Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንደ ገንዘብ ኖቱ ቅያሪ የሚሹ ልምዶች  

የኢትዮጵያ መንግሥት በሳምንቱ መጀመርያ ይፋ ያደረገው የመገበያያ ኖት ለውጥ ዘገየ ካልተባለ በቀር፣ በብዙኃኑ ዘንድ እንደ ወሳኝ ዕርምጃ እየታየ ነው፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ለዕርምጃው አዎንታዊ ምክንያቶች እንዳሉ መገመት ይቻላል፡፡ ሆኖም የብር ኖት የመለወጡ ጉዳይ ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም፡፡

ለውጥ መደረጉ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ጎልቶ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ተደጋግሞ እንደተጠቆመውም ከባንክ ውጪ ያለውን በመቶ ቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ኢኮኖሚውን ከማወክ አደብ ለማስገዛት እንደሚረዳ የሚነገረው ጎልቶ የሚጠቀሰው ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ብሎም በዚህ ተገን እየተደረጉ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ለውጡ እንደሚያስችል ሲታመንበት፣ ከዋና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ጎን ለጎን፣ ገንዘብ በያቅጣጫው በመርጨት አገር ሰላም የሚነሱና የሚያምሱትን ለማስቆም ሚናው እንደሚጎላ ይታመናል፡፡ በአገሪቱ ግጭቶች ለመበራከታቸው አንዱ ምክንያት፣ ከባንክ ውጪ እንዳሻው የሚንቀሳቀሰው፣ መንግሥት የማያውቀው የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ይህ መሆኑ ለሕገወጥ ተግባራት ብቻም ሳይሆን፣ አገሪቱንና ዜጎቿን ለህልውና ሥጋት አጋልጧቸዋል፡፡

የመገበያያ ኖቶች ለውጥ የማድረጉ ሌላው አዎንታዊ ጥቅም፣ ቁጠባን ለማዳበር የሚኖረው አስተዋጽኦ ነው፡፡ ዕርምጃው በአጠቃላዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳርፋቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩ እየተተነተነ ነው፡፡ የዘርፉ ምሁራን የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ፋይዳዎቹንና ትሩፋቶቹን እየነገሩን ነው፡፡  እውነታው ይኼ ከሆነ የገንዘብ ለውጡን በአግባቡ ማስፈጸም ወሳኝ ይሆናል፡፡ ጉዳዩ የመንግሥትና የባንኮች ብቻ አይደለምና ኃላፊነቱን እያንዳንዱ ዜጋ በቅንነት ሊተባበርበት ይገባል፡፡

የገንዘብ ለውጡን ጠቀሜታ በተግባር ተሳክቶ ማየት ከተፈለገ ሁሉም በአግባቡ ገንዘቡን በመለወጥ መተባበር አለበት፡፡ ለብር ኖቱ ቅየራ የተሰጠው የጊዜ ገደብና ርዝማኔው ቢያከራክርም፣ አሮጌውን በአዲስ የመቀየሩን ሒደት በቶሎ ማጠናቀቅ የበዛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ መንግሥት የጊዜ ገደቡ 90 ቀናትን ታሳቢ እንዳደረገ ቢያስታውቅም  ኅብረተሰቡ ከተቀመጠው ቀነ ገደብ በፊት በእጁ ያለውን ገንዘብ በመለወጥ ተባባሪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችና የባንክ ባለሙያዎች የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከሚገባው በላይ ሆኗል በማለት እየሞገቱ ነው፡፡

ይህን ማለታቸው አሳማኝ የሚሆንበት ምክንያትም ይጠቀሳል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ይህንን ከግምት ማስገባቱ እንደተጠበቀው ሆኖ፣ ኅብረተሰቡም የተጠቀመጠው ጊዜ ሳይጠብቅ በቶሎ መገላገል ይበጀዋል፡፡ በእርግጥ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ ያላቸው በአንድ ወር ውስጥ ቀይረው ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ቢታሰብም፣ የብር ኖት የመቀየሪያ ጊዜው በተራዘመ ቁጥር ሕገወጥ ተግባራት እንዲስፋፉና አዳዲሶችም እንዲፈጠሩ በር ይከፍታልና የገንዘብ ኖት መቀየሪያ ጊዜው ከሦስት ወራት በእጅጉ ማጠር ይኖርበታል፡፡

የገንዘብ ለውጡ ጠቀሜታ ከታወቀና የኅብረተሰቡ ክፍሎችም የበኩላቸውን አገራዊ ሚና መጫወት ከቻሉ፣ ከተቀመጠው ጊዜ ገደብ በፊት ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ለውጡን ከተገበረና፣ መንግሥትንም ራሱንም ካገዘ የታመመው ኢኮኖሚ ማገገሙ አይቀርም፡፡ ለመልካም እስከሆነ ድረስ ኅብረተሰቡ መንግሥትን ቀድሞ በመገኘት አዳዲስ መልካም ልማድ ማዳበሩ ለአገር ብዙ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የብር ለውጡን ለማፋጠን ሌሎች አማራጮችንም መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው አሠራር የገንዘብ ለውጡ በባንክ ቅርንጫፎች ብቻ የሚከናወን ሲሆን፣ ብዙውን ለመድረስ ግን አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማክሮ ፋይናንስ ተቋማትን መጠቀሙ በፍጥነት ገንዘቡን ለመለወጥ ያስችላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ተቋማት ባንኮች በማይደርሱባቸው ቦታዎች ጭምር ያሉ በመሆኑ እንዲህ ያለውም አሠራር ማሰብ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህ የገንዘብ ለውጥ በቶሎ መፈጸም ካልተገባ አሠራር ተቆጥቦ ለአገርም፣ ለኢኮኖሚውም ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ይህ በአግባቡ ከተፈጸመ በኋላ ግን ብዙ ችግር አለበት የሚባለውን ገንዘብ ፖሊሲ በመፈተሽና ድጋሚ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ለአገር ኢኮኖሚ ፈተና እንዳይሆን የገንዘብ ፖሊሲያችንን በመፈተሸ ምቹ ማድረግ ያሻል፡፡ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በቶሎ ገንዘቡን መቀየር ብቻ ሳይሆን ሕገወጥ ተግባራትንም በማጋለጥ የዜግነት ድርሻውን በመወጣት የበኩሉን ማድረግ እንዳለበትም መዘንጋት የለበትም፡፡

ይህንን ማድረግ በሥራም ማገዝ ነው፡፡ ለምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ትንተና እንደሚያመላክተውም ሆነ ከመንግሥት እየተሰጠ ካለው ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው ለዜጎች ፈታኝ እየሆነ የመጣውን የዋጋ ግሽበት በመቀነስና ጤናማ የግብይት ሥርዓት የመፍጠር በመሆኑ ጉዳዩ የእኔ ነው ብሎ በመልካም አስቦ ማገዝ ተገቢ ይሆናል፡፡

አንዳንዴ አንዳንድ አጋጣሚዎች ይዘው የሚመጡት መልካም ዕድል አለና ባንኮች በዚህ ገንዘብ ለውጥ ሰበብ ወደ ባንኮቻቸው የሚመጡ ቆጣቢዎች የሚበረክቱ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውም ከፍ ይላልና ይህንን አጋጣሚ ራስንም ኅብረተሰቡንም በሚጠቅም መልኩ መፈጸም ይገባል፡፡

የቁጠባ ዕድገቱ የጥሬ ገንዘብ እጥረትን ከመቅረፍ ባሻገር፣ በብድር መልክ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባው ገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ብድር የወለድ ምጣኔያቸውን ቀነስ አድርገው አገልግሎታቸው እንዲጎላ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ከማስፋፋት አንፃርም ይህ ጊዜ ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ቴክኖሎጂ ወለድ የሆኑ አገልግሎቶቻቸውን ማስፋት ይኖርባቸዋል፡፡    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት