Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገንዘብ ለውጡ ማስተግበሪያዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የኢትዮጵያን የመገበያያ ኖት እንደቀየረ ይፋ ካደረገ ወዲህ፣ ባንኮች ከስድስት ሺሕ በላይ በሚጠጉ ቅርንጫፎቻቸው የብር ኖት ለውጡን በማስተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡ አነስተኛ የገንዘብ ድርጅቶች ወይም ማክሮፋይናንስ ተቋማትም ይህንኑ ተግባር ከባንኮች እኩል ያካሂዳሉ፡፡

የገንዘብ ለውጡ በሚተገበርበት መመርያ መሠረት፣ ነባሩ ገንዘብ በአዲሱ እየተቀየረና ገበያውን እየተቀላቀለ እንደሚገኝ እየታየ ነው፡፡ የብር ኖት ለውጡ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ዕለታዊ አፈጻጸሙን በመገምገም ችግሮች ሲከሰቱም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባንክ ፕሬዚዳንቶች ጋር የሚመክርበት መድረክ ተዘጋጅቶ መረጃ በመለዋወጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

 ውይይቱና የመረጃ ልውውጡም የሚያጋጥሙ ችግሮችን እያዩ መፍትሔ  እንዲሰጥባቸው እያስቻለ ነው፡፡ ግርታ የሚፈጥሩና ግልጽ ያልሆኑ አሠራሮች እንዲለወጡ፣ አዳዲስ መመርያዎችም እንዲወጡ በማድረግ የገንዘብ ለውጡን ከጉልህ ችግር በተላቀቀ መንገድ ለማስፈጸም እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ይገለጻል፡፡

ባንኮች በዚህ ሒደት ትልቁን ሚና በመጫወት ደንበኞች በቂ መረጃ ኖሯቸው እንዲስተናገዱ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የብር ኖት ለውጡ ያለ ችግር እንዲሳለጥ ኅብረተሰቡ የሚያደርገው ትብብር ወሳኝ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ደንበኞች የተሟላ መረጃ ይዘው በመምጣት መስተናገዳቸው ለሥራው ቅልጥፍና እንደሚያግዝ ይጠቅሳሉ፡፡

 ‹‹ዋናው ጠላት የዋጋ ግሽበት በመሆኑ፣ ይህንን የአገር ችግር አቃሎ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲሆን፣ የብር ለውጡን በበቂ መረጃ ማስፈጸም ወሳኝ  ሥራ ነው፤›› በማለት የመረጃ ሥርጭት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፣ የገንዘብ ለውጡ በተለይ ለባንኮች የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዓመታት ባንኮች ሲፈተኑ የቆዩበትን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ለማቃለልና የተቀማጭ ገንዘብ ክምችታቸውን ለማሻሻል አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ወደ ኢኮኖሚው በብድር መልክ የሚሠራጨው የኢንቨስትመንት ገንዘብ፣ ኅብረተሰቡን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ የሚውል በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህንንም በማሰብ የዜግነት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

 ባንኮች የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ እንደመሆናቸው ከባንክ ውጪ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ወደ ባንክ ለማስገባትም የብር ኖት ለውጡ ወሳኝ ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ ሲሳካ የባንኮች የቁጠባ ይዞታ እንዲሻሻል በማገዝ የብድር አቅርቦት እንዲስፋፋ የማርሽ ቀያሪነት ሚናው እንደሚጎላ ተብራርቷል፡፡ ኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም እየተገበረች እንደምትገኝ በማስታወስ፣ በዚህ ፕሮግራምም ሆነ ቀደም ብለው በነበሩ ጅምሮች በኩል ሁሉን አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲፈጠር ማድረግ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ አነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ላይ የሚንቀሳቀሰው የንግዱ ማኅበረሰብ አካታች እንዲሆን በማድረግ ረገድ ጠቀሜታው ፈርጀ ብዙ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይህንን ማዕቀፍ ለማሳለጥ የብድር አቅርቦት በጣም ወሳኝነት አለው ያሉት ፕሬዚዳንቱ አቅርቦቱ ብቻ ሳይሆን፣ ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ተመጣጣኝ ዋጋ የብድር አቅርቦት ካለ ደግሞ የአገር ልማቱን የጥልቀት ያግዛል በማለት ገልጸዋል፡፡ ልማቱ ደግሞ በዋናነት በመካከለኛና በጥቃቅን የንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ስለሆነ ሪፎርሙ እነሱን ለማቀፍ ሥራ ላይ እንደመዋሉ መጠን ያን በጥልቀት ለማገዝ የብር ኖት ለውጡ ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡  የገንዘብ ለውጡ በዘጠና ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ የጊዜ ሰሌዳ የተያዘለት በመሆኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁለቱም የብር ኖቶች እኩል ጎን ለጎን አገልግሎት ላይ የሚውል መሆኑ ነባሩ ብር አሮጌ ተብሎ ከግብይት የሚወጣው ከዘጠና ቀናት በኋላ ግንዛቤ መውሰድ እንዳለበትም ሳያስታውሱ አላለፉም፡፡  

ከሰሞኑ የብር ለውጡ ጋር ተያይዞ እየገጠሙ ያሉ ከባድ ችግሮች የሌሉ ቢሆንም፣ የብር ለውጥ አፈጻጸምን በተመለከተ ግን በአንዳንዶች ዘንድ በቂ ግንዛቤ ያለመኖሩ ግን ይስተዋላል ተብሏል፡፡ አቶ ተፈሪ እንዳመለከቱትም፣ ኅብረተሰቡ መገንዘብ አለበት ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ ለጥሬ ገንዘብ ለውጡ ካልሆነ በቀር በባንክ ያለውን ገንዘብ ለመለወጥ ወደ ባንክ መምጣት የማይጠበቅበት መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶች በባንክ ያለ ገንዘብ በግንባር ወጥተው እንደሚለወጥ በማሰብ ወደ ባንክ ሲመጡ ያጋጠመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በባንክ የቁጠባ ሒሳባቸው ያለው ገንዘብ በማንኛውም ሰዓት ወደ ባንክ ሲመጡ አዲሱ የብር ኖት የሚሰጣቸው በመሆኑ በእጅ ያለ ጥሬ ገንዘብን ብቻ ይዘው በመምጣት መቀየር ይችላሉ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ባንክ መምጣት አስፈላጊ አይደለም ማለት ነው በማለት ገልጸዋል፡፡ ከብር ኖት ለውጡ ጋር ተያይዞ ሌላው ብዥታ ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል የንግድ ድርጅቶች የዕለት ሽያጭ ገቢን በተመለከተ ነው፡፡  የዕለት ሽያጮችን የንግዱ ማኅበረሰቡ በማንኛውም ሰዓት ወደ ባንክ ገቢ መደረግ አለባቸው ያሉት አቶ ተፈሪ ቢቻል በቀን ሁለት ጊዜ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ቢያንስ ግን በቀን አንድ ጊዜ ገቢ ማድረግ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እቤት ወይም መሥሪያ ቤት መቀመጥ ያለበት የጥሬ ገንዘብ መጠን ገደብ ስለተጣለበት ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በቤት ወይም በድርጅት ይዞ መገኘት ገደብ የተጣለበት ስለሆነ በዚሁ አግባብ የዕለት ሽያጮች ወደ ባንክ መግባት አለባቸው፡፡  

ሽያጭን በተመለከተ ግን በደንብ እንደ ቤተሰብ በሚያውቁዋቸው ቅርንጫፎቻችን እያቀረቡ በማንኛውም ሰዓት ማስገባት ይችላሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህ የዕለት ገቢ ከ1.5 ሚሊዮን ብር ሊሆን እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ የዕለት ሽያጭ መሆኑ ግን ከቅርንጫፎቻችን ጋር መተማመን መቻል እንዳለባቸው ያስገነዘቡት አቶ ተፈሪ ደንበኞቻቸው ካልሆነ አካሄድ እንዲቆጠቡም ጠቁመዋል፡፡

 የዕለት ሽያጫቸውን አሳስበው ወደ ባንክ ሳያስገቡ በእጃቸው ሰብስበው ያቆዩትን ገንዘብ ዕለታዊ ሽያጭ ገቢ አስታከውና፣ በስመ ትብብር አሳበው ሕገወጥ ገንዘብ ይዘው እንዳይወጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡ ደንበኞች የራሳቸውን የሽያጭ ገቢ በጥሬ ገንዘብ ብቻ ከሽያጭ ማስረጃዎች ጋር አያይዘው ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን የቀረ እንደሆነ ግን በፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል በኩል ምርመራ እየተደረገና እየተጣራ ችግሩ ተፈልፍሎ ሊወጣ እንደሚችል በማውሳት ደንበኞች ከዚህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡

የብር ኖት የመቀየሩን ተግባር በተቀመጠለት መመርያና በመንግሥት የውሳኔ አቅጣጫ መሠረት ለማስፈጸም ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመምከር እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሥራውን ለማቀላጠፍ አጋዥ ስለመሆኑ በማስታወስ ከባንኮች በሚቀርበው ምክረ ሐሳብ መሠረት የተለያዩ ማሻሻዎች እየተደረጉ ስለመሆኑ ከአቶ ተፈሪ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ እንዲህ ባለው የጋራ ምክክር የደኅንነት የፀጥታ አካላት ትኩረት ከባንክ ውጪ ባሉ ሕገወጥ ገንዘብ ላይ እንዲሁም ከእጀባና በጥቆማ አግባብ ባንኮች ለድጋፍ ሲፈልጓቸው ብቻ ነው የሚሆነው የሚለው በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ይህንን ከብሔራዊ ባንክና ከሚመለከታቸው የኮማንድ ፖስት አካላት ጋር ተወያይተን አጥርተን የትኩረት አቅጣጫቸው በዚያ፣ እነሱም በዚያ አግባብ ሥራቸውን እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የመገበያያ ኖት ቅየራ ሥራውን ለማካሄድ የወጣውንና በውክልና ገንዘብ ማስገባት እንደማይቻል የሚደነግገውን መመርያ በማሻሻል፣ ከመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት ውክልና ያላቸው አካላት እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር በሕጉ መሠረት ወደ ባንክ ገቢ ማድረግ እንዲችሉ መፈቀዱ ሌላው ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በጠረፍ አካባቢ ያሉ ቅርንጫፎች ከጎረቤት አገሮች ገንዘብ ወደ አገር ቤት ባንኮች እንዳይገባ ጠንካራ ሥራ እንዲሠሩና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይህንን ማድረግ የሁሉም ዜጎች  ግዴታና ኃላፊነት እንደሆነ አሳስበዋል፡፡ 

‹‹የሕገወጥ  ገንዘብ እንቅስቃሴን ኢኮኖሚያችንን ከመፈወስ ዓላማ አንፃር ማየት ያለብን ግዴታ ስለሆነ፣ ለፀጥታ አካላት ተገቢውን ጥቆማ በመስጠት፣ የገንዘብ እንቅስቃሴን በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተገቢውን ሚና መጫወት ይገባናል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይህ ግዴታ አለበት፤›› በማለት አቶ ተፈሪ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች