Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልኮቪድ ያጠላበት የዘንድሮ የመስቀል ክብረ በዓል

ኮቪድ ያጠላበት የዘንድሮ የመስቀል ክብረ በዓል

ቀን:

ክርስቲያናዊና ባህላዊ ትውፊቶችን አስተሳስሮ የያዘው ዓመታዊው የመስቀል ክብረ በዓል እንደቀደሙት ዓመታት ምዕመናንና የተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች ከዓለም ዙሪያ የሚሰባሰቡ ቱሪስቶችንም ጨምሮ ዘንድሮ  ለማክበር አልታደለም፡፡

የፊታችን ቅዳሜና እሑድ መስከረም 16 እና 17 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚከበረው የመስቀልና መገለጫው የአደባባይ ደመራ እንደቀደሙት ጊዜያት በተለያዩ የመደመርያ ሥፍራዎችን ጨምሮ እስከ ሚሊዮን የሚደርስ ታዳሚ እንዲያከብረውም አልተፈቀደም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዳስታወቀችው፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሳይጓደል በውስን ካህናት፣ መምህራንና ዘማርያን እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶችና  የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በዓሉ በመስቀል አደባባይ ይከበራል፡፡

- Advertisement -

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ኢትዮጵያ በመስፋፋቱና ሥርጭቱም እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ነው ምዕመናኑ እንደ በፊቱ በብዛት ወጥተው የማያከብሩት፡፡

ከጠቅላይ ቤተክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምርያ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በመስቀል አደባባይ ደመራው በሚለኮስበት ዕለት የሚገኙት ተገቢው ጥንቃቄ እያደረጉና ርቀትን እየጠበቁ በዓሉን የሚያከብሩ ይሆናል፡፡

ከአምስት ሺሕ የማይበልጡ ሰዎች እንደሚገኙበት በሚጠበቀው የመስቀል ደመራ  በዓል ላይ የሚታደሙት የመግቢያ ካርድ (ባጅ) የሚይዙ ይሆናል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓል እንደ ልብ እንዳይከበሩ ቢያደርግም የመስቀል ደመራ በዓል ለቱሪዝም፣ ለአገር ገጽታና፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የግድ መከናወን ስላለበት በአነስተኛ የሰው ቁጥር ብቻ እንዲከበር መወሰኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል የሃይማኖት አባቶችና የፀጥታ አካላት ከሚወስኑት የሰው ቁጥር ውጪ፣ ማንኛውም ሰው መግባት እንደማይችል ያሳሰቡት ምክትል ከንቲባዋ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ብዙ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን ባይከበርም፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በጥቂት ምዕመናን እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭትም ምዕመናን በየቦታቸው ሆነው መከታተል እንዳለባቸውና ለሃይማኖት አባቶችና ለፀጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክብረ በዓሉ ምንነት  

በአራተኛው ምዕት ዓመት፣ በንግሥት እሌኒ አማካይነት ክርስቶስ ኢየሱስ የተሰቀለበት መስቀል መገኘቱ የሚታሰብበት የመስቀል ደመራ በዓል፣ በኢትዮጵያ ለሁለት ሺሕ ግድም ዓመታት ሲከበር ኖሯል፡፡ የበዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ገጽታ የተመለከተው ዓለም አቀፉ የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ አድርጎ ከመዘገበው ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡

 ክብረ በዓሉ በአማራና በትግራይ ‹‹መስቀል›› ሲባል፣ በተለያዩ ብሔረሰቦች እንደየአካባቢው ቋንቋ የተለያየ መጠርያ አለው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ‹‹ጉባ›› ወይም ‹‹መስቀላ›› በሀድያ፣ በወላይታ፣ በዳውሮ፣ በጋሞ፣ በጎፋ ‹‹መስቀላ›› በከምባታ ‹‹መሳላ›› በየም ‹‹ሔቦ›› በጉራጌ ‹‹መስቀር›› በካፊቾና ሻኪቾ ‹‹መሽቀሮ›› ይባላል፡፡

የመስቀል ክብረ በዓል በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ብሔራዊ በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል አጀማመር የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል፣ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተቀበረበት ተቆፍሮ መገኘትና በተለይም የመስቀሉ አንድ ክንፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ዐምባ መቀመጥ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ቁርኝት ቢኖረውም፣ እያንዳንዱ ብሔረሰብ በዓሉን የሚያከብርበት እንደባህሉ፣ አኗኗሩ፣ ወጉ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ገጽታው የራሱ መንገድ አለው፡፡

የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥት እሌኒ፣ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል  ከተቀበረበት ለማውጣት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ የደመራ ሥነ ሥርዓቱ በመጠኑም ቢሆን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በአክሱም፣ በዓዲግራት፣ በላስታ፣ ላሊበላ፣  በዋግ ሕምራ፣ በከፊል ጎጃምና በአዊ ዞን ደመራው መስከረም 16 ቀን ቢደመርም ሥርዓተ ጸሎቱ የሚካሄደውና ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በሸዋና በከፊል ጎጃም፣ በሐዲያ፣ በጉራጌ፣ በሸከቾ፣  ካፊቾ፣ ኮንታ ደመራው የሚበራው በዋዜማው መስከረም 16 ቀን ምሽት ነው፡፡ የደመራው አደማመርና አበራር ሥነ ሥርዓት ግን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ 

ደመራው ወደ አመድነት እስኪለወጥ ይነዳል፡፡ በዚሁ ወቅት ሕዝቡ ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ›› በማለት ይዘፍናል፡፡ ሴቶች እልል ይላሉ፡፡ ደመራው የተጸለየበትና የተባረከ ስለሆነ ሕዝቡ አመዱንና ትርኳሹን እየተሻማ ወደቤቱ ይዞ ይሄዳል፡፡ አንዳንዶቹ በአመዱ ግንባራቸው ላይ የመስቀል ምልክት ያበጃሉ፡፡ አመዱ ለሰውም ሆነ ለከብቶች ፍቱን መድኃኒት ነው የሚል እምነት አለ፡፡ በደመራው ማግስት መስከረም 17 ቀን በሚከበረው ዋናው የመስቀል በዓል ምዕመኑ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሶ ከተመለሰ በኋላ ሲበላና ሲጠጣ፣ ከጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ሲገባበዝና ሲጠያየቅ በፍቅርና በደስታ በዓሉን ሲያከብር ይውላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...