Thursday, June 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጪው ምርጫ ራሳችሁን አዘጋጁ!

መጪው ምርጫ እንዲከናወን የሚያስችል ይሁንታ በመገኘቱ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት ራሳቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት መጀመር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዳኙት የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ በሚታሰበው የሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ የፖለቲካ ፖርቲዎች ሐሳባቸውን ለሕዝብ ለመሸጥ ከመውጣታቸው በፊት፣ የቤት ሥራቸውን መጨረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የሚፈለገውን ዲሲፕሊን ያላሟላ የፖለቲካ ፓርቲ ለሕዝብ ብያኔ መቅረብ አይችልም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ብቃት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ራሳቸውን ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ጨዋታ ሕግ ማስገዛት የማይችሉና ግልጽና የተብራራ አጀንዳ የሌላቸው ፓርቲዎች፣ ሕዝብ ፊት በመውጣታቸው የሚያተርፉት ነገር እንደሌለ ሊረዱ ይገባል፡፡ ሕዝብን በጉልበት፣ በማታለል፣ የማይጨበጥ ቃል በመግባት ወይም አገር በማተራመስ ሥልጣን መሻት እንደማያዋጣ መረዳት ይገባል፡፡ የሐሳብ ልዕልና የሚኖረው በሀቅ፣ በአገርና በሕዝብ ተቆርቋሪነት በሚደረግ ፉክክር ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆነው ሕዝብ ፊት ለመቅረብ ይዘጋጁ፡፡ ገዥው ፓርቲም ከመቼውም ጊዜ በተለየ የፖለቲካ ምኅዳሩን ያስፋ፡፡ ለመጪው ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት የሚያሳትፍ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሐሳብ ልዩነትን የሚያከብር የፖለቲካ ምኅዳር ነው፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጥያቄ መነሻም ይኼ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተከብሯል ከሚባልባቸው መሥፈርቶች አንዱ፣ ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ነው፡፡ በሐሳብ የሚለይ ግለሰብም ሆነ ቡድን የሌሎችን መብት ማክበር መቻል አለበት፡፡ የሐሳብ ገበያው የሚፈልገው አንድን ሐሳብ መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ ሐሳብ ይዞ መገኘትን ጭምር ነው፡፡ ዴሞክራሲ መለምለም የሚጀምረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥም ሆነ በሌላ አደረጃጀት ሁሌም ሰዎች መስማማት አይጠበቅባቸውም፡፡ የልዩነታቸውን ነጥብ አስመዝግበው መወያየትና መከራከር ባህል መሆን አለበት፡፡ ሕዝብ ፊት መቅረብ የሚቻለው የተሻለ አማራጭ በመያዝ ብቻ ነው፡፡ በጨዋነት ለሕዝብ ዳኝነት መቅረብ ሥልጣኔ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በነገር መፈላለግ፣ ደጋፊን ማፋጠጥና ግጭት ለመቀስቀስ ዳር ዳር ማለት ለዚህ ዘመን አስተሳሰብ የማይመጥን ነው፡፡ እስካሁን በብዙዎቹፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ይስተዋል የነበረው እንዲህ ዓይነቱ ኋላቀር ድርጊት ነው፡፡ ራስን የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ፍላጎት ማስገዛት ያስፈልጋል፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ አላስፈላጊ ድርጊቶች መገታት አለባቸው፡፡

የአገሪቱ ኋላ ቀር የፖለቲካ ምኅዳር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አጀንዳ ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገጽታው መለወጥ አለበት፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲለወጥ ደግሞ፣ የጨዋታው ሕግ በአግባቡ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡ የጨዋታው ሕግ ምን ይላል? ልዩነትን በውይይት የመፍታት ዴሞክራሲና ጨዋነት መላበስ፣ ልዩነት አብሮ ለመሥራት አያመችም ከሚል ቅዠት ውስጥ መውጣት፣ ያልተገደበ የሕዝብ ውይይትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ክርክር ማድረግ፣ ዝምታን አስፍኖ አሉባልታንና ሹክሹክታን የሚያባዛ የተወጠረ አየርን ማስተንፈስ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊነት ደግሞ በመብቶችና በልዩነቶች ውስጥ አብሮ ለመኖር መቻል ማለት መሆኑን፣ ይኼንንም መሠረት ለማስያዝ በመረባረብ ችግሮች ወይም አለመግባባቶች ሲከሰቱ፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታትና ውጤቱንም መቀበል የጨዋታው ሕግ አካል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው በሰላም፣ በነፃነትና በእኩልነት የሚያኖረው ሥርዓት እንዲገነባለት ነው፡፡ የተሻለ ገቢ፣ ለኑሮ አመቺ የሆነ መኖሪያ፣ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ፍትሕና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል አጀንዳ ያለው ፓርቲ የሕዝብን ቀልብ ይስባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር መሆን ያለበትም ይህንን ፍላጎት ለማርካት ነው፡፡

በኢትዮጵያ አንድነትና በሕዝቡ አብሮነት ላይ የጋራ ራዕይ ሊኖር የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ሲባል የሚከፋቸውና የሕዝቡን አብሮነት መስማት የማይፈልጉ ወገኖች አሁንም አሉ፡፡ ከሥልጣን በላይ የአገር ጉዳይ ግድ የሚላቸው ፖለቲከኞች ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር ራሳቸውን ዝግጁ ያድርጉ፡፡ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ የአገር ህልውና መቅደም አለበት፡፡ የፖለቲካ ጥበብ ያልገባቸው ወይም ከሴራና ከአሻጥር ውጪ ምንም የማይታያቸው፣ ለሕዝብ ፍላጎት የሚመጥን ባህሪና አቅም እስኪያገኙ ድረስ ራሳቸውን ቢያገልሉ ይመረጣል፡፡ እነዚህ ለውይይትና ለድርድር ከመዘጋጀት ይልቅ፣ በረባ ባልረባው ጉዳይ መነታረክ የሚወዱ የዜሮ ድምር ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ዴሞክራሲን ያነበንቡታል እንጂ በተግባር አይኖሩትም፡፡ ሁሌም ፀብ አጫሪነት፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ሴረኝነት ብቻ ናቸው የሚቀናቸው፡፡ እርስ በርስ ሲጣሉም ገመና መደባበቅ አይችሉም፡፡ እነዚህን ገርቶ ፈር ማስያዝ ትልቅ ጥረት ይፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰለቸው የሴራ ፖለቲካ ሰለባ መሆን ነው፡፡ አገርን ከቀውስ ወደ ቀውስ የሚያንከባልሉ የሴራ ፖለቲካ አራማጆች፣ አሁንም ቢሆን ምርጫውን ከመነታረኪያነት አሳልፈው ደም መፋሰሻ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወኪሎቹን በነፃነት የሚመርጥበት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማሰናዳት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጀምሮ እስከ ግለሰብ ድረስ ከፍተኛ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡

ተደጋግሞ እንደሚነገረው የኢትዮጵያ ችግር ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ ከመሆኑም በላይ፣ በጣም ውስብስብና አታካች ነው፡፡ ነገር ግን ይኼንን የዘመናት ውስብስብ ችግር ለመፍታት የሚያስፈልገው በተለያዩ መስኮች ዕውቀት፣ ብስለት፣ ቅንነትና ጥልቀት ያለው ዕይታ ነው፡፡ አሁን በስፋት እንደሚታየው በስሜታዊነትና በግብታዊነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ ጊዜያዊ እርካታ ከማስገኘትና ቆይቶ ደግሞ ከመሰልቸት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፡፡ በተለይ ለውጥ በሚካሄድባት አገር ውስጥ ከጊዜያዊ ሆይ ሆይታና ግርግር ውስጥ በፍጥነት በመውጣት የተቋማት ግንባታና የሕግ ማዕቀፎች ላይ በፍጥነት ካልተሠራ፣ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የእምቧይ ካብ ከመሆን አያልፉም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) አስተዳደር ከሚጠበቁበት ተግባራት መካከል አንዱ፣ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዙ መደላድሎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሕግ ማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲከበሩ ማድረግ፣ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን በሰፊው መክፈትና መጪው ምርጫ ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቆ እንዲካሄድ የሚረዱ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ችግርን መፍታት የሚጀመረው እንዲህ ነው፡፡

ጨዋውና አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው በሥርዓት መመራት እንደሆነ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ከተደረጉ ውይይቶችና ከሚቀርቡ አስተያየቶች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይኼንን አርቆ አሳቢና አስተዋይ ሕዝብ ጥልቀት ባለው ዕይታ በሚመራ አስተሳሰብ ፍላጎቶቹን መረዳት የግድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር ለመፍታት የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማጤን ብቻ ሳይሆን፣ የጉዳዩ ባለቤትም ስለሆነ ተሳትፎውን በስፋት ማግኘት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ምሁራን፣ ልሂቃን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመሳሰሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች አገራዊ ተሳትፎ ችግርን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔ ለማመንጨትም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አገር በቀል ዕውቀት የታከለበት ሥልጣኔ ማስፈን ከተቻለ የአገር ተስፋ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ ይዞ ዕይታን በመጋረድ አላስፈላጊ ድርጊቶች ውስጥ መርመጥመጥ ያስንቃል፡፡ በተለይ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ወገኖች ከሚያስንቁ ድርጊቶች ራሳቸውን ማላቀቅ አለባቸው፡፡ በተከበረች አገር ውስጥ የሚያስንቁ ድርጊቶች ውስጥ መገኘት የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ፣ ዘለቄታ ያለው ክብርና ዝና አያስገኝም፡፡ ይልቁንም ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ለሆነው ቁምነገር ራስን ማዘጋጀት ይመረጣል፡፡ የኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱት ጥልቀት ባለው ዕይታ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል መጪውን ምርጫ ተዓማኒ ለማድረግ መረባረብ የግድ ይሆናል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለሕዝብ ውሳኔ የሚያዘጋጁበት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢንቨስተሮች አደጋ ሲገጥማቸው ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለው መመርያ ተሻረ

በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች በኢንቨስተሮች ንብረት ላይ አደጋ ቢከሰት፣...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

ለውጭ ገበያ ሳይላክ ለቀረ ቡና ላኪዎች ታክስ እስከ ወለዱ እንዲከፍሉ ተወሰነ

ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ቡና ላኪዎች የሚያቀርቧቸውን ሰነዶች መርምረው ወደ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...