Tuesday, February 27, 2024

ተቃዋሚዎች አንድ መቀመጫ ብቻ ያገኙበት የትግራይ ምርጫ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው መጪው ጠቅላላ ምርጫ በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ተከትሎ፣ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ቀድሞውንም በቋፍ የነበረው ግንኙነት ወደ ተካረረ ደረጃ መድረሱ የሚታወቅ ነው፡፡

ምንም እንኳን በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው ግንኙነት ከምርጫ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ወደ መካረር ቢደርስም ቅሉ፣ ከመነሻው በሁለቱ መካከል የነበረው አለመተማመን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ‹‹ግልጽ የሆነ የሽግግር ማዕቀፍ የለውም›› የሚል የርዕዮተ ዓለም ልዩነትና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) አፍርሶ አዲስ ብልፅግና የተሰኘ ፓርቲ ምሥረታ ይፋ መደረጉ፣ እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ፣ የሕወሓትና የፌዴራል መንግሥቱ ግንኙነት ከመጀመርያም በትብብር መንፈስ ላይ የተመሠረተ አልነበረም፡፡

በዚህ በተካረረ ሁኔታ ውስጥ የነበረው የሁለቱ ግንኙነት ወደ ለየለት ጡዘት ያመራውና ለበርካቶችም የሥጋት ምንጭ የሆነው ግን፣ በዋነኛነት የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በሕገ መንግሥት ትርጓሜ አማካይነት ሥልጣኑን ላልተወሰነ ጊዜ በማራዘሙ ሳቢያ ነው፡፡

የሁለቱን ምክር ቤቶች ውሳኔ ተከትሎ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን መራዘምን ክፉኛ ከተቃወሙት ፓርቲዎች መካከል ዋነኛው ሕወሓት ሲሆን፣ ውሳኔውን ከመቃወም ባለፈ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ በክልሉ እንደሚያደርግ በማስታወቅ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ሰንብቶ ምርጫውንም በክልል ደረጃ በቅርቡ ማከናወን ችሏል፡፡

በፌዴራል መንግሥቱ ይሁንታ ቢነፈገውም የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ ምርጫውን በክልል ደረጃ ለማከናወን ያስችሉኛል ያላቸውን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡ ለአብነት ያህልም በክልል ደረጃ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋም፣ የክልሉን ሕገ መንግሥት በማሻሻል ጭምር የምርጫ ሥርዓቱን ወደ ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት መቀየሩ፣ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ማድረጉን እንደሚገፋበት በተለያዩ ጊዜያት ሲያስታውቅ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ደግሞ የተለያዩ አስተያየቶችን በጉዳዩ ላይ ሲሰነዝር ነበር፡፡ ምርጫው ሊካሄድ የሳምንት ያህል ጊዜ ሲቀረው ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ‹‹የትግራይ ክልል የምርጫ ሒደቶች እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩና ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ናቸው፤›› ሲል መወሰኑ ጉዳዩን የበለጠ አወሳስቦት ሰንብቷል፡፡

በዚህ መሀልም የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ ላይ፣ ‹‹በማንኛውም መልኩ ጣልቃ መግባትና ለማሰናከል መሞከር ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል፤›› በማለት፣ ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ እንደማይቀበል ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ስለሆነም በትግራይ ክልል ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የተከናወነውን ምርጫ፣ ከእነዚህ ሁሉ አውዶች አንፃር መመልከቱ አስፈላጊ እንደሚሆን በርካቶች ያትታሉ፡፡

በትግራይ ክልል የተካሄደው ምርጫ ካስተናገዳቸው ዓበይት ፖለቲካዊ ክስተቶች መካከል የክልሉን የምርጫ ሥርዓት የመቀየሩ ውሳኔ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት የክልሉ የምርጫ ሥርዓት ወደ ቅይጥ ትይዩ ተቀይሯል፡፡ 80 በመቶ የክልሉ ምክር ቤት መቀጫዎች ባለበት የሚቀጥል ሲሆን፣ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ በቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት አማካይነት ሊያዝ እንደሚገባ ወስኗል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በማሻሻያው መሠረት የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት በ38 መቀመጫዎች በመጨመር ወደ 190 ሲያሳድግ፣ ከዚህም ውስጥ 152 መቀመጫዎች አሁን ባለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ቀሪዎቹ 38 ደግሞ በአዲሱ ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት እንደሚያዙ ተገልጾ ነበር፡፡

በክልሉ የተካሄደው ምርጫ በይዘቱም ሆነ በሒደቱ አዲስ ነገር ያስተዋወቀ ነው በማለት የሚያሞካሹት እንዳሉ ሁሉ፣ ምርጫው የፌዴራል መንግሥቱን ቅቡልነት ከማጠልሸት ውጪ የሚፈይደው አንዳችም ፋይዳ የለውም የሚሉ የተለያዩ ሙግቶችን አስተናግዷል፡፡

ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ክልላዊ ምርጫ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን፣ በምርጫው ዕለትም በ2,672 የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከተመዘገቡ መራጮች መካከልም 98 በመቶ የሚሆኑት ድምፃቸውን መስጠታቸው ተገልጿል፡፡

ምርጫው በይዘቱም ሆነ በሒደቱ አዲስ ነገር አስተዋውቋል የሚሉት ወገኖች የክልሉ ገዥ ፓርቲ ከሌሎች በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር ለመነጋገር፣ ለመወያየትና በውሳኔዎች ለማሳተፍ የሄደበትን መንገድ በመንቀስ አድናቆት ችረውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉም ሆነ በመላ አገሪቱ ካለው የዴሞክራሲ እጥረት አንፃር በመነሳት በክልሉ ምርጫ ለማድረግና ተቃዋሚዎችን የማሳተፉ ጥረትን አዲስ መንገድ ቀያሽ በማለት አወድሰውታል፡፡

በተቃራኒው የቆሙት ደግሞ ከመነሻው ጀምሮ በአንፃራዊነት ቅቡልነት ያላቸውን ፓርቲዎች በተለይ አረናን ከምርጫው በማገድ የተጀመረው የምርጫ ሒደት በምንም ዓይነት መለኪያ ነፃ ሊሆን ስለማይችል፣ በክልሉ የሚደረገው ምርጫ ያው እንደተለመደው ዓይነት ምርጫ እንጂ ምንም የሚቀይሰውም ሆነ የሚያስተዋውቀው አዲስ መንገድ የለም በማለት ሒደቱንም ሆነ ይዘቱን ይተቹታል፡፡

ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ ነበር ለማለት እንደሚቸግር ከሚገልጹ ግለሰቦች መካከል በኮቨንትሪ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ናትናኤል ጥላሁን አንዱ ሲሆኑ፣ ‹‹የምርጫው ሒደት በአንፃራዊነት ነፃ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ የምርጫውን ሒደትና ውጤት ነፃ ነበር ለማለትና ለመለካት ይህ ቁንፅል መለኪያ ነው፡፡ ዋነኞቹ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ጫና ምክንያት ወይ በምርጫው እንዳይሳተፉ ታግደዋል፣ አልያም ደግሞ ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል፤›› በማለት፣ የሒደቱን ፍትሐዊነት በመጠየቅ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ የኢሜይል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የምርጫው ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ የተመለከቱትን ውጤት በመጥቀስ፣ በክልሉ የተካሄደውን ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ወይም ነፃ ብሎ መጥራት ‹‹በዴሞክራሲ ማላገጥ›› ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ምርጫው ፖለቲካዊ ግልጽነት ባልሰፈነበት ምኅዳር የተካሄደ በመሆኑ፣ የምርጫው ቅቡልነት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደ እኔ አመለካከት ምርጫው የተካሄደው የፖለቲካ ሥልጣንና አመራር ለመያዝ ሳይሆን፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ለማጠናከር ነው፤›› ሲሉ ምላሻቸውን ቋጭተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በክልሉ ከተካሄዱ ምርጫዎች አንፃር በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ የተካሄደበት ዓውድ፣ ‹‹በአንፃራዊነት የተሻለ ምኅዳር ነበር›› በማለት የሚገልጹት የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ምክር ቤት (ባይቶና) ሊቀመንበር አቶ ኪዳነ አመነ፣ ነገር ግን በምርጫው ዕለትና ከዚያ በኋላ ባሉ ሁኔታዎች ሲለካ ተስፋን የሚያጨልም እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ፓርቲያቸው ከመጀመርያው ወደ ምርጫ የገባው ‹‹በሕጋዊነት ስለሚያምን›› እንደሆነ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ወደ ምርጫ የገባነው ሕገ መንግሥት መጣስ ስለሌለበት ነው እንጂ፣ የተመቻቸ የዴሞክራሲ ምኅዳር ስለነበረ አይደለም፤›› ሲሉ በምርጫው የተሳተፉበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው ሐሙስ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በምርጫው ዕለት በርካታ ችግሮችን መታዘቡን እንዲሁ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት በፓርቲው ተመራጮች፣ በምርጫ ታዛቢዎችና በአባላቱ ላይ በሕወሓት ካድሬዎች አማካይነት ወከባ እንደደረሰቸው አውስቷል፡፡

በምርጫው 93,435 ድምፅ ያገኘው ባይቶና በምርጫው ዕለት በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የታዘባቸውን በርካታ ችግሮች ከመዘርዘር ባለፈ ግን፣ የክልሉን የምርጫ ኮሚሽን እንዲሁም ገዥው ፓርቲ ሕወሓትን ከምርጫው ዕለት በፊት ለነበራቸው መልካም አካሄድ ምሥጋና አቅርቧል፡፡

ሆኖም ሕወሓት እንደ ገዥ ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊነቱን ሊወጣ ሲገባው አባላቱንና ደጋፊዎቹን የተለያዩ ስሞችን በመስጠት ማጠልሸት ውስጥ መግባቱ፣ ለክልሉ ሕዝብ ሞራል ክብር የማይሰጡ ሕገወጥ ሥራዎች ሠርቷል በማለት ባይቶና ተችቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች መራጮችን የማደናገርና የተሳሳተ መረጃ የመስጠት ሥራን በተደራጀ መንገድ ሲያካሂዱ አስተውለናል፡፡ ይህም ቤት ለቤት እየዞሩ ከንብ ምልክት ውጪ መምረጥ እንደማይቻል፣ የተለየ ከመረጡ ዋጋ እንደሌለው፣ ለተቃዋሚዎች 38 ወንበሮች ትተንላቸዋል፣ ወዘተ በማለት ባይቶና በምርጫው ዕለት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ዘርዝራል፡፡

በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ የውክልና ምርጫ መካሄዱን መታዘቡን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹ባል ወይም ሚስት ሙሉ ቤተሰቡን ወክሎ ወይም ወክላ ድምፅ የሰጡበት አጋጣሚ ተከስቷል፤›› በማለት ባይቶና አስታውቋል፡፡

ያገኘውን አንድ የክልል ምክር ቤት መቀመጫ አስመልክቶ ደግሞ፣ ባይቶና ለተሰጠው የሕዝብ ድምፅ ክብር እንዳለው በመግለጽ በወንበር ክፍፍል ሥሌት መሠረት ያገኘው አንድ ወንበርም ይገባዋል ብሎ እንደማያምን አስታውቋል፡፡ ሆኖም፣ ‹‹የሕዝብ  ድምፅ ስለምናከብርና እኛ ያልተመለከትነው ሕጋዊ መንገድ ካለና በዚሁ መሠረት ሕጉ ተተርጉሞ ይገባችኋል ከተባለ፣ ሕጋዊነትን ስለምናከብር በዚህ አግባብ የሚሰጠንን መቀመጫ በፀጋ እንደምንቀበል እንገልጻለን፤›› በማለት አቋሙን አስታውቋል፡፡

ከዚህ አንድ የምክር ቤት መቀመጫ ጋር በተያያዘ ባይቶና ‹‹አጣብቂኝ›› ውስጥ መግባቱን የገለጹት የፓርቲው ሊቀመንበር፣ ‹‹አንዱን ወንበር አንቀበልም ብንል ሕወሓት በምርጫ 97 እንዳደረገው መቀመጫ አንቀበልም አሉ የሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፈትብናል፡፡ ብንቀበል ደግሞ ከሕጉ አንፃር ይጋጫል፡፡ በዚህ መሀል እኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል፤›› ሲሉ ያለውን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

ሆኖም ሊቀመንበሩ በምርጫው ውጤት እንዲህ መሆን፣ ‹‹ሕወሓት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ኪሳራ አጋጥሞታል፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫውን ለብቻው እንደሚያከናውን ካስታወቀ በኋላ ከተከሰቱ ዓበይት ክንዋኔዎች መካከል፣ ዋነኛው የምርጫ ሥርዓቱን መቀየር ነበር፡፡ የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር ያስፈለገበትን ምክንያት ለክልሉ ምክር ቤት በወቅቱ ያብራሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ተቃዋሚዎች በምክር ቤቱ ሥፍራ እንዲያገኙና የተለያዩ ሐሳቦች እንዲስተናገዱ ለማስቻል የሚል ነበር፡፡

ሆኖም ምርጫው ከተካሄደ በኋላ የተመዘገበው ውጤት ያመለከተው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በርካቶች የምርጫ ሥርዓቱን መቀየር በራሱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባትም ሆነ የተለያዩ ሐሳቦች በፌዴራልም ሆነ በክልል ምክር ቤቶች እንዲስተናገዱ ማስተማመኛ ሊሆን እንደማይችል፣ የትግራይን የምርጫ ውጤት እንደ ማሳያነት በማውሳት አስተያየት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡  

በዚህም መሠረት የሐሳብ ብዝኃነትን ለማስተናገድና ተቃዋሚዎች በምክር ቤቶች የተሻለ መቀመጫ እንዲያገኙ የመጫወቻ ሜዳው ለሁሉም እኩል መሆን እንደሚኖርበት በማሳሰብ፣ በዋነኛነት ልዩነቶችን ሊያስተናግድ የሚችል የፖለቲካ ባህልና ምኅዳር መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫም በቀዳሚነት እንዲህ ያሉ ዓበይት ቁም ነገሮች ላይ ሊያተኩር ይገባል ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -