ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የዛሬ አንድ ወር የሾሟቸውን የሦስት ሚኒስትሮች ሹመት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡ ከሚኒስትሮቹ በተጨማሪ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡ 90 ዕጩ ዳኞችን ሹመትም ምክር ቤቱ አፅድቋል፡፡
በሚኒስትርነት የተሾሙት ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) የመከላከያ ሚኒስትር፣ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር፣ ሳሙኤል ሁርቃዮ (ዶ/ር) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሲሆኑ፣ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ደግሞ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆነው ተሹመዋል፡፡ የሚኒስትሮቹና የዳኞቹ ሹመት በድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡