃይለ ሥላሴ ተመላኪነት ግብታዊ እስከ መሆን የጠለቀ፣ ልቦና ውስጥ የማይታይ ተቆጣጣሪ ፖሊስ የፈጠረ (ጃንሆይን እንደ ተራ ሰው ይሸናሉ ብሎ ለማለት እንኳ ሕፃናት የሚሰቀቁበት) እንደነበር፣ የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ተመላኪነት ከአደባባይ ዘወር ሲሉ በስድብ የሚቀወር፣ በፓርቲና የ‹ሕዝብ› ማኅበራትን ተቀጥላው ባደረገ የቢሮክራሲ መረብ አማካይነት የተጫነና ‹‹የሚከበር›› እንደነበር ምን ያህል የዛሬ ልጆቻችን ለይተው ያውቃሉ? ዶ/ር ዓብይ አህመድ ስለእንጦጦ መናፈሻ ባስተዋወቀን ጊዜ የቅጠል ለቃሚዎችን ሕይወት አደባባይ መውጣት ከመናፈሻው መሠራት ጋር ያያዘው የሕይወት ጉዟችንን ተከታትሎ፣ ለተከታዩ ትውልድ ህሊና የማሸጋገር ችግር እሱንም ስለዳበሰው ይመስለኛል፡፡ በቅርብ ትናንትናችን ውስጥ በነበረች አዲስ አበባ ውስጥ ቅጠል በእናቶቻችን ጀርባ ታዝሎ ገዥ ፍለጋ ከአንዱ ሠፈር አንዱ ሠፈር ሲዞር ይውል እንደነበር ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? የቅድሚያ ትዕዛዝ አልነበረም እንጂ አትክልት በቅርጫት፣ ዳቦ በቅርጫት፣ ጨፈቃ በሸክም፣ ወዘተ እየዞረ የብዙ ነገር ገበያ ደጃፍ ድረስ ይመጣ ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ያካተተ ትናንትናን ከዛሬ ጋር እያገናኙ የማሳየት ሥራ ልብ ወለዶቻችን፣ ፊልሞቻችንና መዘክሮቻችን መሥራት ይገባቸው ነበር፡፡ አሁንም ቢያንስ የኃይለ ሥላሴንና የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያምን ጊዜ በተመለከተ የዛሬው ትውልድ ትክክለኛ ሥዕል እንዲያገኝ የሚያስችሉ የጽሑፍና የምሥል መረጃዎች፣ እንዲሁም ቁሳቁሳዊ ቅርሳ ቅርሶች የሚቻለውን ያህል አሰባስቦ ለመዘክርነት ማሰናዳት ግድ ነው፡፡ የተሰናዳ የመረጃ ጎተራ ካለ የሥነ ጽሑፍና የፊልም ባለሙያዎችም የበለፀገ ሥራ ለመሥራት የመረጃ ደሃ አይሆኑም፡፡
ቅርስን እንደ አልባሌ ነገር የትም እየጣሉ ከማባከንና ከማውደም ተንከባክቦ፣ የታሪክ መስታወታችን አድርጎ በህሊናም በገንዘብም ወደ መጠቀም መዞር የሚሰምርልን፣ በፖለቲካም ረገድ ብልጠትን መጨበጥ ከቻልን ነው፡፡ ቆሞ ቀርነትን ቦትርፋችሁ ለወጣችሁና ብርሃን እያበራችሁ ላላችሁ የመላ ኢትዮጵያ ንቁ ወጣቶች ሁሉ! ይህንን አደራ እንደማትዘነጉ ባለኝ ተስፋ፣ ይህችን በተለያየ ጊዜ በግፍ የተደፉ ንፁኃንን የምታስብ ትንሽ መጽሐፍ ስለአዲስ ጧፍነታችሁ በስጦታ አበርክቻለሁ፡፡ እስከ ዛሬ የጻፍኳቸው የታሪክን፣ የፖለቲካንና የኢኮኖሚን መስተጋብር የነካኩ ጽሑፎቼ የእኔ ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አበሳና ተስፋ ትንተናዊ መዝገቦች እንደ መሆናቸው ከአስተማሪነታቸው ባሻገር በገቢ ምንጭነት ተጋድሏችሁን ለማገዝ ብትጠቀሙባቸው ሙሉ ፈቃዴ ስለመሆኑ ይህ ቃሌ ፈርማዬን ሆኖ ያረጋግጥላችኋል፡፡ በመጨረሻም ከደርግ ዘመን አንስቶ ጽሑፎችን በታይፕ (በስተኋላም በኮምፒዩተር) ላሠፈሩልኝ ሁሉ፣ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ውስጥ ጽሑፎቼን እጅ ለእጅ በማዳረስም ሆነ በኢንተርኔት ላይ ተጥደው ለመቀዳት እንዲችሉ ለተባበሩኝ ሁሉ፣ ከሁሉም በላይ በቂመኛ አገዛዝ የመጎሳቆል አደጋን ሳይፈሩ መለዘብ የሚችለውን እያለዘቡ፣ መቆረጥ ያለበትን እየቆረጡ በሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ ላይ ጽሑፎቹ እንዲወጡ ላደረጉ ለሪፖርተር አሰናጆችና ለሪፖርተር ጋዜጣ ከፍ ያለ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ የተማመነ ኅብረትና ነፃነት የሚያበራበት የግስጋሴ ጉዞ ለመላ የአገሬ ሕዝቦች!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡