በአየለ ገላን (ዶ/ር)
ኢዜማዎች በቅርቡ የአዲስ አበባ መሬት ወረራን በተመለከተ አደረግን ያሉትን ባለ 13 ገጽ የጥናት ጽሑፍ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከሁሉ በፊት በጥናት ላይ ለተመሠረተው የውሳኔ ሐሳብም ሆነ ትችት ለማቅረብ ጥረት በማድረጋቸው፣ ኢዜማዎች ምሥጋና ይገባቸዋል። ሊበረታታ የሚገባ ባህል ነው።
እንኳንስ በተቃዋሚ ፓርቲ ደረጃ መንግሥትም ቢሆን በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ የመስጠት ባህል በአገራችን አልዳበረም:: በሚያሳዝን ደረጃ ትልልቅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች፣ ምንም ጥናትና መረጃ ላይ ሳይመሠረቱ እንዲሁ በዘፈቀደ ሲተላለፉ እያየን ቆሽታችን እያረረ እንኖራለን። ምናልባት ከዚህ በኋላ ሌሎች አካላት ኢዜማ የቀደደውን ፈር ተከትለው፣ ለመረጃ ቦታ የመስጠት ባህል (Evidence-Based Decision-Making) እየዳበረ ይሄዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ይህን ካልኩ በኋላ በኢዜማ ጥናት ላይ ያለኝን አስተያየት ወደ መስጠት አመራለሁ። አስተያየቴን የምሰጠው የጥናቱ ጭብጥ የሆነው የመሬት ወረራ የተተረጎመበት መንገድ ላይና ይኼ ደግሞ የጥናቱን ውጤት ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ነው።
የኢዜማ ጥናት ሪፖርት ትኩረቱ የአዲስ አበባ የመሬት ወረራ ላይ እንደሆነ በመግለጽ፣ “የመሬት ወረራ”ን ደግሞ ጠበብ ያለ ትርጉም በመስጠት ይጀምራል። አጥኝው ቡድን ወደ ጥናቱ የተሠማራው ‹‹የመሬት ወረራ ማንኛውንም የሕዝብ/የመንግሥት የሆነ መሬትን ከሕግ ውጪ በሆነ አግባብ በግለሰብ ወይም በቡድን የመያዝ ተግባር ነው፤›› (ገጽ 2)። የኢዜማ ጥናት ችግር ከዚህ ነው የሚጀምረው። ማንኛውንም የግል የሆነ መሬት አላግባብ ቢወረስ አያገባንም የሚሉ ይመስላል። ይህ ደግሞ ለዜነት መብት ጠበቃ ቆሜያለሁ ክሚል የፖለቲካ ቡድን አቋም ጋር ይቃረናል።
አንድ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ለወደፊት አገር ለማስተዳደር በዕጩነት ለመቅረብ እየተዘጋጅሁ ነው የሚል አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ይቅርና፣ ማንም ኢትዮጵያዊ ከዳር እስከ መሀል አገር ያለ ነዋሪ ዜጋ፣ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሀቅ አለ። ይህም የአዲስ አበባ የመሬት ወረራ ሲባል ትልቁ፣ አንጋፋውና ዘግናኙ የአዲስ አበባ ዙሪያ አርሶ አደሮች ከአባቶቻቸውና ከቅድመ አያቶቻቸው መሬት በገፍ የተፈናቀሉበትና ለጎዳና ተዳዳሪነት የተዳረጉበት ሒደት ነው። ይህ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም ተራማጅ ኃይሎች ሁሉ ያስደነገጠ ክስተት ነው።
ሌቦች ዘረፋ አካሂደው ግለሰቦችን ካራቆቱ በኋላ የዘረፉትን ሀብት በመከፋፈል ሒደት ላይ በመካከላቸው አለመግባባት መፈጠር ብዙም አያስገርምም፣ የተለመደ ነው። በዚህ ሒደት ደግሞ፣ ከሌቦቹ መካከል ብልጣ ብልጡና ጉልበተኛው ሌሎቹን ቀማኞች ሸውዶ፣ አብረው ከሰረቁት ሀብት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። የኢዜማ ጥናት ትኩረት ዋናውን ዘረፋ ወደ ጎን በመተው፣ በሌብነት የተገኘን ሀብት በመከፋፈል ሒደት ውስጥ እየተከሰተ ያለ ውዝግብ ላይ ያተኩራል።
መልስ ሊያገኝ የሚገባው ዋናው ጥያቄ፣ ‹‹ኢዜማ ግዙፉን ወንጀል ወደ ጎን ገሸሽ አድርጎ ጥቃቅን ወንጀሎች መመርመርን የመረጠበት ሚስጥር ምንድነው?›› የሚለው ነው። እውነቱን ለመናገር የኢዜማን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምንነት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፍንጭ ላለው ሰው፣ የሆነው ነገር ብዙም አይገርመውም። በግልጽ ለሕዝብ ይፋ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን አላየሁም፣ ግን አልፎ አልፎ የሚሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እሰማለሁ። ከእነዚህ የምረዳው ወደ ገበያ መር (Laissez-Faire) የተጠጋ ፖሊሲ የመከተል አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ኢዜማ የቅንጅት በኩር ልጅ እንደሆነ ይታወቃል። ቅንጅት ደግሞ ስለመሬት ይዞታ ምን ዓይነት የፖሊሲ አቋም እንደነበረው እናስታውሳለን። ቀጥሎም ቅንጅት ይከተል የነበረውን የመሬት ይዞታ ለመከተል ምን ዓይነት ታሪካዊ ሁኔታዎች ከበስተጀርባው እንዳሉም መገንዘብ አዳጋች አይደለም።
አንድ የፋና ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ዴሴምበር 30 ቀን 2019 ባስተላለፈው ፕሮግራም፣ ለኢዜማ መሪ ለዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር። ‹‹ኢዜማ በፊት ቅንጅት ያካሄድ ከነበረው የመሬት ይዞታ የተለየ ወይም ተመሳሳይ ፖሊሲ አለው?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ዶ/ር ብርሃኑ የተድበሰበሰ መልስ ነበር የሰጠው። ስለመሬት ይዞታ የነበረው ምልልስ ለመከታተል፣ ይህን ቪዲዮ (https://www.youtube.com/watch?v=zwFOxk2fSCo) ይጫኑና ከ42፡00 ደቂቃ ጀምሮ ይከታተሉ። በአጭሩ የዶ/ር ብርሃኑ መልስ፣ ለባለሀብቶች ኢንቨስትመንት ዕድል ለመክፈት ሲባል የአርሶ አደሮች መፈናቀል በኢኮኖሚ ዕድገት ሒደት ውስጥ አይቀሬ ክስተት ነው የሚል ነበር።
ከአዲስ አበባ አካባቢ አርሶ አደሮች መፈናቀል ጋር ያለውን ሰቆቃ በሚመለከት ኢዜማ ያለው አቋም ደግሞ፣ ከአጠቃላይ የድርጅቱ የመሬት ይዞታ ፖሊሲ ጠጠርና ጠንከር ያለ ነው። ምክንያቱም አዲስ አበባ ዙሪያ አርሶ አደሮች መፈናቀል፣ ከተፈናቀለው ሕዝብ፣ ማንነትና ባህል ጋር እንዲሁም የመፈናቀሉ ክስተት ያለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውጤት ብቻ ሳይሆን ለምዕተ ዓመታት የዘለቀ፣ ከኢትዮጵያ ኤምፓየር አመሠራረት ጋር የሚዛመድና ጭካኔ የተሞላበት ታሪካዊ ሒደት ስለሆነ ነው።
ይህ እንግዲህ ኢዜማ ሥራችን ብለው የመሬት ዘረፋዎች ሁሉ እናት የሆነውን አዲስ አበባ ዙሪያ መንግሥት አርሶ አደሮችን ያፈናቀለበትን ክስተት ወደ ጎን የተወበትን ምክንያት ይገልጽልናል። ኢዜማዎች ማምለጫ አላቸው ለዚህ፡፡ ቀድሞውንም መሬት የመንግሥት ነው የሚል (ከላይ ያለው ቪዲዮ ውስጥ እንደተብራራው)፡፡ ነገር ግን እነሱ ዝርፊያ ነው ብለው የሚወተውቱት ክፍት ቦታዎችና ኮንዶሚኒየሞችም እኮ በመንግሥት አካላት ነው የተዘረፉት፣ የታችኛው መንግሥት አካል መሆኑ ላይ ነው እንጂ ልዩነቱ!
ኢዜማ ወደ አዲስ አበባ የተጠቃለለውን መሬት እንደ ዘረፋ ያልቆጠረው፣ መሬቱ የተዘረፈው ከኦሮሞ አርሶ አደሮች በመሆኑና የኦሮሞ መሬት የሚባል ነገር ስለማይዋጥለት ነው። የኦሮሞ ምሁራንና አክቲቪስቶች ይህን የመሬት ዘረፋ እንደ ተራ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የአዲስ አበባ አካባቢ ኦሮሞን ባህልና ቋንቋ የማጥፋት ወንጀል እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል። ይህ ደግሞ ከኢዜማ ርዕዮተ ዓለም ጋር ፊት ለፊት ይጋጫል፡፡ ኢዜማዎች ይህን አካሄድ የዘር ፖለቲካ ብለው ይኮንናሉ። መሬቴን ተቀማሁ፣ ባህሌና ማንነቴም አብሮ እንዲጠፋ ተደረገ ለሚል የኦሮሞ አርሶ አደር ኢዜማዎች ጆሮ እንደሌላቸው እንገነዘባለን።
የኢዜማ አጥኚ ቡድን ሥራችን ብለው ከጥናታቸው ራዳር ዕይታ የሰወሩትን የአዲስ አበባ ዙሪያ አርሶ አደር ዕጣ ፈንታ፣ በአስገራሚ ሁኔታ ጥናታቸው መጨረሻ ላይ መልሰው ያመጡታል። ያውም ቀደም ሲል የተፈናቀሉትን የአዲስ አበባ ዙሪያ አርሶ አደሮች ዋና ወራሪ ወንጀለኞች ናቸው ብለው በመፈጅ ነው፡፡ የኢዜማ ሪፖርት እንዲህ ይላል፣ ‹‹በዋናነት በመሬት ወረራው ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበሩት ሰዎች ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶች ናቸውና በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል የሚሉ ግለሰቦችና ወረራ የተፈጸመባቸው ቦታዎች አካባቢ ላይ የሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ኃላፊዎችና ፈጻሚዎች ናቸው፡፡››
ይህ የኢዜማ ጥናትና ውጤቱ በጣም ሸፍጠኛ አካሄድ ከመሆንም አልፎ ዓይን ያወጣ ፍርደ ገምደልነት ነው። ቀደም ብዬ እንዳልኩት፣ የኢዜማዎች አካሄድ እንዴትና ወዴት እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም። ሆኖም ግን ይህን ያህል የወረዱና በርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከታቸው ምክንያት ማየት የተሳናቸው ናቸው ብዬ ገምቼ አላውቅም ነበር። በርዕዮተ ዓለም መታወር ብዛት፣ እንዲህ ፊት ለፊት ያለንና በገሃድ የሚታይን ግልጽ ነገር እንዳያዩ አደረጋቸው። የተቀማውን ባለንብረት የተገላቢጦሽ ወንጀለኛ ሌባ ብለው እስከሚጠሩ ድረስ መሄዳቸው አስነዋሪ ድርጊት ነው።
ጅምሩ ግራ የተጋባ ነገር መጨረሻው አያምርም እንደሚባለው መሆኑ ነው (Wrong Premise, Wrong Conclusion)። የኦሮሞ አርሶ አደሮችን ጉዳይ ገሸሽ ለማድረግ፣ ኢዜማ ሆን ብለው መሬት ወረራን የተጣመመ ትርጉም በመስጠት ጥናታቸውን ጀምረው፣ እንዲህ ዓይነት ትርጉም የለሽ፣ አሳፋሪና ተዓማኒነት የሌለው ውጤት ላይ ደረሱ። ለወደፊቱ ኢዜማዎች ጥናት ሲያካሂዱም ሆነ ፖሊሲ ሲቀርፁ፣ ይህን ብዥታ የሚፈጥርባቸውን የርዕዮተ ዓለም መነጽር አውልቀው ማየት ቢጀምሩ፣ እውነተኛዋን ኢትዮጵያ የማየት ችሎታቸው እያደር ይዳብር ይሆናል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኩዌት ሳይንቲፊክ ምርምር ኢንስቲትዩት (Kuwait Institute for Scientific Research – KISR) ባልደረባ ሲሆኑ፣ ጽሑፊ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡