Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አቋምና የእግር ኳሱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አቋምና የእግር ኳሱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ ካሳለፋቸው የተለያዩ ውሳኔዎች መካከል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በዞን በሚያካሂዳቸው ማጣሪያ ውድድሮች ላይ ዕድሜያቸው ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖችን ማሳተፍ ይገኝበታል፡፡ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቅጥር ጋር ተያይዞም ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ መሠረት ቅጥር እንደሚፈጸም አቅጣጫ ማስቀመጡ ተሰምቷል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ሰኞ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ጤና ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ ውድድሮች እንዲቀጥሉ ለማድረግ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቅጥር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውይይት ላይ ከብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቅጥር በፊት በፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራው ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አለኝ የሚለውን ምክረ ሐሳብ እስከ ረቡዕ መስከረም 14 ቀን ድረስ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ የሚለው አንዱና ዋናው ጉዳይ እንደነበርም ታውቋል፡፡

ሌላውና ሁለተኛው ጉዳይ ካፍ በዞን ደረጃ ለሚያከናውናቸው ማጣሪያ ውድድሮች ዕድሜያቸው ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሳተፉ መወሰኑ ተገልጿል፡፡ በቅርቡ በራሳቸው ፈቃድ ከቴክኒክና ልማት ዳይሬክተርነት በለቀቁት አቶ መኮንን ኩሩ ምትክ፣ ለጥቂት ወራት የክለብ ላይሰንሲንግ ባለሙያ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ መቀጠራቸው ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ውድድሮች እንዴትና በምን ዓይነት የውድድር ሥርዓት (ፎርማት) ይቀጥሉ በሚለው ጉዳይ ላይ መወሰን ይቻል ዘንድ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የፕሪሚየር ሊጉ ካምፓኒ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር በታዛቢነት የተሳተፉበት ውይይት ተደርጓል፡፡

ከማክሰኞ መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል እየተደረገ ባለው ውይይት፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የተቋረጠው ውድድር ይቀጥል ቢባል የውድድር ሥርዓቱ (ፎርማቱ) ምን ይሁን የሚለው በዋናነት ሲጠቀስ፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ በ2012 የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ ላይ ብዙዎቹ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አመራሮችና ኃላፊዎች የተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ 50 ሺሕ ብር ይሁን በሚል ያሳለፉትን ውሳኔ ይመለከታል፡፡

ባለፉት ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው ሲከናወኑ የነበሩት ውድድሮች በፊፋም ሆነ በካፍ የተቀመጠውን የጉዞ መጠን ያላገናዘበ እንደሆነ ሲነገር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ ከተመሠረተበት ከ1990ዎቹ ጀምሮ እስካሁን የድሬዳዋው ወደ መቐለ፣ የመቐለው አርባ ምንጭ አልያም ይርጋዓለም፣ የጎንደሩ አዲስ አበባን ጨምሮ እስከ ድሬዳዋና እንደ አስፈላጊነቱ በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ሁሉም ክለቦች ሲጫወቱ የቆዩት በ1000 ኪሎ ሜትር አካባቢ በመጓዝ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ የፊፋ መመርያ አንድ ቡድን ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሄዶ ለመጫወት ከ250 ኪሎ ሜትር መብለጥ እንደሌለበት ይደነግጋል፡፡

የውድድር ሥርዓቱ ከዚህም በላይ ክለቦችን ለከፋ የፋይናንስ መራቆት ሲዳርግ ከመቆየቱ ባሻገር ለበርካታ ክለቦች መፍረስም ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ውድድሮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እስከተቋረጡበት ድረስ በተለይም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ለመሰሉ ከመንግሥት ምንም ዓይነት የፋይናንስ ድጋፍ ለማይደረግላቸው ክለቦች ችግሩ ትልቅ ፈተና ሆኖ መቆየቱ ክለቦቹ ከሚሰጧቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡

የ2013 የውድድር መርሐ ግብር ከመጀመሩ በፊት ክለቦችን ለከፋ የፋይናንስ ቀውስ ሲዳርግ የቆየው የውድድር ሥርዓት (ፎርማት) አሁን ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከኢትዮጵያ ቡና በተጨማሪ አዳማ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማና የሌሎችም ክለቦች ችግር  መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በቀድሞ የተዟዙሮ የጨዋታ ሥርዓት ምትክ አማራጭ የውድድር ሥርዓት እንደሚመቻች ይጠበቃል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዚሁ ጉዳይ ከአንድ ወር በፊት ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የወጣቶች እግር ኳስ አካዴሚ፣ በየደረጃው ከሚገኙ የክለብ አመራሮች ጋር አድርጎት በነበረው ውይይት፣ የ2013 ውድድር በኮቪድ ምክንያት ቀድሞ በነበረው ሥርዓት መቀጠል እንደማይችል፣ በአማራጭነት ውድድሮች በተመረጡ ሜዳዎችና ከተሞች አምስት አምስት ጨዋታ የሚያደርጉበትን የውድድር ሥርዓት እንደሚከተል ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡

ይሁንና በዚህኛው ውይይት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአማራጭነት ያስቀመጠው የውድድር ሥርዓት ክለቦቹ ከገጠማቸው የፋይናንስ ችግር በመነሳት አዋጭ እንደማይሆን፣ ከዚህ ይልቅ ክለቦች በሚቀርቧቸው ከተሞች ውድድሮቻቸውን አድርገው መጨረሻ ላይ ደረጃ ውስጥ የገቡ ክለቦች በአንድ በተመረጠ ከተማ የውድድሩ ስያሜ በስምምነት የሚወሰን ሆኖ፣ ጨዋታ የሚያደርጉበት የውድድር ሥርዓት እንዲፈጠር ፍላጎት የነበረ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ሁለተኛው የውይይት አጀንዳ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ሲሆን፣ ይህን ጉዳይ በሚመለከት የቢሾፍቱው ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ፣ ይሁን ከተባለም ውሳኔው በተጫዋቹና በቀጣሪው ክለብ መካከል መሆን ሲገባው አንዱ በሌላው ላይ መወሰኑ የሕግም ሆነ የሞራል  እንደሌለው የሚያንጸባርቁ አስተያየቶች በስፋት መደመጣቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ጎን ለጎን ቀድሞ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት እግር ኳስ ክለብ ለረዥም ዓመታት በበረኝነት ሲያገለግል ቆይቶ በአሁኑ ወቅት በሕመም ላይ ለሚገኘው ይልማ ከበደ (ጃሬ) የ50 ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ ከዚህ በፊት ያልተለመደ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ይልማ ከበደ ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ለሚገኙ የቀድሞ ስፖርተኞች ድጋፉ አነሰ በዛ ሳይባል “አይዞዋችሁ” ቢባሉ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው በሚል በርካቶች ለፌዴሬሽኑ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...