- እንዴት ይዞሃል ታዲያ?
- ትንሽ ችግር አለ እባክህ፡፡
- ምን ተፈጠረ?
- የቀድሞው ሚኒስትር ቢሮ እንዲያስረክቡኝ ብጠይቅም የማስረክበው ነገር የለም፣ አልመጣም ብለው ተቸግሬያለሁ እባክህ፡፡
- እኔም የአለቃ የሹመት ደብዳቤ ከደረሰኝ ጀምሮ ጥሩ አይደለሁም፡፡
- ምነው?
- እንዲሁ ፍርኃት ፍርኃት ይለኛል።
- የማላውቀው ነገር አለ እንዴ?
- የአለቃ የሹመት ደብዳቤ ቢደርሰኝም ፓርላማው አላፀድቅም እንዳይል ሠግቼ ነው!
[የፓርላማው ፕሮቶኮል ሚኒስትሮቹን ወደ አዳራሹ ይዞ በመግባት ላይ ሳለ የሁሉም ዕጩ ሚኒስትሮች ሹመት በድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ መፅደቁን አፈ ጉባዔው ገልጸው ሚኒስትሮቹ ቃለ መሃላ ፈጽመው ከአዳራሹ ወጡ]
- ፍርኃትህ ጠፋ፡፡ ተገላገልክ አይደል?
- አሁን ወደ ቀድሞ ስሜቴ ተመልሻለሁ፡፡
- እኔ ግን ግር ብሎኛል?
- ለምን?
- የፓርላማ አባላቱ ለምንድነው ድምፀ ተዓቅቦ ያደረጉብን?
- ዋናው በአብላጫ መፅደቁ ነው። ከዚህ ወዲህ ክቡር ሚኒስትር ልትለኝ ትችላለህ። እኔም ክቡር ሚኒስትር ብዬ እጠራሃለሁ፡፡
- አንተማ ክቡር ሚኒስትር ብቻ ብለህ አይደለም እኔን መጥራት ያለብህ፡፡
- እና ምን ልጨምርበት?
- ባለውለታዬ፡፡
- ለምን?
- ተዓቅቦህን ስለተጋራሁልህ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የፖለቲካ አማካሪያቸው ጋ ደወሉ]
- ሃሎ. . . .ነገሮች እንዴት እየሄዱ ነው?
- ያለፈው ሳምንት ተልዕኮዎች በሰጡኝ አቅጣጫ መሠረት በጥሩ ሁኔታ ተፈጽመዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- መልካም። በመጪዎቹ ቀናት ትኩረት የምታደርግባቸውን ተግባራት እንነጋገር፡፡
- ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር እንዳሉት ይፈጸማል፡፡
- አንተ በምትመራው ኮሚቴ ከእኛ ሚዲያዎች አመራሮች ጋር የግማሽ ቀን ውይይት ታደርጉና የቀጣይ ሳምንታት አጀንዳዎችን ትነጋገራላችሁ፡፡
- ጥሩ እየሰማሁ ነው፡፡
- የእኛ ሚዲያዎች በቀጣይ ሳምንታት አጀንዳቸው አገር አቀፉ ምርጫ ዘንድሮ እንዲካሄድ መወሰኑ ተገቢነት ላይ እንዲሆን አድርጉ፡፡
- ጥሩ፡፡
- ይህንን አጀንዳ በደንብ አድርገው ማስረፅ እንዳለባቸው ጠንከር ያለ ትዕዛዝ ይሰጥ፡፡
- እንዳሉት ይደረጋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለዚህ ይረዳቸው ዘንድ በዋናነት አጋር ፓርቲዎችን ይጠቀሙ . . .
- አጋር ነው ያሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- አዎ፡፡
- አጋሮች የእኛው አካል ሆነዋል ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አዎ! አጋር አልኩ እንዴ?
- እ. . .
- ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለማለት ፈልጌ ነው።
- ጠርጥሬያለሁ ቢሆንም አልተሳሳቱም፡፡
- አልተሳሳቱም?
- አዎ! ተቃዋሚ ቢሆኑም በአጋርነታቸው ልክ ስለሆነ ወንበር እንዲያገኙ የምንፈቅድላቸው አጋር ብለው መጥራቶ ስህተት አይደለም። አጋር ተፎካካሪ ናቸው።
- ይህንን ለራስህም ቢሆን ደግመህ እንዳትለው! [ተቆጡ]
- አጠፋሁ እንዴ?
- አጠፋሁ ይለኛል እንዴ? ፈንጂ ከመርገጥ በላይ ምን ስህተት አለ?
- ስህተቴ ባይገባኝም ይቅርታ ያድርጉልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- አድምጠኝ። ኢሕአዴግ አንድ ለአምስት ብሎ የተገበረው ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውጤታማ ያልሆነው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- አላውቅም፡፡
- አንድ ለአምስት የሚለውን እንቅስቃሴ እንደ ቅዱስ ተግባር ቆጥሮ በይፋ ስላስተዋወቀው ነው። ስህተቱ መነገሩ ነው።
- ገባኝ ክቡር ሚኒስትር ፡፡
- መስሎህ ነው፣ አልገባህም።
- እሺ፡፡
- አድምጠኝ ስለአጋር ተፎካካሪዎች ያልከው ነገር ይተገበራል እንጂ በፍፁም አይነገርም።
- ተፀፅቻለሁ ክቡር ሚኒስትር አሁን በደንብ ግልጽ ሆኖልኛል። ይተገበራል እንጂ አይነገርም፡፡
- ትክክል። ሌላው ነገር ሚዲያዎቹ ከአጋር ፓርቲዎች በተጨማሪ. . .
- እርስዎ ተናገሩት፡፡
- ምን አልኩ?
- አጋር?
- አንተ አሳሳትከኝ። ለማንኛውም ሚዲያዎቹ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ውጪ የእኛን ሐሳብ የተቀበሉ ምሁራንንም እንዲጠቀሙ አድርጉ።
- ጥሩ፡፡
- ምርጫው ዘንድሮ እንዲካሄድ መወሰኑ ተገቢ እንደሆነ፣ እንዲሁም ከሕግና ከዴሞክራሲ ሥርፀት አንፃርም ትክክል ስለመሆኑ ምሁራዊ አስተያየት እንዲሰጡበት ይደረግ፡፡
- እሺ፡፡
- ጎን ለጎን ደግሞ ለዚሁ ነው እንዴ የሚል ትችት እንዲሰነዝሩ ይደረግ፡፡
- ለዚሁ ነው የሚለው ትችት ግልጽ አልሆነልኝም?
- ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ምርጫ ያደረገው አካል ጥድፊያ ለዚሁ ነው ተብሎ በምሁራን ይተች፡፡ ለወራት ተብሎ ሕገ መንግሥት አይጣስም ይበሉ ምሁራን፡፡
- እንዳሉት ይደረጋል ክቡር ሚኒስትር!
[የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመከታተል የሚታወቁ የአንድ አውሮፓ አገር የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ለሚኒስትሩ ደወሉላቸው]
- ቢዘገይም እንኳን አደረሰዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አመሠግናለሁ ወዳጄ፡፡
- ድንቅ ታሪክና ከዓለም ልዩ የሆነ ባህል ያላት አገር መሪ መሆን መታደል ነው መቼም፡፡
- እንዴታ! እውነት ብለዋል።
- ታዲያ በአዲሱ ዓመት ከእርስዎ ምን እንጠብቅ?
- ታሪካዊ ምርጫ ይጠብቁ። እርስዎና መንግሥትዎ ብቻ ሳትሆኑ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ምርጫ ነው የሚሆነው።
- ግን እኮ አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮች በኢትዮጵያ እየተከሰቱ መሆኑን እየሰማን ነው?
- ከሥልጣን የተወገዱት ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
- አዲስ አበባ ካለው ኤምባሲያችን ያገኘነው መረጃ ነው። መረጃው ትንሽ አሳስቦናል ክቡር ሚኒስትር።
- ይመኑኝ ያለፈውን በጭራሽ አንደግመውም። ሥጋት አይግባዎት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እየደገማችሁት መሆኑ ነው ሥጋት ያጫረብን?
- የተሳሳተ መረጃ እንዳይሆን?
- ፖለቲከኞችን ስለማሰራችሁ የሰማነው ሐሰት ነው?
- አይደለም፣ የተወሰኑትን አስረናል፡፡
- ዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የመከፋፈል እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸውም መረጃ ደርሶናል፡፡
- ተደርጎ ሊሆን ይችላል፡፡
- ታዲያ ያለፈውን አንደግመውም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ድርጊቱ ቢመሳሰልም የእኛ ዓላማና ግብ ይለያል።
- ዓላማው ምንድነው?
- የተበታተኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ማደረግ።
- እ. . .
- ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ግማሾቹ ወደ ብልፅግና ግማሾቹም ሰብሰብ ብለው ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው እንዲወዳደሩ ለማድረግ ነው እጃችንን ያስገባነው።
- እሺ የአመራሮቹ መታሰርስ?
- ለጊዜው ነው።
- ለጊዜው ማለት?
- ተፎካካሪ ፓርቲዎቹን ሰብሰብ አድርገን እስክንጨርስ ገለል ማድረጋችን ነው፡፡
- ታሪካዊ ምርጫ ይሆናል ሲሉ በዴሞክራሲያዊነቱ መስሎኝ ነበር፡፡
- በግሌ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ነፃ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
- ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው፡፡
- ምን አሉኝ?
- ልድገመው?
- አይድከሙ ሰምቻለሁ!