Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንድ ኪሎ 2,600 ዶላር የሚሸጠው የኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ቡና አምራቾች ይሸለማሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የቡና ኦሊምፒክ›› የሚል ቅጽል ስም አትርፏል፡፡ በየዓመቱ ከፍተኛ የቡና ጥራት ውድድር ይካሄድበታል፡፡ በውድድሩ የልዩ ጣዕም ቡናዎች በከፍተኛ ዋጋ በጨረታ ይሸጣሉ፡፡ ከሰሞኑም 40 የኢትዮጵያ ቡናዎች ለመጨረሻው ዙር ቀርበው፣ ከእነዚህ መካከል 28 ቡናዎች ከፍተኛ ዋጋ አውጥተዋል፡፡ ዝቅተኛ ዋጋ ያወጣው ቡና በፓውንድ (ግማሽ ኪሎ ገደማ) የተሸጠው በ11.30 ዶላር ነበር፡፡ ከፍተኛው ግን በፓውንድ 185 ዶላር መሸጡ ይታወሳል፡፡

እነዚህን ቡናዎች በማቅረብ በዓለም አቀፍ የጥራት ውድድሩ የተሳተፉ አምራቾችና ነጋዴዎች ሐሙስ፣ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ዕውቅና እንደሚሰጣቸው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል፡፡ 

‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› የተሰኘውን የቡና ጥራት ውድድር አዘጋጁ አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ የተሰኘው የአሜሪካ ተቋም፣ ከ40ዎቹ የመጨረሻ ደረጃ ተወዳዳሪ ቡናዎች 28ቱን ለጨረታ አቅርቦ ማገበያየቱን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ እነዚህ ቡናዎች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላቸውና በአገር ውስጥ ዳኞች አማካይነት የጥራት ደረጃቸው ተለይቶ፣ ውጤታቸውም ከ87 እስከ 91 በመቶ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ማስመዝገባቸው ይታወቃል፡፡

አንድ ኪሎ 2,600 ዶላር የሚሸጠው የኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ቡና አምራቾች ይሸለማሉ

 

ይህንን ተከትሎም ከሰሞኑ ሲኤንኤን ያወጣው ዘገባ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በለንደን ከፍተኛ የገቢ ደረጃ ባላቸው ዘንድ ከሚወዘተሩ የቡና መሸጫ መደብሮች አንዱ በሆነው ‹‹ክዊንስ ሜይፌይር›› ሬስቶራንት ውስጥ በውድ ዋጋ እየተሸጠ የሚገኘው ይኸው ከፍተኛ የጥራት ደረጃ የተሰጠው የኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ በሬስቶራንቱ ቡና የሚቀርብልዎ እንደወትሮው በስኒ አይደለም፡፡ ልክ እንደ ወይን ጠጅ ባማረ፣ ሽንጣም የወይን ብርጭቆ ተሞሽሮ ነው፡፡ ለአንድ የወይን ብርጭቆ ቡና የሚጠየቁት ግን 65 ዶላር ነው፡፡ ይህን ያህል ዋጋ የሚያወጡበት ቡና ከኢትዮጵያ ማሳያዎች የተለቀመ፣ በጥራቱ ዓለም የመሰከረለት ውዱ ቡና ስለሆነ ነው ይላል የሲኤንኤን ዘጋቢ፡፡ ቡናው በወይን ዋንጫ መቅረቡ ብቻም አይደለም ልዩነቱ፡፡ የቡናው ባሪስታ እንደ ፍላጎትዎ ሳይሆን፣ ለቡናው በወጣለት ከፍተኛ የጥራትና የአቀራረብ መስፈርት መሠረት ያስተናግድዎታል፡፡

‹‹ኢትዮጵያን ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ኩዊንስ ኮፊ›› በተሰኘ መጠሪያው የሚንቆረቆርልዎ ቡና፣ የተለመደው ላቴ፣ ወይም ወተት የበዛበት ወይም ያነሰው ማኪያቶ እንዳይመስልዎና ተጨማሪ ወተት ወይም ስኳር ልጨምርበት እንዳይሉ ይመከራሉ፡፡ አሊያም ባናቱ የቸኮሌት ዱቄት ልነስንስበት የሚሉት ዓይነት ቡና እንዳልቀረበልዎ የሚገነበዙትም፣ የቡና መሸጫ መደብሩ ከገዛው የኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከግማሽ በላይ ሸጦ መጨረሱን፣ ጠጪዎቹም ከተለያዩ የዓለም አገሮች የሚከንፉ፣ አፍቃሪ ልዩ ጣዕም ቡና አነፍናፊዎች መሆናቸውን ሲገነዘቡ ነው፡፡

እነዚህ ቡናዎች በችርቻሮ የሚሸጡበት የአንድ ኪሎ ዋጋ እስከ 2,600 ዶላር ማሻቀቡን ያወሳው የሲኤንኤን ዘገባ፣ ይህ በመሆኑም ዋናዎቹ አምራች ገበሬዎች ከመደበኛው ገበያ እስከ 145 እጥፍ ጭማሪ ያለው ዋጋ እንዲከፈላቸው የሚያስችል የጥራት ውድድር እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ በለንደን ቡና መሸጫ ሱቆች የተለመደውን ኤስፕሬሶ ቡና በሁለት ፓውንድ ስተርሊንግ መጠጣት ይችላሉ፡፡ ለተጠበሰ ዳቦና ለቺዝ ወይም ዓይብ ስድስት ፓውንድ ሊጠየቁም ይችላሉ፡፡ ለአንድ ሳንድዊችም ከአምስት ፓውንድ በታች ከፍለው ቁርስ ወይም ምሳ ሊመገቡ ይችላሉ፡፡

በለንደኑ ቡና ቤት የሚሸጠው ቡና፣ በኢትዮጵያዊው ገበሬ አቶ ንጉሤ ገመዳ የተመረተው በተፈጥሮ ሒደት ተቀነባብሮ ለውድድር የቀረበው ባለልዩ ጣዕም የሲዳማ ቡና ነው፡፡ 91.04 ከመቶ የጥራት ውጤት የተሰጠው ይህ ቡና በጥሬው ግማሹ ኪሎ 185.10 ዶላር መሸጡ ይታወቃል፡፡ አቶ ንጉሤ ያቀረቡት 595.25 ኪሎ ግራም ጠቅላላ ቡና 110180.78 ዶላር ማውጣቱን የቡና ጥራት አወዳዳሪው ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አስተናባሪ አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ የተሰኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ በጠቅላላው 28 ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያገኙ ቡናዎች በዓለም አቀፍ ጨረታ ተሸጠው ከ1.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ማውጣታቸው ሲዘገብ ከርሟል፡፡

ይህ ይባል እንጂ በፓናማ በተካሄደው የጥራት ውድድር ጌሻ በተሰኘው የቡና ዝርያ የተወዳደረው የፊንካ ሶፊያ እርሻ በፓውንድ 1300 ዶላር አውጥቶ ክብረ ወሰኑን ወስዷል፡፡ ከዚህ ቀደም በዓለም ክብረ ወሰንነት የተመዘገበው የግማሽ ኪሎ የልዩ ጣዕም ቡና ዋጋው 601 ዶላር ነበር፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. በ2017 በፓናማ በተካሄደው የቡና ጨረታ የተመዘገበ ነበር፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ በዋጋም ባይሆን 1400 የቡና ናሙናዎችን ለውድድር በማቅረብ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ አልቀረም፡፡ 

የቡና ጥራት ውድድሩ ኢትዮጵያውያን የቡና ጥራት ቅምሻ ዳኞችም በሚሳተፉበት አግባብ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ታቅዶ እንደነበር፣ ሆኖም በኮሮና ጦስ ምክንያት ባጋጠሙ የሎጂስቲክስና ሌሎች ችግሮች አወዳዳሪው አካል ጽሕፈት ቤቱ በሚገኝበት በአሜሪካ ኦሪጎን ግዛት እንዲካሄድ በመወሰኑ፣ ቡናዎቹ ወደ አሜሪካ ተልከው መወዳደራቸው ይታወቃል፡፡

እርግጥ ነው የለንደኑ ኩዊንስ ቡና ቤት አንድ የወይን ዋንጫ ቡና በ65 ዶላር ይሽጥ እንጂ፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ለአንድ ስኒ የልዩ ጣዕም ቡና 75 ዶላር የተከፈለበት ውዱ ቡና፣ በፓናማ ጫካዎች የበቀለው የተፈጥሮ ቡና እንደነበር ከአሊያንስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ምንም እንኳ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የልዩ ጣዕም ቡናዎች በዚህን ያህል ዋጋ ቢሸጡም፣ በ2012 ዓ.ም. ከጠቅላላው የኢትየጵያ የቡና ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከ860 ሚሊዮን ዶላር ፈቅ አላለም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች