Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገንዘብ ኖት ቅየራው በጎ ጎኖችና ውዥንብሮች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሞኑ የተቀየሩትን የገንዘብ ኖቶች ተከትሎች በርካታ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ እየተመደጡ ነው፡፡ ለውጡ ተገቢ እንደሆነ የሚገልጹ እንዳሉ ሁሉ ሥጋቶችንም የሚያንጸባርቁ ምልከታዎች አልታጡም፡፡

ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ ማኅበሩ ባወጣው መግለጫ መሠረት የመገበያያ ገንዘቦች መለወጣቸው የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ትሩፋቶች አሉት፡፡ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብን ብሎም ቁጠባን ሊያሳድግ መቻሉ፣ የተጭበረበሩ የብር ኖቶችን ከገንዘብ እንቅስቃሴ ማስወገድ ማስቻሉ፣ ሕጋዊ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውርን ከኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ማስወገዱ፣ በታክስ መረቡ የሚታቀፈውን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማሳደግ መቻሉ፣ የባንክ ሒሳብ የሚኖራቸውን ዜጎች ቁጥር በማሳደግ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ተደራሽ ማድረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊታዩ የሚችሉ የለውጡ ትሩፋቶች ስለመሆናቸው ማኅበሩ አውስቷል፡፡

በመካከለኛና ረዥም ጊዜ ሊታዩ ስለሚችሉ አዎንታዊ ጉዳዮችም ማኅበሩ ሐሳቦቹን አጋርቷል፡፡ የታክስ አስተዳደሩን በማሳለጥ የመንግሥት ገቢ እንዲያድግ ማገዙ ከመገበያያ ገንዘቦች ለውጥ ጋር ሊመጣ እንደሚችል የሚጠበቅ ውጤት ነው፡፡ የንግድ አሠራርን በማዘመን የታክስ መሠረትን እንዲሰፋ ማገዙ ሌላኛው ጎኑ ነው፡፡ የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር ማገዙ፣ ኢንቨስትመንትን ማሳደጉ፣ በዜጎች እጅ በጥሬ ገንዘብ ይንቀሳቀስ የነበረ ወይም የተቀመጠ ገንዘብ ወደ ባንኮች እንዲመጣ ማድረጉ ከለውጡ ጠቀሜታዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በርካታ ገንዘብ ወደ ባንኮች መምጣቱ ያጋጠማቸውን የብድር ገንዘብ የአቅርቦት እጥረት በመቅረፍ ለኢንቨስትመንት የሚውል ብድር እንዲያድግ ማስቻሉም የገንዘብ ለውጡ ተጠባቂ ውጤት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ውስጥ ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ከባንኮች ውስጥ እንደሚዘዋወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስለ መገበያያ ገንዘቦች መለወጥ አስፈላጊነት ሲያብራሩ የኢኮኖሚውን ስብራት ለመጠገን የተወሰደ ዕርምጃ ነው ብለዋል፡፡ ይኸውም አብዛኛው ገንዘብ ከመንግሥት ወይም ከማዕከላዊው ባንክ ዕውቅና ውጭ መንቀሳቀሱ ብቻም ሳይሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ በጎረቤት አገሮች ውስጥ በስፋት እንደሚዘዋወር፣ ይህም ከኢኮኖሚው ባሻገር ለአገሪቱ ፀጥታ ጭምር ሥጋት መሆኑን፣ የወንጀል ማስፈጸሚያ መሣሪያ እየሆነ ችግር መፍጠሩን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ስለ ለውጡ ባብራሩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያውና ጦማሪው ዋሲሁን በላይም ስለ መገበያያ ኖቶች ለውጥ ጠቀሜታ ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚስት ቪው›› በሚለው የማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡ ከባንኮች ውጭ የሚንቀሳቀሰውን፣ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ወደ መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓቱ ለማስገባት፣ የባንኮችን የገንዘብ እጥረት፣ የቁጠባ መጠን ማሳደግና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል ያለው ጠማሪው፣ ለውጡ ግን የኢኮኖሚውን ሁሉንም ችግሮች ይፈታል ማለት እንዳልሆነ ያሳስባል፡፡

በሌላ በኩል ሥጋቶች እንዳሉም ይጠቀሳል፡፡ የኢኮኖሚክስ ማኅበር እንዳስቀመጠው ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ነባሮቹን የብር ኖቶች በአዲስ ለመተካት የሚወስደው ጊዜ ከተራዘመ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን ሊቀንሰው ስለሚችል፣ የለውጡ ሒደት ቢፋጠን የሚል ሐሳብ ማኅበሩ አቅርቧል፡፡ መንግሥት አብዛኛውን የመለወጥ ሥራ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ፣ ሙሉ ለሙሉ ግን እስከ ሦስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ አዳዲሶቹ የብር ኖቶች ኢኮኖሚውን እንደሚያንቀሳቅሱ አስታውቋል፡፡ ጠንካራ የሕግ መሠረት መዘርጋትና መተግበር ያስፈልጋል ያለው ማኅበሩ፣ ብሔራዊ ባንክ በዜጎች እጅ ሊገኝ የሚገባው የገንዘብ መጠን እንዲሁም ከባንክ ወጪ የሚደረገውን መጠን ለመወሰን የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ተገቢ ናቸው ይላል፡፡

ይሁንና በወጣው መመርያ መሠረት ዜጎች እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ከባንክ ውጭ ይዘው መገኘት ቢፈቀድላቸውም፣ በተለይ የፀጥታ አካላት ከዚህ በታች መጠን ያላቸው ገንዘቦች ይዘው በተገኙት ላይ ዕርምጃ ሲወስዱ እየታየ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የብሔራዊ ባንክ ገዥውና የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፣ ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. መግለጫ ለመስጠት ተገደዋል፡፡ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ድረስ ይዘው የተገኙ ዜጎችን አትንኩ ብለዋቸዋል፡፡ ከሰሞኑ የታየው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ በርካታ የነባር ገንዘብ ኖቶች እየተያዙ፣ ሰዎችም እየታሠሩ መሆናቸው ነው፡፡

ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ መገኘትን የሚከለክለው መመርያ የነዳጅ ማዳያዎችንና ሌሎችም ከፍተኛ የእጅ በእጅ ሽያጭ የሚያከናውኑ ተቋማትን እንደማይመለከት ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ይህ ይባል እንጂ ከፍተኛ ገንዘብ በእጃቸው የሚገኝ ዜጎች እንዲህ ባሉ ተቋማት በኩል ገንዘባቸውን ወደ ባንክ ለማስገባት ከሞከሩ፣ የንግድ ተቋማቱ የሽያጭ መጠን ታሪክ ክትትል ስለሚደረግበት በዚህ መንገድ ሙከራ ማድረግ አደገኛ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል፡፡

መመርያው ባንኮችን ብቻ የሚመለከት መስሏቸው በአነስተኛ ገንዘብ ተቋማት ወይም በማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች በኩል ገንዘባቸውን ለማስገባት ሲሞክሩ መታየታቸው ተጠቅሶ፣ እነዚህ ተቋማትም መመርያው የሚመለከታቸው በመሆኑ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ ሒሳብ በመክፈት ያከማቹትን ገንዘብ በታትነው ለማስገባት የሚሞክሩም እንዲታቀቡ ተነግሯቸዋል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ አሽርካሪዎች በተለይም ወደ ጅቡቲ በሚጓዙበት ወቅት እስከ 30 ሺሕ ብር ይዘው እንደሚወጡ፣ ሲገቡም እስከ አሥር ሺሕ ብር ይዘው መምጣት ሕግ እንደሚፈቅዳቸው በማስታወስ የፀጥታ አካላት ይህንን እንዲያከብሩ የባንክ ገዥውና ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አመላክተዋል፡፡

ይህም ይባል እንጂ በጥቁር ገበያ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ በተደረገ ክትትል በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ገንዘቦች እየተያዙ ነው፡፡ ፖሊስ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ለጥቁር ገበያ ምንዛሪ የቀረበ 100 ሺሕ ዶላር፣ አምስት ሚሊዮን ብርና ሌሎችም የውጭ መገበያያ ገንዘቦችን እንደያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር፡፡ ቤት ለቤት ከሚደረገው አሰሳ በተጨማሪ በተሽከርካሪዎች ላይ በሚደረግ ፍተሻም ከፍተኛ ገንዘብ እየታየ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

እንዲህ ያሉት ጉዳዮች ብቻም ሳይሆን፣ የ200 ብር አዲስ ኖት በሥራ ላይ መዋሉ ዜጎች በባንኮች ከማስቀመጥ ይልቅ ጥሬ ገንዘብ እንዲያዘዋውሩ የሚያበረታታ ሊሆን እንደሚችል የኢኮኖሚክስ ማኅበር ሥጋቱን አመላክቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሲንሸራሸሩ በሰነበቱበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና አሰጣጥ መድረክ ላይ የተናገሩትን ለማሳረጊያ ማውሳቱ የገንዘብ ለውጡን ጡዘት ሊያሳይ ይችላል፡፡ እንዲህም አሉ፡፡

‹‹ሰሞኑን የገንዘብ ኖት ከቀየርን በኋላ አዲስ አበባ ላይ የእንቅልፍ ክኒን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ይባላል፡፡ ብዙ ሰዎች መተኛት ተቸግረዋል ይባላል፡፡ ከፍተኛ የእንቅልፍ ኪኒን በመጠየቅ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት በእኛ ውስጥ ያሉ ሹማምንት ናቸው የሚችል ጭምጭምታዎች እየሰማን ነው፤›› በማለት በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያከማቹ፣ ተገቢውን ግብር የማይከፍሉ ሰዎችን በማስጠንቀቅ ታክስ አጭበርባሪዎችና የመንግሥት ሌቦች ባሏቸው ላይ መንግሥት የሚከተላቸውን አዳዲስ የቅጣትና የዕርምጃ ስልቶች፣ ለትጉሃንና ታማኞችም የታሰበውን ማበረታቻ ጠቆም አድርገዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች