በቻይና የቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን በቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር ማስተማር እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው፣ ትምህርቱ የሚሰጠው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መሠረት ነው፡፡
የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር መጀመሩን አስመልክቶ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው በተከናወነው የምሥረታ ሥነ ሥርዓት ላይ ‹‹ለኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት 2013 ዓ.ም. እንኳን አደረሳችሁ›› በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን የጀመሩት የቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጂያ ውጂን፣ በቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የአማርኛ ቋንቋ በቅድመ ምረቃ ደረጃ በዩኒቨርሲቲያቸው መሰጠት በመጀመሩ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታና ክብር ገልጸዋል። አክለውም ለዚህ ፕሮግራም ምሥረታ ስኬታማነት የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ስንቅነሽ አጣለ (ዶ/ር) እንዲሁም በቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪካ ጥናቶች ትምህርት ክፍል ያላቸውን ልባዊ ምሥጋናና አድናቆት ገልጸዋል፡፡
ይህ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ቻይናውያን ተማሪዎች ስለኢትዮጵያና ስለአፍሪካ የበለጠ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ዕድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተማሪዎቹ በሚኖራቸው የትምህርት ቆይታ ቋንቋውንና ባህሉን በርትተው በማጥናት፣ በኢትዮጵያና በቻይና ብሎም በአፍሪካና በቻይና መካከል ላለው ወዳጅነት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ የሆነች፣ ረዥም ታሪክና ልዩ ልዩ ባህላዊ ዕሴቶች ያሏት እንዲሁም በአፍሪካ ለቻይና ቁልፍ ስትራቴጂያዊ አጋር ከሆኑ አገሮች መካከል ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰዋል። ስለሆነም ቻይናውያን ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ውጤታማ ሆነው ለወደፊቱ የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ እምነታቸው የፀና መሆኑን ተናግረዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር አቶ ሳሙኤል ፍፁም ብርሃን በበኩላቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ በቻይና የመጀመሪያ የሆነውን የአማርኛ ቋንቋ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ብሎም ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል እያከበሩ ባሉበት በዚህ ወቅት በማስጀመሩ ኤምባሲው ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።