የመገበያያ ገንዘብ ለውጥ መደረጉ በይፋ ከተነገረ በኋላ፣ ትግበራውን በአግባቡ ለማስኬድ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ ባንኮችም አዲሱን መገበያያ ገንዘብ በመቀበል ከሳምንቱ አጋማሽ ጀምሮ ለደንበኞቻቸው ማዳረስ ጀምረዋል፡፡
ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ጥቅም እንዳይሰጥ ለማድረግ መንግሥት የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በጥሬ ገንዘብ በሚፈጸም ግብይት እንደማይስተናገዱ ደንግጓል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ገንዘቦች በፀጥታ ኃይሎች እየተያዙ መወረሳቸው የብር ለውጡ ያስከተላቸው ክንውኖች ናቸው፡፡ በተለይም ባንኮች የብር ለውጡን በተመለከተ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባንኮች እንዳመለከቱት፣ ለዚሁ ሥራ ኮሚቴ ከማዋቀር ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት አሮጌዎቹን የብር ኖቶች በአዲሶቹ በመቀየር ላይ ናቸው፡፡
እስከ ዓርብ፣ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ሁሉም ባንኮች አዲሱን የብር ኖት ከብሔራዊ ባንክ ተረክበዋል፡፡ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ ቅርንጫፎቻቸውም በማሠራጨት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የነባሮቹ መገበያያዎች በአዲሶቹ መተካታቸውን አስመልክቶ ካነጋገርናቸው መካከል የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ አንዱ ሲሆኑ፣ ዳሸን ባንክ ከብሔራዊ ባንክ የተረከባቸውን አዲስ የብር ኖቶች በአዲስ አበባና አልፈው በሚገኙ ቅርንጫፎቹ በማሠራጨት ቅየራውን በጥንቃቄ እያካሄደ ነው፡፡ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘበነ እንዲሁም የኦሮሚያ ኢንተርናሸናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን ተመሳሳይ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከብሔራዊ ባንክ የተረከቡትን የብር ኖት ወደ ቅርንጫፎች የማዳረስና አዲሱን የብር ኖት ለደንበኞቻቸው የማዳረስ ሥራ እንዳከናወኑ ገልጸዋል፡፡
ባንኮች አዲሶቹን የብር ኖቶች ተቀብለው ከማሠራጨት ባሻገር፣ ብሔራዊ ባንክም በራሱ መንገድ የሚያሠራጨው መጠን እንዳለ ይገለጻል፡፡ ይህም በአጭር ጊዜ በተለይ ዋና ዋና በሚባሉ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ አዲሱ የብር ኖት ወደ ባንኮች ቅርንጫፎች ደርሰው አሮጌውን የብር ኖት የመተካቱ ሥራ በሰፊው ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባንኮች የገንዘብ ለውጡን ተከትሎ ቅርንጫፎቻቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንዲሠሩ አመራር መስጠትና መከታተል ስለሚጠበቅባቸው ይህንኑ ለመወጣትም የየራሳቸውን ዕርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ኃላፊዎቹ ይጠቅሳሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በገንዘብ ቅየራው ሒደት የሚያጭበረብሩ ወይም አጭበርባሪዎችን የሚተባበሩ ባንኮች ከተገኙ የማያዳግም ዕርምጃ ይወሰድባቸው በማለት ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያና መመርያ ከባድ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም የገንዘብ ቅየራውን የሚተገብሩት ባንኮች ለየቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆቻቸው ጥብቅ መመርያ እንዳስተላለፉ ማወቅ ተችሏል፡፡ ሐሰተኛ ሰነዶችና የተጭበረበሩ ኖቶች እንዳይገቡ፣ እያንዳንዱ የባንክ ደንበኛም ማስገባት ከሚጠበቅበት በላይ ይዞ እንዳይገኝ በንቃት እንዲሠሩና እንዲከታተሉ እየተደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አስፋው፣ ከብሔራዊ ባንክ የመጣው መመርያም ለእያንዳንዱ ቅርንጫፍ እንዲደርስ መደረጉን፣ በዚህ ዙሪያ ለሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች አስቸኳይ ምላሽ የሚሰጥባቸው አሠራሮች መዘርጋታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የገንዘብ ኖቶቹን በተገቢው መንገድ የመየቀር ሥራውን የሚያስተገብሩ ኮሚቴዎች ዳሸን ባንክ እንዳቋቋመ ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ቅርንጫፍም ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመርያ ተከትሎ በጥንቃቄ እንዲሠራ፣ መመርያውም እንዲደርሰው ከማድረግ ባሻገር፣ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ለኃላፊዎቹ እንደተላለፈ አብራርተዋል፡፡
የገንዘብ ለውጡን በአግባቡ ለማስፈጸም በቂ ዝግጅት እያደረግን ነው ያሉት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ በበኩላቸው፣ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር (ዶ/ር) ጋር በየሦስት ቀኑ በስብሰባ በመገናኘት ስለትግራውና ሌሎችም ሁኔታዎች መረጃ እንደሚቀርብ፣ ሥራውን በአግባቡ ለማስኬድ ስለሚከናወነው እንቅስቃሴ በሁለቱ ወገኖች መካከል የመረጃ ልውውጦች እንደሚደረጉ ጠቅሰዋል፡፡ በጠረፍ አካባቢ በሚገኙ ቅርንጫፎች የሚገኙ ሠራተኞችም በምንም መልኩ ከጎረቤት አገሮች የሚገቡ ገንዘቦችን እንዳይቀበሉ ጥብቅ መመርያ ተላልፎላቸዋል ብለዋል፡፡ ‹‹ተጨማሪ ሠራተኞችን በእነዚህ ቅርንጫፎች መድበን ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ የብር ኖት ለውጡን በአግባቡ ለማሳለጥ እንደ ሌሎች ባንኮች ሁሉ ዓብይ ኮሚቴ በማቋቋም እየሠራን ነው፤›› በማለት አቶ ተፈሪ ስለሒደቱ ገልጸዋል፡፡
ዘመን ባንክም ለዚሁ ሥራ የሚሆን በፕሬዚዳንቱ የሚመራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ አዲሱን የብር ኖት ከብሔራዊ ባንክ በመቀበል በአዲስ አበባ በአብዛኛው የባንኩ ቅርንጫፎች ማሠራጨቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ አስታውቀዋል፡፡
‹‹መመርያው ለሁሉም ቅርንጫፎች ደርሷል፡፡ ከቅርጫፍ ሥራ አስኪያጆች ጋር ምክክርና ገለጻ በማድረግ በቂ ግንዛቤ ተሰጥቶ፣ ለውጡን እያካሄዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በገንዘብ ለውጡ ትግበራ ሒደት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ካሉም በቀጥታ መረጃ የሚለዋወጡት መስመር ባንኩ ስለማዘጋጀቱ ያስታወሱት አቶ ደረጀ፣ በለውጡ ሒደትና ትግበራ ላይ በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ለሚመጡ ደንበኞችም መረጃ በመስጠትና በማገዝ የገንዘብ ለውጡን እንዲያስፈጽሙ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት ባወጣው መመርያ መሠረት፣ የብር ለውጡ ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወራት መጠናቀቅ ይጠበቅበታል፡፡ ቢሆንም ባንኮች ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት አላቸው፡፡ የብር ለውጡ ግፋ ቢል ከአንድ ወር ተኩል ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ ይችላል የሚለውን አብዛኞቹ ይጋሩታል፡፡ አቶ ደረጀ እንደሚሉት የተቀመጠው የሦስት ወራት ጊዜ ረዝሟል በሚለው ላይ ብዙም አልተስማሙበትም፡፡ ‹‹ጊዜው ረዝሟል የሚሉ ሰዎች እንደየአመለካከታቸው ዕይታቸው ቢለያይም፣ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ማስገባት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ በአዲስ አበባና በክልል ክተሞች ላይ በቀላሉ የገንዘብ ልውውጡን ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ አካባቢዎች በሳምንት ወይም በአሥራ አምስት ቀን ውስጥ ይጠናቀቅ ቢባል ያን ያህል ችግር የለውም፡፡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በአንዳንዱ ራቅ ያለው የአገራችን ክፍል መረጃውን በትክክል ማግኘት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህን ታሳቢ ያደረገ የገንዘብ ቅየራ መካሄድ አለበት፤›› ይላሉ፡፡ አክለውም፣ ‹‹ስለዚህ የተሰጠው ጊዜ ረዝሟል አይባልም፡፡››
መመርያው ከያዛቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የብር ኖት ለመቀየር በተሰጡት 90 ቀናት ውስጥ ነባሮቹና አዲሶቹ ገንዘቦች መሳ ለመሳ ሆነው አገልግሎት ይሰጣሉ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኮች በጥሬ ገንዘብ መክፈል የሚችሉት እስከ አምስት ሺሕ ብር ብቻ ሲሆን፣ ከአምስት ሺሕ ብር በላይ ግን በተከፈተ የባንክ ሒሳብ ወይም አዲስ በሚከፈት ሒሳብ ማስገባት ግዴታ ሆኖ በመደንገጉ በዚሁ መሠረት እየተሠራ እንደሚገኝ ተብራርቷል፡፡
የብር ኖት ለውጡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች እየተሠራጨ ይገኛል፡፡ በመጪው ሳምንትም ከአዲስ አበባ ውጪ ወደሚገኙ ቅርንጫፎች በማሠራጨት ለውጡን በአግባቡ ማስተግበር ባንኮች የተጣለባቸው ግዴታ ነው፡፡ ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ያመቻል ያሉት አቶ አስፋው፣ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ የሚያስችል እንደሆነም ያምናሉ፡፡
የገንዘብ መቀየሪያው ሥርዓት በቅርቡ የወጡትን መመርያዎች ለመተግበር እንደሚያስችል አቶ አስፋው ጠቅሰዋል፡፡ ግለሰቦች በጥሬ ገንዘብ ከ200 ሺሕ ብር በላይ ከባንክ ማውጣት እንደማይችሉ፣ ኩባንያዎችም ከ300 ሺሕ ብር በላይ በጥሬ ማንቀሳቀስ እንደማይችሉ የሚደነግገውን መመርያ አንዱ ሲሆን፣ ከባንክ ውጪ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ መገኘት እንደማይቻል የወጣው መመርያ ይተገበር ዘንድ፣ አዲሱ የብር ኖት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የባንኮቹ ፕሬዚዳንቶች ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ ዋጋ ግሽበት ያሉ አገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ያምናሉ፡፡
የገንዘብ ለውጡና መመርያዎቹ የሚናበቡ በመሆናቸው ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በመጥቀስ፣ የመንግሥት ውሳኔ ኢኮኖሚውን ይታደገዋል የሚል ሐሳብም አካፍለዋል፡፡ በዚህ ሳይገደብ፣ የገንዘብ ዝውውሩን በቴክኖሎጂ በማገዝ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግም አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡፡
የገንዘብ ለውጡን አቶ ተፈሪ መኮንን ‹‹የዓመቱ ሰርፕራይዝ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለኢኮኖሚያችን ስብራት መጠገኛ መሣሪያ ነው፤›› ያሉት አቶ ተፈሪ፣ ምሥጢራዊነቱ እንደተጠበቀ የብር ኖቱን በአዲስ የለወጠበት ሒደት ትልቅ ግራሞት ፈጥሯል፡፡ ለውጡንና ጠቀሜታውን በተለያየ አቅጣጫ የሚተነትኑ በርካቶች ሲሆኑ፣ እንደ አቶ ተፈሪ ግን ለውጡ በዋናነት የዋጋ ግሽበትን ለመግታት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በሌላ መልኩም የሀብት ሥርጭት ሚዛንንም ለማስጠበቅ ይረዳል ይላሉ፡፡
አቶ ደረጀና አቶ አስፋውም የመገበያያ ለውጡ ለባንኮችም ጭምር በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ደረጀ ሌሎች የባንክ ፕሬዚዳንቶች የሰጡትን ማብራሪያ ተጋርተው፣ የብር ኖት ለውጡ ከባንክ ውጭ የሚሽከረከረውን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ ማድረጉ በባንኮች የሚገኘውን የገንዘብ መጠን ያሳድገዋል፡፡ የባንኮቹ ዋና ሥራ ካፒታል መፍጠር በመሆኑና ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብ ካፒታል ለሚያስፈልገው የኅብረተሰብ ክፍል፣ ገንዘቡን በብድር በማቅረብ ለኢኮኖሚው ዕድገት ዕገዛ ማድረግ ነው፡፡
ስለዚህ ከባንክ ውጭ ያለ ገንዘብ ወደ ባንክ ሥርዓት ሲመጣ የባንኮች ሪሶርስ ያድጋልና የባንኮች የብድር መጠንም በዚያው ልክ ስለሚያድግ አገር በሚጠቅም ኢኮኖሚን በማሳደግ ረገድ የባንኮች ሚና እንዲጎላ ያደርጋል የሚል አመለካከታቸውን አክለዋል፡፡
አቶ ደረጀ ጨምረው እንደገለጹት፣ የባንኮች የብድር መጠን ማደግ ሌላም ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ‹‹የብድር መጠን ባደገ ቁጥር ተወዳዳሪነትን ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም ባንኮች በጥቂት ሪሶርስ የሚሰጡትን የብድር ወለድ ምጣኔ ዝቅ ያደርገዋል፤›› በማለት የገንዘብ ለውጡ ለብድር ወለድ ዋጋ መቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡ ‹‹በቂ ሪሶርስ ካለና ሪሶርሱን አውጥተህ የምትሠራበት ከሆነ፣ በተዘዋዋሪ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡››
እንደ አቶ ተፈሪ ከሆነም፣ የብር ኖቶች ለውጡ በአግባቡ እንዲተገበር ኅብረተሰቡ ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ ባንኮችም በቂ መረጃ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የብር ኖት ለውጡና ሒደቱ ላይ ሁሉም የበኩሉን ቢያበረክት የጋራ ጠቀሜታው ለሁሉም ነው ይላሉ፡፡ ከባንኮች ኃላፊዎች ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ የገንዘብ ቅየራውን ማካሄድ በጀመሩባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ችግር አላጋጠማቸውም፡፡ የብር ኖቶችን በማዘዋወሩ ረገድ ከፀጥታ ኃይሎች እያገኙት ያለው ትብብርና ድጋፍ ሥራቸውን ያለችግር ለማከናወን እንዳስቻላቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡