ላለፉት ሁለት ወራት በእስር ላይ የነበሩትና ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ቀናት የፀና ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የኢዴፓ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው፣ በ100 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ውሳኔ ተሰጠ፡፡
የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ እንዳስታወቀው፣ አቶ ልደቱ ካላቸው አጠቃላይ መግለጫ (ፕሮፋይል) አንፃር ወደ ውጭ ሄደው ይቀራሉ የሚለው የዓቃቤ ሕግ ክርክር አሳማኝ አለመሆኑን ገልጾ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ውሳኔ መስጠቱን የኢዴፓ ሊቀመንበር በአዳማ ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አቶ ልደቱ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. የፌዴራል ፖሊስ ስልክ ደውሎ እንደሚፈለጉ ሲነግራቸው፣ በራሳቸው መሄዳቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ሲደርሱ የጠበቃቸው በኦሮሚያ ክልል የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ በወንጀል እንደሚፈልጋቸው ተነግሯቸው፣ በፌዴራል ፖሊስ አጃቢነት ወደ ቢሾፍቱ ተወስደው፣ ለቢሾፍቱ ፖሊስ መሰጠታቸውንም ተናግረው ነበር፡፡ የቢሾፍቱ ፖሊስ ስለተጠረጠሩበት ወንጀል ማለትም በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት የቢሾፍቱ ወጣቶች ሁከትና ብጥብጥ እንዲያስነሱ በገንዘብ ረድተሃል መባላቸውን፣ ፍርድ ቤት ቀርበውም የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንደተፈቀደባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በቀጣይ የቀጠሮ ቀናቸው ቤታቸው ሲበረበር ሁለት ፈቃድ የሌላቸው ሽጉጦች፣ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም የሚል መጣጥፍና ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› የሚል ጅምር ጽሑፍ ማግኘቱን ፖሊስ ገልጾ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁንም መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ከአንድ ወር በላይ የወሰደውን የምርመራ ጊዜ ጨርሶ ፖሊስ ምርመራውን ማጠናቀቁን በመግለጹ፣ መዝገቡን ያለ ትዕዛዝ በመዝጋቱ፣ አቶ ልደቱ ለቀናት ዝም ብለው በመታሰራቸው ራሳቸው ማመልከቻ ጽፈው የዋስትና መብት ሲጠይቁ፣ ዓቃቤ ሕግ መቃወሙም ተዘግቧል፡፡ መጨረሻ ላይ የፀና ፈቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሣሪያ ይዘው በመገኘት ወንጀል ተከሰው በዋስትና ጉዳይ ተከራክረው፣ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በመቶ ሺሕ ብር ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ለመደበኛ ክርክር ለመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡